ባይደን፤ ትራምፕን በተመለከተ ከዚህ ቀደም የሰጧቸውን አስተያየቶች እንደማያርሙ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ተቀናቃኛቸው ላይ ከተደረገው የግድያ ሙከራ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ቃለ-መጠይቅ ሰጥተዋል።
ፕሬዝደንቱ ከዚህ ቀደም ትራምፕን በተመለከተ የሰጧቸውን አስተያየቶች እንደሚያምኑባቸው አስረግጠው ተናግረዋል።
ባይደን እንደሚሉት በሚያደርጉት የምርጫ ቅስቀሳ ትራምፕ ድጋሚ ከተመረጡ አደጋ እንደሚሆን መናገር ግድ እንደሆነ አስረድተው ንግግራቸውን እንደማያርሙ አሳውቀዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ቅዳሜ በፔንሲልቬኒያ ግዛት የምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ ሳለ ነው የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው።
ነገር ግን ከግድያ ሙከራው ከጥቂት ቀናት በፊት ባይደን በገንዘብ ከሚደግፏቸው ጋር ባደረጉት ውይይት ትራምፕን “ዒላማ ውስጥ ማስገባት ግድ ነው” ብለው የተናገሩት “ስህተት” መሆኑን ኤንቢሲ ለተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።
ፕሬዝደንት ባይደን፤ የዲሞክራት ፓርቲ አባላት ትኩረታቸውን ትራምፕ ላይ ሊያደርጉ፤ ፖሊሲያቸውን ሊያጤኑ ይገባል፤ አልፎም ባለፈው ወር በነበረው ፕሬዝደንታዊ ሙግት የተናገሩት ሀሰት መሆኑን መረዳት አለባቸው ማለታቸው እንደሆነ አስረድተዋል።
ባይደን በቃለ-መጠይቃቸው ከፕሬዝደንታዊው ምርጫ ራሳቸውን እንደማያገሉ በተደጋጋሚ ቢያስረግጡም በፕሬዝደንታዊው ሙግት ባሳዩት የወረደ አቋም ምክንያት የፓርቲያቸው አባላት ጫና እያሳደሩባቸው ይገኛል።
“ዕድሜዬ ገፍቷል” ያሉት ባይደን ነገር ግን ከትራምፕ በሶስት ዓመት ብቻ እንደሚበልጡ አውስተዋል። የአዕምሮ ጤናቸው መልካም መሆኑን ተናግረው በፕሬዝደንትነት ዘመናቸው ያሳኳቸውን ጉዳዮች ዘርዝረዋል። አክለው ለአሜሪካዊያን ማስረገጥ የሚፈልጉት ለሥራው ብቁ መሆናቸውን እንደሆነ ተናግረዋል።
“ሰዎች «የፈጣሪ ያለህ፤ 81 ዓመታቸው እኮ ነው» ሲሉ ይገባኛል። «ዕድሜያቸው 83 አሊያም 84 ሲሆን ምን ሊሆኑ ነው?» ይላሉ። ይህንን ጥያቄ መጠይቅ ውሀ ያነሳል” ብለዋል።
ዲሞክራቲክ ፓርቲን ወክሎ ለመወዳደር በሚደረገው ምርጫ አብላጫ ድምፅ በሰጧቸው ደጋፊዎቻቸው እምነት እንዳላቸው የተናገሩት ባይደን “እኔ የምሰማው እነሱን [መራጮችን] ነው” ብለዋል።
ትራምፕ ባለፈው ቅዳሜ በተደረገባቸው የግድያ ሙከራ ምክንያት ጆሯቸውን ከተጨረፈ በኋላ አሜሪካዊያን “በስሜታዊነት እንዳይነዱ” ባይደን አሳስበዋል።
በግድያው ሙከራው ምክንያት አንድ ታዳሚ ሲገደል ሁለት ሰዎች ደግሞ ክፉኛ ቆስለው ሆስፒታል ገብተዋል።
በርካታ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ባይደን እና ዲሞክራቶች ናቸው በትራምፕ ሕይወት ላይ አደጋ እንዲመጣ አመፅ የጠሩት ሲሉ ወቅሰዋል። በርካቶች ባይደን “ትራምፕን ዒላማ ውስጥ ማስገባት” የሚለውን ንግግር ጠቅሰዋል።
ሰኞ ዕለት የትራምፕ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው የተመረጡት ጄዲ ቫንስ የተባሉት ፖለቲከኛ ዲሞክራቶች ፕሬዝደንት ትራምፕ ላይ ያነጣጠሩ ንግግሮች ማድረጋቸው ነው “ለትራምፕ ግድያ ምክንያት የሆነው” ብለዋል።
ከኦቫል ቢሮ እሑድ ዕለት ንግግር ያሰሙት ባይደን ጥቃቱን አውግዘው አሜሪካዊያን “ረጋ ብለው” እንዲያስቡ ካስጠነቀቁ በኋላ “በሀገራችን የፖለቲካ ንግግሮች እየጋሉ መጥተዋል” ብለዋል።
ከኤንቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ-መጠይቅ ከዚህ ቀደም ትራምፕን በተመለከተ የተናገሯቸው ንግግሮችን ያጤኑ እንደሆን የተጠየቁት ባይደን ጠብ አጫሪ የሚባሉትን ንግግሮች ያሰሙት እሳቸው እንዳልሆኑ ተናግረዋል።
“እኔ እንዲህ ያለ ንግግር አድርጌ አላውቅም። ተቀናቃኜ ናቸው እንዲህ ያሉ ንግግሮችን የሚያሰሙት” ብለዋል።
“እኔ አይደለሁም አንድ ቀን አምባገነን መሪ መሆን እፈልጋለሁ ያልኩት፤ እኔ አይደለሁም የምርጫ ውጤትን አልቀበልም ብዬ አሻፈረኝ ያልኩት።”
ኤፍአቢአይ ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ ያደረገው ግለሰብ የ20 ዓመቱ ቶማስ ማቲው ክሩክስ የተሰኘ ወጣት መሆኑን ይፋ ያደረገ ሲሆን ግለሰቡ የሚደግፈው ፓርቲ ሪፐብሊካን መሆኑን አሳውቋል።
ክሩክስ ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ ካደረገ በኋላ በደኅንነት መሥሪያ ቤት አነጣጥሮ ተኳሽ ተገድሏል።












