በርካታ ሕንዳውያን ሠራተኞች በጣልያን ‘ከባርነት’ ነጻ ወጡ

ህንዳውያን የእርሻ ሰራተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በጣልያን በባርነት መሰል የሥራ ሁኔታ ውስጥ ተሰማርተው ነበር የተባሉ በርካታ ሕንዳውያን የእርሻ ሠራተኞች ነጻ መውጣታቸውን ፖሊስ ገለጸ ።

በአሁኑ ወቅት ነጻ የወጡት 33ቱ ሠራተኞች ወደ ጣልያን የተወሰዱት የተሻለ ሥራ እና የወደፊት ተስፋቸው የለመለመ እንደሚሆን በሁለት የሕንድ ዜጎች ተጭበርብረው መሆኑንም ፖሊስ አክሎ ገልጿል።

ነገር ግን ሠራተኞቹ የገጠማቸው በቀን ከ10 ሰዓታት በላይ በሳምንት ለሰባት ቀናት እንዲሠሩ እና ይከፈላቸው የነበረውም በጣም አነስተኛ ደመወዝ እንደሆነ ተገልጿል።

ወደ ጣልያን ያመጧቸው ግለሰቦችም ይህንን አነስተኛ ክፍያ እዳ አለባችሁ በሚል እየወሰዱት ነበር።

እነዚህ ሁለቱ ሕንዳውያን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ሲውሉም 545 ሺህ ዶላር በእጃቸው ይዘው ነበር።

በጣልያን በእርሻ ስፍራዎች ላይ በአገሬው ሠራተኞችም ሆነ በስደተኞች ላይ ከፍተኛ ብዝበዛ ይፈጸምባቸዋል።

በወይን እርሻዎች ወይም በሌሎች የእርሻ ስፍራዎች ላይ የተሰማሩ እነዚህ ሠራተኞች በአደገኛ ሁኔታዎች እንዲሁም አብዛኛውን ጊዜ ውል ሳይፈራረሙ ነው የሚቀጠሩት።

ባለፈው ወር አንድ ሕንዳዊ ፍሬ ለቃሚ ሥራውን ሲያከናውን እጁ በመቆረጡ ምክንያት ሕይወቱ አልፏል። አደጋውን ተከትሎ አሠሪዎቹ ግለሰቡን መንገድ ዳር ትተውት ከሄዱ በኋላም እግሩ ላይ ተጨማሪ አደጋ ደርሶበት ነው ሕይወቱ ያለፈው።

አሠሪዎቹ በቸልተኝነት እና በሰው መግደል ወንጀሎች ምርመራ ተከፍቶባቸዋል።

ፖሊስ ከባርነት የታደጋቸው 33ቱ ሰዎች እያንዳንዳቸው ለወቅታዊ የሥራ ፈቃድ በሚል 1.5 ሚሊዮን ሩፒ (18 ሺህ 554 ዶላር) እንደከፈሉ ፖሊስ ለቢቢሲ ከላከው መግለጫ መረዳት ተችሏል።

ይህንን ገንዘብ ለማሰባሰብ አንዳንዶች የቤተሰቦቻቸውን ንብረት በመያዣነት አስይዘው እንደተበደሩ፣ ሌሎች ደግሞ ገንዘቡን ከአሠሪዎቻቸው ተበድረዋል ተብሏል።

ነገር ግን ጣልያን ከመጡ በኋላ በቀን ከ10 እስከ 12 ሰዓታት እንዲሠሩ የተገደዱ ሲሆን ይከፈላቸው የነበረውም በሰዓት 4 ዩሮ የነበረባቸውን እዳ ለመክፈል መዋሉ ተገልጿል።

ሠራተኞቹ ጣልያንን እንደረገጡ ፓስፓርታቸው እንደተወሰደባቸው እና ከፈራረሰው አፓርትመንታቸው እንዳይወጡም ተከልክለዋል።

“በየዕለቱ ማለዳ ሠራተኞቹ በሸራ በተሸፈኑ ተሽከርካሪዎች ውስጥ በድብቅ እንዲጫኑ ተደርገው ቬሮና ገጠራማ ቦታ ወዳለው የእርሻ ስፍራ ይወሰዱ ነበር” ብሏል የፖሊስ መግለጫ።

ይኖሩበት በነበረው አፓርትመንቶች ላይ በተደረገ ፍተሻ ሠራተኞቹ ንጽህና በጎደለው፣ በፈታኝ እና ውርደት በተሞላበት መልኩ እንዲኖሩ መገደዳቸውን አሳይቷል።

ከባርነት ነጻ የወጡት ሠራተኞች ፓስፖርታቸውን መልሰው የተቀበሉ ሲሆን፣ ወደ ደህና መኖሪያ ቤቶች እና የተሻለ ወደ ሥራ ሁኔታ እንዲዛወሩ ለማድረግ የተለያዩ ተቋማት እየሠሩ ነው።

ሁለቱ ወሮበላ ናቸው የተባሉት ግለሰቦች ከብዝበዛ እና ከባርነት ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ክስ እንደሚመሰረትባቸው ፖሊስን ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።