ካናዳ የዓለማችን የመኪና ስርቆት መናኸሪያ የሆነችው ለምንድነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሎጋን ላፍሬኒዬር በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2022 አንድ ንጋት ተነስቶ የግቢውን ሲመለከት ለወትሮ በር ላይ የምትቆመው መኪናው የለችም።
ራም ሬቤል የተሰኘችው አዲስ ዕቃ ጫኝ መኪናው ደብዛዋ ጠፍቷል።
የደኅንነት ካሜራውን ሲመለከት ሁለት ባለቆብ ሹራብ ያደረጉ ወንዶች ሰብረው ገብተው ሚልተን ኦንታሪዮ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ መኪናውን እያሽከረከሩ ተሰውረዋል።
ከጥቂት ወራት በኋላም ላቡን ጠፍ አድርጎ የገዛት መኪና 8500 ኪሎ ሜትር ርቃ በትምገኘው ጋና ውስጥ የሚገኝ አንድ ድረ-ገፅ ላይ ለሽያጭ ቀርባ ተመለከተ።
“የእኔ መኪና መሆኗን ያወቁት ለልጄ ላፕቶብ ማስቀመጫ ይሆናል ብዬ ከጋቢናው ወንበር ጀርባ የሰቀልኩት ቦርሳ ቆሻሻ መጣያ ሆኖ ማየቴ ነው” ሲል ሎጋን ለቢቢሲ ተናግሯል።
ይህ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የእሱ መኪና መሆኗን የሚያጠቁሙ መለያዎች ተመልክቷል።
“የእኔ መኪና መሆኗን ለማወቅ ምንም አላዳገተኝም፤ ጥርጣሬም አልገባኝም።”
ሎጋን መኪናው የተሰረቀበት ብቸኛው ሰው አይደለም። በአውሮፓውያኑ 2022 በካናዳ 105 ሺህ መኪኖች የስርቆት ሰለባ ሆነዋል። ይህ ማለት በአምስት ደቂቃ አንድ መኪና ይሰረቃል ማለት ነው።
መኪና ከተሰረቀባቸው ካናዳውያን መካከል የፍትሕ ሚኒስትሩ ይገኙበታል። መንግሥት የሰጣቸው ቶዮታ ሃይላንደር ኤክስኤልኢ የተሰኘው መኪና ሁለት ጊዜ የሌቦች ሲሳይ ሆኗል።
ዓለም አቀፉ ፖሊስ ኢንተርፖል ካናዳን አስከፊ የመኪና ስርቆት ካለባቸው 137 አገራት መካከል ከ1 እስከ 10 ካሉት ውስጥ ትካተታለች ይላል። ካናዳ መረጃዎቿን ለዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት መስጠት የጀመረችው ባለፈው የካቲት ነበር።
ባለሥልጣናት እንደሚሉት መኪኖቹ ከተሰረቁ በኋላ ሌላ ወንጀል ይፈፀምባቸዋል፤ አሊያም ለማይጠረጥሩ ካናዳውያን ይሸጣል፤ ካልሆነ ደግሞ በመርከብ ተጭነው ወደ ሌሎች አገራት ተወስደው ይሸጣሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢንተርፖል ካለፈው የካቲት ጀምሮ ከካናዳ የተሰረቁ 1500 መኪናዎች በለተያዩ ክፍለ ዓለማት ተሠራጭተው ተመልክቻለሁ ያለ ሲሆን፣ በየሳምንቱ ከ200 በላይ መኪኖች ወደሌላ አገር ሲገቡ ድንበር ላይ እንደሚያዙ አሳውቋል።
የካናዳ የኢንሹራንስ ቢሮ የመኪና ስርቆት እጅግ ከመስፋፋቱ የተነሳ “ብሔራዊ አደጋ” ነው ያለው ሲሆን፣ መኪኖቹ የኢንሹራንስ ሽፋን የሚሰጡ ተቋማትም ባለፈው ዓመት ብቻ 1.5 ቢሊዮን የካናዳ ዶላር መክፈላቸውን ይናገራል።
የመኪና ስርቆት መስፋፋትን ተከትሎ የአገሪቱ ፖሊስ፤ ዜጎች ተሽከርካሪያቸውን እንዴት ከስርቆት መካለከል እንደሚችሉ የሚያሳይ በራሪ ወረቀት መበተን እና መመሪያ መስጠት ጀምሯል።
የመኪና ስርቆት ያስመረራቸው አንዳንድ ካናዳውያን ደግሞ መከታተያ ቴክኖሎጂ ከመግጠም ጀምሮ ሰፈራቸው ውስጥ በተራ ጥበቃ ማካሄድ ይዘዋል።
አቅሙ ያላቸው ሰዎች ደግሞ ልክ እንደባንክ እና ኤምባሲዎች ከመሬት ውስጥ ብቅ የሚሉ ማገጃ የብረት ምሰሶዎች በመግጠም የመኪና ሌቦችን ለመከላከል እየሞከሩ ነው።
ናውማን ኻን ከቶሮንቶ ወጣ ብላ የምትገኘው ሚሲሳውጋ ነዋሪ ነው። እሱ እና ወንድሙ መኪናቸው ከተሰረቀ በኋላ ነው መኪና እንዳይተላለፍ የሚያግዱ ቋሚዎችን ወደ መግጠም ሥራ ፊቱን ያዞረው።
ኻን እንደሚለው በአንድ ወቅት ከባለቤቱ እና ከሕፃን ልጆቹ ጋር ተኝቶ ሳለ ዘራፊዎች ወደ ቤቱ መጡ። ዘራፊዎቹ ውጭ የቆመውን መርሰዲስ ጂኤልኢ መኪናውን ቁልፍ እየፈለጉ ሳለ ነበር የነቃው። ድምፅ የሰሙት ሌቦች ያሰቡት ሳይሳካላቸው ሮጠው አልምጠዋል።
ይህን ተከትሎ ነው ወደ መኪና ስርቆት መከላከያ ቢዝነስ የገባው ኻን በርካታ ደንበኞቹ መሰል ታሪኮችን እንደሚነግሩት ገልጿል።
“ሥራ በጣም ደርቷል” ይላል ኻን። “አንድ ደንበኛችን በሠፈሩ በጣም ዝርፊያ ከመብዛቱ የተነሳ የግል ጥበቃ ቀጥሮ እንደሚያስጠብቅ ነግሮናል።”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሕዝብ ቁጥሯ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ያነሰው ካናዳ ከሁለቱ አገራት በበለጠ የመኪና ስርቆት እያስቸገራት ነው ይላሉ የአሜሪካው ፍትሕ ቢሮ የስታቲስቲክስ ኃላፊ አሌክሲስ ፒኪየሮ።
“ካናዳ ልክ እንደ አሜሪካ በርካታ የድንበር በሮች ባይኖሯትም የመኪና ስርቆት ግን አሳሳቢ ሆኗል” ይላሉ።
በካናዳ፣ አሜሪካ እና ዩኬ በተለይ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ የመኪና ስርቆት እየጨመረ መጥቷል። በካናዳ ከ100 ሺህ ሰው 262.2 መኪና ይሰረቃል፤ በእንግሊዝ እና በዌልስ ይህ ቁጥር በ100 ሺህ ሰው 220 ነው።
ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ስንመጣ ይህ ቁጥር ከፍ የሚል ሲሆን፣ ከ100 ሺህ ሰው 300 ያክሉ የመኪና ስርቆት ሰለባ ይሆናል ይላል በ2022 የወጣው መረጃ።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የመኪና ስርቆት እየተባባሰ የመጣው በወረርሽኙ ምክንያት የተሽከርካሪ እጥረት ማጋጠሙ እና ያገለገሉ እና አዳዲስ መኪኖች ገበያ በመድራቱ ነው።
የካናዳ አውቶሞቢል ማኅበር አባል የሆኑት ኤሊየት ሲልቨርስታይን እንደሚሉት በተለይ አንዳንድ መኪኖች በገበያው በጣም ተፈላጊ መሆናቸው ዝርፊያ እንዲስፋፋ አድርጓል ይላሉ።
እሳቸው እንደሚሉት ካናዳ ጠረፍ አካባቢ ያለው አሠራር የመኪና ዘራፊዎች በቁጥጥር ሥር እንዳይውሉ ተጠያቂ ነው።
“ጠረፍ ላይ ወደ አገር ውስጥ የሚገባ ዕቃ እንጂ ከአገር የሚወጣው ላይ ትኩረት አይደረግም” የሚሉት ኤሊየት መኪኖች አንድ ጊዜ መርከብ ላይ ከተጫኑ በኋላ ለመቆጣጠር ከባድ መሆኑን ይገልጻሉ።
ፖሊስ ከተሰረቁ መኪኖች መካከል የተወሰኑትን ማስመለስ ችሏል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ባለፈው ጥቅምት የቶሮንቶ ፖሊስ አገልግሎት ለ11 ወራት ባደረገው ምርመራ 60 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር የሚያወጡ 1080 ተሽከርካሪዎችን ማስመለሱን አሳውቋል። በምርመራው ምክንያት 550 ክሶች ተመሥርተዋል።
ከታኅሣሥ አጋማሽ እስከ መጋቢት መጨረሻ ባለው ጊዜ የጠረፍ ጠባቂዎች እና የፖሊስ መኮንኖች በሞንትሪያል ጠረፍ በኩል የሚተላለፉ 400 የጭነት መርከቦችን መርምረው 600 የተሰረቁ መኪኖችን አግኝተዋል።
ባለሙያዎች እንደሚሉት በጠረፍ በኩል የሚተላለፉ መኪኖችን መቆጣጠር እጅግ በጣም ከባድ ነው፤ ምክንያቱም ተሽከርካሪ ብቻ ሳይሆን በጣም በርካታ ዕቃዎች ይጓጓዛሉ።
በ2023 ብቻ በሞንትሪያል ጠረፍ በኩል 1.7 ሚሊዮን ዕቃ ጫኝ መርከቦች ተላልፈዋል።
የካናዳ ጠረፍ ጥበቃ ላይ ያሉ ሠራተኞች ለቁጥጥር በቂ አለመሆናቸው፣ እንዲሁም አስፈላጊው ቴክኖሎጂ አለመገጠሙ እንደ እክል ይጠቀሳሉ።
በመኪና ስርቆት እየታመሰች ባለችው የኦንታሪዮ ግዛት የብራምፕተን ከተማ ከንቲባ የሆኑት ፓትሪክ ብራውን በቅርቡ ወደ አሜሪካ ተጉዘው እንዴት ቁጥጥር እንደሚደረግ ተመልክተው፤ ልምድ ቀስመው ተመልሰዋል።
ባለፈው ግንቦት የካናዳ መንግሥት የጠረፍ ጥበቃውን ለማጠናከር በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለመበጀት ማቀዱን አሳውቋል። የፖሊስን ቁጥጥር ለማጠናከርም ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚመደብ ተሰምቷል።
ራም ሬቤል የተሰኘች መኪናው የተሰረቀችበት ሎጋን ቶዮታ ታንዱራ ገዝቷል። “የህልሜ መኪና” ሲል በእጅጉ የሚሳሳላት መኪና መሆኗን ይገልጣታል። አሁን ሌቦች በቀላሉ እንዳይዘርፉበት የሚያደርግ ቴክኖሎጂ አስገጥሟል።
ነገር ግን ቴክኖሎጂው ዘራፊዎችን ያስደነገጣቸው አይመስልም። ቶዮታ ታንዱራዋን ለመስረቅ የመጡ ዘራፊዎች የኋላውን መስታወት ሰብረው ሲገቡ ነው ሎጋን ከእንቅልፉ ነቅቶ ለፖሊስ የደወለው። ፖሊስ በአራት ደቂቃ የሎጋን ቤት ቢደርስም ሌቦች ደብዛቸው ጠፍቷል።
ሎጋን አዲሱን መኪናውን መስታወት አስገጥሞላት ለመሸጥ ተገዷል።












