በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ መኪና ማሽከርከር ምን ያህል ያዋጣል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢትዮጵያ ስለኤሌክትሪክ መኪኖች ብዙ ይወራል።
ቢበላሹ የሚጠግናቸው ባለሙያ የለም፣ ባትሪያቸው ኪስ ያራቁታል፣ ዕድሜውም አጭር ነው፣ ቻርጅ ማድረግ ፈተና ነው፣ ወኪል የላቸውም፣ መለዋወጫቸውም ውድ ነው ይባላል።
በተጨማሪም ይጓዙበታል የሚባሉትን ያህል ኪሎ ሜትር አይጓዙም፣ ለኢትዮጵያ አይሆኑም. . . ሌላም ሌላም ይባላል።
እነዚህ ስጋቶች አሉባልታ ወይስ እውነት?
ከዚያ በፊት አንድ ነገር እናንሳ!
ዓለም ነዳጅ ከሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች እየተላቀቀ ወደ ኤሌክትሪክ እየተጓዘ ይመስላል። ኢትዮጵያስ?
ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ አሕመድ በአንድ ወቅት የኤሌክትሪክ መኪና “በብዙ መልኩ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ቴክኖሎጂ ነው” ብለዋል።
“ይህቺ አገር ኤሌክትሪክ የማምረት አቅም አላት። ከወዲሁ ይህንን መኪና [የኤሌክትሪክ] መገጣጠም እና ማምረት ከጀመርን የዛሬ አምስት እና አስር ዓመት የምንመኛትን፣ የበለጸገች አገር ለማየት የሚቻል መሆኑን ያመላክታል” ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የትራንስፖርት ዘርፍ የ10 ዓመት ዕቅድ ውስጥ ታዳሽ ኃይል ቅድሚያ ተሰጥቶታል።
በዚህ ዕቅድ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የሕዝብ ማመላለሸ እና አንስተኛ ተሽከርካሪዎች በብዙ ቁጥር ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ታቅዷል።
በኢትዮጵያ የኤክትሪክ መኪና ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚጣለው ግብር ዝቅ ተደርጓል።
ከቀናት በፊት ደግሞ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ “ማንኛውም የቤት አውቶሞቢል የኤለክትሪክ ካልሆነ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ መንግሥት ውሳኔ አሳልፏል” ሲሉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልጸዋል።
ታዲያ የመንግሥት ፍላጎት እና የዓለም ጉዞ እንዲህ ከሆነ፣ በኢትዮጵያ ተሽከርካሪዎቹ ላይ ለምን ጥርጣሬ እና ጥያቄ በዛ? እውነታው ምንድን ነው?
የአውቶሞቲቭ ምርቁ ብሩክ አወቀ የትራንስፖርት አማካሪ ነው።
ሚኪ አወቀ በሚል ስም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከተሽከርካሪዎች ጋር በተያያዘ በሚሠጠው መረጃ ይታወቃል።
ብሩክ፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለነዳጅ የሚወጣ ወጪን በመቀነስ እንዲሁም ከባቢ አየርን ለመጠበቅ ጠቃሚ እንደሆኑ ያነሳል።
እንደ አገር ለነዳጅ የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ እና የውጪ ምንዛሬን ለማዳንም እንዲሁ።
ይህንን ሀሳብ ኢክራም ኢድሪስም ትስማማበታለች።
ኢክራም የመኪና አካል ጥገና ባለሙያ ስትሆን፣ በዚህ ሙያ ላይ ለዓመታት ቆይታለች።
አውቶሞቲቭን የተመለከተ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ያላት ኢክራም በኢትዮጵያ መኪና ነክ ጉዳዮችን በትኩረት ትከታተላች።
“ካርበን የሚለቁ አሮጌ መኪኖች የሚነዱበት ከተሞች ነው ያሉን” የምትለው ኢክራም የኤሌክትሪክ መኪኖች ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ጠቃሚ እንደሆነ ታስረዳለች።
ኮረንቲ ሞተርስ ላለፉት አምስት ዓመታት ገደማ የኤለክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ ያስገባል።
የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ እና ባለቤት አቶ ሚካኤል ከአራት ዓመታት በላይ ኤሌክትሪክ መኪና ነድተዋል።
እሳቸው ኤሌክሪክ መኪና ከሚጠቀስለት ጥቅሞች አንዱ ድምጽ አልባ መሆኑ ነው ይላሉ።
ብሩክ እና ኢክራም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ምቹ መሆኗ ያጠራጥራቸዋል።
አቶ ሚካኤል ደግሞ ብዙ ተስፋዎች ይታያቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጥገና እና ባለሙያዎች
ኢክራም እነዚህ ተሽከርካሪዎች በየጊዜው ‘ሰርቪስ’ የሚደረጉበት እና ችግር ሲያጋጥማቸው የሚጠገኑበት ማዕከላት አሉ ወይ? የሚል ጥያቄ ታነሳለች። በቂ ባለሙያዎችስ?
“መኪኖቹ በብዛት እየገቡ የመሆናቸውን ያህል ባለሙያዎች ላይ ምን ያህል ተሠርቷል? ቀጣይ የሚመረቁ የአውቶሞቲቭ ተማሪዎች የኤሌክትሪክ መኪናን በተመለከተ እየተማሩ ነው ወይ?” የሚል ጥያቄም አስከትላለች።
ቀጥላም እራሳቸውን በራሳቸው ያስተማሩ ግን ያላቸው እውቀት ያልተረጋገጠ ‘ባለሙያዎች’ በአሁኑ ወቅት “ትንሽ መፍትሄ እየሰጡ ነው” ትላለች።
ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች እነዚህ ‘ባለሙያዎች’ ላይ የተመረኮዙ ይሆናል።
ብሩክ፣ “በማንበብ በራሳቸው ተነሳሽነት ሥራ የጀመሩ ባለሙያዎች አሉ። አነሱም ቢሆን በቂ ናቸው የሚል እምነት የለኝም” ሲል ይገልጻል።
በተጨማሪም በኤሌክትሪክ መኪና ላይ ያተኮሩ በቂ የጥገና ማዕከላት አለመኖር ተጠቃሚዎች ላይ ስጋት ሊያጭር እንደሚችል ባለሙያዎቹ ያነሳሉ።
አቶ ሚካኤልም፣ በቂ የጥገና ማዕከላት እና ባለሙያዎች የሉም በሚለው ሐሳብ ይስማማሉ።
መልካሙ ነገር ግን፣ የእነዚህን ተሽከርካሪዎች ችግር መለየት ቀላል መሆኑ ነው ይላሉ።
እንደእሳቸው ገለጻ፣ ችግሩን በቀላሉ በመለየት መቀየር ወይም መስተካክል ያለበትን ነገር የሚጠቁሙ ቴክኖሎጂዎች አሉ።
ለአብት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የኤሌክትሪክ መኪኖች ተገቢ ባልሆነ የኃይል ምንጭ (ቻርጅ) አሞላል ምክንያት ማገናኛቸው (ቻርጀር ፖርት) ላይ ተደጋግሞ ችግር እንደሚከሰት ገልጸው፤ ቴክኖሎጂው ይህንን በፍጥነት እንደሚለይ አስረድተዋል።
ይህ መሆኑ በፍጥነት መፍትሔ ለመስጠት እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በናፍጣ እና ቤንዚን እንደሚሠሩ መኪኖች ዘይት፣ ‘ፊልትሮ’ እና መሰል ነገሮች እንደማይጠቀሙ ገልጸው፣ ይህም ለጥገና ቀላል ያደርጋቸዋል ሲሉ ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባትሪ ዋጋ እና የሚያገለግልበት ዕድሜ
ወደ አገር ውስጥ ለሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ግልጽ የሆነ የባትሪ መስፈረት አልተቀመጠም የሚለው ብሩክ ነው።
“ይህ መኪኖቹ ምን ያህል ያገለግላሉ የሚለውን ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ነው” ካለ በኋላ “አንድ ምስሌ ለማንሳት፣ አገር ውስጥ የሚገጣጠሙ መኪኖች ‘ስገዛው እስከ 400 ኪሎ ሜትር [ቻርጁ ሙሉ ሆኖ] ይሄዳሉ ተብሎ ነበር፤ አዲስ የገዛሁት ወደ 120 ኪሎ ሜትር ወርዶብኛል’ የሚሉ ቅሬታዎችን እንደ ባለሙያ እሰማለሁ” ይላል።
በኢትዮጵያ አብዛኞቹ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚጠቀሙት ሊቲየም ባትሪ ነው። ይህ ባትሪ በጊዜ ሂደት አቅሙ ያሽቆለቁላል።
የሚሰጠው ዋስትና ደግሞ፣ እስከ 10 ዓመት ድረስ ከ80 በመቶ ዝቅ አይለም የሚል ነው።
“አሁን መሬት ላይ ያለውን ሲታይ ግን ዓመት ከስድስት ወር ተጠቅመው ከ50 ፐርሰንት በታች የወረደባቸው አሉ። ከዚህ አንጻር የአስተማማኝነታቸው ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው” ሲል ይገልጻል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባትሪ እጅግ ውድ ነው የሚል መረጃ እንዳላት ኢክራም ትናገራለች። “ባትሪው ከመኪናው ዋጋ እኩል ነው ይባላል” ትላለች።
እዚህ ጋር የአቶ ሚካኤል ሐሳብ ግን የተለየ ነው፤ እሳቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የኤሌክሪክ ተሽከርካሪዎች ዋጋ እየቀነሰ ነው ይላሉ።
ከ10 ዓመታት በኋላ ደግሞ ከዚህም በበለጠ እየቀነሰ እንደሚሄድም ያምናሉ።
ምክንያታቸውን ሲገልጹ፣ አሁን ላይ የሚመረቱት ባትሪዎች በዓይነት እና በብዛት ሰፋ ያሉ መሆናቸውን ነው።
በሌላ በኩል እሳቸው ይህንን ሥራ ከጀመሩ በኋላ ባሉት ዓመታት፣ አንድም ባትሪው አገልግሎት ያቆመ ወይም የተበላሸ ተሽከርካሪ ገጥሟቸው እንደማያውቅ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።

የፎቶው ባለመብት, Nissan
ቻርጅ ማድረግ እና ተያያዥ ጉዳዮች
የኤሌክትሪክ ኃይል ፍሰት ‘በአምፔር’ ይለካል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኃይል መሙያ ደግሞ በ8፣ በ16 እና በ32 አምፔር ይመረታሉ።
ብሩክ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት ተሽከርካሪዎች በፈጣን ቻርጅ ማድረጊያ ከ30 እስከ 40 ደቂቃ ሙሉ ኃይል ሊይዙ እንደሚችሉ ያነሳል።
ችግሩ፣ በአዲስ አበባ የፈጣን ኃይል መሙያዎች አለመኖሩ ነው።
በዚህም ምክንያት ገዢዎች ቤት ውስጥ በሚዘረጋ ነጠላ ‘ፌዝ’ ቻርጅ ለማድረግ ይገደዳሉ።
ለምሳሌ 8 አምፔር ኃይል መሙያ ያለው ተሽከርካሪ ቤት ውስጥ በሚገኝ መደበኛ ኃይል (በ7 ኪሎዋት) ከዜሮ እስከ 100 ‘ቻርጅ’ ለማድረስ ከ12 እስከ 40 ሰዓት ሊፈጅ እንደሚችል ይጠቅሳል።
በትልቁ ኃይል፣ 32 አምፔር ብናሰላው ደግሞ እስከ 8 ሰዓት ሊያስፈልገው ይችላል።
ሆኖም በተመሳሳይ ሰዓት እንደ ምጣድ ያሉ የቤት ውስጥ ቁሶች ጥቅም ላይ ከዋሉ ቆጣሪ ሊመልስ ይችላል።
አቶ ሚካኤልም በዚህ ችግር ይስማሙበታል። በቂ ቻርጅ ማደርጊያ ቦታዎች አለመኖርም አንስተው ድርጅታቸው እዚህ ላይ የመሥራት ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ 100 ‘ፐርሰንት’ የኃይል ከሞላ በኋላ ከሳምንት እስከ 10 ቀን በማገለግል ሊቆይ የሚችል ነው ይላሉ።
ባትሪው፣ ከ20 እስከ 80 ፐርሰንት ለመሙላት በአንጸራዊነት ጊዜ አይወስድም። ከዜሮ እስከ ሃያ እና ከ80 እሰከ 100 ለመድረስ ተጨማሪ የመሙያ ጊዜ ይፈልጋል።
ባትሪው ከዜሮ ተነስቶ 100 ለማድረስ እስከ 12 ሰዓት ሲፈጅ፣ ከ 20 እስከ 80 ግን ከ7 እስከ 8 ሰዓት ይወስዳል።
ወኪል አለመኖር እና የመለዋወጫ ዋጋ
ኢክራም በአንድ ወቀት የሆነውን ስታስታውስ “አንድ ሰው የኤሌክትሪክ መርሴዲስ ወደ ኦርቢስ [በኢትዮጵያ የመርሴዲስ ወኪል] ለሰርቪስ ወስዶ ‘ይህ መኪና በኢትዮጵያ ስታንዳርድ አልተመረተም። እኛ ይህንን የመጠገን ፍቃድ የለንም” ብለው መመለሳቸውን ታስታውሳለች።
በዚህም ሳቢያ የኤሌክትሪክ መኪኖች አሁን ባለው ሁኔታ “ልክ እንደተለመዱት መኪና ሲበላሹ ቶሎ ሰርቪር አግኝቶ የሚመለሱበት አይደሉም” ትላለች።
ወኪሎች ሲኖሩ መኪናው ዋስትና እንዲኖው እና ችግር ሲያግጥም በአምራቹ ኪሳራ እንዲጠገኑ እንሚያደርግ የሚያነሳው ደግሞ ብሩክ ነው።
ኢክራምም “የወኪሎች ጉዳይ በቀላሉ የሚታይ አይደለም” ትለለች።
በቅርቡ ያጋጠማትን ሌላ ጉዳይ ስታነሳ፣ ቮልክስ ዋገን አይዲ 6 መኪና ቁልፉ ጠፍቶ ለብዙ ችግር መዳረጓን ታነሳለች።
“ቁልፉን ለማግኘት እየተሰቃየን ጉዳዩ ወደ መኪና አምራቹ ሄዶ ቁልፍ እንዲያትም ሲጠየቅ የመጀመሪያ ገዢው ካልመጣ” እንደማይሰጥ ማሳወቁን ትነገራለች።
“ነጋዴ ከነጋዴ ተቀባበብሎ ነው መኪናው [ኢትዮጵያ ውስጥ] ባለቤቱ ጋ የደረሰው። ይኼ ነገር ሳይመቻች ኤሌክትሪክ መኪና ብንል እንደተጠቃሚ ችግሮች ይገጥማሉ” ካለች በኋላ ቁልፉ “በደላሎቹ” በመቶ ሺዎች እንደተጠየቀበት ገልጻለች።
እንደ ስፖኪዮ ያሉ መለዋወጫዎችም በመቶ ሺዎች እንደሚጠየቅባቸው አስረድታለች።
በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ለመለዋወጫ ፍላጎት እየዳረገ ያለው ስርቆት ነው የሚሉት አቶ ሚካኤል፣ ዋጋቸው እጅግ የተጋነነ ነው በመባሉ አይስማሙም።
ለዚህ መፍትሔ ይሆናል የሚሉት ደግሞ፣ የሚኖረውን ፍላጎት እየተከተለ አቅርቦት ሲጨምር ዋጋቸው ከሌሎቹ መኪኖች መለዋወጫ ጋር ሊቀራረብ ይችላል ብለው ያምናሉ።
ሆኖም አንዳንድ የመኪና ንግድ ውስጥ ያሉ “ደላሎች” በሚፈጥሩት “ወሬ” ገበያው እንደሚታወክ አንስተዋል።
ከመደበኛው መኪና የተለየ ጎማ ለማይጠቀመው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ “ጎማ እስከ 80 ሺህ ብር እንደተሸጠ” ያስታውሳሉ።
በሌላ በኩል አቶ ሚካኤል እንደሚሉት ቁልፍን የመሰሉ የመኪና ቁሶች ለማግኘት መቸግር ለኤሌክትሪክ መኪና ብቻ ሳይሆን ለዘመናዊ የነዳጅ መኪኖችም እንደሚሠራ ነው።
ይህ ማለት በወኪል አማካኝነት ያልተገዛ እና በነዳጅ የሚሠራ የዘመኑ ተሽከርካሪም ቁልፍ ቢጠፋ ተመሳሳይ ዕጣ ይገጥመዋል።
አቶ ሚካኤል የወኪሎች መኖር የመኪናውን ዋስትና ለማረጋገጥ ያለውን ጥቅም ይስማሙበታል። ሆኖም ወኪል አለመኖሩ የሚያጎድለው ትልቅ ነገር የለም ይላሉ።
እሳቸው በኢትዮጵያ የሚጋጥመው አብዛኛው ችግር ከቻርጅ ጋር የተያያዘ ያልተገባ አጠቀቀም እንደሆነ ነው። በዚያ ሳቢያም ኢትዮጵያ ውስጥ ወኪል ቢኖር እንኳን ለዚህ ችግር ዋስትና ሊሰጥ አይችልም ይላሉ።
“ስለዚህ ወኪል ካለመጣቸው መኪኖቹ [ወደ ኢትዮጵያ] መምጣት የለባቸወም ወደሚል ደምዳሜ መሄድ የለብንም” ብለዋል።
ተሽከርካሪዎቹ በወኪል አማካኝነት ሲመጡ ቁጥጥሩ ሊጠብቅ ስለሚችል የምርት እጥረት በመፍጠር ዋጋቸውን እጅግ ሊያሻቅበው እንደሚችል ይጠቅሳሉ።

በሚጓዙት ኪሎ ሜትር ላይ ያለ ልዩነት
ከኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ጋር በተያያዘ ደጋግሞ የሚነሳው ጥያቄ ‘100 ፐርሰንት ቻርጅ ተደርገው’ ምን ያህል ይጓዛሉ የሚል ነው።
አምራቹ ወይም ሻጩ ይህንን ያህል ይላል። ብሩክ ‘ይህንን ቁጥር አምነን በአንድ ጉዞ በመቶ ኪሎ ሜትሮች እንጓዝ ብንል ጉድ እንሆናለን’ ሲል ይጠቅሳል።
“መኪኖቹ 500 ወይም 600 ኪሎ ሜትር በፉል ቻርጅ ይጓዛሉ ይባላል እንጂ በአንዱ ጉዞ ያለማቋረጥ ‘እንደልብ’ ከተነዱ” ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ መሻገር እንደሚሳናቸው ይገልጻል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሰጫ ‘ፔዳላቸው’ ሳይረገጥ የሚቆይ ከሆነ ራሳቸውን በራሳቸው ኃይል የሚሞሉበት ሥርዓት አላቸው።
“እንደልብ” ሲነዱ ግን ሙሉ በሙሉ ያላቸውን ኃይል ያሟጥጣሉ።
በተጨማሪም፣ ፍጥነትን በሰዓት ከ80 ኪሎ ሜትር በታች ማድረግ እንዲሁም አየር መቆጣጠሪያን (AC) ማጥፋት የግድ ይሆናል።
ያ ካልሆነ ተሽከርካሪዎቹ ከተነገረላቸው ርቀት እጅግ ቀድመው ኃይል ይጨርሳሉ። በተቃራኒው “የነዳጅ መኪኖች ከከተማ ውጪ ሲነዱ የሚጠቀሙት ነዳጅ ይቀንሳል።”
ይህንን ሐሳብ የሚቀበሉት አቶ ሚካኤልም፣ የአየር መቆጣጠሪያ ረጅም ሰዓት ተከፍቶ በሚሽከረከርበት ጊዜ የባትሪውን ኃይል ሊጋራ እንደሚችል ያነሳሉ።
ሆኖም መኪናው የፍጥነት ፔዳሉ ሳይነካ በሚነዳበት ጊዜ ራሱን በራሱ ኃይል መሙላት መቻሉ በቀላሉ የማይታይ ትልቅ ጥቅም መሆኑን ያስረዳሉ።
ለኢትዮጵያ አይሆኑም?
ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት ተሽከርካሪዎች ለኢትዮጵያ የማይሆኑ ናቸው የሚለው ብሩክ፣ አብዛኞቹ መኪኖች የቻይናን ገበያ ታሳቢ ያደረጉ እንደሆኑ ያነሳል።
ለአብነት ‘ዳሽቦርዱን’ እንኳን ብናይ በቻይንኛ ቋንቋ የተጻፈ ነው ይላል።
ኢክራምም እንዲሁ መኪኖች ለኢትዮጵያ የሚመቹ መሆናቸው ላይ ጥያቄ አላት።
አቶ ሚካኤል፣ የኤሌክትሪክ መኪኖች በነዳጅ ኃይል እንደሚንቀሳቀሳቀሱት “ለአፍሪካ፣ ለመካከለኛው ምሥራቅ ወይም ለአውሮፓ ተብለው የሚሠሩበት መነሻ የለም” ይላሉ።
ምክንያት ሲጠቅሱ ይህ የምርት ክፍፍል የሚመጣው ከነዳጅ ጥራት ጋር የተያያዘ መሆኑ ነው።
ሆኖም፣ እጅግ ከፍተኛ ሙቀት ወይም የቅዝቃዜ መጠን ላላቸው አካባቢዎች የተለየ ባትሪ ሊገጠም እንደሚችል በመጥቀስ፣ “ስለዚህ ለቻይና ተብሎ የተሠራ የኤሌክትሪክ መኪና መኖሩን እኔ በግሌ አለውቅም” ይላሉ።
ቀጥለው፣ ‘ውማ’ ከሚሰኘው የኤሌክትሪክ መኪና ውጪ መሠረታዊ ቋንቋው ቻይንኛ ብቻ የሆነ ተሽከርካሪ እንደማያውቁ ይናገራሉ።
ወደ ኢትዮጵያ በስፍት እየገቡ ያሉት ቮልክስ ዋገን፣ ቶዮታ እና ቮለቮን ጨምሮ እንግሊዝኛ እና ሌሎች አማራጮች ያላቸው ናቸው ብለዋል።
ሁሉም ባለሙያዎችን በኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ መኪና የተሰጠው ትኩረት ተገቢነት ቢያስማማቸውም ለእነዚህ ተሽከርካሪዎች የሚያስፈልጉ ግብዓቶች አቅርቦትን መሟላት እንደሚያስፈልግ ይጠቅሳሉ።
ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎችን ጨምሮ በቂ መሠረተ ልማቶችን መዘረጋት፣ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡበትን አሠራር ቀላል ማድረግ፣ የተጠና፣ ፍርሃት እና ጥርጣሬን የማይፈጥሩ ውሳኔዎችን ማሰለፍን በዋናነት አስፈላጊ ናቸው ይላሉ።












