የኤሌክትሪክ መኪኖች በቅርብ ጊዜ ውስጥ ገበያውን ይቆጣጠሩት ይሆን?

የኤሌክትሪክ መኪኖች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

መኪና ስለመግዛት ይቅርና ስለመንዳትም አያስቡ ይሆናል። ስለዚህ ትንበያው ትንሽ ድፍረት የተቀላቀለበት ሊመስል ይችላል።

ሄንሪ ፎርድ ብረት ገጣጥሞ የመጀመሪያውን ማምረቻ በአውሮፓውያኑ 1913 ከመሠረተ ወዲህ የተሽከርካሪዎች ትልቁ አብዮት ጫፍ ላይ ነን።

እርስዎ ከሚያስቡትም በጣም በፍጥነት ሊከሰት ይችላል።

የመኪና ኢንዱስትሪ አጥኚዎች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽያጭ የቤንዚን እና የናፍጣ መኪናዎችን የሚበልጥበትን ጊዜ አልፈናል ብለው ያምናሉ።

በእርግጥም የዓለም ታላላቅ መኪና አምራቾች የሚያስቡትም ይህንኑ ነው።

ጃጉዋር ከአውሮፓውያኑ 2025 ጀምሮ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ብቻ ነው የምታገኙት ብሏል። ቮልቮም ከ2030 ጀምሮ ተመሳሰሳይ እርምጃ እወስዳለሁ እያለ ነው።

ባለፈው ሳምንት የእንግሊዙ የቅንጡ መኪኖች አምራች ሎተስ እአአ ከ2028 ጀምሮ ኤሌክትሪክ መኪኖችን ብቻ ለገበያ አቀርባለሁ ሲል አስታውቋል።

ጉምቱ ስም ያላቸው አምራቾች ብቻም አይደለም ተመሳሳይ ዕቅድ ያላቸው።

ጄኔራል ሞተርስ እአአ በ2035 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ብቻ አመርታለሁ ሲል፤ ፎርድ ደግሞ እስከ 2030 በአውሮፓ የሚሸጡት ሁሉም ተሽከርካሪዎቼ የኤሌክትሪክ ይሆናሉ ብሏል።

ቮልስዋገን በ2030 ከሽያጩ 70 በመቶው የኤሌክትሪክ መኪኖች እንደሚሆኑ አስታውቋል።

ለዚህ ደግሞ መንግሥታት የቤንዚን እና የናፍጣ ተሽከርካሪዎች እንዳይሸጡ ለማገድ ማለማቸው አንድ ምከንያት መሆኑ አሙን ነው።

ነዳጅ በማቃጠል የሚሠራው ሞተርን መቃብር አፋፍ ያደረሰው የቴክኖሎጂ አብዮት ነው። የቴክኖሎጂ አብዮቶች ደግሞ በጣም በፍጥነት የሚከሰቱ ናቸው።

ይህ አብዮት ኤሌክትሪክ ይሆናል። በይነ መረብን ወይም የኢንተርኔትን ጅማሮ ይመልከቱ።

በዚያን ወቅት ኮምፒውተሮች እርስ በእርስ የሚነጋገሩበት አዲስ ዘዴ የዓለማችን መነጋገሪያ ነበር።

ጄፍ ቤዞስ አማዞንን አቋቁሞ ነበር። ጉግል እንደ አልታቪስታ፣ አስክ ጂቭስ እና ያሁ ያሉትን በለጠ። አንዳንድ ኩባንያዎች የማይታመን ዋጋ ወደ ካዝናቸው አስገቡ።

በይነመረብ ልክ እንደ ሁሉም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጉዞው አልጋ በአልጋ አልሆነም። የማቀጃ ጊዜ የሚሰጥ ዝግመተ ለውጥ አልነበረውም።

ዕድገቱ ፈጣን እና ከፍተኛ ነበር። ነባር ንግዶችን አፈራርሶ ሁሉንም አሠራር ለወጠው። በቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ዘንድ ተምዘግዛጊ ኤስ-ከርቭ የተባለውን መንገድ ተከተለ።

በይነመረብን ኤስ-ከርቭ ላይ ማሽከርከር፤ እውነታው የተራዘመ ኤስ ነው።

ሀሳቡ እንዲህ ነው። ፈጠራዎች ቀስ ብለው ጉዞ ይጀምራሉ። ፍላጎት የሚኖራቸውም የቴክኖሎጂ ረሃብተኛ ከሆኑትም በጣም በተራቡት ዘንድ ነው። የኤሌክትሪክ መኪናዎች በዚህ ኤስ ቁልቁል ታችኛው ጫፍ ላይ ይገኛሉ።

ለበይነመረብ ግራፉ በጥቅምት 29 ቀን 1969 ከ 22፡30 ሲል ይጀምራል። ወቅቱ በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የሚገኝ ኮምፒውተር በጥቂት መቶ ማይሎች ርቆ ከሚገኘው የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ኮምፒውተር ጋር መልዕክት የተለዋወጠበት ነው።

ተመራማሪዎቹ መጀመሪያ L፣ ከዚያ O እና በመጨረሻም G ብለው ተየቡ። "login" የሚለውን ቃል ከማጠናቀቃቸው በፊት ሥርዓቱ ተበላሸ።

ከአስር ዓመት በኋላም በኔትወርኩ ላይ ጥቂት መቶ ኮምፒውተሮች ብቻ ነበሩ። ለውጡ ግን ፈጣን ነበር።

በ1990ዎቹ የቴክኖሎጂ ፍቅር ተጠናውቶናል የሚሉት የግል ኮምፒተሮችን መግዛት ጀመሩ።

ገበያው አደገ። ዋጋው በፍጥነት ወደቀ። አፈጻጸሙ ተሻሻለ። ብዙ ሰዎች ወደ በይነመረብ እንዲገቡ ተበረታቱ።

ኤስ (S) በዚህ ወቅት ወደ ላይ መጓዝ ጀመረ። ዕድገቱ ከአእምሮም በላይ ሆነ። በፈረንጆቹ 1995 ብቻ 16 ሚሊዮን ሰዎች በይነመረብ ላይ ነበሩ።

አሁንስ ቁጥሩ ከሦስት ቢሊዮን በላይ ሆኗል። ቀጥሎ ኤስ (S) አግዳሚው ተከትሎ ወደ ኋላ ማዘንበል ይጀምራል።

እውነታው ጋር ሲደረስ በይነመረብ የዕድገቱ ፍጥነት ይቀንሳል።

የዘገመ ጅምር፣ እጅግ ፈጣን ዕድገትን እና መቀዛቀዝን በዘመናዊ ስልኮች፣ በፎቶግራፍ እና አንቲባዮቲክስ በተመሳሳይ ተስተውሏል።

የነዳጅ ዘይት እያቃጠለ የሚንቀሳቀሰው ሞተርም ባለፈው ምዕተ-ዓመት ተመሳሳዩን ዱካ ተከትሏል።

የእንፋሎት ሞተሮች እና ማተሚያዎችም እንዲሁ ነበሩ። እናም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችም ተመሳሳይ መንገድ ይከተላሉ።

በእርግጥ ከበይነመረቡ የበለጠ ረዥም መስመር አላቸው።

የመጀመሪያው የኤሌክትሪክ መኪና በ1830ዎቹ በስኮትላንዳዊው የፈጠራ ባለሙያ ሮበርት አንደርሰን ተሠራ።

ቴክኖሎጂው ለገዢዎች በሚመጥን ዋጋ ለገበያ የቀረበው ባለፉት ጥቂት ዓመታት ነው።

ከ20 ዓመታት በፊት ጄኔራል ሞተርስ EV1 የተባለውን ተሽከርካሪ ለሙከራ አቀረበ። ይህንንም ለመሥራት አንድ ቢሊዮን ዶላር ፈጅቷል።

የኤሌክትሪክ መኪኖችን በሚያሽከረክሩ ሞተሮች፣ በሚቆጣጠሯቸው ኮምፒውተሮች፣ በባትሪ መሙያ ሥርዓቶች እና በመኪኖቹ ዲዛይን ላይ ግዙፍ መሻሻሎችን ተመልክተናል።

በጣም አስገራሚ ለውጥ ግን በዋጋው ላይ ነው።

ልክ ከአስር ዓመት በፊት በአንድ ኪሎዋት በሰዓት የባትሪ ኃይል አንድ ሺህ ዶላር ያስከፍላል ሲሉ በአሜሪካን የተቋቋመው አርኤምአይ ባልደረባ ማዲሊን ታይሰን ተናግረዋል። አሁን 100 ዶላር ነው።

ከባለዘይት ሞተር ተሽከርካሪዎች አንጻር ርካሽ ለመሆን የሚጀምሩበት ነጥብ እንደሆነም ተቆጥሯል።

ከነዳጅ እና ከጥገና አንጻር ብዙ የኤሌክትሪክ መኪኖች ቀድሞውኑም ከነዳጅ ወይም ከናፍጣ መኪኖች የረከሱ ናቸው።

በተመሳሳይ ጊዜና የኃይል ጥግግት በእያንዳንዱ ባትሪ የሚያዘው ኃይል እየጨመረ መሄዱን ይቀጥላል።

ባለፈው ዓመት መኪናን ከአንድ ሚሊዮን ኪሎ ሜትር በላይ ኃይል መስጠት የሚችል የመጀመሪያው ባትሪ በቻይናው ባትሪ አምራች ሲኤቲኤል (CATL) ይፋ ሆኗል።

እንደ ኡበር እና ሊፍት ያሉ ትልልቅ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ኩባንያዎች የቅያሪውን አቅጣጫ እየመሩ ነው። ምክንያቱም ቁጠባው ረዥም ርቀት ላላቸው መኪኖች ከፍተኛ ነው።

የኤሌክትሪክ መኪና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በምን ያህል ፈጣን ይሆናል?

መልሱ በጣም በፍጥነት የሚል ነው።

ልክ በይነመረብ በ90 ዎቹ እንደነበረው የኤሌክትሪክ መኪና ገበያው በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ነው።

በኮርኖናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የመኪና ሽያጭ በአንድ አምስተኛ ቀንሶ ቢቆይም እአአ በ2020 በዓለም አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ መኪኖች ሽያጭ በ43 በመቶ ጨምሮ ወደ 3.2 ሚሊዮን አድጓል።

ቁጥሩ ከጠቅላላው የመኪና ሽያጭ ውስጥ 5 በመቶ ብቻ ነው። ግን ወደ ኤስ የዕድገት መስመር እየገባ ነው።

በ2025 በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚሸጡት አዳዲስ መኪኖች ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት ኤሌክትሪክ ይሆናሉ ሲል የኢንቨስትመንት ባንኩ ዩቢኤስ ግምቱን አስቀምጧል።

ይህ ቁጥር በ2030 ወደ 40 በመቶ ከፍ ይላል። በ2040 በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሸጠው አዲስ መኪና በሙሉ ኤሌክትሪክ ይሆናል ይላል ዩቢኤስ።

ለሌላው ምስጋና ደግሞ አምራቾች በሥራ ላይ የሚገኝ ልምድ ነው።

አንድ ነገር በብዛት በተሠራ መጠን የተሻለ ከመሥራት ባለፈ ርካሽም እንዲሆን እየተደረገ ይሰራል። ለዚያም ነው የቤንዚን እና ናፍጣ መኪናዎችን ጨምሮ ኮምፒውተሮች እና የወጥ ቤት ቁሳቁሶች በጣም ተመጣጣኝ ዋጋ የኖራቸው።

ተመሳሳዩ አካሄድ የባትሪዎችን ዋጋ ሲያሽቆለቁለው የኤሌክትሪክ መኪኖች እየተከተሉ ነው።

በካሊፎርኒያው ሲንግላሪቲ ዩኒቨርስቲ የኃይል እና የአካባቢ ተባባሪ ሊቀመንበር የሆኑት ራሜዝ ናም ወደ አንድ ጫፍ ላይ እየደረስን ነው ብለዋል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከነዳጅ ተሽከርካሪዎች ጋር በዋጋ ተወዳዳሪ ሲሆኑ በፍጥነት ጨዋታው ያበቃል ብለው ያምናሉ።

የቴስላው ንጉሥ ኤሎን መስክም የሚያምነው ይህነኑ ነው።

ባለፈው ወር ሞዴሉ 3 የተባለው ተሽከርካሪ ጥሩ ሽያጭ ያስመዘገበ ምርጥ ብራንድ ሲሆን አዲሱ እና ርካሹ ሞዴል ዋይ [Y] ደግሞ ከየትኛውም የመኪና ዓይነት የበለጠ ሽያጭ እንደሚያስመዘግብ ለባለሃብቶች ይነግራቸው ነበር።

መስክ ለተሰብሳቢዎች "በደንበኞች ዘንድ ስለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ያለው ግንዛቤ እውነተኛ ለውጥ አምጥቷል። ያለን ፍላጎትም እስካሁን ካየነው በእጅግ የላቀ ነው" ሲል ተደምጧል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የቤንዚን እና የናፍጣ ተፎካካሪዎቻቸውን ከመንገድ ከማስወጣታቸው በፊት አንድ ሥራ ይቀራቸዋል።

በጣም አስፈላጊው ነገር ሁሉም ሰው በቤታቸው መኪናው ቢኖራቸውም ባይኖራቸውም መኪናዎቻቸውን በቀላሉ እና በርካሽ ዋጋ ቻርጅ ማድረግ መቻል አለባቸው።

ይህ ሥራ እና ኢንቨስትመንት ቢፈልግም ግን ይሳካል። ከአንድ መቶ ዓመት በፊት የነዳጅ መኪኖችን ገበያ ያሟሟቁት በርካታ የነዳጅ ማደያዎች በፍጥነት እንደተከፈቱት ማለት ነው።