አይፎን አምራቹ ኩባንያ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ማምረት ሊጀምር ነው

የፎክስኮን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የንግ ሊዩ ኩባንያው ከሚያመርተው የኤሌክትሪክ መኪና ጋር
የምስሉ መግለጫ, የፎክስኮን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የንግ ሊዩ ኩባንያው ከሚያመርተው የኤሌክትሪክ መኪና ጋር

የአሜሪካ እና የቻይና ግንኙነት መሻከር ያሳሰበው አይፎን አምራቹ ኩባንያ ፎክስኮን ፊቱን የኤሌክትሪክ መኪኖች ወደማምረት ሊያዞር እንደሆነ ተገለጸ።

የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ የንግ ሊዩ በመጪዎቹ አስርት ዓመታት የሚመሩትን ኩባንያ እድገት የኤሌክትሪክ መኪኖች ምርት ሊያረጋግጥ ይችላል ብለዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለቢቢሲ ሲናገሩ ይህ የታይዋን ኩባንያ የሁለቱ ኃያላን አገራት ግንኙነት መሻከር በንግድ ላይ ሊያመጣ ስለሚችለው ጫና እራሱን ማዘጋጀት አለበት ብለዋል።

የ67 ዓመቱ የፎክስኮን መሪ “የሁለቱ አገራት መሪዎች ለሰላም እና መረጋጋት ቅድሚያ ይሰጣሉ ብለን እናስባለን” ሲሉ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ የንግድ ተቋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንደመሆናቸው መጠን “የከፋ ምን ሊከሰት ይችላል ብዬ ማሰብ አለብኝ” ሲሉ ታይዋን መዲና ከሚገኘው መስሪያ ቤታቸው ሆነው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቻይና የግዛቴ አካል ነች ብላ የምታስባትን ታይዋንን ከተቀረው ዓለም ዘግታ ማቆየት ሊከሰቱ ከሚችሉ አንዱ መጥፎ ክስተት ሊሆን እንደሚችል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይገልጻሉ።

“የንግድ ሥራ መቀጠሉን ከማረጋገጥ እቅድ ጋር በተያያዘ” ፎክስኮን ከምርት ሰራዎቹ ጋር የተያያዙ ሚስጢራዊ ሰነዶችን ወደ ሌሎች አገራት ማለትም ወደ ሜክሲኮ እና ቪዬትናም እየዘዋወረ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አመላክተዋል።

ፎክስኮን ወይም በይፋዊ መጠሪያው ሆን ሃይ ቴክኖሎጂ ኩባንያ እአአ በ1974 የተመሠረተ ሲሆን በ200 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ በዓለማችን ከሚገኙ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ውስጥ ተጠቃሽ ነው።

ኩባንያው በስፋት የሚታወቀው የአፕል ምርት የሆኑትን አይፎን ስልኮችን እና አይማክ ኮምፒየተሮችን በማምረት ቢሆንም ማይክሮሶፍት፣ ሶኒ፣ ዴል እና አማዞን ጋርም አብሮ ይሰራል።

ይህ ኩባንያ ባለፉት አስርት ዓመታት ዋና መቀመጫውን ታይዋን አድርጎ ምርቶችን በአሜሪካ ዲዛይን አድርጎ፤ በቻይና አምርቶ በመላው ዓለም ለገበያ ያቀርብ ነበር።

ይሁን እንጂ ከቀርብ ዓመታት ወዲህ የዋሽንግተን ዲሲ እና የቤይጂንግ ግንኙነት መሻከሩን ተከትሎ ፎክስኮን እራሱን አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ አግኝቷል።

አሜሪካ እና ቻይና በንግድ ጦርነት ውስጥ ከመግባታቸው በተጨማሪ በታይዋን ጉዳይ ጽንፍ ይዘዋል።

ታይዋን ራሷን እንደ ሉዓላዊ ግዛት ትቆጥረለች። አገሪቱ የራሷ የሆነ ሕገ-መንግሥት ያላት፣ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጡ መሪዎች እና ከ300 ሺህ ያላነሰ የጦር ሠራዊት አባላትም ባለቤት ብትሆንም ቻይና ግን እንደ ተገነጠለች ግዛቷ ነው የምትመለከታት።

ቻይና አስፈላጊ ከሆነ በኃይል ታይዋንን መልሳ የግዛቷ አካል ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማትል ከዚህ ቀደም ገልጻለች።

አሜሪካ በበኩሏ ታይዋን ራሷን እንድትከላከል ትረዳለች። ይህን እንድታደርግም የሚያስገድድ ሕግ አላት። አሜሪካ ከታይዋን ጋር ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የለኝም ብትልም የጦር መሳሪያዎችን ግን ስትሸጥላት ቆይታለች።

በንግድ እና ፖለቲካ ውጥረት ባየለበት ቀጠና ውስጥ ንግዱን እያቀላጠፈ ያለው ፎክስኮን ታዲያ ከሁሉም ጋር የንግድ ሥራውን እያስኬደ ሊቀጥል እንደማይችል ባለሙያዎች ይተነብያሉ።

“አሜሪካ እና ቻይና ስትራቴጂክ የሆነ እሽቅድምድም ውስጥ እንደገቡ ማየት እንችላለን። ፎክኮን ከሁለቱም ጋር ንግድ ለማካሄድ እየሞከረ ነው። ግን አሸናፊ ሊሆን የሚችለው አንዱ ብቻ ነው” ሲሉ በዊልሰን ማዕከል የኢሲያ ፕሮግራሞች ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ሺሆኮ ጎቶ ይገልጻሉ።

የፎክስኮን ሥራ አስፈጻሚ ግን ኩባንያቸው በሁሉም አገራት በርካታ ሠራተኞችን ቀጥሮ እያሰራ መሆኑን በማስታወስ አገራቱ ዜጋ ሠራተኞቻቸውን ለመደፍ ሲሉ በኩባንያው ሥራ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ላያሳድሩ እንደሚችሉ ተስፋቸውን ይገልጻሉ።