ቦክሰኛው ማክግሬገር በቅርጫት ኳስ ጨዋታ ወቅት ወሲባዊ ጥቃት አድርሷል ተብሎ ተከሰሰ

ኮነር የቅርጫት ኳስ ጨዋታ እየተመለከተ ሳለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

እውቁ የዩኤፍሲ ተቧቃሹ ኮነር ማክግሬገር በአሜሪካ በቅርጫት ኳስ ጨዋታ ወቅት አንዲት ሴት ላይ ወሲባዊ ጥቃት አድርሷል የሚል ክስ ቀረበበት።

በአሜሪካዋ ማያሚ ከተማ፤ ሂትስ የተሰኘው ቅርጫት ኳስ ክለብ ከናጌትስ ጨዋታ ወቅት ነው ኮነር ጥቃቱን እድርሷል የተባለው።

ቢቢሲ የተመለከተው የክስ መዝገብ እንደሚያሳየው ማክግሬገር በካሴያ ስታድየም በሚገኝ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ነው ጥቃት ፈጽሟል የተባለው።

የኮነር ማክሬገር ጠበቃ “ክሱ የሐሰት ነው። ደንበኛዬ ማክግሬገር በዚህ አንገታቸውን አይደፉም” ብለዋል።

የማያሚ ከተማ ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ምርመራ መጀመሩን ይፋ አድርጓል።

ዩኤፍሲ የተሰኘው የቡጢ ውድድር መድረክ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ ስለክሱ መስማቱንና መረጃዎችን እያሰባሰበ መሆኑን ገልጧል።

ማያሚ ሂት የተሰኘው የቅርጫት ኳስ ክለብም በተመሳሳይ ሙሉ ምርምራ እንደሚከፍት አስታውቋል።

ክሱን ያቀረበችው ሴት ጠበቃ የሆኑት ኤሪየል ሚቼል፤ ደንበኛቸው በፈረንጆቹ ሰኔ 9 ቅርጫት ኳስ እየተመለከተች ሳለ ይህ ክስተት እንደተፈጠረ ተናግረዋል።

ጠበቃዋ ለኮነር ማግሬገር የላኩት ደብዳቤ፤ ክስ አቅራቢዋ በቦክሰኛው ጠባቂዎች በግዴታ ወደ ወንዶች ሽንት ቤት እንድትገባ ተደርጎ ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባት ያትታል።

ደብዳቤው አክሎ ከሳሽ ከሽንት ቤቱ ብትወጣም ቦርሳዋን ጥላ ከወጣች በኋላ የሥፍራው ጠባቂዎችን ተለማምጣ ማስመለስ ችላለች።

ጠበቃዋ ሚቼል በሰጡት ቃለ-መጠይቅ የጥቃቱን የተወሰነ ክፍል የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል እጃቸው ላይ እንደገባ ተናግረዋል።

የማያሚ ከተማ ፖሊስ ለቢቢሲ እንደተናገረው ፖሊስ ስለሆኔታው አቤቱታ የደረሰው እሑድ ሰኔ 11 ነው።

የከተማዋ ፖሊስ ቃል አቀባይ “ይህ ያልተጠናቀቀ ምርመራ ነው ስለዚህ ተጨማሪ አስተያየት ከመስጠት እንቆጠባለን” ሲሉ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።

የቅርጫት ኳስ ጨዋታ ለመመልከት በሥፍራው ተገኝቶ የነበረው ኮነር ማግሬገር የማያሚ ሂትስ አሻንጉሊት ያደረገ ግለሰብን በቦክስ ሲማታ ታይቷል።

ነገር ግን ይህ የሆነው በድንገት ሳይሆን የሕመም ማስታገሻ ማስታወቂያ አካል ነው።

ቢሆንም በቦክስ የተነደለው ግለሰብ ወደ ሆስፒታል አቅንቶ ሕክምና እንደተደረገለት ዘ አትሌቲክ ዘግቧል።