የመጀመሪያው አውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ አወዛጋቢ የሆነበት ምክንያት ምን ነበር?

የማርሴ ቡድን አባላት በ1993 (እአአ) የቻምፒየንስ ሊግን በሸነፉበት ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የማርሴ ቡድን አባላት በ1993 (እአአ) የቻምፒዮንስ ሊግን በሸነፉበት ጊዜ

የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ድፍን ሦስት አሥርታትን አስቆጥሯል። ነገር ግን እንደመጀመሪያው ያለ አከራካሪ የዋንጫ ጨዋታ የለም።

ማርሴ፤ የአውሮፓ ቻምፒዮን ሊግን ያነሳ ብቸኛው የፈረንሳይ ክለብ ነው።

በፈረንጆቹ 1992/93 ውድድሩ ዩሮፓ ካፕ የሚለውን ስም ፍቆ ቻምፒዮንስ ሊግ ይባል ጀመር።

በወቅቱ ማርሴ ዝነኛውን የነፍራንኮ ባሬዚ፣ ፓውሎ ማልዲኒ፣ ፍራንክ ራይካርድ እና ማርኮ ቫን ባስተንን ኤሲ ሚላንን ረትቶ ዋንቻጫ አነሳ።

ባሲል ቦሊ ያስቆጠራት ብቸኛ ጎል ሙኒክ ላይ ለተካሄደው የፍፃሜ ፍልሚያ በቂ ነበረች።

እነ ሊዮኔል ሜሲ፣ ምባፔ እና ኔይማር ከፒኤስጂ ጋር ሊያሳኩት ያልቻሉትን ግምት ያልተሰጠው ማርሴ አሳካ።

ቢሆንም ይህ የማርሴ ድል በውጤት ማስቀየር ቀውስ ስሙ ጠለሸ።

የፈረንሳይ ሊግ 1 ዋንጫን በዚያው ዓመት ያነሳው ማርሴ፣ ውጤት አስቀይሯል ተብሎ ክብሩ ተገፈፈ። ይህ አልበቃ ብሎት ከሊጉ እንዲወርድ ተገደደ።

ጎል አስቆጣሪ ቦሊ እና የክለቡ ፕሬዝደንት በናርድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

መጀመሪያ መልካም መልካሙን እናውራ።

የድሮው ቻምፒዮንስ ሊግ እንደ ዘንድሮው አይደለም። በቡድን ውድድር የሚሳተፉት ስምንት ቡድኖች ብቻ ነበሩ። ማርሴ ምንም ሽንፈት ሳይቀምስ ነው ለፍፃሜ የበቃው።

የክለቡ ፕሬዝዳንት በናርድ ታፔ [ስሙን እንዳይዘነጉ] በ1991 ለዩሮፓ ካፕ ፍፃሜ ደርሰው መሸነፋቸው አንገብግቧቸው ይሄን መዋዕለ ነዋይ ያፈሱት ጀመር።

ግብ ጠባቂው ፋቢያን ባርቴዝ እና ተከላካዩ ማርሴል ዴሳዬ ወደ ክለቡ መጡ። አጥቂው አለን ቦክሲች ፊርማውን አኖረ።

ሦስት ጨዋታዎችን አሸንፈው ሦስቱን አቻ ወጥተው ከምድቡ አልፈው ለፍፃሜ በቁ። ቢሆንም ማንም ዋንጫውን ያነሳሉ ብሎ አልጠበቀም።

የጣሊያኑ ክለብ ከዚያ ቀደም በ89 እና 90 የአውሮፓ ዋንጫን አንስቷል። በምድቡ ስድስቱንም ጨዋታዎች አሸንፎ ነው ለፍፃሜው የበቃው።

ግንቦት 26/1993 ግን ኤሲ ሚላን የማርሴን መረብ መንካት ተሳነው።

በ44ኛው ደቂቃ ቦሊ ከአቤዲ ፔሌ የተሻገረለትን የማዕዘን ምት ኳስ ከኤሲ ሚላን መረብ ላይ አሳረፈው።

ጓሮ በቦርሳ የተቀበረው ብር

የማርሴ 92/93 ውድድር ዘመን ድል መቀዳጀት ይጠለሽ የጀመረው ከፍፃሜው ጨዋታ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ነው።

የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግን ለማንሳት ከሚያደርጉት ሩጫ እኩል አገር ቤት ሊጉን እየመሩ ነበር።

ፒኤስጂ እና ሞናኮ ዋንጫውን ከማርሴ መዳፍ ለመመንተፍ የአቅማቸውን እያደረጉ ነበር። ነገር ግን በመጨረሻው የሊጉ ጨዋታ ማርሴ፤ ቫሌንሲየንስን በመርታት የሚያስፈልገውን ሦስት ነጥብ አገኘ።

ነገር ግን የማርሴው አማካይ ዢን-ዣክ አይደሊ፤ ለቫሌንሲየንሱ ዣክ ግላስማን፤ 250 ሺህ የፈረንሳይ ፍራንክ ጉቦ አቅርቦለታል የሚሉ ወሬዎች መውጣት ጀመሩ።

ክሪስቶፍ ሮበርትን ጨምሮ ሌሎች ሁለት የቫሌንሲየንስ ተጫዋቾች ጉቦ እንደቀረበላቸው ተሰማ። የሮበርት ሚስት የማርሴ ተጫዋቾች ወዳረፉበት ሆቴል ሄዳ ረብጣ ፍራንክ በቦርሳ ይዛ ተመለሰች።

ይህ ገንዘብ በኋላ ላይ ከእናቷ ጓሮ ተቀብሮ ተገኝቷል።

የወቅቱ የማርሴ ቡድን ስብስብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የወንጀል እና የእግር ኳስ ሕግ ጥሰት መርማሪዎች ሥራቸውን ተያያዙት።

ማርሴ የሊግ 1 ዋንጫውን ተነጥቆ ከሊጉ እንዲወርድ በመደረጉ በሚቀጥለው ዓመት የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ እንዳይሆን ታገደ።

የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነት እና የሊግ 1 ዋንጫ ውሰዱ የተባሉት ፒኤስጂዎች ይቅርብን አሉ። ይህ የሆነው የፒኤስጂ ባለቤት የነበረው ካናል+ የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ በደቡብ ፈረንሳይ ያሉ ተመልካቾቹን እንዳያጣ ሰግቶ ነው።

ሦስተኛ የወጣው ሞናኮ በቻምፒዮንስ ሊግ እንዲሳተፍ ሲደረግ፤ የአውሮፓውያኑ 92/93 ውድድር አሸናፊ አልባ ሆኖ ቀረ።

የማርሴ ቡድን በአውሮፓ ውድድር ውጤት ማስቀየሩን የሚያሳይ ማስረጃ ባለመገኘቱ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫውን አልተነጠቀም።

ታፔ [ስማቸውን እንዳልረሳችሁ ተስፋ እናደርጋለን] በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት የሁለት ዓመት እሥር ተከናነቡ።

ከእሳቸው በተጨማሪ አይደሊ ለ18 ወራት ወደ እግር ኳስ ዝር እንዳይል ተደረገ።

አይደሊ በፈረንጆቹ 2006 ባሳተመው መፅሐፍ ከአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ጨዋታ በፊት አንዳች ኃይል ሰጪ መርፌ እንደተወጉ ይናገራል።

ሌሎችም ተጫዋቾች እንዲሁ ኃይል ሰጪ ነገር እንደወሰዱ ተናግረው ያውቃሉ።

ቶኒ ካስካሪኖ ስለተሰጠው መድኃኒት ሲናገር “እስከዛሬ ምን እንደሆነ አላውቅም። ዶክተሩ ያነቃቃሃል ሲል ነው የሰጠኝ። ምን እንደሰጡኝ ባላውቅም የዚያን ቀን አቋሜ ጨመረ። ሕጋዊ ነው ብዬ ባስብም እንዳልሆነ ውስጤ ይነግረኛል ነበር” ይላል።

በጊዜው የማርሴ ተጫዋቾች አበረታች መድኃኒት ወስደው እንደሁ ምርመራ ተደርጎባቸው ደማው ንፁህ ሆኖ ተገኝቷል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር በወቅቱ የተደረገውን ምርመራ እንደ አዲስ ቢያጣራም ምንም ሊያገኝ አልቻለም።

ማርሴዮች የመጀመሪያውን የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊነት ታሪክ ቢሠሩም አወዛጋቢነቱ ግን የሚረሳ አይሆንም።