ቢዮንሴ ስዊድን ውስጥ ለተፈጠረው የዋጋ ግሽበት ምክንያት ሆናለች ተብላ ተወቀሰች

ቢዮንሴ የሙዚቃ ሥራዋን መድረክ ላይ ስታቀርብ

የፎቶው ባለመብት, SIAN BLACKHAM/PA WIRE

የዩክሬኑ ጦርነት አሊያም የአቅርቦት ሰንሰለቱ መበጠስ ለኑሮ ውድነት ምክንያት ይሆናል ብለው አስበው ይሆናል። ስለቢዮንሴ አልሰሙም ማለት ነው።

ባለፈው ወር ቢዮንሴ የሙዚቃ ሥራዋን ለማሳየት አውሮፓን ስታካልል አንዱ መዳረሻዋ ስዊድን ነበር።

የሙዚቃ ኮከቧን ለማየት በመጡ እንግዶች ምክንያት ሆቴልና ምግብ ቤቶች ጠጠር መጣያ አጥተው ከርመዋል።

ስዊድን ምጣኔ ሃብታዊ ቁጥሮችን ስታሰላ የቢዮንሴ ስም ሰነዱ ላይ ተገኝቷል።

አውሮፓዊቷ ሃገር በወርሃ ግንቦት 9.7 በመቶ የዋግ ግሽበት አሳይታለች። ይህ ደግሞ ከተጠበቀው በላይ ነው።

ለዚህ ምክንያት የሆነው የሆቴልና የምግብ ዋጋ ማሻቀቡ መሆኑ ተገልጧል።

የዳንስኬ ባንክ የምጣኔ ሃብት ሙያተኛ የሆኑት ሚካኤል ግራን ቢዮንሴ እንደውም የሆቴል ኢንዱስትሪውን ታነቃቃዋለች ብለው አስበው ነበር።

ነገር ግን የመዝናኛ ሥፍራዎች ዋጋ ለመጨመሩ አንዷ ምክንያት ቢዮንሴ ሳትሆን እንደማትቀር ባለሙያው ይገምታሉ።

“እኔ ቢዮንሴን ለዋጋ ግሽበቱ ተወቃሽ አላረጋትም። ነገር ግን እሷ በስዊድን የሙዚቃ ሥራዋን ለማሳየት ስትመጣ የዋጋ ግሽበት ትንሽ ከፍ ብሏል” ይላሉ።

ቢዮንሴ ከሰባት ዓመታት በኋላ ብቻዋን የሙዚቃ ሥራዋን በተለያዩ ሃገራት ማሳየት ጀምራለች።

ይህ ትልቅ ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ ያመጣል ማለት ከባድ ቢሆንም እስከ መስከረም የሚዘልቀው የዘፋኟ የሙዚቃ ትርዒት 2 ቢሊዮንድ ፓውንድ ገቢ ሊያመጣ እንደሚችል ይገመታል።

ኤርቢኤንቢ የተሰኘው የሆቴል ሰንሰለት ቢዮንሴ የሙዚቃ ሥራዎቿን በምታሳይባቸው አካባቢዎች የተጠቃሚዎች ፍላጎት መጨመሩን ገልጧል።

ቲኬት ይፋ በሆነ በቀናት ጊዜ ውስጥ ያልቅና በትይዩ ገበያ በውድ ዋጋ ይሸጣል።

ለምሳሌ በዩናይትድ ኪንግደም ካርዲፍ በተሰናደው የሙዚቃ ድግስ 60 ሺህ ሰዎች ቢዮንሴን ለማየት መጥተዋል።

ከሊባኖስ፣ አውስትራሊያና አሜሪካ ሳይቀር በመጡ እንግዶች ምክንያት ለንደን ውስጥ ሆቴል ማግኘት ዘበት ነበር።

እንደውም በአንድ ሆቴል በመንግሥት ወጪ ተጠልለው የነበሩ ቤተ አልባ ሰዎች መባረራቸው መነጋገሪያ ሆኖ ከርሟል።

በስዊድኗ ስቶክሆልም ቢዮንሴ በ46 ሺህ ተመልካቾች ፊት ባቀረበችው የሙዚቃ ድግስ በርካታ አሜሪካዊያን ታድመዋል።

በወቅቱ ቲኬት ገበያ ላይ ይሸጥ የነበረው በስዊድን ክሮና ሳይሆን በአሜሪካ ዶላር ነበር።

ቪዚት ስቶክሆልም አሊያም ስቶክሆልምን ይጎብኙ የተሰኘው ተቋም ባለፈው ወር የነበረውን የቱሪዝም ማሻቀብ የቢዮንሴ ተፅዕኖ’ ብሎ ጠርቶታል።

የስዊድን ገበያ የዋጋ ግሽበቱ 9.4 ይሆናል ብሎ ቢጠብቅም ቁጥሩ ግን 9.7 ደርሷል።