ሁለት ሴት ልጆች ተጠልፈውበት የተመሳቀለው የደጊቱ ቤተሰብ ሰቆቃ

በአንዲት ሴት ላይ ለጥቃት የተዘረጉ እጆችን የሚያሳይ ሥዕል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ደጊቱ ዳቃሟ ሲዳማ ክልል፣ ጭሪ ወረዳ፣ ላሌሳ ቀበሌ ነው ተወልዳ ያደገችው።

የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እያለች ለሚኒስትሪ ካርድ የሚያገለግል ፎቶ ተነስተው እንዲያመጡ እንደተነገራቸው ትዝ ይላታል።

ቀኑ ሐሙስ ነው ትላላች ደጊቱ፣ ዓመተምህረቱ ደግሞ 2004።

እና ፎቶ ለመነሳት በአቅራቢያቸው ወደ ሚገኝ ከተማ መሄድ ግድ ይላታል።

መንደራቸው በዛፎች መካከል የሚገኝ፣ እንሰት የከበባቸው ጎጆዎች እዚህም እዚያም የሚታዩበት፣ ጉሬዛ እዚህም እዚያም የሚዘልበት ነው።

ከጎጆዎቹ ውስጥ የነገ ሕልማቸውን ያረገዙ ሕጻናት ውር ውር ይላሉ።

ለወላጆቿ የመጀመሪያ ልጅ የሆነችው ደጊቱ አምስት እህቶች አሏት።

በወቅቱ የ13 ዓመት አዳጊ እንደነበረች የምትናገረው ደጊቱ፣ ፎቶ ለመነሳት ወደ ከተማ የሄደችው ከጓደኛዋ ጋር ነበር።

ደጊቱ በአካባቢው የሞተር ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ቢኖሩም በአቋራጭ በእግር መሄድ ያፈጥናታል።

ፎቶ ተነስተው ሲመለሱ ግን ጓደኛዋ ሞተር እንዲጠቀሙ ወተወተቻት።

የሞተሩ መንገድ ወደ መንደራቸው ለመድረስ ሌላ መንገድ መጠቀሙ እና እርሱ ደግሞ የራቀ መሆኑ ደስ አላለትም።

ደጊቱ የጓደኛዋን ስለመሸ በሞተር እንሂድ የሚል ውትወታ ተቀብላ፣ ሁለቱም በአንድ ሞተር ተሳፍረው መሄድ ሲጀምሩ ከጀርባቸው በርከት ያሉ ጎረምሶች በሞተር ሲከተሏቸው ተመለከተች።

“ጓደኛዬን 'ምንድን ናቸው እነዚህ የሚከተሉን?' ብዬ ስጠይቃት ምን አገባሽ አለችኝ” ትላለች ሁኔታውን ስታስታውስ።

ደጊቱ ግን የጎረምሶቹን የሞተር አጀብ አልወደደችውም። ደጋግማ ጓደኛዋን ብትጠይቅም የምታገኘው መልስ ተመሳሳይ ነበር።

ደጊቱ የሚከተሏትን ጎረምሶች አታውቃቸውም፣ እነርሱ የተሳፈሩበትን ሞተር እየተጠጉ ሲከተሏቸው ልቧ አንዳች ነገር ጠረጠረ።

ጓደኛዋ ተባባሪ ሆና ልታስጠልፋት መሆኗን የጠረጠረችው ደጊቱ ከሞተሩ ላይ ዘልላ ወረደች።

ዘላ ስትወርድ ድንጋይ ላይ ወደቀች።

ድንጋዩ እጇን እና እግሯን ስለመታት መነሳት አልቻለችም።

በአካባቢው ያሉ ሰዎች ጉልበት ይሆኗት ዘንድ፣ ፈጥነው እንዲደርሱላት በማለት ጩኸቷን አቀለጠችው።

የጠላፊዋ ጓደኛ ከወደቀችበት ፀጉሯን ጨምድዶ ይዞ በማንሳት መታት።

ደጊቱ ግን የድረሱልኝ ጥሪዋን ልታቋርጥ አልቻለችም።

በአካባቢው የሚገኙ የፀጥታ አካላት እና የቀበሌ አመራሮች ደረሱላት።

ይህ ለደጊቱ እፎይታ ነበር።

ጎረምሶቹ የመቷት ፊቷ አብጧል፣ የወደቀችበት ድንጋይ እጇን እና እግሯን ልጧታል።

የአካባቢው አስተዳደር አባላት “አይዞሽ ደርሰንልሻል” በማለት እንባዋን ሲያብሱላት ተረጋጋች።

የጠለፋ ሙከራውን ያደረጉት ጎረምሶች በፀጥታ አካላት ታጅበው፣ እርሷም የአካባቢው አስተዳደሪ ይዘዋት በአቅራቢያ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰዱ።

ከፀጥታ አካላቱ የምታገኘው 'አይዞሽ፣ አታልቅሺ' ማባበያ፣ የበዳይዎቿ በቁጥጥር ስር ውሎ እስር ቤት መግባት አረጋጋት።

የፀጥታ አባላቱ፣ አባት እና እናቷ መጥተው እንደሚወስዷት ነገሯት።

“በከተማዋ የምትገኝ አንዲት አነስተኛ ቤት አስቀምጠውኝ ወላጆቼ አንደሚመጡ ቢነግሩኝም እየመሸ መሄዱ ልቤን ሌላ የስጋት ቀጭን ንፋስ ሽው አለው” ትላለች ደጊቱ።

ከለላ ያጣችው ደጊቱ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“ወላጆቼ የታሉ?” ብላ ስትጠይቅ የቀበሌው አስተዳደር እና የፀጥታ አካል አባላት እየመጡ ነው እያሏት ጨለማ የብርሃንን ስፍራ ተረከበ።

ወላጆቼ ይመጣሉ እያለች ተስፋ ስታደርግ የነበረችው ደጊቱ፣ ዐይኗ ከእንቅልፍ ተኳርፎ የማለዳውን ውጋጋን ተቀበለ።

አርብ ማለዳ የፀጥታ አካላቱ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት ጠላፊዋ እና ግብረ አበሮቹ ማምለጣቸውን ነገሯት።

የቤተሰቦቿን ዐይን፣ የእናቷን እቅፍ እና የዘመድ አዝማድን ተገን ትናፍቅ የነበረቸው ደጊቱ ምድር ዞረችባት።

እንባ ፊቷን እያራሰው አባቴ መጥቶ ይወሰደኝ እያለች ብትለምንም፣ ይመጣሉ ከሚል ባዶ ምላሽ በስተቀር መጥቶ የሚታደጋት አልተገኘም።

ረፈድፈድ ሲል ጠላፊዋ እና ግብረ አበሮቹ መጥተው እንዲወስዷት አደረጉ።

ደጊቱ ዳግም ጩኸቷን አቀለጠችው፣ የእንባዋ ከረጢት ተነደለ። የአካባቢው ሰዎች ወጥተው የቀበሌ አመራሮች ለምን ይህንን እንደሚያደርጉ ቢጠይቁ ምላሽ አጡ።

ጠላፊዎች ደጊቱን አንከብክበው በአቅራቢያው ወደሚገኝ ጫካ ይዘዋት ገቡ።

የልጇን መጠለፍ የሰማች እናት ወልዳ አራስ የነበረች ቢሆንም ባዶ እግሯን፣ በአራስ ጉልበቷ እየሮጠች ወደ አመራሮች ቤት ሄደች፤ ሆኖም ሰሚ ሳታገኝ ቀረች።

ጠላፊዎቹ ከፖሊስም ሆነ ከአመራሮች ተቃውሞ ስላልገጠማቸው በማን አለብኝነት እንደፈለጉ ደጊቱን ደበደቧት።

አቆሰሏት። ጫካ ውስጥ በጠላፊዋ ተደፈረች።

እናቷ የልጃቸውን በሕይወት መኖርን መስማት ናፍቀዋል።

በጨካኞች እጅ ተጠልፋ መጫወቻ ስትሆን ማሰብ አልፈለጉም።

የስድስት ሴት ልጆች እናት የሆኑት፣ ወ/ሮ ብዙነሽ አርጊሶ ያላቸው ንብረት ከብቶች ብቻ ነው።

እና አንዷን ጥጃ ሸጠው፣ ማመልከቻ አስጽፈው ልጄ በነጣቂዎች ተወስዳብኝ አድራሻዋ ጠፍቶብኛል እና . . . ብለው ከሰሱ።

የፀጥታ አካላት ግን እናትየው ልጄን ፈልጉልኝ ለሞተር ይሁናችሁ እያሉ የሚሸጉጥላቸውን ገንዘብ ተቀብለው ጫካ ውስጥ ደጊቱን ጠልፎ ለተቀመጠው ጎረምሳ “ልንመጣ ነው ሽሽ” ሲሉ መረጃ ያቀብሉ እንደነበር ቤተሰብ ይናገራል።

ጠላፊው እና ግብረ አበሮቹ ደግሞ ያሉበትን ጫካ በመቀየር ዱካቸውን ያጠፋሉ።

ደጊቱ “ለመጸዳዳት እንኳ ከዐይናቸው እንድርቅ አይፈቅዱም ነበር” ትላለች።

በወጠምሻ ወንዶች ተከብቦ የተፈጥሮ ጥያቄን መመለስ ደግሞ ለእርሷ ከባድ ነበር። ስለዚህ የሚያመጡላትን እህል አልበላም ማለት ጀመረች።

በዚህ ሁኔታ እየተዳከመች፣ ከአንድ ጫካ ወደ ሌላ ጫካ እያዘዋወሯት ሁለት ወር ቆዩ።

“በአንድ ቀን አራት አምስት ጫካ የቀየርንበት ጊዜ ሁሉ አለ።”

ለምንድን ነው ወደ ቤቱ ይዞሽ ያልሄደው? ጫካ ውስጥ ለምንድን ነው ያቆዩሽ? የቢቢሲ ጥያቄ ነበር።

“በወቅቱ እናቴ ክስ አቅርባ ነበር። እኔም አልተስማማሁም። ወደ ቤት ይዞኝ ከሄደ በቀጥታ ፖሊስ መጥቶ ይይዘዋል። ለዚያ ነው።

“እስከዚያ ድረስ አባቴ ልጄን ነው የምፈልገው እያለ ነበር። እናቴም አልተስማማችም። ጥሎሽ [የሽማግሌዎችን ምልጃ] አልተቀበለም ነበር። እኔ የምፈልገው ልጄን ነው እያለ ነበር።”

እራሷን የምትከላከል እጇ ብቻ የሚታይ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በደጊቱ ላይ የተጫነው ሽምግልና

ስድሳ ቀናት በጫካ ውስጥ ደጊቱ ተቀምጣ፣ ሽማግሌዎች የተለያዩ መማለጃዎችን ይዘው የቤተሰቦቿን ቤት ደጋግመው ያንኳኳሉ።

እናት የመጀመሪያ ልጃቸው ድምጽ ጠፍቶባቸው የአራስ ወገባቸውን አስረው እህህ ይላሉ።

አባት በቀናት ብዛት ከዚህ በኋላ ምን ማድረግ ይቻላል ሲሉ ተረቱ።

ሽማግሌዎች ይዘው የመጡትን ስጦታ ተቀበሉ።

የጠላፊው አባት ከተጠላፊዋ አባት ጋር እርቅ አወረዱ።

ጠላፊዋ እና ግብረ አበሮቹ ለደጊቱ ይህንን መርዶ እየተቀባበሉ አረዷት።

“አሁን የምታመጪው ነገር ስለሌለ ምግብሽን ብዪ” ሲሉ ተሳለቁባት።

ዙሪያዋን በጫካ ተከብባ ተገን ትፈልግ የነበረችው ደጊቱ የቆመችበት መሬት ሲከዳት ተሰማት።

ይኼኔ ጠላፊዋ ደጊቱን ከጫካ ወደ ቤት ይዟት ገባ።

በዚህ ወቅት ነው ያላት ተስፋ ራሷ ለራሷ መቆም ብቻ እንደሆነ የወሰነችው።

አባቷ ሽማግሌዎቹ ጋር መስማማታቸውን ከሰማች በኋላ የቀረበላትን ምግብ ጥርግ አድርጋ እየበላች፤ ከጠላፊዋ ጋር ደግ ደጉን መነጋገር ጀመረች።

ይህ ደግሞ ያለ በቂ ምግብ ሁለት ወር መቆየቷ ስጋት የፈጠረባቸው ጎረምሶችን አዘናጋ።

መረጋጋቷን ሲያዩ ወደ እናቱ ቤት ይዘዋት ሄዱ።

እዚያም ስትገባ ፊቷን በሳቅ አፈካችው። ለሚጠይቋት ሁሉ የምትመልሰው በፈገግታ ሆነ።

ከአባቷ ጋር የተደረገው ሽምግልና መሳካት፣ የደጊቱም ፊት በፈገግታ መድመቅ ሁሉንም ዘና አድርጓቸዋል።

“እናቱ ቤት የደረስነው ስምንት ሰዓት አካባቢ ነበር፤ ወደ 12 ሰዓት አካባቢ ሲሆን ሽንቴን መሽናት እንደምፈልግ ነግሬ ወደ ጓሮ ዞር አልኩ።”

ቤተሰቡ በደስታ እያወካ፣ አዲሷ እንግዳቸውን ለማስተናገድ ሽር ጉድ እያለ ነው። እርሷ ግን ከዚህ ሳትፈልግ ከተሰጠችበት ትዳር ራሷን ማዳን እንዳለባት ወስናለች።

ለሽንት ዞር ካለችበት ጓሮ እግሯ ወደመራት እየሮጠች አመለጠች፣ ለዐይን ያዝ ማድረግ ቢጀምርም ጫካ ጫካውን እያሳበረች ከጠላፊዋ እናት ቤት ለመራቅ ጣረች።

እየመሸ ሲሄድ የጅቦች ጩኸት ልቧን በፍርሃት ቢያርደውም እርሷ ግን ዳግም በጠላፊዋ እና በግብረአበሮቹ እጅ መውደቅ አልፈለገችም።

እግሯ እስከ ቻለ፣ ዐይኗ ጨለማውን ሰንጥቆ ማየት እስከደፈረበት ርቀት ገሰገሰች።

ምን ያህል ከጠላፊዋ መንደር እንደራቀች አታውቅም።

የጅብ ጩኸት የጨለማውን ግርማ ሞገስ እየሰነጠቀ ሲመጣ ብቻ ይሰማታል።

ከዚህ በላይ መሄድ አልቻለችም። ከጫካው ሳትወጣ ዛፍ ላይ ወጥታ ለማደር ወሰነች።

ዛፍ ላይ ወጥታ ስታድር እንዳትወድቅ፣ ራሷ ላይ ሸብ የተደረገውን ሻሽ ፈትታ ወገቧን ከግንድ ጋር አሰረችው።

ሰሚ ያጣችው ደጊቱ

በማግስቱም ጫካ ጫካውን እየተጓዘች፣ ዋናውን መንገድ እየተወች ወደ ወረዳ ከተማ ገሰገሰች።

ከሁለት ቀን ጉዞ በኋላ ጭሪ ወረዳ ደረሰች።

“ጭሪ ወረዳ ላይ ዘመድ ቢኖረኝም ወደ እርሱ ለመሄድ ፈራሁ። አባቴ ጥሎሽ ስለተቀበለ ወደ ጠላፊዬ ይመልሰኛል ብዬ ሰጋሁ።”

ጭሪ ወረዳ ስትደርስ መቼም አባቴ ከጠላፊዬ ቤተሰቦች ጋር ቢስማማም፣ ጥሎሽ ቢቀበልም እናቴ ግን አሁንም ቢሆን አትጥለኝም በማለት ወደ ፖሊስ ጣቢያ አመራች።

የአካባቢው አስተዳደር ጋር ቀርባ “ደጊቱ ማለት እኔ ነኝ፤ ተጠልፌ ስወሰድ እናቴ ክስ መስርታ ነበር” እያለች ብታስረዳም ሰሚ ጆሮ አላገኘችም።

ከዚያ ይልቅ ያላግጡባት እንደነበር ታስታውሳለች።

እርሷ እዚያ እያለች ጠላፊው፣ ወንድሞቹ፣ አባቱ እና ግብረ አበሮቹ በጋራ መጡ።

ደጊቱ አቤቱታዋን የሚሰማ፣ በዳይዎቿን በሕግ ቁጥጥር ስር የሚያውል አካል አላገኘችም።

አንድ የፀጥታ አካል ባልደረባ በከተማ ውስጥ ዘመድ ይኖራት እንደሆን ጠየቃት።

እርሷም ዘመድ እንዳላት፣ ነገር ግን አባቷ ከሽማግሌዎች ጋር በመስማማቱ አሳልፎ ሊሰጣት እንደሚችል ያላትን ፍርሃት ገለጸችለት።

“በአደራ እርሱ ጋር እናስቀምጥሻለን” ብለው ወስደው ዘመዷ ጋር በአደራ አስቀመጣት።

አባቷ ልጃቸው የወረዳ ከተማ መጥታ ዘመዳቸው ቤት መቀመጧን ሲሰሙ መጥተው ተመለሺ ሲሉ ተቆጡ፣ አስጠነቀቁ።

አጎቶቿ “የአንቺ ነገር አልቋል፣ ወደ እርሱ ተመለሺ፣ ለምንድን ነው የምትደክሚው፣ ከአሁን በኋላ አንገትሽን መድፋትሽ እኮ ነው” ሲሉ ተቆጡ።

አባቷ እናቷን ሄደው ክሷን እንድታነሳ ማስጠንቀቅ በመጀመራቸው እናቷ እርሷ ጋር መጥተው ያለቅሳሉ።

ደጊቱ ግን አሻፈረኝ አለች።

መጠጊያ የምትፈልገው ደጊቱ

በአደራ ያስጠጋት ዘመዷ በእርሷ ምክንያት ከሌሎች ዘመዶቹ ጋር ሊቆራረጥ መሆኑ አሰጋው።

የፈራው አልቀረም እርሷን በማስጠለሉ ብቻ ከዘመድ ወዳጅ ጋር እንዳይቀላቀል በሽማግሌዎች ተገለለ።

የአገር ባሕል በማፍረሷ፣ ከሽማግሌዎች ቃል በመውጣቷ መጠቋቆሚያ ሆነች።

አንድ ወር በወረዳ ከተማ ያለፍትህ ከቆየች በኋላ ወደ ሐዋሳ መሄድ እንዳለባት ወሰነች።

ሰው ለምና ወደ ሐዋሳ በመምጣት የሴቶች ጉዳይ የእርሷን ጉዳይ እንዲመለከተው አቤት አለች።

ሐዋሳ ከተማ ደርሳ የዞን ሴቶች እና ህፃናት ጉዳይ ጽህፈት ቤት አቤቱታዋን አሰምታ፣ እነርሱም ልብሷን ቀይረው አፅናንተው ወደ ፖሊስ ወስደው ቃሏን ተቀበሉ።

ደጊቱ በዳይዋ ተይዞ ፍትህ አገኛለሁ ብላ ብታስብም ጠላፊዋ እና ግብር አበሮቹ ግን በቁጥጥር ስር ሊውሉ አልቻሉም።

የሐዋሳ ዞን ሴቶች ጉዳይ ደጊቱን በከተማዋ በሚገኝ የሴቶች ማረፊያ ውስጥ አስቀምጧት ጉዳዩን መከታተል ቀጠለ።

በ2004 የተጠለፈችው እና የተደፈረችው ደጊቱ ምንም ፍትህ ሳታገኝ 2005 ዓ.ም መጣ።

ትምህርቷን አቋርጣ ያለ ፍትሕ ዕድሜዋ መባከኑ ሲያብከነክናት ትምህርቴን መከታተል እፈልጋለሁ ስትል የሴቶች ጉዳይ ኃላፊዎችን ጠየቀች።

በቀጣይ በሴቶች እና ህፃናት ቢሮ አማካኝነት ይርጋለም ከተማ ጣሊታ ራይዝ አፕ ማዕከል ተቀላቀለች።

ይህም የሆነው በ2005 ዓ.ም. ሐሙስ ቀን ነው።

ጣሊታ ራይዝ አፕ በክልሉ ውስጥ ለጾታዊ ጥቃት የተጋለጡ ሴቶችን በማስጠለል፣ ፍትሕ እንዲያገኙ ይታገላል።

በጾታዊ ጥቃት በተፈጠሩ እርግዝናዎች የተወለዱ ልጆችን በማሳደግ ይረዳል።

ደጊቱ በወቅቱ ሕክምና እንድታገኝ ይርጋለም ሆስፒታል ሄዳ ታክማ ከተለያዩ ተጠርጣሪ ህመሞች ነፃ መሆኗ ተረጋገጠ።

ያቋረጠችውን ትምህርት ከስምንተኛ ክፍል እንድትቀጥል ተደረገ።

ሆኖም ፍትሕ እንድታገኝ ከዞኑ ሴቶች እና ሕፃናት ጋር ለበርካታ ዓመታት የጣሊታ መሥራች ወ/ሮ አትክልት ጃንካ ቢለፉም አልተሳካም።

የጠላፊው ቤተሰብ ብዙ ገንዘብ በማፍሰስ፣ ጉቦ በመስጠት አልፎም ደብዳቤ በመፃፍ እና በማስፈራራት ፍትሕን ማራቅ እንደቻሉ ትናገራለች።

ጠላፊው ደጊቱ ተጠልላ ባለችት ይርጋለም ዛቻ ጽፎ እንዲደርሳቸው ሲያደርግ፣ ወ/ሮ አትክልት ደጊቱን ወደ አዲስ አበባ አሸሿት።

የደጊቱ ወላጆች ትዳር መፍረስ

ደጊቱ አዲስ አበባ ከገባች በኋላ ከቤተሰቧ ጋር የነበራት ግንኙነት ተቋረጠ። ትኩረቷን ትምህርቷ ላይ አደረገች።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ማጠናቀቋን ተከትሎ የቤተሰቦቿን ሁኔታ ስታጠያይቅ ሁለተኛ እህቷ ተጠልፋ ማግባቷን ሰማች።

ሦስተኛ እህቷም ልትጠለፍ እንደምትችል ስትሰማ ለአሳደገቻት አትክልት ነገረቻት።

ከጭሪ ወረዳ ወጥታ ሐዋሳ ሰው ቤት ተቀጥራ እንድትሰራ አደረገች።

የደጊቱ እና ልጃቸውን ከጠላፊዎች ብርቱ ክንድ ለማስጣል የመሠረቱትን ክስ ለማቋረጥ አለመስማማታቸው በአካባቢያቸው ጥርስ አስነክሶባቸው ነበር።

የአካባቢው ሽማግሌዎችም ከባህሉ ከወጉ ውጪ በመሆናቸው እንዲገለሉ አደረጉ።

ማህበራዊ ሕይወት ላይ ከሌሎች ጋር እንዳይቀላቀሉ፣ የሰሩትን ማንም እንዳይበላው ተደረገ።

ይህ አእምሯቸውን ረበሸው።

እናቷ በዚህ እና የሴቶች ብቻ እናት በመሆናቸው ከባለቤታቸው ጋር ነጋ ጠባ ግጭት ሆነ።

አባትየው ሌላ አግብተው ወንድ ልጅ ወለዱ።

በዚህም የተነሳ የነበራቸውን ንብረት ሁሉ ወደ ሁለተኛዋ ሚስት አዞሩ።

ወ/ሮ ብዙነሽ አርጊሶ የመጀመሪያ ልጃቸውን ከጉያቸው ማጣታቸው ሳያንስ ሁለተኛ ልጃቸው መጠለፏ፣ ሦስተኛ ልጃቸውም ጠለፋ ሽሽት ሐዋሳ መግባቷ ረበሻቸው።

የባለቤታቸው ሌላ አግብቶ መውለድ፣ ንብረታቸውን በሙሉ ወደሌላ ማሸሽ ጤና ነሳቸው።

ወ/ሮ ብዙነሽ ሦስት ልጆች ይዘው የሚኖሩበት ጎጆ ዘመመ፣ በበጋው ከፀሐይ፣ በክረምት ከዝናብ የማያስጥል ጎጆ ውስጥ ሦሰት ሴት ልጆች ይዘው መቀመጣቸው አአምሯቸውን አወከው።

አባቷ ወንድ ወደ ወለደችላቸው አደሉ።

የመጀመሪያ ልጃቸው ድምጽ መጥፋት፣ የሁለተኛ ልጃቸው መጠለፍ፣ የሦስተኛ ልጃቸው ወደ ሐዋሳ ሄዳ ከጉያቸው መራቅ ዓለማቸውን ገለባበጠው።

ደጊቱ በሒሳብ መዝገብ አያያዝ ተመርቃ “እማዬ ደርሼልሻለሁ” ልትል ስትደውል "እናትሽ አእምሮዋ ታሞ ሌሊት ከቤት ወጥታ ለብቻዋ ጎዳና ነው የምታድረው" የሚል መርዶ ሰማች።

ምስቅልቅሉ ያስከተለው መታወክ

ደጊቱ የእናቷ የአእምሮ ታማሚ መሆንን ስትሰማ አሳዳጊዋን ለምና እናቷን ለማሳከም ወደ ይርጋለም አመጧት።

ሦስት እህቶቿንም ወደ ይርጋለም አምጥተው አስቀምጧቸው።

“እናቴ እኔን አታቀኝም፤ የምታወራው የድሮ ታሪክ ነው። አባቴ ምን እንዳደረጋት ብቻ ነው የምታወራው። አልጋ ላይ እያለ መሬት ላይ ኩርምት ብላ ተቀምጣ ያንንም ያንንም ትቀበጣጥራለች” ስትል ያሉበትን የጤና ሁኔታ ትናገራለች።

ይርጋለም ከተማ የአእምሮ ታማሚ እናቷን ከእህቶቿ ጋር ተከራይቶ ለማኖር የኪራይ ቤት ማግኘት ተቸግራ መቆየቷን ደጊቱ ትናገራለች።

የእናቷ ጤና መታወክን፣ በቤት ውስጥ ሴቶች ብቻ መሆናቸውን አከራዮች በተደጋጋሚ ለማከራየት እምቢ በማለታቸው ከከተማው መውጫ አካባቢ ለመከራየት ተገደደች።

ደጊቱ በአሁኑ ጊዜ ትምህርቷን ጨርሳ በሂሳብ መዝገብ አያያዝ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝታ ባሳደጋት ድርጅት ውስጥ የሂሳብ ባለሙያ ሆና እየሰራች ትገኛለች።