ከየትኛውም አገር በተለየ የግል መኪና በመግዛት ባለቤት መሆን ከባድ የሆነባት አገር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሌሎች አገራት በተለየ ሲንጋፖራውያን የመኪና በለቤቶች ላቤን ጠብ አድርጌ የገዛሁት መኪና ነው ቢሉ ያምርባቸዋል።
አገሪቱ መኪና ላይ ታክስ እና ግብር ጥላለች። ታዲያ ይህ ምን አዲስ ነገር አለው? ሊሉ ይችላሉ።
ሲንጋፖር መኪና ለመግዛት የምስክር ወረቀት መያዝ ግዴታ ነው ካለች ዓመታት ተቆጥረዋል። ነገር ግን ይህንን የመኪና መግዛት የምስክር ወረቀት ለማግኘት ከመኪናው ዋጋ በላይ መክፈል ኣስፈልጋል።
አገሪቱ ያወጣችው የመኪና ባለቤትነት አሠራር ታክስ እና ግብሩ ላይ ሲደመርበት መኪና በውድ ዋጋ ከሚሸጥባቸው አገራት ቀዳሚ አድርጓታል።
ካለዚህ የምስክር ወረቀት የመኪና ባለቤት መሆን አይቻልም።
እአአ በ1990 ተግባራዊ የተደረገው የምስክር ወረቀት አሠራር ለ10 ዓመታት ብቻ የሚያገለግል ነው።
ለምሳሌ ትልቅ የቤተሰብ መኪና ለመግዛት አስበዋል እንበል። ይህንን መኪና ለመግዛት የሚያስችለውን የምስክር ወረቀት ቀድመው መግዛት ያስፈልጋል።
ምስክር ወረቀቱ ዋጋ በአሁኑ ወቅት 106,619 ዶላር መድረሱ ተነግሯል። ለዚያውም ከተገኘ ነው።
የምስክር ወረቀቱን ደግሞ ማንም በፈለገበት ጊዜ በቀላሉ ገንዘቡን አውጥቶ ልግዛ ቢል አያገኘውም፤ ምክንያቱም የሚሸጠው ከበርካታ ሰዎች ጋር በጨረታ ነው።
ምስክር ወረቀቶቹ በየሁለት ሳምንቱ ብቻ ለጨረታ ይቀርባሉ።
የሚሸጡት ምስክር ወረቀቶች ብዛት ደግሞ በመንግሥት ቁጥጥር ይደረግባቸዋል።
ሲንጋፖር ይህንን ጥብቅ አሠራር የተከተለችው በአገሪቱ ያለውን ትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነስ ነው። የመኪና ዋጋን በማስወደድ መንገድ ላይ የሚዘወሩትን የግል መኪናዎችን ቁጥር ለመቀነስ በማለም ነው።
በዚህም ሳቢያ የመኪና ዋጋ እጅግ ሲበዛ ውድ ነው። በሲንጋፖር ያለውን የመኪና ዋጋ ከአሜሪካ ጋር በማነጻጸር እንመልከት።
አዲስ ቶዮታ ካምሪ መኪና ለመግዛት አስበዋል እንበል። መኪናውን ሲንጋፖር ላይ ልግዛ ቢሉ 182,759 ዶላር ገደማ ማውጣት ይጠበቅቦታል።
ይህም የምስክር ወረቀቱን እና ታክስን ዋጋ ያካተተ ነው።
ተመሳሳይ መኪና አሜሪካ ውስጥ ለመግዛት ወደ ገበያ ቢወጡ 30,459 ዶላር ገደማ ብቻ ነው መክፈል የሚጠበቅብዎት።
የምስክር ወረቀቱ ዋጋ ከመኪና መኪና ይለያያል። አነስተኛ ተሽከርካሪዎች፣ ሞተር ብስክሌቶች እና የንግድ ተሽከርካሪዎች የተለያየ የምስክር ወረቀት አላቸው። ዋጋቸውም በተመሳሳይ ይለያያል።
በኮቪድ ወረርሽን ወቅት የመኪና ፍላጎት በመቀነሱ የመኪኖቹ ምስክር ወረቀት የጨረታ ዋጋ ቀንሶ ነበር።
የኮቪድ ወረርሽኝ ክልከላዎች መነሳታቸውን ተከትሎ ደግሞ የተሽከርካሪ ገበያ በድጋሚ ማንሰራራት ጀመረ።
በዚህም ምክንያት የተሽከርካሪዎች የምስክር ወረቀት ዋጋም ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሻቀቡን ቀጠለ።
ጨረታ ነውና ለጨረታ የሚቀርቡት የምስክር ወረቀቶች ቁጥርም አነስተኛ በመሆኑ ዋጋው ማሻቀቡ የሚጠበቅ ነው።
መንግሥት በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ዓመት ለገበያ የሚቀርቡ የምስክር ወረቀቶችን ቁጥር እንደሚቀንስም ይፋ አደረጓል።
ይህም ሌላኛው ለምስክር ወረቀቱ ዋጋ ማሻቀብ እንደምክንያት ቀርቧል።
የሲንጋፖር መንግሥት የተለያዩ የተሽከርካሪ የምስክር ወረቀቶችን ለገበያ ያቀርባል።
ዝቅተኛው የመኪና ምስክር ወረቀት ዋጋ 76,028 ዶላር ደርሷል።
ይህ ዝቅተኛ የተባለው ዋጋ እአአ ከ2020 በኋላ እንኳን በሦስት እጥፍ ገደማ ጨምሯል።
‘ኦፕን’ የሚባል የመኪና የምስክር ወረቀት ዓይነት አለ። ይህ ለሁሉም የመኪና ዓይነቶች የሚያገለግል የምስክር ወረቀት ሲሆን፣ ዋጋ 111,118 ዶላር መድረሱ ታውቋል።
ሲንጋፖር የበርካታ ባለሃብቶች አገር ናት። በአንጻራዊነት ትንሽ አገር ብትሆንም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሚሊየነሮች እንዳሏት በየጊዜው ተዘግቧል።
በርካታ ሚሊየነሮች ላላት አገር ይህ ምን ይገርማል ሊባል ይችላል። ይህ ግን ሙሉውን ምስል አያሳይም።
የተራ ሲንጋፖራውያን አማካይ ደሞዝ 51,172 ዶላር ገደማ ነው። በደሞዛቸው በመኪና ዋጋ መካከል ያለው ዋጋ ደግሞ ለርካታዎቹ መኪና መግዛት ለማሰብ እንኳን እንዲቸገሩ ምክንያት ሆኗል።
በርካታ አገራት ዜጎቻቸው የሕዝብ ማመለሻ ዘዴዎችን እንዲጠቀሙ ማበረታት ይዘዋል። ይህ የሲንጋፖር መንግሥትም አቋም ነው።
አገሪቱ በሕዝብ ትራንስፖርት ረገድ የተሻሉ ከሚባሉት የዓለም አገራት ተርታ ትሰለፋለች።
መንግሥት ዘርፉን ለማዘመንም ወገቤን አይልም።
በሚቀጥሉት አስር ዓመታት የአገሪቱን የባቡር መስመር ለማዘመን እና ለማደስ ከ60 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድቧል።
ሲንጋፖር 5.5 ሚሊዮን ሕዝብ አላት። እስካለፈው የፈረንጆች ዓመት ድረስ በአገሪቱ የሚገኙ የግል መኪኖች ቁጥር አንድ ሚሊዮን እንኳን አልደፈነም።
በየጊዜው ለጨረታ የሚቀርቡት እና የመኪና ባለቤት የሚያደርጉት የምስክር ወረቀቶች በየዓመቱ ከአገልግሎት ውጪ በሚሆኑት መኪናዎች ቁጥር ይወሰናሉ።












