ቻይና ጃፓንን በመብለጥ የዓለም ዋነኛዋ መኪና ላኪ አገር ሆነች

መኪና ፋብሪካ ውስጥ የምትሰራ ቻይናዊ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻይና ባለንበት የአውሮፓውያን ዓመት ሦስት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ መኪኖችን ወደ ሌሎች አገራት በመላክ ጃፓንን በመብለጥ የዓለም ቀዳሚ አገር መሆኗን አስታወቃለች።

ቻይና በሦስት ወራት ውስጥ 1 ሚሊዮን 70 ሺህ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሌሎች አገራት መላኳን እና ይህም ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር በ58 በመቶ እንደሚልቅ ባለፈው ሳምንት ይፋ የሆነ አሃዛዊ መረጃ አመልክቷል።

በተመሳሳይ ወቅት ጃፓን ወደ ሌሎች አገራት የላከቻቸው ተሽከርካሪዎች ቁጥር 954 ሺህ 185 የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት በ6 በመቶ አድጓል።

የኤሌክትሪክ መኪና ፍላጎት ከፍ ማለቱ እና ለሩሲያ ገበያ የምትልከው መኪኖች መጠን መጨመሩ ቻይና የምትልካቸው መኪኖች ቁጥር ከፍ እንዲል ምክንያት ሆኗል።

ባለፈው ዓመት ቻይና ጀርመንን በመብለጥ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ተሽከርካሪዎችን በመላክ ሁለተኛዋ የዓለም አገር ሆና ነበር።

የቻይና የጉምሩክ አገልግሎት አስተዳደር እንዳለው ቻይና ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ወደ ውጭ የላከቻቸው ተሽከርካሪዎች ቁጥር 3.2 ሚሊዮን ሲሆን፣ ጀርመን ደግሞ 2.6 ሚሊዮን መኪናዎችን ልካለች።

ቻይና በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ከማምረት እራሷን እያራቀች መሄዷ የመኪና ኢንደስትሪዋ እንዲያደግ አግዟል።

በፈረንጆች 2023 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ቻይና የኤሌክትሪክን ጨምሮ አዲስ የኃይል ምንጭ በሚጠቀሙ መኪኖችን የላከችበት ቀጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ90 በመቶ ጨምሯል።

በቻይና የሚገኙት ቴስላ፣ ኤምጂ እና ቢዋይዲ የተሰኙት ዝነኛ የአሜሪካ ተሽከርካሪ አምራቾች የቻይና የውጭ ሽያጭ እንዲያድግ ጉልህ ሚና ያላቸው ናቸው።

ባለቤትነቱ የኤሎን መስክ የሆነው የኤሌክትሪክ መኪና አምራች በሻንጋይ ግዙፍ ፋብሪካ ያለው ሲሆን፣ ጃፓን እና አውሮፓን ጨምሮ ለቀጠናው ምርቶቹን ይልካል።

ግዙፉ የቴስላ መኪና ፋብሪካ አሁን ላይ እስከ 1.25 ሚሊዮን መኪኖችን በዓመት ማምረት የሚችል ሲሆን፣ ኩባንያው ምርቱን ከዚህም በላይ ከፍ ለማድረግ እየሰራ ነው።

ፋብሪካው ባለፈው ወር 'ዋይ' የተሰኘ የቅንጦት መኪና ለካናዳ ገበያ ለመላክ ምርት ጀምሯል።

በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ምዕራባውያን ሞስኮ ላይ የንግድ ማዕቀብ ከጣሉበት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ቻይና ወደ ሩሲያ የምትልከው ምርት ጨምሯል።

ባለፈው ዓመት ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ እንደ ቮልስ ዋገን እና ቶዮታ ያሉ መኪኖች አምራቾች አገሪቱን ጥለው መውጣታቸው ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ ጂሊ፣ ቼሪ እና ግሬት ዎል የተሰኙትን ጨምሮ የቻይና መኪና አምራች ኩባንያዎች በሩሲያ ያላቸው የገበያ ድርሻ ተመንድጓል።