አቢሲኒያ ‘በድንጋይዋ ከተማ’

ከኢትዮጵያ ውጭ የኢትዮጵያ ምግብ ቤት (ሬስቶራንት) ለመጀመሪያ ጊዜ ብቅ ያለችው በአሜሪካ ውስጥ ነበር።
በየነ ጉልላት የተባለ ፓይለት ለመሆን እየተማረ የነበረ ግለሰብ ሎንግ ቢች፣ ካሊፎርኒያ ውስጥ መኖሪያ ቤትን ወደ ሬስቶራንት ቀይሮ ለአሜሪካውያን እንጀራ እንካችሁ አለ።
ወቅቱም ከዛሬ 57 ዓመታት በፊት ነበር።
ማልኮልም ኤክስ ከተገደለ ከአንድ ዓመት በኋላ፣ በአሜሪካ የጥቁሮች የእኩልነት ጥያቄ የተፈፋመበት፣ የጥቁሮች የሶሻሊስት ፓርቲ ብላክ ፓንተር የተመሠረተበት ወቅት ነበር።
የሬስቶራንቷንም መከፈት አስመልክቶ የአካባቢው ጋዜጣ አንድ ጽሑፍ ይዞ ወጣ።
“በእውነቱ በከተማዋ ውስጥ ያልተለመደ አዲስ የኢትዮጵያ ሬስቶራንት በ10ኛው ጎዳና ተከፍቷል። ቀድሞ መኖሪያ ቤት የነበረው ይህ መጠነኛ ምግብ ቤት 30 ደንበኞችን የሚይዝ ሁለት ክፍል አለው።…ለእራት ከተዘረዘሩት ዶሮን ጨምሮ ዋነኛ አገርኛ ምግብንም ያካትታል። እንደ ምርጫችሁ ከ2 እስከ 4 ዶላር ትከፍላላችሁ” ይላል።
ከኢትዮጵያ ውጭ ዕውቅና ያለው ሬስቶራንት በመክፈት በየነ ፈር ቀዳጅ መሆኑን ሃሪ ክሎማን “መሶብ አክሮስ አሜሪካ፡ ኢትዮፕያን ፉድ ኢን ዘ ዩኤስኤ” በተሰኘው መጽሐፉ ይገልጻል።
ኢትዮጵያ በአሜሪካውያን ምናብ በጣም ሩቅ በምትመስል ሁኔታ ስለ ሬስቶራንቱ በወጣውም አጭር ጽሁፍ ላይ “ከንግሥተ ሳባ ምድር” ሲልም ነው ሬስቶራንቱን የጠራው።
የበየነ ጉልላት በካሊፎርኒያ የተከፈተው የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ለወራት ያህል ብቻ ነበር የቆየው።
በተለያዩ አገራት የኢትዮጵያ ሬስቶራንቶች እንዲከፈቱ በር የከፈቱ እንዲሁም የምግቡን ጣፋጭነት ያስተዋወቁት ደስታ ባይሩ ወይም እማማ ደስታ ናቸው።
በአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ መጨረሻ በዋሽንግተን ዲሲ የተከፈተችው ማማ ደስታ ሬስቶራንት የአጼ ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን መገርሰስ ተከትሎ የመጣው አብዮት ያስከተለውን ደም አፋሳሽ ፍጅት ፈርተው ለተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ከአገር ውጭ ቤት ሆነች።
በድርቆሽ ተወስኖ፣ ትኩስ እንጀራ በወጥ ያምረው የነበረም ዲያስፖራ ቀን ወጣለት።
በሚቀጥሉት ዘመናትም ምግብ፣ ባህል እና ማንነታቸውን ይዘው በርካታ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ስደተኞች ባሕር አቋረጡ።
በተለያዩ አህጉራት በከፈቷቸው ሬስቶራንቶች እንጀራን በዓለም መድረክ ላይ ስፍራ እንዲኖረው አደረጉ።

የፎቶው ባለመብት, Brikti
አቢሲኒያ በድንጋይዋ ከተማ
በቅርቡም የኢትዮጵያ መንግሥትን እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ታሪካዊ ውይይት ለመዘገብ ራስ ገዝ አስተዳደር በሆነችው ዛንዚባር በሄድንበት ወቅት ብቸኛዋን የኢትዮጵያን ሬስቶራንት ጎበኘን።
በውጭ ታሪክ ተመራማሪዎች ዘንድ ጥንታዊ ኢትዮጵያን (የሰሜን ኢትዮጵያን) በሚጠሩባት አቢሲኒያ ተሰይማለች።
አቢሲኒያ - የባሕር ዳርቻዋ መናገሻ፣ የምዕተ ዓመታት የአረብ፣ የፋርስ፣ የሕንድ፣ የአፍሪካ፣ የአውሮፓ አሻራዎችን ለያዘችው ለዛንዚባሯ መዲና ስቶንታውን (የድንጋይዋ ከተማ) ድምቀት ናት።
በዓመት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ወደ ሚጎርፉባት ዛንዚባር የሚመጡ እንግዶችን ታስተናግዳለች።
ዛንዚባርን ለሚጎበኙ የዓለማችን ዜጎች ጥብስ፣ ሽሮ፣ ዶሮ፣ ጠጅ፣ ቡና ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ታሪክንም ታስተምራለች።
በሬስቶራንቷ የአክሱም እና የላሊባላ ሥልጣኔዎችን ታሪክ የሚዘክሩ ጽሑፎች ተሰቅለዋል።
አቢሲኒያ ሬስቶራንት በስቶን ታውን እንደሚገኙት አብዛኞቹ ሬስቶራንቶች በልምላሜ የተሞላች ናት።
የቢቢሲ ዘጋቢዎች ዛንዚባር በነበርንበት ወቅት ለቀናት ያህል በእድሳት ላይ በመሆኗ አገልግሎት እየሰጠች ስላልነበረ፣ ተመጋቢዎችን አግኝተን መጠየቅም ሆነ ድባቡን ማየት አልቻልንም።
ምግቡን ለመቅመስም ዕድሉን አላገኘንም።
ነገር ግን ስቶን ታውን ውስጥ ከሚገኙ ምርጥ ሬስቶራንቶች እንደተመደበች በሙያዋ ሼፍ የሆነችው የሬስቶራንቷ ባለቤት ብሪክቲ ወልዱ ነገረችን።
የዛንዚባር ኢንቨስትመንት ቢሮ እንደኮራባት በመንገር እንዲሁም በዳሬ ሰላም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባት በሚል የሰርቲፊኬት ዕውቅና ሰጥቷታል።
ስለ ሬስቶራንቷ ለማወቅ ኢንተርኔት ላይ የተባሉ ምስክርነቶችን በጥቂቱ ዳሰስን።
“በዓለም ማዕዘናት የኢትዮጵያ ምግብ በሚያቀርቡ ሬስቶራንቶች ውስጥ ተመግበናል። አቢሲኒያ ማሪታይም ባለቤቴን ወደ ልጅነት ትዝታ መለሰቻት። ያደገችበትን ምግብ አስታወሰቻት። በጣም ግሩም ምግብ። መስተንግዶውም የቤተሰብ አይነት ነበር” ይላል አንደኛው ጽሑፍ።
“በዛንዚባር ቆይታችን የአገሬው ሰውም ጎብኚውም አቢሲኒያ እንድንሄድ እና የኢትዮጵያ ምግብን እንድንሞክር በተደጋጋሚ ተመከርን። እኛም እስቲ እንየው ብለን ሄድን። ምግቡም፣ መስተንግዶውም ምስክር ነበር። አስተናጋጆቹ ምን መመገብ እንዳለብን መከሩን፤ እንደ ንጉሥ እና ንግሥት ተንከባክበውን ጣፋጭ ምግብ ተመገብን። ከምግብ በኋላም የሬስቶራንቷ ባለቤት እና ሼፏ ደስ በሚል ፈገግታ ስለ ምግቡ ነገረችን። ስለ ምግቡም ሆነ ደስ ለሚለው አቀባበል እናመሰግናለን” ይላል ሌላኛው ምስክርነት።

“የጀመርነው ሩዝ በዶሮ ወጥ ነው”
አቢሲኒያ የተጀመረችው ከ12 ዓመታት በፊት ነበር።
ሬስቶራንቷ በተጀመረችበትም ወቅት እንጀራ ማግኘት ፈታኝ ስለነበር ዶሮ ወጥ በሩዝ ይቀርብ እንደነበር ብርክቲ ስትናገር እየሳቀች ነው።
በደሴቷ ዛንዚባር ላይ የጤፍ እንጀራ ማግኘት የሚታሰብ ስላልነበረ፣ ብርክቲ እንጀራን በሩዝ ተክታ በዶሮ ወጥ ማቅረብ ጀመረች።
የሬስቶራንቷ የመጀመሪያ ደንበኞችም ‘ጣዕሙን ወደውት’ መምጣት ቀጠሉ።
ከሩዝ በዶሮ ወጥ በመቀጠልም ተከታዩ እንጀራን ከሩዝ ዱቄት መጋገር ነበር።
ሩዝን የእንጀራ መልክ ለማስያዝም ሆነ ለማምጣት ሞከረች። ነገር ግን ፈታኝ ሆነባት።
“አንዳንዴ እጅ ላይ ተጣብቆ እንደ ገንፎ ይሆናል” ረጅም ሳቅ።
የሩዝ እንጀራ ቀላል አይደለም። ለእንጀራ የሚሆነው ዓይነት ሩዝ ደግሞ የተለየ ነው።
ብርክቲ ትጠቀመው የነበረው ሩዝ “ከምጣድ ላይ እንኳን ለማውጣት አስቸጋሪ ነበር” ትላለች።
“ሰው ሲበላው እንደ ገንፎ እያላቀቀ ነበር” የምትለው ብርክቲ “ወጣችን በጣም ይጣፍጥ ነበር” እናም የሬስቶራንቱ ተመጋቢ ጣዕሙን ወዶ መምጣቱን ቀጠለ።
ብርክቲም ተስፋ አልቆረጠችም።
“አይዞሽ” ከሚሏት በተጨማሪ በዛንዚባር ትኖር የነበረች ኢትዮጵያዊቷ መሃንዲስ የሩዝ እንጀራ ሙከራዋ አጋሯ ነበረች።
የሩዙ እንጀራ የእንጀራ መልክ እስኪኖረው ድረስ ሙከራቸውን ቀጠሉ።
ሳይሳካ ሲቀር የሩዝ ሊጥ በተደጋጋሚ መድፋቱ የሙከራው አካል ነበር።
ከዚህ ቀደም ከሩዝ እንጀራ የሞከሩ ቢኖሩም በትክክል አሰራሩን የሚነግራት አልነበረም።
በመጨረሻም አንዲት ኢትዮጵያዊት ለአንድ ወር ቀጥራ አስመጣች።
ይህች ሠራተኛ ናት ከሩዝ እንጀራ መጋገር ያስተማረቻት።
ብርክቲ በሩዝ እንጀራ አልቆመችም። ሌላ አዝርዕትም መሞከር ጀመረች።

የፎቶው ባለመብት, Brikti
የዳጉሳ እንጀራ
ጤፍ ለሺህ ዓመታት የኢትዮጵያውያን እና የኤርትራውያን የምግብ ሆኖ ቆይቷል።
ጤፍ የአዳም እና የሔዋን ምግብ ነበር ከሚሉት ጀምሮ ጥንታዊቷን ‘ኢትዮጵያ’ ለመቶ ዓመታት ገዝቷል የሚባለው ድራጎን ሲገደል ተገኘ ከሚለው ጀምሮ የጤፍ አፈታሪክ ብዙ ነው።
አመጣጡ በትክክል ባይታወቅም ከሺዎች ዓመታት በፊትም ለምግብነት ይውል እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ።
ሆኖም ጤፍን ሁሉ እንደ ልቡ ማግኘት አይችልም።
በተለይም በገጠሪቷ አካባቢዎች ጤፍን ከማሽላ ጋር እንዲሁም ከሌሎች አዝርዕቶች ጋር በማቀላቀል እንጀራ ይጋገራል።
ብርክቲ በአንድ ወቅት ጤፍ አስመጥታ ነበር። ነገር ግን ከአምስት ኪሎ በላይ ማስገባት ስላልተፈቀደላት ነበር ሌላ አማራጭም ያሰበችው።
ብርክቲ ጤፍን በጣዕምም ሆነ በጤና በኩል ባለው ከፍተኛ ጥቅም የሚተካ አዝርዕት ስታስብ ነው ዳጉሳን ያገኘችው።
ዳጉሳንም ከማሽላ ጋር ቀላቅላ እንጀራ መጋገርም ቻለች።
“ትክክለኛ የጤፍ ጣዕም ያለው እንጀራ ነው ያለን” ትላለች።
እንጀራው ቀለል ያለ እና የጤፍ ጣዕም ቢኖረውም የመድረቅ እና የመጥቆር ባህርይ አለው።
በዚህም ምክንያት እንጀራ ጋግሮ ማስቀመጥ የሚባል ነገር የለም።
ትኩስ እንጀራ ብቻ ነው የሚያቀርቡት።
መካከለኛ ወፍጮም ስላላት ዝግጅቱን ቀለል አድርጎላታል።
ሽሮ እና በርበሬም በዚህ ወፍጮ በማዘጋጀት ለሽያጭም ያቀርቡታል።
ሬስቶራንቷ በዓመታት ውስጥ እንጀራ ዝግጅትን ጨምሮ ከፍተኛ ለውጥ አልፋለች።
አቢሲኒያ ሬስቶራንት ለነዋሪውም ሆነ ዛንዚባርን ለሚጎበኙ ቱሪስቶች ጥብስ ከአትክልት ጋር፣ ማኅበራዊ፣ ሽሮ፣ ጠጅ ... እንዲሁም ቤቱ የሚታወቅበት አቢሲኒያ ሰንሻይን ጭማቂ ታቀርባለች።

የፎቶው ባለመብት, Brikti
ምግቧን በልተው በጣዕሙ ተደምመው የሚሄዱትን ያህል ሂሳብ አንከፍልም ብለው የሚያንገራግሩ እንዲሁም “የኢትዮጵያ ምግብ እንዲህ አይሰራም” ብለው አሰራሩን ለማሳየት ወደ ኩሽና የሚገቡም አይታጡም።
ብርክቲ እንደምትለው የሂሳብ አንከፍልም ክርክሮች በተለይ የሚነሱት የምግቡን መጠን ሳያውቁ ካዘዙት ጋር ነው።
እንደ ማኅበራዊ (ስፔሻል) ያሉ ምግቦች መጠኑ ከሁለት በላይ ሰዎች የሚመገቡት እንደሆነ ብርክቲም ሆነ አስተናጋጆቹ ይነግሯቸዋል።
ሆኖም አሻፈረኝ ብለው አምስት ስድስት ምግብ ያዙና “መልሱት የሚሉ” ወይም ሂሳቡ ሲመጣ በዝቷል “አንከፍልም” የሚሉም አይታጡም።
በአተካራ ብቻ አይቆምም።
አንከፍልም ብለው ሲወጡም እነ ብርክቲ ፖሊስ ጠርቶ እንዲከፍሉም ማስገደድ ይጠበቅባቸዋል።
ምግቡ “እንዲህ አይሠራም” የሚሉ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ “ይሄ ቅመም መጨመር አለበት” ብለው ማዕድ ቤት ውስጥ ገብተው ማስተማር የሚቃጣቸው ሕንዳውያንም ብርክቲ አጋጥመዋታል።
በሬስቶራንቷ ውስጥ ብቸኛ ሼፍ የሆነችው ብርክቲ ሁሉንም እንደ አመጣጡ ትቀበላለች።

የፎቶው ባለመብት, Brikti
“ባለ ረከቦቱ ዛንዚባራዊው ስምዖን”
አቢሲኒያ ሬስቶራንት ሥራ በጀመረችበት ወቅት ትታወቅ የነበረው በቡና ዝግጅት ነበር።
ቱሪስቶች የጥንታዊቷ ስቶን ታውን ታሪካዊ ስፍራዎች መለያዎች የሆኑት የሱልጣኖች ቤተ መንግሥት፣ የባሮች ክፍት ገበያ፣ በዛንዚባር የመጀመሪያው ኤሌክትሪክ የገባለት እና በምሥራቅ አፍሪካ አሳንሰር የተገጠመለት ሃውስ ኦፍ ዋንደርስ የቡና ዝግጅትም አንዱ የሚጎበኝ ትዕይንት ሆኖ ነበር።
ዛንዚባራዊው ስምዖን የባህል ልብስ ለብሶ፣ ቄጠማውን ጎዝጉዞ፣ ስኒውን ከነረከቦቱ ይዘረጋል።
ቡናውን ይቆላል፣ ጭሱን ያጫጭሳል፣ ሽርጉድ ይላል፤ ቡናውን ያፈላል።
በርካታ ቱሪስቶች በመደመም የቡና አፈላል ዝግጅቱን በካሜራቸው ለማስቀረት ፎቶ ያነሳሉ።
ቪዲዮም ይቀርጻሉ።
አድናቆታቸውን የሚገልጹትን ያህል የዛንዚባሯን አቢሲኒያ በሚጎበኙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ብዙ ተቀባይነት አልነበረውም።
ከተለያየ አገራት የሚመጡ ኢትዮጵያውያን ይስቁበት፣ ይሳለቁበትም እንዲሁም ፎቶ እያነሱ ያፌዙበት ስለነበር ዛንዚባራዊው ስምዖን መሳቀቅ ጀመረ።
ቡና ማፍላት “የሴት የሥራ ድርሻ ነው” እያሉ መሳቅ እና መሳለቅ ብቻ ሳይሆን “ኧረ እንዲያውም አንጠጣም የሚሉ ነበሩ” ትላለች ብርክቲ።
በዛንዚባር ስቶን ታውን ጆ ኮርነር ተብላ በምትታወቀው ስፍራ ቡና በአደባባይ የሚያፈሉት ወንዶች ናቸው።
ቡናቸውን በቀረፋ፣ በቅርንፉድ እና በዝንጅብል በመቀመም ካፈሉ በኋላ ከባልዲያቸው ሲኒ እያወጡ ቡናውን በአገሬው አጠራር 'ካሃዋ' ሲያድሉም ተመልክተናል።
ምናልባትም ለዚህም ይሆናል ለስምዖን ረከቦት መዘርጋቱ፣ ቡና መቁላቱም ሆነ ማፍላቱ አዲስ ነገር ያልሆነበት።
ብርክቲ እንደምታስታውሰው ስምዖን የቡና ዝግጅቱንም ሆነ ማፍላቱን በጣም ነበር የሚወደው።
“ስኒ አትዘረጋም ከተባለ ያኮርፍ ነበር” በማለት ብርክቲ ትስቃለች።
ሆኖም ፌዝ፣ ሳቅ፣ ስላቁ ሲበዛበት ስምዖንም ቡና ማፍላቱን አቆመ።

የፎቶው ባለመብት, Brikti
አቢሲኒያ እንዴት ተጀመረች?
መቀለ ተወልዳ ያደገችው ብርክቲ በታንዛንያ ለሃያ ዓመታት ያህል ኖራለች።
በአሁኑ ወቅት መኖሪያ ያደረገቻትን እና እንደ አገሯ ስለምታያት ዛንዚባር የሰማችው በአዲስ አበባ ጂቲዜድ ገስት ሃውስ በሼፍነት ተቀጥራ በምትሰራበት ወቅት ነበር።
አለቃዋ ዛንዚባር የሚል ስካርፍ አመጣላት።
በወቅቱ “ዛንዚባር አገር አልመሰለችኝም ነበር” ትላለች ፈገግ ብላ ብርክቲ።
ታንዛንያም ሆነ ዛንዚባር መኖሪያዋ ይሆናሉ የሚለውንም አስባው አታውቅም ነበር።
አብራቸው ትሰራ የነበሩ ሰዎች ወደ ታንዛንያ ሲዛወሩ አብራቸው እንድትሄድ ጠየቋት።
ለረጅም ዓመታት አብራቸው ስለሰራች አላቅማማችም ወደ ታንዛንያ ተጓዘች።
ከመዲናዋ ዳሬ ሰላም በ700 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኢሪንጋ ኑሮን ጀመረች።
ኢሪንጋ ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ነው።
ኢትዮጵያ ለምለም ሲባል ብታድግም “ወይ ልምላሜ” የታንዛንያ ልምላሜ ዐይን ለአዋጅ ሆነባት።
ከዚያም ሬስቶራንት የመክፈት ሃሳቧ የተጠነሰሰው አጋጣሚ ተፈጠረ።
ልጇ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ትማር ስለነበር “ኢንተርናሽናል ናይት” የሚባል ፕሮግራም ይዘጋጃል።
ዝግጅቱም ከተለያዩ አገራት የመጡ ወላጆች ምግባቸውን፣ አለባበሳቸውን፣ ማንነታቸውን የሚያሳዩበት ነበር።
በዚያች ከተማ ብርክቲን ጨምሮ ሁለት ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች የሚያመጧቸው ምግቦች፣ የቡና ዝግጅቱ፣ አለባበስ ሰዉን ያስደመመ ነበር።
በዚህ ወቅት ነበር ለምን “የኢትዮጵያ ሬስቶራንት አትከፍቺም?” የሚል ሃሳብ የተበራከተው።
በነበረችበት ኢሪንጋ ሬስቶራንቷን ለመክፈት ብታስብም ኢትዮጵያውያን ባለመኖራቸው፣ እንዲሁም ያሉትም የውጭ አገር ዜጎች በጎ ፈቃደኛ እና በነጻ የሚያገለግሉ በመሆናቸው ብዙም የሚያስኬድ አልሆነላትም።
በዚህም ወቅት ነበር አንዲት ጓደኛዋ የዛንዚባርን ሃሳብ ያመጣችው።
ብርክቲም ሬስቶራንቷን ለመክፈት ወደ ዛንዚባር አቀናች።
የመጀመሪያዎቹ ወቅቶች ተስፋ አስቆራጭ ነበሩ። ቦታ ማግኘት፣ ለዓለም አቀፍ ሬስቶራንት የሚጠየቀው 300 ሺህ ዶላር ካፒታል መነሻም ማግኘት የማይታሰብ ነበር።
በመጨረሻም የዛንዚባር የኢንቨስትመንት ቢሮ እንደ መጀመሪያ የአፍሪካ ሬስቶራንት ለሙከራ ያህል ተቀበሏት።
አቢሲኒያም በትንሽ ካፒታል ተጀመረች “ትንሿ ኢንቨስተር እኔ ሳልሆን አልቀርም” ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Brikti
“ሼፍ የሆንኩት በአጋጣሚ ነው”
ብርክቲ የተወለደችው መቀለ ሲሆን። እድገቷ ደግሞ በሁለት ከተሞች መቀለ እና ናዝሬት ውስጥ ነው።
አሁን ሕይወቷን የምትመራበትን እንዲሁም አጥብቃ ወደ ምትወደው የሼፍነት ሙያ የገባችው በአጋጣሚ ነው።
“ልጅ እያለሁ የምታወቀው የበላሁበትን ባለማንሳት ነው” ትላለች የልጅነቷን ጊዜ ስታውስ።
አጋጣሚውንም ወደኋላ መለስ ብላ ስታስታውሰው የልጅነት የዋህነቷ ሳቋን ያመጣዋል።
ወደ አዲስ አበባ የመጡ የመቀለ አብሮ አደጎቿን ልትጠይቅ ብትፈልግም ልታገኛቸው አልቻለችም። የት ሄዱ ስትል? ቤይሩት የሚል ምላሽ ተሰጣት።
ቤይሩት በብርክቲ እሳቤ መርካቶ ደርሶ መምጣት እንደሆነ ነበር ያሰበችው።
ለዚያም ነው የጓደኛዋ ወንድም “መሄድ ትፈልጊያለሽ?” ሲላት ያለማቅማማት የእሺታ መልሷን የሰጠችው።
በወቅቱም ለቤተሰቡ ሱቅ እቃ እንድትገዛ አምስት ሺህ ብር ተሰጥቷት ነበር።
ከዚያም ላይ ሁለት ሺህ ቆርጣ ከሰጠችው እንደሚወስዳት ነገራት። ብሩንም ሰጠችው። በወቅቱ ዕድሜዋ 17 አካባቢ የነበረ ሲሆን ዕድሜዋን ከፍ አድርጎ ፓስፖርት አወጣላት።
ለቤተሰቧም ሳትናገር ወደ ቤይሩት አቀናች።
“ግብፅ ስደርስ ነው መጥፋቴን ያወቅኩት፤ ካይሮ ስንደርስ ሩቅ እንዳለሁ ተሰማኝ። ማልቀስ ጀመርኩ” ትላለች ብሪክቲ ያንን ጊዜ ስታስታውሰው።
እንደ ዕድል ሆኖ ቤይሩት ውስጥ መልካም ቤተሰቦች አጋጠሟት። እንክብካቤያቸውንም ስታስታውስ “እንደ ልጃቸው ነበር የሚያዩኝ” ትላለች።
በሦስት ዓመት ቆይታዋም የነበረችባቸው አረብ ቤተሰቦች ትምህርት አስተሟሯት። የምግብ ሙያም ተማረች።
ወደ አገር ቤት ስትመለስም የሼፍነት ሙያዋ ሀ ብሎ ተጀመረ። የሕይወቷም መስመሯም ሆነ።

የፎቶው ባለመብት, Brikti
“ዛንዚባራውያኑ ዘይቱኑ የሚል ስም ሰጥተውኛል”
ብርክቲ አሁን የአገሬው ብሔራዊ ቋንቋን የሆነውን ስዋሂሊ አቀላጥፋ ትናገራለች።
ብርክቲ ራሷን እንደ ዛንዚባራዊ ነው የምታየው።
የዛንዚባርም ዜግነት ለማግኘት ጠይቃለች።
ሕዝቡ ያለው መተሳሰብ፣ ያሳያት ፍቅር ከኢትዮጵያ ምንም እንዳትናፍቅ አድርጓታል።
ቤተሰብ ሆነዋታል፣ ስትታመም፣ ስትጠፋ ፈላጊዎቿ ናቸው።
ቤቷ ወይም ሬስቶራንቷ ድረስ መጥተው “በደህናሽ ነው ወይ? አላየንሽም?” ብለው ይጠይቋታል።
ካልታዬች ያስጨንቃቸዋል። ኢድ ሲሆን ቤታቸው ትሄዳለች። ቤቷ ለበዓል ይመጣሉ።
ኮሌጅ ተማሪ የሆነችው ልጇ ቤተሰቦችም ጓደኞቿ ናቸው።
ዛንዚባራዊያኑም “ዘይቱኑ” የሚል ስም ሰጥተዋታል።
ገና ወደ ዛንዚባር እንደመጣች የሚነግሯትን ዋጋ ተቀብላ ነበር እቃ የምትገዛው።
የኋላ፣ የኋላ በጣም ተከራካሪ ስለወጣት ነው ዘይቱኑ (የወይራ ዘይት) ሲሉ መጠሪያ ያወጡላት።
“በጣም መልካም ሕዝብ ነው። ሰላምተኞች ናቸው። መንገድ ላይ መተላለፍ የለም። ሕዝቡ በጣም የተረጋጋ ነው” ትላለች።
እንደ አገርም ሆነ እንደ ሕዝብ መረጋጋት ይታይባቸዋል ብላ የምትጠቅሰው ብሔራዊ መዝሙራቸውን ነው።
“አምላክ የታንዛንያን ሕዝብ ይባርክ፣ ሴቶች ልጆቿን፣ ወንዶች ልጆቿን፣ ምድሯን ይባርክ” የሚለው የስዋሂሊ ብሔራዊ መዝሙር “ዝም ብለው ሲበራረኩ እና ሲመራረቁ ነው” በምናቤ የሚታየኝ ትላለች ብርክቲ ወይም በእነሱ አጠራር ዘይቱኑ።












