በቻይና ጦር ሠራዊት ላይ የቀለደው ኮሜዲያን ለእስር ተዳረገ

የቻይና ጦር ሠራዊት አባላት

የፎቶው ባለመብት, AFP

ቻይናዊው ኮሜዲያን የውሾቹን ባህሪ ከአገሪቱ ጦር ሠራዊት መሪ መፈክር ጋር በማነጻጸር ባቀረበው ቀልድ ምክንያት ለእስር ተዳረገ።

ኮሜዲያኑን ይህንን የቻይና መንግሥትን ያስቆጣውን ቀልድ እንዲያቀርብ ያደረገው ድርጅትም ወደ ሁለት ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ቅጣት ተጥሎበታል።

የቻይናን ጦር ሠራዊት ክብርን የሚነካ ቀልድ አቅርቧል የተባለው ኮሜዲያን ሊይ እስከ እስር የሚደርስ ቅጣት ሊጠብቀው እንደሚችል ተነግሯል።

የቤይጂን ፖሊስ “ከባድ ማኅበራዊ ተጽእኖ አስከትሏል” ባለው በኮሜዲያኑ ቀልድ ላይ ይፋዊ ምርመራ እያካሄደ መሆኑንም አመልክቷል።

ኮሜዲያኑ ሊይ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ የአገሪቱን ጦር ሠራዊት በሚመለከት ባቀረበው ቀልድ “በጣሙን ማፈሩን እና መጸጸቱን በመግለጽ” ይቅርታ ጠይቋል።

ኮሜዲያኑ ባለሥልጣናትን ያስቆጣውን ቀልድ ባለፈው ቅዳሜ በዋና ከተማዋ ቤይጂንግ ውስጥ ነበር ያቀረበው።

በዝግጅቱ ላይ ያሉትን ውሾች በማንሳት የቻይና ጦር ሠራዊት መሪ መፈክር አካል የሆነውን ‘ለማሸነፍ ታገሉ፣ ምሳሌ የሚሆን ባህሪ ፍጠሩ’ የሚሉትን ቃላት ተጠቅሞ መሳለቂያ አድረጓል ተብሎ ነው ለእስር የተዳረገው።

ይህ መሪ መፈክር ከ10 ዓመት በፊት የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ለአገራቸው ጦር ሠራዊት ግብ እንዲሆን ይፋ ካደረጉት መመሪያ የተወሰደ ክፍል ነው።

ዌቦ በተባለው ከትዊተር ጋር በሚመሳሰለው የቻይና የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ላይ በተሰራጨ የኮሜዲያኑ ድምጽ ላይ ተመልካቾች ሲስቁ ይሰማል።

ይህ ቀልድ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት የተሰራጨ ሲሆን፣ አንዳንድ ሰዎችም በኮሜዲያኑ ቀልድ መበሳጨታቸውን ሲገልጹ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ የኮሜዲያኑ ሊይ የዌቦ አካውንት የታገደ ሲሆን፣ ኮሜዲያኑን ቀጥሮ ቀልድ እንዲያቀርብ ያደረገው ‘ሻንጋይ ዢያጉ’ የተባለው ድርጅትም ቤይጂንግ ውስጥ እንዳይሰራ ታግዷል።

በቤይጂንግ የቻይና ባህል ሚኒስቴር ክፍልም “ታላቁን የቻይና ሕዝባዊ ሠራዊትን የሚሳደብ ማንኛውም ድርጅት ዋና ከተማ ቤይጂንግን እንደመድረክ እንዲጠቀም ፈጽሞ አንፈቅድም” በማለት ባወጣው መግለጫ የጣለውን እግድ አስታውቋል።

የኮሜዲ ዝግጅቱን ባሰናዳው ድርጅት ላይ ከፍተኛ የተባለ የገንዘብ ቅጣት የተጣለ ሲሆን፣ ይህም ተመሳሳይ ከባድ መቀጮን በመፍራት በቻይና ውስጥ የሚቀርቡ የኮሜዲ ዝግጅቶችን እንዲጠፉ ሊያደርጋቸው ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።