የሪፐብሊካኖች ‘ፋሽን’ ሆኖ የሰነበተው የትራምፕ ጆሮ መሸፈኛ ፋሻ ለምን መነጋገሪያ ሆነ?

የፎቶው ባለመብት, EPA
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አሁን ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ፕሬዝዳንት ለመሆን ዕጩ ሆነው በቀረቡት ዶናልድ ትራምፕ ላይ የተጸመው የግድያ ሙከራ ሳምነቱን ሙሉ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል።
ከጥቃቱ ፈጻሚ ጥይት እሳቸው እንዳሉት “በዕድል እና በፈጣሪ ጥበቃ” ለጥቂት ባይተርፉ ኖሮ የእሳቸው ዕጣ ፈንታ ብቻ ሳይሆን የአሜሪካ አጠቃላይ ሁኔታ ምን ሊሆን ይችል እንደነበር መገመት አዳጋች መሆኑ ሲነገር ቆይቷል።
ትራምፕ ላይ የተተኮሰው ጥይት ጭንቅላታቸውን ሳይመታ ቀኝ ጆሯቸውን ጨርፎ ሊያልፍ የቻለው ንግግር በሚያደርጉበት ጊዜ ፊታቸውን መለስ በማድረጋቸው እንደሆነ ቪዲዮዎች አሳይተዋል።
ይህ ክስተት ፕሬዝዳንት ባይደንን ጨምሮ አሜሪካውያንን ያስደነገጠ ሲሆን፣ ትራምፕ ከጆሯቸው የሚፈሰው ደም በከፊል ፊታቸው ላይ እየወረደ እዚያው መድረክ ላይ የተነሷቸው ፎቶዎች የዓለም መገናኛ ብዙኃንን የፊት ገጾችን ተቆጣጠረውት ሰንብተዋል።
በተለይ ትራምፕ በጠባቂቻቸው መካከል ሆነው እጃቸውን ጨምብጠው ወደ ላይ በማንሳት በተቆጣ ገጽታ የተነሷቸው ፎቶግራፎች የምርጫ ዘመቻቸው ዋኛ መለያ ለመሆን ተቃርቧል።
የግድያ ሙከራውን ተከትሎ በሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊዎች እና ማንን እንደሚመርጡ ባልወሰኑ አሜሪካውያን ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት የጨመረው ትራምፕ፤ ከፓርቲያቸው ቁልፍ ሰዎች ጭምር ድጋፍ እየተነፈጋቸው ያሉትን ፕሬዝዳንት ባይደንን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ እየተነገረ ነው።

የፎቶው ባለመብት, AP
ከጥቃቱ በኋላ ትራምፕ በዊስከንሲን
ቅዳሜ ሐምሌ 6/2016 ዓ.ም. ፔንሲልቬንያ ግዛት በትለር ከተማ በምርጫ ዘመቻ ላይ ሳሉ በጥይት የተመቱት ትራምፕ በፕሬዝዳንታዊ የጥበቃ አባላት (ሴክሬት ሰርቪስ) ታጅበው ወደ ሕክምና ከተወሰዱ በኋላ ለሕይወታቸው የሚሰጋ ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ያሳወቁት እራሳቸው ነበሩ።
ለቆሰለው ቀኝ ጆሯቸው ሕክምና ካገኙ በኋላ ሰኞ የሚጀመረው የፓርቲያቸው ጉባኤ በእሳቸው ምክንያት ለሌላ ጊዜ እንደማይተላለፍ በማሳወቅ ጊዜ ሳያጠፉ ነበር ወደ ዊስከንሲን የተጓዙት።
በጉባኤው መጀመሪያ ላይ ሁሉም ታዳሚ ትራምፕን በአካል በማየት የደረሰባቸውን ጉዳት ለማወቅ በጉጉት እየጠበቀ የነበረ ሲሆን፣ ቀኝ ጆሯቸው አሁን የትራምፕ መለያ በሆነውን ነጭ ፋሻ ተሸፍኖ በመድረክ ላይ ከጥቃቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ታይተዋል።
ከተፈጸመባቸው የግድያ ሙከራ በኋላ ከሰኞ ጀምሮ እስከ ሐሙስ በዊስከንሲን ግዛት ሚሊዎኪ ከተማ ውስጥ በተካሄደው የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ወሳኝ ጉባኤ ላይ የተገኙት ትራምፕ የጠበቃቸው አቀባበል የተለየ ነበር።
ከጥቃቱ አንድ ቀን በኋላ በተጀመረው ጉባኤ ላይ እስከ 50 የሚደርሱ የፓርቲው አባላት እና ደጋፊዎች የተገኙት በመጪው ኅዳር በሚካሄደው ምርጫ የፓርቲያቸውን ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ለመሰየም ብቻ ሳይሆን ትራምፕንም ለማወደስ ጭምር ነበር።
ከግድያ መኩራው በኋላ በአደባባይ ለመጀመሪያ ጊዜ የታዩት ትራምፕ በጥይት የቆሰለ ቀኝ ጆሯቸው በአራት ማዕዘን ነጭ ጨርቅ ተሸፍኖ ሲሆን፣ ታዳሚው በታላቅ አድናቆት ነበር የተቀበላቸው።
ለአራት ቀናት በቆየው የፓርቲው ጉባኤ ላይ የቆሰለ ጆሯቸውን ሸፍነው የታደሙት ዶናልድ ትራምፕ በፓርቲ አባሎቻቸው ዘንድ የጽናት እና የአሸናፊነት ምልክት ሆነው ታይተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የትራምፕ ጆሮ የተሸፈነበት ፋሻ
የ20 ዓመቱ ቶማስ ማቲው ክሩክስ የትረምፕን ጭንቅላት ለመምታት አልሞ የተኮሳት ጥይት ጆሯቸውን ጨርፋ ስትሄድ ከባድ ህመም እንደተሰማቸው እና አንዳች ነገር እንደመታቸው የተገነዘቡት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆሯቸውን በእጃቸው ሸፍነው አጎንብሰው ነበር።
ለስላሳ ከሆኑት የሰውነት ክፍሎች መካከል አንዱ የሆነው የጆሮ የውጭኛው ክፍል ጉዳት ከደረሰበት እና ለመድማት ከተጋለጠ ደሙ በቀላሉ መቆም እንደማይችል የቀድሞው የዋይት ሐውስ ሐኪም የሆኑት ሮኒ ጃክሰን ይናገራሉ።
ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው እኚህ ሐኪም ናቸው የትራምፕ መለያ እየሆነ ያለውን የጆሮ መሸፈኛ ፋሻ በመጀመሪያ በቆሰለው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆሮ ላይ ያደረጉት።
ምንም እንኳን በጥይት የተመታው የትራምፕ ጆሮ የላይኛው ክፍል ቢሆንም ፋሻው ግን ከሞላ ጎደል አብዛኛውን የቀኝ ጆሯቸውን ሸፍኖት ነበር።
ጆሯችን ጉዳት ከደረሰበት “እንደ ጉድ ደም ይፈሰዋል” የሚሉት የሪፐብሊካን ፓርቲ አባል እና ሐኪሙ ሮኒ ጃክሰን ይህንን የሚያስቆም ፋሻ ማስፈለጉ የግድ ነበር ይላሉ።
“የትራምፕ ጆሮ የሚሸፈንበት ጨርቅ ከውጭ ደሙ እየታየ እንዲንቀሳቀሱ አልፈለግንም። እናም ደም የሚፈስ ከሆነ መጥጦ እንዲይዘው ፋሻው ወፈር እና ተለቅ ማለት ነበረበት” በማለት የፋሻው ትልቅ መሆን ለምን እንዳስፈለገ አስረድተዋል።
በዚህ ምክንያት ነው ዶናልድ ትራምፕ ተለቅ ያለ ፋሻ በማድረግ በፓርቲያቸው ጉባኤ ላይ ለመታደም የተገደዱት። ይህ ግን ጥያቄ ከማስነሳት ባሻገር የየዶናልድ ትራምፕ አልበገር ባይነት መለይ ምልክት ሆኖ ለመታየት በቅቷል።
በጉባኤው የታደሙ እና ከዚያ ውጪ ያሉ ደጋፊዎቻቸውም ድጋፋቸውን ለመግለጽ በተመሳሳይ መንገድ ጆሯቸውን ሸፍነው ታይተዋል። እንደ ፋሽንም በሪፐብሊካኖች ዘንድ በስፋት እየታየ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ብዙዎች ፋሻውን እንዴት ሊያደርጉ ቻሉ?
በሚልዌኪ የሪፐብሊካን ፓርቲ ጉባኤ ሦስተኛ ቀን ላይ ትራምፕ ብቻ አልነበሩም ጆሯቸውን ሸፍነው የተገኙት፤ ቁጥራቸው በርካታ ደጋፊዎቻቸውም እንደ እሳቸው አድርገው ነበር።
ከአሪዞና ግዛት የመጡ የሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካዮች ጆሯቸውን በፋሻ የሸፈኑት ከግድያ ሙከራው በኋላ ለትራምፕ ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት መሆኑን ገልጸዋል።
አንድ ደጋፊያቸውም ጆሮዋን የሸፈነችው ለትራምፕ ያላት ፍቅር ምን ያህል መሆኑን ለማሳየት እና በእሳቸው የሚሰየም “አዲስ የፋሽን መገለጫን ለማስፋፋት” ነው ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
በሪፐብሊካን ፓርቲ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉ ታዳሚዎች በሙሉ የትራምፕን ጽናት እና አሸናፊነት ከተሰነዘረባቸው የግድያ ጋር እያዛመዱ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ከግድያ ሙከራው ከአንድ ቀን በኋላ በተጀመረው የፓርቲው ጉባኤ ላይ ትራምፕ ለዕጩ ፕሬዝዳንትንት የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እንደማያጡ እርግጥ ሆኖ ነበር።
ጥቃቱ አሜሪካውያንን ያስደነገጠ እና ሪፐብሊካንን ያስቆጣ ከመሆኑ አንጻር የትራምፕ ዕጩነት በምንም መልኩ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አልነበረም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትዕምርታዊው የጆሮ ፋሻ
ሪፐብሊካን የትራምፕ ጉዳትን እንደ ራሳቸው ጥቃት ከመመልከታቸው ባሻገር ድጋፋቸውን የገለጹላቸው ጆሯቸውን በመሸፈን ብቻ አልነበረም። በየደቂቃው በጭብጨባ ቁጭ ብድግ ሲያደርጓቸው በነበሩ ንግግሮች ሁሉ ትራምፕን ሲያወድሱ ለቀናት ቆይተዋል።
የትራምፕ ቁስል የተሸፈነበት እና ደጋፊዎቻቸውም ያደረጉት ትዕምርታዊ ፋሻ የግድያ ሙከራው ምልክት ባቻ ሳይሆን የፓርቲያቸው የአሸናፊነት ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
ትራምፕ በጉባኤው ማብቂያ ላይ ከዚህ በፊት በየትኛውም ዕጩ ተደርጎ በማያውቅ ሁኔታ ረጅም ነው በተባለው የአንድ ሰዓት ተኩል ንግግራቸው መጀመሪያ ላይ ስለተቃጣባቸው ጥቃት በዝርዝር ተናግረዋል።
ይህም የትራምፕ የዕጩነት ውሳኔ ላይ ጉልህ ተጽእኖ እንደነበረው እና በሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ዘንድም የትራምፕ አልበገር ባይነት ማሳያ እንዲሁም ከወራት በኋላ ለሚካሄደው ምርጫ ቅስቀሳም ወሳኝ አጀንዳ ሆኗል።
በጆ ባይደን ተሸንፈው ከሥልጣን ከለቀቁ በኋላ በበርካታ ክሶች ፍርድ ቤት ሲመላለሱ የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ የቀረቡባቸው ክሶች ዳግም ወደ ዋይት ሐውስ እንዳይመለሱ ፖለቲካዊ ሴራዎች ናቸው ሲሉ እንደነበር ይታወሳል።
ከሁለቱ ፓርቲዎች ደጋፊዎች ውጪ ባሉ አሜሪካውያን መራጮች ዘንድ ለትራምፕ ያለው ድጋፍ ጠንካራ ሳይሆን ቆይቷል። ዳግም ለምርጫ እንደሚወዳደሩ ከታወቀ በኋላ ከቀረቡባቸው ክሶች ተርፈው በሪፐብሊካኖች ዕጩ ሆነው የመቅረብ ዕድል ላይኖራቸው ይችላል የሚሉም ነበሩ።
ነገር ግን ባለፉት ወራት ባካሄዷቸው የምርጫ ዘመቻዎች በተለይ ግንቦት ማብቂያ ላይ ከፕሬዝዳንት ባይደን ጋር ክርክር ባደረጉበት ጊዜ ከፍተኛ ትኩረትን አግኝተዋል።
የ81 ዓመቱ አዛውንት ባይደን ከዕድሜ መግፋት ጋር በተያያዘ በክርክሩ ወቅት ከትራምፕ ተሽለው አለመገኘታቸው ትራምፕ ጎልተው እንዲወጡ አድርጓቸው ነበር።
ፔንሲልቬንያ ውስጥ የተቃጣባቸው የመግደል ሙከራ ደግሞ የበለጠ ድጋፍ እንዲያገኙ በር እንደከፈተላቸው ይታመናል።

የፎቶው ባለመብት, AP
የትራምፕ ፋሻ የፖለቲካዊ ጥቃት ምልክት
የጆሮ መሸፈኛ ፋሻው በመጀመሪያው የጉባኤው ቀን ትራምፕ ብቻ አድርገውት የነበረ ሲሆን፣ በሁለተኛው ቀን ግን የተወሰኑ ተሰብሳቢዎች ድጋፋቸውን ለመግለጽ እራሳቸው ያዘገጇቸውን የጆሮ መሸፈኛዎች አድርገው ታይተዋል።
ከዚያም በሦስተኛው ቀን ግን ከስብሰባው አዳራሽ ውጪ የጆሮ መሸፈኛ ፋሻ በነጻ ለጉባኤው ታዳሚዎች መታደል ጀምሮ ነበር። በዚህም ለትራምፕ ያላቸውን ፍቅር ለመግለጽ እና ለደረሰባቸው ጉዳት ከጎናቸው መቆማቸውን ለማሳየት በርካታ ጉባኤተኞች አድርገውት ታይተዋል።
የትራምፕ የጆሮ ቁስል መሸፈኛ ፋሻ “በመለኮታዊ ኃይል” ከተፈጸመባቸው ጥቃት ተረፈዋል የሚሉትን ደጋፊዎቻቸውን በአንድ አሰልፏል።
ትራምፕ ራሳቸውም “ሊታሰብ የማይችለውን እግዚአብሔር ብቻ ነው ያስቀረው” በማለት ፈጣሪ ከጎናቸው ባይኖር ኖሮ በዚያ ጉባኤ ላይ አብረዋቸው አንደማይገኙ ተናግረዋል።
ትራምፕ ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው በኋላ የተነሷቸው የማይረሱ ኃያል ፎቶዎች እንዲሁም ወደ መኪናቸው ከመወሰዳቻው በፊት ደጋፊዎቻቸው ወደ ኋላ ሳይሉ እንዲፋለሙ ያስተላላፉት ምልዕክት እንደ ጆሮ ፋሻቸው ሁሉ የክስተቱ አንድ አካል ሆነዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በጥቃቱ ቀን እና ከጥቃቱ በኋላ የተነሷቸው ምሥሎች ያሉባቸው የተለያዩ አልባሳት እና ቁሳቁሶች በደጋፊዎቻቸው ዘንድ እየተሰራጩ ነው።
ይህ ትራምፕ በጥይት የቆሰለ ጆሯቸውን የሸፈኑበት ፋሻ ከእሳቸው የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ ባሻገር ፖለቲካዊ ጥቃትንም የሚወክል ምልክት እየሆነ ነው።
ከቴክሳስ ግዛት ለሪፐብሊካን ፓርቲ ጉባኤ ተወክለው የመጡት ጃክሰን ካርፔንተር “ፖለቲካዊ ጥቃት በአሜሪካ ውስጥ ተቀባይነት እንደሌለው የሚያሳይ ምልክት ያስፈልገናል” በማለት የትራምፕ ፋሻ ለዚህ ሊሆን እንደሚችል ለዋሽንግተን ፖስት ተናግረዋል።












