ካማላ ሃሪስ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩ መሆን የሚያስችላቸውን በቂ ድጋፍ ከፓርቲው ተወካዮች አገኙ

ካማላ ሀሪስ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ምክትል ፕሬዝደንቷ ካማላ ሃሪስ በሚቀጥለው ምርጫ ዕጩ ሆነው ለመቅረብ ከዲሞክራቲክ ፓርቲ ተወካዮች በቂ ድጋፍ ማግኘታቸው ተሰምቷል።

ሀሪስ በቂ ድጋፍ ማግኘታቸውን የዘገበው ሲቢኤስ የተሰኘው የአሜሪካው የቢቢሲ አጋር ሚድያ ነው።

ሰኞ ዕለት አንድ ጥናት የሠራው አሶሺየትድ ፕሬስ፤ ሃሪስ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ከ1976 በላይ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ተወካዮች ድጋፍ ማግኘታቸውን ይፋ አድርጓል።

ካማላ ሃሪስ “ሰፊ ድጋፍ” በማግኘታቸው “መኩራታቸውን” ገልጠው ከፓርቲው በይፋ የዕጩነት ማዕረግ እስኪሰጣቸው እየተጠባበቁ እንደሆነ አሳውቀዋል።

የዲሞክራቲክ ተወካዮች የሚባሉት በምርጫ ጣቢያዎች ፓርቲያቸውን የሚወክሉ ሲሆኑ ዲሞክራቲክ ናሽናል ኮንቬንሽን በተሰኘው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ዕጩ የመምረጥ ኃላፊነት አለባቸው።

ምንም እንኳ ተወካዮቹ ለካማላ ሃሪስ ያላቸውን ድጋፍ ቢያሳውቁም ምክትል ፕሬዝደንቷ በይፋ ዕጩ ሆነው የሚቀርቡት በአውሮፓውያኑ ነሐሤ ወር መባቻ በሚደረገው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በሚደረግ ድምፅ አሰጣጥ ነው።

ቢያንስ የ27 ግዛቶች የዲሞክራቲክ ፓርቲ ተወካዮች ለካማላ ሃሪስ ያላቸውን ድጋፍ አሳውቀዋል ይላል የሲቢኤስ ዘገባ።

ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ባሳለፍነው እሑድ ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸውን ተከትሎ ምክትል ፕሬዝደንቷ ካማላ ፓርቲያቸውን ወክለው እንደሚወዳደሩ በስፋት ሲዘገብ ነበር።

ከባይደን መግለጫ በኋላ በሚሊዮን ዶላሮች የሚገመት የገንዘብ ድጋፍ ወደ ካማላ ሃሪስ የምርጫ ዘመቻ ካዝና ገብቷል። ይህ ደግሞ ዲሞክራቶችን ካማላን ዕጩ አድርገው እንዲመርጡ ይገፋፋል የሚል ግምት አለ።

ሰኞ አመሻሹን ለምርጫ ዘመቻ አባላቶቻቸው ንግግር ያደረጉት ካማላ “የድምፅ መስጫ ቀን እስኪደርስ ድረስ 106 ቀናት ናቸው ያሉን። እስከዚያው ድረስ ከባድ ሥራ ይጠብቀናል” ብለዋል።

ምክትል ፕሬዝደንቷ ለሀገራቸው ያላቸውን ራዕይ ካስቀመጡ በኋላ ከትራምፕ ቡድን የሚለያቸውን በርካታ ነገር እንዳለ ዘርዝረው ከተቀናቃኛቸው ጋር በዚህ ጉዳይ ለመፎካከር ብቁ እንደሆኑ ተናግረዋል።

አልፎም የባይደን አስተዳደር ያሳካቸውን ድሎች አሞግሰው ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው ማገልገላቸውን “በሕይወቴ ካደረግኳቸው አኩሪ ሥራዎች መካከል አንዱ ነው” ሲሉ ገልጠውታል።

ሃሪስ ንግግር ለማድረግ ወደ መድረክ ከመውጣታቸው በፊት በሚቀጥለው ምርጫ እንደማይሳተፉ ያሳወቁት ባይደን ስልክ ደውለውላቸው ነበር።

ለሃሪስ ስልክ የደወሉት ባይደን ለረዳቶቻቸው ባስተላፉት መልዕክት “እሷ በጣም ምርጧ ስለሆነች ተቀበሏት” ብለዋል።

“እኔ የትም አልሄድም” ያሉት ባይደን የምርጫ ዘመቻ ቡድናቸው ላደረገው ጥረት ምስጋና አቅርበው ምክትላቸው በሚያደርጉት ዘመቻ የበኩላው ለመወጣት ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳውቀዋል።

ባለፈው ሳምንት በኮቪድ-19 በመያዛቸው ምክንያት ዴላዌር በሚገኘው ቤታቸው የከረሙት ባይደን ማክሰኞ ወደ ዋይት ሐውስ ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።