ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቱሪስቶች መጡብን ያሉ ስፔናውያን ተቃውሞ እያሰሙ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
የስፔን ቱሪስት መናኽሪያ ከሆኑት ግዛቶች መካከል አንዷ ወደ ሆነችው ማዮርካ ከተጓዙ ሁለት ጉዳዮችን ይመለከታሉ።
የመጀመሪያው የተለመደው የባሊያሪክ ባሕር ሞገድ ቀኑን ሙሉ የባሕር ዳርቻዎችን አሸዋ ወዲያ ወዲህ ሲያመላልስ መዋሉ ነው።
ሁለተኛው እና ያለተለመደው ትዕይንት የቱሪስቶች መጠን ከልክ በላይ መብዛት ነው።
እያንዳንዱ የባሕር ዳርቻ በቱሪስት ተሞልቶ መንቀሳቀሻ የለም። የመኪና ማቆሚያ ቦታ ማግኘት ልክ ወርቅ እንደማግኘት ሆኗል።
የአካባቢው ንግድ እንቅስቃሴም ሞቅ ደመቅ ብሏል።
በተመዘገበ ከፍተና የጎብኚዎች ብዛት የተነሳ የደራ የንግድ እንቅስቃሴ ግዛቲቷን ተፈላጊ አድርጓታል።
ይህ ግን ለአካባቢው ማኅበረሰብ ትልቅ ዕድል ይዞ መጥቷል ብለው ካሰቡ ከሶንያ ሩዊዝ ሐሳብ ጋር ይቃረናሉ።
የ31 ዓመቷ ሶንያ የአንድ ልጅ እናት ናት።
ከግዛቲቱ ዋና ከተማዋ ፓልማ የባሕር ዳርቻው ጥቂት መቶ ሜትሮች ርቆ በሚገኝ መናፈሻ ውስጥ ነበረች።
አራት ዓመት ሆነው ልጇ ሉካ በሜዳው ላይ ያለምንም ሀሳብ ወዲያ ወዲህ እያለ ይጫወታል።
ሶንያ ግን ከኑሮ ጋር ግብግብ ይዛለች። ቤት አከራይዋ ቤቴን ልቀቂ ቢላትም የሚከራይ ቤት ማግኘት ዳገት ሆኖባታል።
“በየዕለቱ ቤት ብፈልግም ከቀኑ ቀን የቤት ኪራይ እየጨመረ ነው” ትላለች።
“ሰዎችን መንገድ ላይ እያስቆምኩ የኪራይ ቤት እንዳላቸው እጠይቃለሁ። አፓርታማውን የምለቅበት ቀን እየቀረበ ነው። እኔ እና ልጄ ቤት አልባ እንደምንሆን እያሰብኩ።”
ሶንያ እና ባለቤቷ ተለያይተዋል። በጋራ የሚያገኙት ወርሃዊ ገቢ 2400 ዩሮ ቢሆንም ለየብቻ መከራየት ስለማይችሉ አብረው ለመኖር ተገደዋል።
“አከራዮች የበርካታ ወራት ተቀማጭ ገንዘብ ይጠይቃሉ። አንዳንዶችማ ልጆች ያላቸውን ተከራዮች እንደማይፈልጉ፣ እንስሳት እንደማይፈልጉ ነግረውኛል። በተጨማሪም ብዙ ሰዎች ቤት እየፈለጉ ነው” ብላለች።

ቱሪስቶች ናቸው ኑሮ ያስወደዱብን በሚል በሺህዎች የሚቆጠሩ ማዮርካውያን ባለፈወ ሳምንተ መጨረሻ ሰልፍ ወጥተው ነበር። ሶንያም ተቀላቅላቸዋለች።
አክቲቪስቶች እንደሚሉት የመኖሪያ ቤት ዋጋ እጅግ በጣም የጨመረው በርካታ ቁጥር ያላቸው ቤቶች እና አፓርትመንቶች በውጭ ዜጎች ስለሚገዙ ወይም በበጋ ወራት ስለሚከራዩ ነው።
የ25 ዓመቱ ፒየር ዮአን ፌሜኒያ በማሎርካ ዋና ከተማ ፓልማ ከሚገኘው ካቴድራል ሆኖ “እንዲህ ዓይነቱን አካሄድ ማስቀጠል አይቻልም” ሲል ይገልጻል።
“ትንሽ ቱሪሰት፣ ጥሩ ህይወት” የተሰኘ እንቅስቃሴ አባል ነው።
የቱሪስቶች መጨመር የአካባቢውን ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቤት ገበያው ውጪ ከማድርግ ባለፈ ሕዝባዊ ቦታዎችን፣ የሐዝብ አገልግሎቶችን እና የተፈጥሮ ሃብቶችን እየተሻሙ ነው ይላል።
ፒየር እንቅስቃሴውን የጀመረው ከአምስት ዓመት በፊት የግሬታ ተንበርግ የአየር ንብረት እንቅስቃሴ አካል በመሆን ነው። አሁን ግን ትኩረቱን በደሴቶቹ ነዋሪዎች የኑሮ ውድነት ላይ አድርጓል።
“ሱቆች ባህላዊ ምርቶችን ከመሸጥ ወደ እንደአይስ ክሬም ያሉ ዘመናዊ ምርቶችን መሸጥ እየተቀየሩ ነው። ማንነታችን እየጠፋ ነው። ባህላችንን መጠበቅ እንፈልጋለን” ብሏል።
የባሕር ዳርቻዎች በጎብኚዎች እና በጎዳና ላይ ነጋዴዎች ተሞልቷል። ፒየርም ወደ ዳርቻው እያመለከተ አንዳንድ መርከቦች በየቀኑ 12 ሺህ የሚደርሱ ጎብኚዎች ወደ ደሴቲቱ እንደሚያስገቡ ገልጿል።
ማዮርካ እንድትቀጥል እያደገ የሚሄድ ቱሪዝም ያስፈልጋታል የሚባለው ተረት ነው ይላል። እውነታው ግን ብዙዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች አቅም ስለሌላቸው ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግሯል።

ፒየር በበረራዎች እና በመርከቦች ቁጥር ላይ ቁጥጥር በማድረግ በደሴቲቱ ያለውን ጫና በፍጥነት ማቃለል ይቻላል ሲል ተከራክሯል።
ይህንንም በፓልማ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ በመፈክሮች እና በባነሮች አሰምተዋል።
የስፔን ብሔራዊ የስታቲስቲክስ ተቋም ባለፈው ዓመት 14.4 ሚሊዮን የውጭ ቱሪስቶች የባሊያሪክ ደሴቶችን ጎብኝተዋል ብሏል። ከእነዚህም ውስጥ ማዮርካ ትልቁን ድርሻ ስትይዝ ሜኖርካ እና ኢቢዛ ይከተላሉ።
ተቋሙ እንደገለጸው የደሴቲቱ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ቁጥር ከ2022 ጋር ሲነጻጸር በ9.1 በመቶ ጨምሯል። ወጪያቸው ደግሞ 16.4 በመቶ ከፍ ብሏል።
የስፔን ጎብኚዎች ከግምት ውስጥ ሲገቡ በዚህ ዓመት 20 ሚሊዮን ጎብኚዎች ባሊያሪክን ሊጎበኙ እንደሚችሉ አክቲቪስቶች ይናገራሉ።
የስፔን የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ባለፉት አስርት ዓመታት እያደጉ ይገኛሉ። ይህ ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩት ጎብኚዎች ከጥቅማቸው ይልቅ ብዙ ችግሮችን ያመጣሉ ወይ የሚል ክርክር እያስነሳ ነው።
በዚህ ዓመት የሆነ ነገር የተለወጠ ይመስላል። የአብዛኞቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ቁጣ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው።
በማላጋ እንዲሁም በካናሪ ደሴቶችም ሰልፎች ተካሂደዋል። የስፔን የቱሪስት መስህቦች አሁን ጎብኚዎችን ለመከልከል እያሰቡ ነው።

አንዳንድ የብሪታኒያ ጋዜጦች በ2024 የበጋ ወቅት ቱሪስቶች ሊጎበኟቸው የማይገቡ “አደገኛ የቱሪስት ቦታዎችን” ዘርዝረው አዘጋጅተዋል።
በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ብሪታንያወያን የዕረፍት ጊዜ መዳረሻ ተደርገው ለረዥም ጊዜ በሚታሰበው የማጋሉፍ የባሕር ዳርቻ ላይ ከሮዘርሃም የመጣው የግሪን ቤተሰብ በደስታ እያሳለፈ ነው።
አባታቸው አዳም የመጀመሪያ የውጪ ጉዞው ነው። እረፈት ነው ቢሉም እሱ እና ባለቤቱ ሰባት ልጆቻቸውን ሲከታተሉ ነው ጊዜያቸውን ያሳለፉት።
“አስቸጋሪ ቢሆንም እዚያ እየደረስን ነው። ከሙቀት ውጪ በጣም ጥሩ ነው” ይላል።
እየተካሄዱ ስላሉት የተለያዩ ተቃውሞዎች ሰምተው እንደሆነ እና ወደ ማዮርካ ስለመጓዛቸው ደጋግመው አስበውበት እንደሆነ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።
ሻርለት “በዜና ላይ ትንሽ አይቻለሁ” ስትል ተናግራለች። “ሆኖም ላለመመልከት ሞከርኩኝ ምክንያቱም ቀድመን ስለከፈልን ለመጨነቅ እና ለመቅረት ስላልፈለግኩ ነው” ብላለች።
የአካባቢው ነዋሪዎች እያደገ ያለው ቱሪዝም በጣም አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው የሚለው ቅሬታስ?
“ቱሪስቶቹ ገንዘብ እያፈሰሱ አካባቢውን አያሳድጉትም?” ሲል አዳም ጠየቀ።
“ሰዎች በዓለም ዙሪያ ይጓዛሉ እና ይሄው ነው። ቱሪስቶች ከሌሉ ምንም ሥራ እና ደመወዝ አይኖርም። በቱሪዝም አይደለም እንዴ የሚተዳደሩት?” ሲል ጠይቋል።












