አበበ ቢቂላ ሁለት መጽሐፍት በፃፉለት ጣልያናዊ ጋዜጠኛ እንዴት ይታወሳል?

ጣልያናዊው የስፖርት ጋዜጠኛ ቫሌሪዮ ፒቾኒ
የምስሉ መግለጫ, ቫሌሪዮ ፒቾኒ ‘La Gazzetta dello Sport’ በተባለ ታዋቂ የጣልያን ዕለታዊ የስፖርት ጋዜጣ ከ20 ዓመታት በላይ ሰርተዋል።

ቅዳሜ ጳጉሜ 5/1952 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ዋዜማ።

ከወደ ሮም ዓለምን ያስደነቀ፣ የጥቁሮችን አንገት ያቃና ድል ተሰማ። የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ የማራቶን ውድድርን አሸነፈ።

የዓለም ሕዝብ እጁን አፉ ላይ ጫነ።

“ሶርፕረንደንቴ!” አሉ ጣልያኖች። አስገራሚ ማለታቸው ነው።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የአበበ ቢቂላ ስም ከጣልያናውያን አፍ ተነጥሎ አያውቅም።

ውድድር በሚካሄዱባቸው ስታዲየሞች እና ጎዳናዎች ‘ኩሜ አበበ ቢቂላ!’ . . . ‘ልክ እንደ አበበ ቢቂላ! . . . ልክ እንደ አበበ ቢቂላ!’ . . . እያሉ ተወዳዳሪዎችን ያበረታታሉ።

የአትሌቲክስ ኮሜንታተሮችም ቢሆኑ “ይህ አበበ ቢቂላ የሮጠበት ጎዳና ነው” በማለት ስሙን ማስታወሳቸው ለአስርተ ዓመታት የዘለቀ ነው።

አገራቸው ጣልያንም ለአበበ አልሰሰተችም። በስሙ ጎዳና ሰይማለች። ከሮም 40 ኪሎ ሜትር ገደማ በምትርቀው የባሕር ዳርቻዋ ከተማ - ላዲስፖሊ በስሙ የተሰየመ ድልድይ አለ።

በሮም ከተማ ውድድሩን ባጠናቀቀበት ሳን ግሪጎሪዮ ጎዳና ከኮንስታንቲን ግንብ ዝቅ ብሎ በሚገኝ ግንብ ላይም ስሙ በጉልህ ተፅፎ ይገኛል።

በጣልያናዊው ጋዜጠኛ ቫሌሪዮ ልብ ላይ ደግሞ ላይፋቅ ታትሟል።

ቫሌሪዮ ስለአበበ ሲነሳ የተደበላለቀ ስሜት ነው ፊታቸው ላይ የሚነበበው።

በአጭር መቀጨቱን ሲያስቡ እንባ በዐይናቸው ላይ ያቀራል። ገድሉን እና ድሉን ሲያስታውሱ ደግሞ አንዳች የጀግንነት ስሜት ይወራቸዋል።

ቫሌሪዮ ፒቾኒ የስፖርት ጋዜጠኛ ናቸው። ‘La Gazzetta dello Sport’ በተባለ ታዋቂ የጣልያን ዕለታዊ የስፖርት ጋዜጣ ላይ ከ20 ዓመታት በላይ ሠርተዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ1896 በተቋቋመው በዚህ ጋዜጣ በተለይ በአትሌቲክሱ፣ በስፖርቱ እና በስፖርት ፖለቲካው ላይ በጣልያንኛ በሚጽፏቸው ጠንካራ ጽሑፎቻቸው ይታወቃሉ።

ቫሌሪዮ ጋዜጠኛ ብቻ ሳይሆኑ በስድስት የማራቶን ውድድሮች ላይ ተሳትፈዋል። የሩጫ አድናቂ ናቸው። በዚህ የስፖርት ዘርፍ እንዲሳተፉ ካነሳሷቸው ምክንያቶች አንዱ ደግሞ ለአበበ ቢቂላ ያላቸው የማይደበዝዝ ፍቅር ነው።

አበበ በሮም ማራቶን ብቻውን ተነጥሎ የመጨረሻውን ኪሎ ሜትር የሮጠበትን ‘ሰባስቲያኖ’ ጎዳናን ባዩ ቁጥር አሁንም ድረስ የተለየ ስሜት ነው የሚሰማቸው።

ስለእርሱ አብዝተው ይብሰለሰላሉ። ከአድናቆት በዘለለ ለአበበ ያላቸውን ፍቅር እንዴት እንደሚያሳዩ፣ እርሳቸው የተሰማቸውን ለሌላው ዓለም እንዴት እንደሚያጋሩ ሲያስቡ ዘመናትን ዋጅተዋል።

ይህንን ሃሳብ ይበልጥ እያጎለበቱ የመጡት እንደ አውሮፓውያኑ በ1982 የጋዜጠኝነት ሙያን ከተቀላቀሉ በኋላ ነበር።

ለአትሌቲክስ የተለየ ፍቅር ያላቸው ቫሌሪዮ፣ ስለመጀመሪያው አፍሪካዊ የኦሊምፒክ ሻምፒዮና ግለ ታሪክ እና እሱ የፈጠረው ዓለም አቀፍ ንቅናቄ ላይ የሚያጠነጥኑ ሁለት መጽሐፍትን ከባልደረባቸው ሎ ጁዲቼ ጋር በመሆን በጣልያንኛ ጽፈዋል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, የአፍሪካን የሩጫ ታሪክ የቀየረው ኢትዮጵያዊ

አበበ ቢቂላ እንዴት በቫሌሪዮ ልብ አደረ?

አበበ በቫሌሪዮ ልብ ውስጥ የገባው ገና በልጅነታቸው ነው።

የ13 ዓመት ታዳጊ ሳሉ በስፖርት በምትታወቀው ጥንታዊቷ እና ታሪካዊቷ ከተማ - ሮም በተካሄደ የሩጫ ውድድር ላይ ተሳትፈው ነበር።

በውድድሩ የመጨረሻውን ዙር የሮጡት በታሪካዊው አፒያ አንቲክ ጎዳና ላይ ነበር። ይህ ጎዳና የሮም ማራቶን አሸናፊው አበበ የሮጠበት እና የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘበት ነው።

“በወቅቱ በአፕያንቲካ ጎዳና የተሰማኝ ስሜት ልዩ ነበር” ይላሉ።

በታዳጊነታቸው ያካሄዷቸው ውድድሮች ስለአበበ ያላቸውን ስሜት ቢያጭረውም በዚህ ላይ የአባታቸው አስተዋፅኦም ከፍተኛ ነው።

አባታቸው የኦሊምፒክ ውድድሮችን አብዝተው ይወዱ ነበር። ለአበበ ቢቂላ ያላቸው አድናቆትም የተለየ ነበር።

ቫሌሪዮ እንደሚሉት አባታቸው የአበበ የኦሊምፒክ ድል ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ አብዝተው ያወሩ ነበር።

ጣልያን በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመችው የመጀመሪያው ወረራ በኢትዮጵያውያን ድል ከተደረገ በኋላ በአውሮፓውያኑ 1935 በድጋሚ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ፈጽማ ነበር።

በዚህም ያሰበችው ሳይሳካ ከዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን ለቃ ወጥታለች። ይህ በሆነ በ24 ዓመታት ውስጥ ደግሞ አበበ ቢቂላ ዳግም ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን ኩራት የሆነ ድልን ተቀዳጀ።

ለአባቱ የተለየ ትርጉም የሰጣቸውም ይህ ነበር።

አባታቸው የጣልያን ወረራ ፍትሐዊ እንዳልሆነ ነበር የሚያምኑት።

ይህም በታዳጊው ቫሌሪዮ ልብ ውስጥ የማይናወጥ ሐቅ አስቀመጠ።

“አበበ ቢቂላ ግላዊ ታሪኩም የሚደንቅ ነው። በአውሮፓውያኑ 1960 የሮም ኦሊምፒክ ውድድር ደግሞ ኢትዮጵያን እና አፍሪካን በማራቶን በዓለም ቁንጮ ላይ አስቀምጧል” ሲሉም ያሞካሹታል።

ቫሌሪዮ ፒቾኒ ከአባታቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Valerio Piccioni

የምስሉ መግለጫ, ቫሌሪዮ እንደሚሉት የአበበ ቢቂላ ድል ለአባታቸውም የተለየ ትርጉም ነበረው።

የአበበ ቢቂላ ህልም እና አብዮት

አበበ ቢቂላ የተከሰተበት ዘመን ለጥቁሮች አስከፊው ዘመን ነበር።

በርካታ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት አልወጡም። በተለይ ነጮች ጥቁሮችን እንደ ሰው የማይቆጥሩበት እና የነጮች የበላይነት የነገሰበት ዘመን ነበር።

በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ አበበ ኦሊምፒክን ያሸንፋል ብሎ የገመተ አልነበረም።

“ከ1960 በፊት ማራቶንን የሮጡ አትሌቶች አፍሪካዊ ያሸንፋል የሚል እምነት አልነበራቸውም። አበበ እንደሚሮጥ ሲሰሙም እንደ እብድ ነበር የቆጠሩት፤ ነገር ግን አበበ እንደሚችል ለዓለም አሳይቷል” ይላሉ ቫሌሪዮ።

ቫሌሪዮ ይህንን የአበበን ህልም ከባልደረባቸው ሎ ጁዲቼ ጋር በመሆን በጣልያንኛ ከጻፏቸው ሁለት መጽሐፍት መካከል አንዱ በሆነው ‘ኡን ሶኞ ኤ ሮማ’ (A Dream in Rome) መጽሐፋቸው አትተውታል።

መጽሐፉ አበበ በሮም ሰንቆት ስለነበረው ህልም እና ስላስመዘገበው ድል የሚያወሳ ነው።

ቫሌሪዮ የአበበን ሕይወት በመጽሐፍ የመሰነድ ጉዟቸው ግን በ‘ሮማ ህልም’ አላቆመም። ‘ላ ሪቮሊዚዮኔ ዲ ቢቂላ’ [የቢቂላ አብዮት] የተሰኘውን ሁለተኛ መጽሐፋቸውን አስከትለዋል።

'ኡን ሶኞ ኤ ሮማ [የሮማ ሕልም] እና 'ላ ሪቮሊዚዮኔ ዲ ቢቂላ' [የቢቂላ አብዮት] መጽሐፍት የፊት ገጽ

የፎቶው ባለመብት, Valerio Piccioni

የምስሉ መግለጫ, ጋዜጠኛ ቫሌሪዮ ከባልደረባቸው ሎ ዲቼ ጋር በመሆን 'ኡን ሶኞ ኤ ሮማ [የሮማ ሕልም] እና 'ላ ሪቮሊዚዮኔ ዲ ቢቂላ' [የቢቂላ አብዮት] የተሰኙ ሁለት መጽሐፍትን ለንባብ አብቅተዋል።
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

‘ላ ሪቮሊዚዮኔ ዲ ቢቂላ’ የተሰኘው መጽሐፋቸው አትሌቲክሱ ላይ ብቻ የሚያጠነጥን አይደለም። ስለአበበ ልጅነት፣ አስተዳደግ፣ ልዩ ተሰጥኦ እና ወደ ሩጫ ሕይወት ስለገባበት አጋጣሚ ያወሳል።

ይህንን መጽሐፍ ለመጻፍ ቫሌሪዮ እንደ አውሮፓውያኑ 2010 ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው ነበር። አበበ ቢቂላ የተወለደበትን በወቅቱ የሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ ደብረ ብርሃን አውራጃ፣ ደነባ ልዩ ስሟ ጃቶ የምትባል ቦታን ጎብኝተዋል።

የአበበ ቢቂላን ልጅ የትናየት አበበን አግኝተው ስለሥራዎቹ አውግተዋል። በሮም ከተማ ይኖሩ ከነበሩት የአበበ ቢቂላ ባለቤት ወ/ሮ የውብዳር ጋርም መረጃዎችን ተለዋውጠዋል።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ልምምድ የሚያደርጉበትን እንጦጦንም ጎብኝተዋል።

በዘመኑ ከነበሩት አትሌት ዋሚ ቢራቱ ጋርም አውግተዋል።

የአበበ ቢቂላ አሠልጣኝ የነበረውን ስዊድናዊው ኦን ኒስካነንን ለማግኘትም ወደ ስዊድን አቅንተዋል።

ኒስካነን [1910-1984] የክብር ዘበኛ ስፖርት ክፍል አሠልጣኝ የነበሩ ናቸው። ኦኒ ኒስካነን አበበን ወደ ሩጫ እንዲገባ ባያደፋፍሩት አትሌት ላይሆን ይችል እንደነበር ይነገራል።

ቫሌሪዮም ኒስካነን ስለአበበ ታሪክ ለመጻፍ ወሳኝ ሰው ናቸው ይላሉ። ከእርሳቸውም ጋር ስለ ሩጫ ልምምዱ፣ ስለ ቅርጫት ኳስ ጨዋታ እንዲሁም ስለሚደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ ተጨዋውተዋል።

መጽሐፉ የአበበ ቢቂላ ድል በፖለቲካው እና በታሪክ ረገድ ለጥቁሮች የነጻነት እንቅስቃሴ ያበረከተውን አስተዋፅኦም ያትታል።

“አበበ ቢቂላ ማራቶንን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የቀየረ ነበር። የአፍሪካን ገጽታ በማይሻር መልኩ ለውጦታል” ይላሉ ቫሌሪዮ።

አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሩጫውን በአሸናፊነት ካጠናቀቀ በኋላም አልደከመም ነበር። ስፖርት ሲሠራ እና ሰውነቱን ሲያፍታታ ታይቷል።

“ይህም አብዮት ነበር” ይላሉ።

ጥቂት ስለአበበ ቢቂላ

  • አበበ ወደ አትሌቲክሱ ከመግባቱ በፊት በክብር ዘበኛ ሠራዊት ወታደርነት ነበር።
  • በክብር ዘበኛ የስፖርት አሠልጣኝ ኦኒ ኒስካነን አማካኝነት በ24 ዓመቱ የሩጫውን ዓለም ተቀላቀለ።
  • በ1960 ሐምሌ ወር ላይ በአዲስ አበባ በተካሄደ የመጀመሪያው የማራቶን ውድድር ሁለተኛ ሆኗል።
  • በ1960 መስከረም ወር ላይ በሮም ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር በ2፡15፡16 ሰከንዶች በባዶ እግሩ ሮጦ በማሸነፍ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ ለመሆን በቃ።
  • በ1964 በቶክዮ ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር የራሱን ክብረ ወሰን በማሻሻል እና 2:12:11.2 ሰከንዶች በመግባት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል።
  • አበበ በሁለት ተከታታይ የኦሊምፒክ ውድድሮች ላይ በማራቶን በማሸነፍ በዓለም የመጀመሪያ ነው።
  • ሻምበል አበበ በ13 የማራቶን ውድድሮች ላይ የተሳተፈ ሲሆን፣ በ12ቱ ድልን ተቀዳጅቷል።
  • እአአ በ1969 የመኪና አደጋ ከደረሰበት በኋላም በዊልቸር ላይ ሆኖ በፓራሊምፒክ ውድድሮች ላይ በብቃት ሲሳተፍ ነበር።
  • እአአ ጥቅምት 25/1973 በ41 ዓመቱ ሕይወቱ አልፏል።

የአበበ በባዶ እግር መሮጥ

አበበ ኦሊምፒክን ድል ከማድረጉ ባለፈ በባዶ እግሩ መሮጡ ከድል በላይ ድልን አጎናጽፎታል።

ለምን በባዶ እግሩ ሮጠ? የሚለው ግን አሁንም መነጋገሪያ እንደሆነ ነው።

አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ የሮጠበትን ምክንያት በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ሲንፀባረቁ ተሰምተዋል።

በርካታ መዛግብት ለአበበ የሚስማማ ጫማ መጥፋቱን፣ የሞከረውም ጫማ ስለጠበበው ያለጫማ መሮጥን መምረጡን ጽፈዋል።

ሌሎች ደግሞ ሆነ ብሎ የፈጸመው ገድል እንደሆነ ነው የሚናገሩት።

ጋዜጠኛው ቫሌሪዮም አሠልጣኙን በማነጋገር እንዲሁም በእርሱ ላይ ባደረጉት ጥናት የደረሱበት ጉዳይ አበበ አስቦበት ያደረገው እንደሆነ ነው።

“አሠልጣኙ መኪና ተከራይተው የማራቶን ውድድር የሚካሄድባቸውን ጎዳናዎች ሲያጠኑ ነበር። አንዴ በባዶ እግሩ፣ አንድ ጊዜ በጫማ ልምምድ ሲያደርግ ነበር” የሚሉት ጋዜጠኛው፣ በመጨረሻ በባዶ እግሩ ለመሮጥ ከአሠልጣኙ ጋር ተወያይቶ መወሰኑን ተናግረዋል።

ቫሌሪዮ ስለዚሁ ጉዳይ በውድድሩ የነሐስ ሜዳሊያ ያገኘውን ኒውዚላንዳዊ ቤሪ ማጌንም ጠይቀውት ነበር።

“‘ቢቂላ በጣም ጎበዝ አትሌት ነው። በባዶ እግሩ መሮጡም የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም። ውሳኔው ቴክኒካዊ ነበር። ገራሚ አትሌት ነው!” ነበር ያላቸው።

ጋዜጠኛው እንደሚሉት በወቅቱ በድህነት እና በኋላ ቀርነት የሚታሰበውን የአፍሪካ ሕዝብ ከፍ ለማድረግ አስቦ ያደረገው ነው።

አትሌት አበበ ቢቂላ ከድል በኋላ ታዳሚዎች በትከሻቸው ተሸክመውት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በጣልያን “ ‘ ኩሜ አበበ ቢቂላ!’ . . . ‘ልክ እንደ አበበ ቢቂላ! . . . ልክ እንደ አበበ ቢቂላ!’ . . . እያሉ ተወዳዳሪዎችን ማበረታታት የተለመደ ነው።

“አሁን ላይ በሚካሄዱ ውድድሮች የሚታየው ከ60 ዓመት በፊት የሆነውን የሚያሳይ አይደለም። አፒያ አንቲካ እና የባሶሊ ጎዳናዎች በባዶ እግር ለመሮጥ አስቸጋሪ ነበሩ” የሚሉት ጋዜጠኛ ቫሌሪዮ፣ አበበ በባዶ እግሩ ለመሮጡ ሌላ መላ ምት እንዳለም ይጠቅሳሉ።

ይህም በባዶ እግር ከሮጠ የእግር ዱካው ስለማይሰማ በቅርብ ርቀት ለሚከታተሉት ተፎካካሪዎቹ ምልክት ላለመስጠት ነው የሚል ነው።

አበበ በውድድሩ ካደረጋቸው አስደናቂ ነገሮች መካከል ሌላኛው በሮም ፒያሳ ተተክሎ በነበረው የአክሱም ሐውልት ሲደርስ ፍጥነቱን መጨመሩ ነበር።

በጣልያን ወረራ ማብቂያ ላይ በሞሶሎኒ ትዕዛዝ ከኢትዮጵያ ተነቅሎ በተወሰደው እና በሮም ተተክሎ ወደ ነበረው የአክሱም ሐውልት ሲደርስ ተፈትልኮ መውጣቱም ትርጉም ነበረው።

“አበበ በዚያ ውድድር ያደርጋቸው የነበሩት እያንዳንዱ እንቅስቃሴዎቹ በታሪክ አውድ ተመንዝረው የሚተነተኑ ናቸው” ይላሉ ቫሌሪዮ።

አበበ በሩጫው ብዙ ሳይገፋበት በአውሮፓውያኑ በ1969 በአዲስ አበባ በደረሰበት የመኪና አደጋ ምክንያት መንቀሳቀስ ተሳነው።

ቫሌሪዮ እነዚያን ዓለምን ያነጋገሩ የአበበ ቢቂላ እግሮች በአደጋ ምክንያት ዊልቸር ላይ መዋላቸውን በሰሙ ጊዜም መቀበል ከብዷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።

ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ባደረጉበት ወቅትም ይህንኑ ቀን ረግመውታል።

አበበ ከአደጋው በኋላ በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ላይ ሲሳተፍ የነበረ ሲሆን፣ ብዙም ሳይቆይ በ1973 በ41 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

አበበ በሮም ጎዳና በባዶ እግሩ ሲሮጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአበበ ቢቂላ ድል በጥቁሮች ዘንድ የፈጠረው ንቅናቄ

ቫሌሪዮ እንደሚሉት ከአበበ ድል አስቀድሞ በጣልያን ለጥቁሮች ያለው አመለካከት የተዛባ ነበር።

እስከ1970ዎቹ ድረስ በጣልያን የሚኖሩ ጥቁሮችም በቁጥር አነስተኛ ነበሩ።

በ1928 በተካሄደ የቦክስ ውድድር ጥቁሩ ጣልያናዊ ቦክሰኛ ሊዮኔ ጃኮቫች ድል ቢቀናውም፣ ለጣልያናውያን ትልቅ ድል አልነበረም። ስለድሉ ለማወቅም ፍላጎት አልነበራቸውም።

“የአበበ ቢቂላ ድል ግን ይህንን የሻረ ነበር። የመጀመሪያው አፍሪካዊ ድል ነበር። ጥቁር ሕዝቦች ባልተለመደ ሁኔታ በሮም ሲወደሱ ነበር” ይላሉ ቫሌሪዮ።

“ጣልያናውያን አበበን በጣም ይወዳሉ” የሚሉት ቫሌሪዮ፣ ከእርሱ ድል በኋላ ጣልያን ስደተኞች ተቀባይ አገር መሆኗን እና በርካታ ጥቁሮችም በጣልያን በነጻነት እንደሚኖሩ ይናገራሉ።

በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ተይዘው የነበሩት በርካታ የአፍሪካ አገራትም ከአበበ ድል በኋላ ነጻ ወጥተዋል።

የእርሱ ድል የጥቁሮች አልሸነፍ ባይነትን በመፍጠር ረገድ የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ እንዳለው ቫሌሪዮ ይናገራሉ።

በ1960 አስራ ሦስት የአፍሪካ አገራት ነጻነታቸውን ያወጁበት ነበር። ስፖርቱም ይህንን ለውጥ የገለጸ ነበር።

አበበ በኦሊምፒክ አገራቸውን እና አፍሪካን ብሎም መላ ጥቁር ሕዝቦችን ለሚያስጠሩ በርካታ አፍሪካውያን ሯጮችም ፈር ቀዷል።

“አበበ ቢቂላ በፍፁም የማይጠፋ ስም ነው። ስለአበበ ሲወራ ነው የኖረው። ወደፊትም ልክ እንደ እኔ እና እንዳንቺ ያሉ ጋዜጠኞች ስለአበበ ቢቂላ ማውራታቸው የማይቀር ነው” ይላሉ ቫሌሪዮ።