አበበ ቢቂላ፡ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአውሮፓውያኑ 1960 ዓ.ም. በሞቃታማዋ ሮም ከተማ አንድ የገበሬ ልጅ ባዶ እግሩን ሮጦ ባለድል በመሆን ብዙዎችን አስደነቀ። ለአፍሪካም አዲስ ደማቅ ታሪክ ፃፈ።
በዚያች ምሽት የከተማዋ ነዋሪዎች ነቅለው ወጥተው የሩጫ ውድድር ይመለከቱ ነበር። የኦሊምፒክ የማራቶን ተወዳዳሪዎች የሕዝቡን ጭብጨባና ድጋፍ ተገን አድርገው ይገሰግሳሉ።
ከሁሉም ቀደሞ ወደ ማጠናቀቂያ የመጣው አበበ ቢቂላ ነበር። የጣሊያን ወታደሮች ችቦ አብርተው ኢትዮጵያዊ አትሌትን ይከተላሉ።
ቀይ ቁምጣ እና ጥቁር ካናቴራ ያደረገው አበበ ቢቂላ አብዛኛውን የማራቶን ክፍል ወርቅ ይወስዳል ተብሎ ትልቅ ግምት ከተሰጠው ሞሮኳዊው ራዲ ቤን አብዲሰላም ጋር በመፎካከር ነው የዘለቀው።
ነገር ግን ሩጫው ሊጠናቀቅ አንድ ኪሎ ሜትር ገደማ ሲቀረው አበበ ቢቂላ ተቀናቃኙን ጥሎት መሄድ ጀመረ። የመጨረሻዎቹን ሜትሮች በአስደናቂ ፍጥነት የሮጠው አበበ እጆቹን በድል እያወናጨፈ ድሉን አስመሰከረ።
አበበ ቢቂላ በዚያች ምሽት የመጀመሪያው በኦሊምፒክ መድረክ ወርቅ ያመጣ ጥቁር አፍሪካዊ ሆነ።
ይህ ብቻ ሳይሆን ውድድሩን በ2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ16 ሰከንድ በማጠናቀቅ አዲስ የኦሊምፒክ ክብረ-ወሰን አስመዘገበ።
ድሉ ብዙዎችን በግርምታና አድናቆት አፍ ያስያዘ ነበር። አበበ ቢቂላ በወቅቱ ማንም የማያውቀው ሯጭ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ማራቶኑን በባዶ እግሩ ጀምሮ በባዶ እግሩ መጨረሱ ብዙዎችን አስደንቋል።
አበበ ይህ ያደረገው ይዞት የመጣው ጫማ ያረጀ በመሆኑ፤ አዲስ ጫማ ደግሞ እግሬን ይልጠኛል ብሎ በመስጋቱ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“ለወትሮው ቢሆን ኖሮ ሻምፒዮኖች ቀስ እያሉ ነው ወደላይ የሚመጡት። ቁንጮ ሲሆኑ ሁሉም ሰው ያውቃቸዋል። አበበ ቢቂላ ግን ማንም አያውቀውም ነበር” ይላል ስለሯጩ መፅሐፍ የፃፈው ብሪታኒያዊው ቲም ጁዳህ።
“ይህ ነው በባዶ እግሩ ማራቶን ያሸነፈውን አፍሪካዊ ሯጭ በአንድ ጊዜ ታዋቂ ያደረገው።”
አበበ ቢቂላ ወደ ሀገሩ ሲመለስ የጀግና አቀባበል ተደረገለት። በሺዎች የሚቆጠሩ አደባባይ ወጥተው አጀቡት።
የአበበ ቢቂላ የ1960 የሮም ድል አንደምታው ከሀገሩ አልፎ ለመላው አፍሪካ እና ጥቁር ሕዝብ ክብር ነበር።
“ወቅቱ በርካታ ሀገራት ከቅኝ-አገዛዝ ቀንበር ነፃነት እየወጡ ያሉበት እና አፍሪካዊያን በዓለም መድረክ ደምቀው መታየት የጀመረቡት ነበር” ይላል ጁዳህ።
“ይህን ታሳቢ በማድረግ አበበ ቢቂላ እንደ ተወርዋሪ ኮከብ ያለ ምሳሌ ነው ማለት ይቻላል።”
የአበባ ቢቂላ ተምሳሌትነት ዛሬም እንደቀጠለ ነው።
“የአፍሪካ ታሪክን የምታውቅ ከሆነ በርካታ ሀገራት ከቅኝ-ግዛት ነፃ የወጡት የእርሱ ድል ካመጣ በኋላ ነው” የሚለው ደግሞ የቀድሞው የኦሊምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ባለቤት ኢትዮጵያ የረዥም ርቀት ሯጭ ኃይሌ ገብረስላሴ ነው።
አበበ ቢቂላ ከድሉ በኋላ ወደ ሀገሩ ሲመለስ የኬንያው ኔሽን ጋዜጣ፤ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ የኢትዮጵያ ኒሻን ሸለሙት ሲል ዘግቧል። ኃይለ ስላሴ ከኒሻኑ በተጨማሪ የፖሊስ ማዕረግ፣ መኖሪያ ቤት እና አዲስ ቮክስቫገን ቢትል መኪና ሸልመውታል።
ከገጠር እስከ ከተማ
አበበ ቢቂላ በ1932 ዓ.ም. ጃቶ ከምትባል መንደር የተወለደ የእረኛ ልጅ ነው።
በወጣትነት ዕድሜው ወደ አዲስ አበባ መጥቶ የወቅቱ ብሔራዊ ዘብ የነበረውን ክብር ዘበኛ ተቀላቀለ። ሥራው ደግሞ ታላቅ ክብር የሚሰጠው ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴን መጠበቅ ነው።
በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮችን እንዲያሰለጥን የተቀጠረው ስዊድናዊው ኦኒ ኒስካነን የአበባ ቢቂላን እምቅ ችሎታ መታዘብ ቻለ።
ኒስካነን፤ አበበ ቢቂላን ለማራቶን ውድድር ብቁ ለማድረግ የልምምድ ሥራውን ተያያዘው።
ነገር ግን አበበ ኢትዮጵያ አሉኝ ከምትላቸው ሯጮች ተርታ የሚመደብ አልነበረም። ባይሆን የቡድን አጋሩ ዋሚ ቢራቱ ወደ ሮም አቅንቶ ሀገሩን እንደሚያስጠራ ተጠብቆ ነበር። ራጮቹ ወደ ሮም ሊሄዱ ጥቂት ቀናት ሲቀራቸው ዋሚ በሕመም ምክንያት መብረር እንደማይችል ተሰማ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሁለተኛው የኦሊምፒክ ወርቅ
አበበ ቢቂላ ሮም የተከለውን ሌጋሲ በ1964 ቶኪዮ ላይም ደገመው። የኦሊምፒክ ማራቶንን በተከታታይ በማሸነፍ የመጀመሪያ ሰው ሆኖ ስሙ ተፃፈ።
አበበ ቢቂላ፣ ዋልደማር ቺዬርፒንስኪ እና ኢሊዩድ ኪፕቾጌ ብቻ ናቸው በኦሊምፒክ ታሪክ በተከታታይ የወቅር ሜዳሊያ ማምጣት የቻሉት።
ምንም እንኳ አበበ ቢቂላ በሁለተኛው የኦሊምፒክ ውድድሩ ጫማ ተጫምቶ ቢሮጥም እክል አላጣውም።
የማራቶን ውድድሩ ከመካሄዱ ከ40 ቀናት በፊት አበበ ድንገተኛ የትርፍ አንጀት ቀዶ ጥገና ማድረግ ነበረበት።
በሙሉ ጤንነት ለመሮጥ የነበሩት ቀናት ጥቂት ቢሆኑም በቶኪዮ ብሔራዊ ስታድየም የመጨረሻዎቹን ሜትሮች ተቀናቃኞቹን ጥሎ በመግባት 2፡13፡11 የሆነ አዲስ ክብረ-ወሰን አስመዘገበ።
ዎርልድ አትሌቲክስ እንደሚለው አበበ ቢቂላ ከ1960 እስከ 66 ባለው ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካደረጋቸው 13 የማራቶን ውድድሮች 12ቱን ማሸነፍ ችሏል። ነገር ግን ሁለተኛው የኦሊምፒክ ድሉን ካስመዘገበ ከአምስት ዓመታት በኋላ ሐዘን አጠላበት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መከራን መቋቋም
መጋቢት 1969 አበበ ቢቂላ ቮክስቫገን ቢትል መኪናውን እያሽከረከረ ሳለ ባጋጠመው አደጋ ምክንያት ከአንገት በታች ‘ፓራላይዝድ’ ሆነ (ሰውነት የማንቀሳቀስ ችግር ገጠመው)።
እንግሊዝ ወደሚገኘው ስቶክ ማንዴቪል ሆስፒታል ለሕክምና ቢወሰድም ድጋሚ መራመድ እንደማይችል ዶክተሮቹ ነገሩት።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ አበበ እጆቹን ማንቀሳቀስ ቻለ። ይሄኔ ነው ወደ ቀስት ውርወራ እና ቴኒስ ዓይነት የስፖርት መስኮች የተሰማራው።
በ1970 ለንደን በሚካሄደው የስቶክ ማንዴቪል ጨዋታዎች ላይ ተሳተፈ። ይህ ውድድር አሁን ፓራሊምፒክስ ተብሎ የሚጠራው ውድድር አባት ነው።
በቀጣዩ ዓመት አካላዊ ጉዳት ያለባቸው ሰዎች በሚሳተፉት ውድድር ለመሳተፍ ወደ ኖርዌይ አቅንቶ በፈረስ ጋሪ ግልቢያ አሸናፊ ሆኖ ተመለሰ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአበበ ሌጋሲ
አበበ ቢቂላ በአውሮፓውያኑ 1973 በአደጋው ምክንያት በደረሰበት ሕመም ምክንያት በ41 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ በወቅቱ ብሔራዊ የሀዘን ቀን ያወጁ ሲሆን አበበ ቢቂላ በክብር እንዲቀበር አደረጉ።
ምንም እንኳ አበበ ብዙ በሚሠራበት ዕድሜው ከዚህች ዓለም ቢሰናበትም ሌጋሲው ግን ዓመታትን ተሻግሮ እዚህ ደርሷል። አዲስ አበባ የሚገኘውን አበበ ቢቂላ ስታድየም ጨምሮ በርካታ ትምህርት ቤቶች እና ሽልማቶች በሱ ስም ይጠራሉ።
ከሁሉም የላቀው የአበበ ቢቂላ ሌጋሲ ግን በምስራቅ አፍሪካ ያሉ ሯጮች በረዥም ርቀት ውድድር የዓለም ቁንጮ እንዲሆኑ ማስቻል ነው።
ከአበበ በኋላ የመጡ እንደ ኃይለ ገብረስላሴ እና ኤሊዩድ ኪፕቾጌ ያሉ ኢትዮጵያዊያን እና ኬንያዊያን ሯጮች መስኩን ተቆጣጥረውት ቆይተዋል።
“እኛ [አፍሪካዊያን ሯጮች] የአበበ ቢቂላ ውጤቶች ነን። በአበበ ቢቂላ ምክንያት እኔ ዓለም ያወቀኝ አትሌቶች መሆን ችያለሁ” ይላል ኃይሌ ገብረስላሴ።
በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ኢትዮጵያን ወክሎ በፓሪስ ኦሊምፒክ የሚሳተፈው ጌትነት ዋሌ፤ አበበ ቢቂላን “አልፋ ነው” ይለዋል።
“እሱ የመጀመሪያው ነው። ሁሌም ሲዘከር ይኖራል።”












