ጎበዝ ሯጭ ለመሆን በተፈጥሮ መታደል አለብን ወይስ በልምምድ ሊመጣ ይችላል?

በ2023 ሲያራ ማጊያን በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን 1500 ሜትር ስትሳተፍ

የፎቶው ባለመብት, PACE Sports Management

አንዳንዶች በተፈጥሮ ጎበዝ ሯጮች ናቸው። ሌሎች ደግሞ በፍጥነት ለመሮጥ ያላቸውን ኃይል ያሟጥጣሉ። “በተፈጥሮ ጎበዝ ሯጭ መሆን ይቻላል?” የሚለው ጥያቄ የሚነሳው ይሄኔ ነው። መልሱን ዘረ-መል ውስጥ ሊያገኙት ይችላሉ።

ሩጫ ዓለም አቀፍ እና እጅግ ታዋቂ ሰውነት ማጎልመሻ ስፖርት ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ 64 ሚሊዮን ሯጮች አሉ ይባላል። በየክፍለ ዓለማቱ ያሉትን ቆጥሮ መዝለቅ ከባድ ነው።

ከምንምጊዜውም በላይ የማራቶን ሯጮች ቁጥር እየጨመረ ነው። የአዳዲስ ተመዝጋቢዎች ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል የሚለው ስትራቫ የተባለው የእንቅስቃሴ መተግበሪያ [አፕ] ነው።

በአውሮፓውያኑ 2023 ፓርክራን የተባለው የማኅበረሰብ ሩጫ የሚያሰናዳ ድርጅት 8.5 ሚሊዮን ሰዎችን መዝግቢያለሁ ይላል።

ምናልባት ሩጫ እንደሌሎች ስፖርቶች ብዙ ቁስ የማይጠይቅ መሆኑ ይሆናል ተወዳጅነቱን ያናኘው።

ሩጫ ለመሮጥ ጂም ተመዝግበው ወረፋ መጠበቅ፤ አሊያም ውድ ቁስ መሸመት አይጠበቅብዎትም። ቁምጣ እና አመቺ ጫም ተጫምቶ መውጣት ይቻላል።

ለመሆኑ ፈጣን ሯጮችን ቀርፋፋ ከሚባሉት የሚለያቸው ምንድነው? አሁን አሁን ብቅ የሚሉ ማስረጃዎች ዘረ-መላችን ትልቅ ሚና እንዳለው ያሳያሉ።

ሲያራ ማጊያን በዘንድሮው የ2024 ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ቆርጣ ተነስታለች። ከፍተኛ አልቲትዩድ አለው በሚባለው የአሜሪካዋ አሪዞና ግዛት በሚገኘው ፍላግስታፍ ቀን ተሌት ሳትል ልምምዷን እያጦፈችው ነው።

ከዚህ በፊት በተሳተፈችባቸው ሩጫዎች ላይ ድል ቀንቷታል። በኮመንዌልዝ ጌምስ እና በአውሮፓ ሻምፒዮን የብር ሜዳሊያ አሸንፋለች። በዓለም ሻምፒዮና ደግሞ አራተኛ ወጥታለች።

የ31 ዓመቷ አትሌት የአየርላንድ የ800 ሜትር፣ 1000 ሜትር እና የ1500 ሜትር ክብረ-ወሰን ባለቤት ናት። በቅርቡ የፓርክራን የ5 ሺህ ሜትር ውድድርን በ15 ደቂቃ ከ13 ሰከንድ በማጠናቀቅ የዓለም ክብረ-ወሰንን ጨብጣለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከጥዋቱ 1፡00 ወጥታ ልምምዷን ማድረግ ተያይዛዋለች። ለሩጫ ያላት ፍቅር እና ቀና አመለካከት ለየት ያለ ነው። ነገር ግን ተወዳዳሪዎቿ ደግሞ ቀላል የሚባሉ አይደሉም።

“ልጅ ሳለሁ ሆኪ [ገና ጨዋታ ዓይነት] ጨዋታ ስጫወት ነው ያደግኩት። ፈጣን ስለነበርኩ መሐል ላይ ያደርጉኛል። ግን ከሁሉም ፈጣን ነበርኩ ማለት አልችልም። የስፖርት ቀን በጣም የምወደው ቀን ነው። ነገር ግን ሁሉንም ውድድር አሸንፊያለሁ ማለት አልችልም” ትላለች።

ማጊያን የአጭር ርቀት አሊያም የረዥም ርቀት ተወዳዳሪ አይደለችም፤ የመካከለኛ ርቀት እንጂ።

“የውድድርን ስሜት በጣም እወደዋለሁ። ሁሉንም ነገር ለማድረግ ዝግጁ ነበርኩ። ስቃዬን ሁሉ ችዬ ወጥቼ መወዳደር ነበር ፍላጎቴ። ፈጣን እንደሆንኩ አውቅ ነበር? በፍፁም።”

እንደመታደል ሆኖ ማጊያን ያላት ዘረ-መል በአትሌቲክስ ዘርፍ ከፍተኛ የሚባለው ሥፍራ የሚያደርሳት ነው። “ያለኝ ዘረ-መል በአትሌቲክስ ዘርፍ እዚህ ያደርሰኛል ብዬ አስቤ አላውቅም” ትላለች።

ሳይንቲስቶች ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት “ፈጣኑ ዘረ-መል” የሚባል ነገር ያለ እንደሆነ ለማጣራት ጥናት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ውጤቶች የሚያሳዩት በአትሌቲክስ ዘርፍ ጠንካራ የሆኑ ሰዎች ዘረ-መል ለየት ያለ ነው።

በሰውነታችን ውስጥ 200 ዓይነት ስፖርታዊ አቅማችንን ሊወስኑ የሚችሉ የተለያዩ ዘረ-መሎች ሲኖሩ፣ ከእነዚህ መካከል 20 የሚሆኑት አንድ ሰው ጠንካራ አትሌት እንዲሆን ሊያግዙ ይችላሉ።

ነገር ግን ይህ ማለት ዘረ-መላቸው ለሯጭነት የተመቻቸ ሁሉ ጠንካራ ሯጮች ይሆናሉ ማለት አይደለም። ታዋቂ እና ጠንካራ አትሌት ለመሆን ብዙ ነገሮችን ማለፍ ይጠይቃል።

ልምምድ፤ አካባቢያዊ ሁኔታዎች ከዘረ-መል ጋር ሲደባለቁ ትልቅ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ።

የሯጮች እግር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በእንግሊዝኛው ‘ስፒድ ጂን’ የሚባለው ዘረ-መል አሊያም ኤሲቲኤን3 በፈጣን የጡንቻ ጅማቶች ውስጥ ያለ ፕሮቲንን የሚያጎለብት ነው።

ስኬሌታል መስልስ የሚባሉት ደግሞ በመቶዎች አንዳንዴም በሺዎች የሚቆጠሩ ጅማቶች ተጠላልፈው የሚሠሩት ጡንቻ ነው። እኒህ ጡንቻዎች ጥንካሬያቸው የሚለካው በፍጥነታቸው ነው። ዓይነታቸው ደግሞ ሁለት ነው።

አንደኛው ዓይነት ጡንቻ ያሏቸው በጣም ታዋቂ የሆኑ የረዥም ርቀት ሯጮች እና ብስክሌተኞች ናቸው። ሁለተኛው ዓይነት ጡንቻ ደግሞ የአጭር ርቀት ሯጮች እና ክብደት አንሺዎች ላይ የሚስተዋል ነው።

የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ኤሴክስ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ዘረ-መል በአንድ ሰው የአትሌቲክስ ብቃት ላይ ያለውን ተፅዕኖ ሲያጠኑ ነበር።

የስፖርት ሳይንቲስቱ ሄንሪ ቻንግ እና የምርምር ቡድናቸው ዕድሜያቸው ከ20 አስከ 40 ካሉ 45 ሴት እና ወንድ ሯጮች የዘር ቅንጣቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ዘረ-መሎች ወሰዱ።

የጥናቱ ተሳታፊዎች ለስምንት ሳምንታት በሳምንት ሦስተ ጊዜ ለ30 ደቂቃዎች እንዲሮጡ ተደረጉ። ምንም እንኳ በተሰጣቸው ጊዜ ተመሳሳይ ዓይነት መሻሻል ማሳየት ቢገባቸውም አንዳንዶች 20 በመቶ ለውጥ ሲያሳዩ፣ ሌሎቹ ደግሞ 15 በመቶ ለውጥ ማሳያታቸውን ቻነግ ይናገራሉ። አንዳንዶቹ ግን ምንም ዓይነት ለውጥ አላሳዩም።

የቻንግ ቡድን ከዚህ ውጤት በኋላ የሯጮቹን የዘረ-መል ዓይነት ማጥናት ያዙ። ይሄኔ ነው 19 ዓይነት ለየት ያሉ ዘረ-መሎች ያገኙት።

“20 በመቶ ለውጥ ያሳዩት ሯጮች 19ኙ የዘረ-መል ዓይነቶች አሏቸው። በሌላ በኩል ምንም ለውጥ ያላሳዩት ደግሞ አንድ ወይም ሁለት ዓይነት ብቻ ነው የተገኘባቸው” ይላሉ።

ከ19ኙ ዓይነቶች መካከል አንደኛው በሳይንሳዊ አጠራሩ ኤምኤኦኤ የተባለው ሲሆን፣ ይህ ዘረ-መል ከኃይለኛነት እና ከአደጋ መጋፈጥ ባሕሪ ጋር የሚያያዝ ነው።

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በሩጫው ዘርፍ ከዘመናዊ አትሌቲክስ መጀመር በኋላ የተሻሻሉ ክብረ-ወሰኖች ከልምምድ ጋር ግንኙነት አላቸው። የሩጫ ጫማ እና መሮጫ ሜዳው የራሳቸው አስተዋፅዖ እንዳላቸው ይነገራል።

አልፎም ባለሙያዎች እንደሚሉት ልምምድ እያደረግን እያለን የጡንቻዎቻችን ገመዶች ከቀርፋፋ ወደ ፈጣን መቀየር አለብን። ምናልባትም ፍጥነት ለሚጎላቸው ሰዎች አንድ ተስፋ ሊሆን ይችላል።

“በፍጥነት መሮጣ መቻል በጣም ቀላል ነው” የሚሉት ደግሞ የባዝ ዩኒቨርሲቲ የባዮሜካኒክስ ተመራማሪዋ ስቴፊ ኮልየር ናቸው። “በፍጥነት ለመሮጥ ያለንን ኃይል ሁሉ መሬት ላይ ማሳረፍ መቻል አለብን” ይላሉ።

አንዲት አትሌት በሩጫ ተራራ ስትወጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፍጥነት የሚጨምረው ሩጫ ሲጀመር ነው። ውድድሩ እየጨመረ ሲመጣ ፍጥነት እየቀነሰ ይመጣል። ባለሙያዋ እንደሚሉት ፍጥነታችንን ጠብቀን ለመሮጥ ጡንቻችን ኃይል እንዲያወጣ ማስቻል አለብን። ለዚህ ነው ፍጥነትን ለመጠበቅ ጠንካሬ፣ ኃይል እና ቴክኒክን ማጣመር አለብን የሚሉት።

ነገር ግን ስንሮጥ ከመሬት ጋር ያለንን ግንኙነት ከቀነስን ጉልበታችንን መቆጠብ እንችላልን ይላሉ ኮልዬር።

ማጊያን “የተለያዩ ነገሮችን ማድረግ” እንችላለን ስትል ትመክራለች። “አኔ ስሮጥ እየቆጠርኩ ነው። ታፕ፣ ታፕ፣ ታፕ እያልኩ በጭንቅላቴ እየቆጠርኩ ነው የምሮጠው። መሬትን በፍጥነት ነክቼ ስመለስ በፍጥነት እንድሮጥ ያግዘኛል” ትላለች።

ማጊያን ልምምድ ስናደረግ በሩጫ ተራራ መውጣትን ማካተት ትመክራለች። “አጠር ያለ ተራራ በፍጥነት መውጣት ያስደስተኛል። ከ10 ሰከንድ በላይ አልሄድም። ተራራውን እወጣለሁ። ተመልሼ አገግማለሁ። እንደገና እወጣለሁ።”

ተወዳዳሪ ያልሆኑ ሰዎች 5 ኪሎ ሜትር ሩጫን በ30 ደቂቃ ሊያጠናቅቁ ይችላሉ። ሩጫ ለልብ ጤና መልካም ነው። ለአጥንታችንም ይበጃል። ለአእምሮ ጤናችንም ጠቃሚነት አለው። ብዙ ዓመት ለመኖር ጠቃሚ እንደሆነም ይመከራል።

እንደውም ሳይንስ የሚለው ቀስ ብሎ መሮጥ በፍጥነት ከመሮጥ በላይ ጥቅም አለው። ምክንያቱም ለአደጋ ከመጋለጥ ይጠብቃል፤ ቀስ በቀስ ፍጥነታችንን እንድንጨምርም ያግዛል።

ማጊያን ሰውነታቸው ውስጥ ለሩጫ አስፈላጊ የሚባለው ዘረ-መል ሳይኖራቸው ሩጫን ለሚያዘወትሩ ሰዎች አክብሮት አላት።

“በተፈጥሮ በጣም ጎበዝ ሯጮች ሆነው ነገር ግን በውድድር ለመሳተፍ የሚያስችል ጥንካሬ የሌላቸው በርካታ አትሌቶችን አውቃለሁ። ተፈጥሮ ብዙም ያላደላቸው ግን ባላቸው አቅም የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን አከብራለሁ።”

በሌላ በኩል ቹንግ “ዘረ-መሉ ካላችሁ እና ጠንክራችሁ ከተለማመዳችሁ፤ የሚያቆማችሁ የለም” ይላሉ።