አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ ሲታወስ

ሻምበል አበበ በቂላ መስከረም 11 1960 ሮም

የፎቶው ባለመብት, Keystone-France

በዛሬው ዕለት ጥቅምት 25 ታዋቂው የማራቶን ሯጭ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ 41 ዓመታትን አስቆጥሯል። አትሌቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካውያን በአትሌቱ ዘርፍ በር ከፋች ነበር። የዚህ ታላቅ ሰው መካነ መቃብር አዲስ አበባ በሚገኘው ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስትያን ይገኛል። ድሉ ደግሞ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ታትሟል።

የአበበን ታሪክ የታሪክ ሰነዶች፣ የስፖርት መዛግብት፣ የዓለም መገናኛ ብዙኀንና ኢትዮጵያውያን በጉልህ ያስታውሱታል። ከድሎቹ ሁሉ ደምቆ የሚታወሰው ደግሞ በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ ለአገሩ ኢትዮጵያ እና ለጥቁር ህዝቦች ያስመዘገበው ድል ነው።

17ኛው የዓለም ኦሎምፒክ ውድድር እኤአ በ1960 በጣልያን መዲና ሮማ ነበር የተካሄደው። በዚህ ውድድር ከ83 ሀገራት የተወጣጡ ከ5 ሺህ በላይ ስፖርተኞች መሳተፋቸው ይነገራል።

በሮም ኦሎምፒክ ከተሳተፉ ጥቁሮች መካከል ግን ሌላ ባለድልም አለ። መሐመድ ዓሊ በቀላል ሚዛን የወርቅ ሜዳልያ ተጎናፅፎ ነበር። ቢሆንም ኦሎምፒኩ በመሐመድ ዓሊ ወርቅ ሜዳልያ እምብዛም የደመቀ አልነበረም።

በወቅቱ ታሪክ የሚያስታውሰው ሌላ ክስተትም ነበር። ጊዜው ደቡብ አፍሪካ በአህጉራዊ ውድድሮች ለመጨረሻ ግዜ ተሳትፋ የታገደችበት ነበር። የእገዳዋ ምክንያት ደግሞ ትከተለው በነበረ የአፓርታይድ ስርአት መሆኑ ነው። ቢሆንም የያኔ የሮሙ ኦሎምፒክ በመሐመድ ዓሊ የወርቅ ሜዳልያም ብሎም በደቡብ አፍሪቃ መታገድ አይደለም የሚታወሰው።

ታድያ በምን ይታወሳል ያሉ እንደሆነ በውድድር ዘመኑ የማራቶን ሩጫ ያለ ጫማ ሮጦ የርቀቱ አዲስ ክብረወሰን ባስመዘገበው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሻምበል አበበ በቂላ ነው።

በወቅቱ በርካታ ሊጠቀሱ የሚችሉ ነገሮች ቢከናወኑም አበበ ግን ታሪኮችን ሁሉ ልቆ የሚታወስ ድንቅ ታሪክ አስመዘገበ።

ያኔ፣ አይደለም አበበ በቂላ የሚባል አትሌት፣ ኢትዮጵያ ተብላ ስለምትጠራ ሀገርም የሚያውቅ የውጭ ዜጋ ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም።

ይሁን እንጂ ውድድሩ በጣልያን መካሄዱ እና የጣልያን ወረራ በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት ተጠናቅቆ ነጻነቷን የማግኘቷ ወሬ ገና ከዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች የወሬ አጀንዳነት ባለመረሳቱ፣ የአበበ ቢቂላ ድል ገነነ።

የዓለም አቀፍ ሚድያዎች ሳይቀር ባልተጠበቀው የአትሌት አበበ በቂላ ድል ተደምመው ደጋግመው፣ በባዶ እግር ሮጦ የወርቅ ሜዳልያ ስላገኘው ኢትዮጵያዊው አትሌት ተናገሩ።

ጥቅምት 23 1964 ቶክዮ ኦሎምፒክ

የፎቶው ባለመብት, Keystone

"ሙሶሎኒ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች አሰልፎ እና መድፍ እና መርዛማ ጋዝ ተጠቅሞ ኢትዮጵያን ሲወር፣ አንድ ኢትዮጵያዊ ወታደር ግን ጣልያንን ብቻ ሳይሆን መላውን አለም አሸነፈ" የሚል ዘገባዎች ተሰራጩ።

ያቺ አጋጣሚ…

የኦሎምፒክ ውድድር እየተካሄደ በነበረበት ግዜ ጥቂት ኢትዮጵያውያን በጣልያን ሮም ይኖሩ ነበር። እነዚህ ኢትዮጵያውያን በካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን አማካኝነት የሥነ መለኮት ትምህርት እንዲማሩ ተብለው ከኢትዮጵያ የተላኩ ናቸው።

እኤአ በ1960 አንዲት እናት በስራ ምክንያት ከአስመራ ወደ ሮም ተጉዘው ነበር። እኚህ ወ/ሮ ሳራ ሰለባ፣ የተሰኙ እናት "የጥቁሮች ፊት ሳላይ እኖራለሁ፣ ያቺ ተወልጄ ያደግኩባት አስመራም በምናቤ ትመላለስ ነበር። አልፎ አልፎ እነዛ የተባረኩ የሥነ መለኮት ተማሪዎች ብቸኝነቴ ተረድተው እየመጡ ይጠይቁኝ ነበሩ" ብለው ያጫውቱት እንደነበር ልጃቸው ያስታውሳል።

ወ/ሮ ሳራ፣ አበበ በቂላ ሮጦ ድል ያደረገበ ዕለት ውደድሩ በቴሌቭዥን መስኮት ተከታትለዋል። አብረዋቸው የነበሩ ነጮች ተሰብስበው "የሀገርሽ ልጅ አሸንፏል" እያሉ ይጮሁ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ታድያ ወ/ሮ ሳራ አብረዋቸው ከመደሰት ይልቅ ማልቀስን መረጡ። ለወ/ሮ ሳራ የለቅሶ ምክንያት የነበረው ደግሞ የአበበ ባዶ እግር መሮጥ ነበር።

ሻምበል አበበ እና አሰልጣኙ ኦኒ ኒስካነን

አበበ ቢቂላ ነሐሴ 30 ቀን 1925 ዓ.ም በሸዋ ጠቅላይ ግዛት በደብረ ብርሃን አውራጃ፣ ደነባ ልዩ ስሟ ጃቶ በምትባል ሥፍራ ከአባቱ አቶ ቢቂላ ደምሴና ከእናቱ ከወይዘሮ ውድነሽ መንበሩ ተወለደ።

ወጣቱ አበበ እንደአካባቢው ልምድ በእረኝነት ቤተሰቡን አገልግሏል። በአሥራ ሁለት ዓመቱም የቄስ ትምህርቱን አጠናቋል። በዚህ በጨቅላ ዕድሜው ስመ ጥር የገና ተጫዋች እንደነበር ይነገርለታል። በ1944 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመሄድ በክብር ዘበኛ ሰራዊት በወታደርነት ተቀጥሮ በገና ጨዋታ እና በስፖርት እየዳበረ ቆየ።

ስዊድናዊው ኦኒ ኒስካነን [1910-1984] የክብር ዘበኛ ስፖርት ክፍል አስልጣኝ ነበር። በወቅቱ የስፖርት ክፍሉ ባልደረቦች ከነበሩት መካከል የሁለቱ አበበዎች የሩጫ ልምድ ትኩረቱን ስቦት እንደነበር ትቶት የሄደው ማስታወሻ ያሳያል።

ስዊድናዊው ኦኒ ኒስካነን [1910-1984] የክብር ዘበኛ ስፖርት ክፍል አስልጣኝ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አበበ በቂላ ወደ አትሌቱ መንደር የተቀላቀለው በ24 አመቱ ነበር። ኦኒ ኒስካነን አበበን ወደ ሩጫ እንዲገባ ባያደፋፍረው አትሌትም ላይሆን ይችል እንደነበር ይነገራል። እርግጥ ነው አበበ እግር ኳስ እና ቅርጫት መጫወት ይወድ ነበር።

አስለጣኝ ኦኒ ኒስካነን አበበ የሩጫ ውድድር እንዲሞካክር ይገፋፋው ነበር። በአራራጡ እና በራስ መተማመኑ ይወድለት ስለነበር በክቡር ዘበኛ ውድድሮች ሲያሳትፈው ጥሩ ውጤት ያመጣ ጀመር።

ኒስካነን የአበበ በቂላ እና አበበ ዋቅጅራ የሩጫ ልምድ አይቶ ሮም ላይ በተካሄደው የዓለም ኦሎሚፒክ ውድድር እንዲሳተፉ አዘጋጃቸው።

አበበ ዋቅጅራ ከአበበ ቢቂላ በ10 ዓመት ያህል የሚበልጥ ሲሆን በሮም ኦሎምፒክ ላይ እንደ አበበ ሁሉ በባዶ እግሩ ሮጦ ሰባተኛ መውጣቱን ድርሳናት ያሳያሉ።

ሁለቱ አበበዎች ለምን በባዶ እግር ሮጡ

በሮም ኦሊምፒክ አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ የሮጠበት ምክንያት በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ሲንፀባረቁ ተሰምተዋል። በርካታ መዛግብት ለአበበ የሚስማማ ጫማ መጥፋቱን፣ የሞከረውም ጫማ ስለጠበበው ያለጫማ መሮጥን መምረጡን ጽፈዋል።

እነዚህ መዛግብት አበበ ዋቅጅራም በባዶ እግሩ ስለመሮጡ ያነሱት አንዳች ነገር የለም። ይሁን እንጂ እውነታውን በተመለከተ የአበበ ቢቂላ ልጆች እንዲሁም አሰልጣኙ ትተዋቸው ያለፉ ድርሳናትና የይድነቃቸው ተሰማ እሸቴ ማስታወሻዎች ይህንን ይናገራሉ።

ኦኒ ኒስካነን እነ አበበን ይዞ ወደ ሮም ከተጓዘ በኋላ እዚያው ሮም የሩጫ ልምምድ ያደርጉ ነበር።

ልምምዱ የሚካሄደውም ጫም ተጫምተው እና በባዶ እግር ነበር። ኦኒ ኒስካነን በልምምዱ ሂደት ታድያ አንድ ነገር አስተዋለ። ሁለቱም አትሌቶች በባዶ እግር ሲሮጡ የተሻለ ፍጥነት ማስመዝገብ ችለው ነበር። ውድድሩን በድል ያጠናቅቁ እንጂ እንደ ፍላጎታቸው መሮጥ እንዲችሉ ፈቀደላቸው። አበበ ቢቂላ ጫማ ተጫምቶ ሲሮጥ በአንዲት ደቂቃ ከ5-6 ስንዝር ይዘገይ እንደነበርም አሰልጣኙ ኦኒ ኒስካነን መስክሯል።

ከውድድሩ በኋላ ስለ ሁኔታው የተጻፉት እውነታነት እንዳልነበራቸውም ኒስካነን ተናግሮ ነበር። 'ጫማ ስላልተገዛላቸው ነው' እና 'የተገዛላቸው ጫማ ስለጠበባቸው ነው' የሚሉ ሀሳቦች ሀቅ አይደሉም ብሏል ኒስካነን።

ኦኒ ኒስካነን እንደሚተርከው ሁለቱም ተወዳዳሪዎች ወደ ሮም ከመሄዳቸው በፊት ስለ ውድድሩ በቂ መረጃ ተሰጥቷቸው ነበር። በውድድሩ የተሻለ ፍጥነት ያላቸው ተወዳዳሪዎች እነማን ሊሆኑ ይችላሉ ከሚለው ጀምሮ እስከ የመወዳደርያ ማልያ ቁጥራቸው በሚገባ ተነግሯቸዋል።

እነ አበበ ቢቂላን ከሚፎካከሩት መካከል ደግሞ ሞሮኳዊው ሯጭ ራዲ ቢን አብደልሰላም ይገኝበታል። ስለራዲ እነ አበበ መረጃ ቢኖራቸውም የመወዳደሪያ ቁጥሩ መቀየሩን ግን አያውቁም ነበር።

ራዲ ቀድሞ የተሰጠው የመወዳደርያ ቁጥር ስላልተገኘ ነበር ሌላ አዲስ ቁጥር የተሰጠው።

እነ አበበ ግን ራዲ አዲስ ቁጥር እንደተሰጠው መረጃው የላቸውም። አበበ ከቀሪዎቹ ተወዳዳሪዎች በሰፊ ርቀት ፈንጠር ብሎ በሚሮጥበት ግዜ ሞሮኳዊው ራዲ ግን በቅርብ ርቀት ይከተለው ነበር።

በወቅቱ ሞሮኮ በውድድሩ ሶስት ተወዳዳሪዎች አሰልፋ ስለነበር፣ አበበ ከሶስቱ አንዳቸው ይሆናሉ በሚል ሮም የሚገኘው የአክሱም ሀውልት እስኪደርሱ ድረስ ብዙም ግምት አልሰጠውም ነበር።

አበበ በውድድሩ በአስልጠኙ እንዲያደርጋቸው ከተነገሩት ነገሮች መካከል አንዱ የአክሱም ሀውልት ሲደርስ ፍጥነቱ እንዲጨምር ነበር።

አበበም በተሰጠው ትእዛዝ መሰረት ውድድሩ ሊያልቅ 2 ኪሎ ሜትር ሲቀረው ሮም ፒያሳ በተተከለው አክሱም ሀውልት ሲደርስ በፍጥነት ተፈተለከ።

አበበ ያኔ ለጥቂትም ቢሆን ቢዘናጋ ኖሮ ራዲ የማሸነፍ እድል እንደነበረው ይነገራል።

እንደ አስልጣኙ ኦኒ ገለጻ ከሆነ አበበ 40 ኪሎ ሜትር ድረስ አብሮት የተጓዘው ራዲ መሆኑን ቢያውቅ ኖሮ ቀድሞት ሊሮጥ ምናልባትም ያስመዘገበው ክብወሰን በተሻለ ያሻሽለው ነበር ይላል።

ሻምበል አበበ በቂላ በ1964 በቶክዮ ጃፓን በተካሄደው ውድድርም የራሱን ክብረወሰን በማሻሻል አሸናፊ ሆነ። ከውድድሩ አንድ ወር በፊት ግን ቀዶ ጥገና ተደርጎለት የነበረ ቢሆንም ውድድሩ በአስደናቂ ሁኔታ ለማጠናቀቅ ችሏል።

በ1968 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ36 ዓመቱ በኦሎሚፒክ ውድድር ለ3ኛ ግዜ የተሳተፈ ቢሆንም በጉዳት ምክንያት ሳይጨርስ የቀረ ሲሆን፣ ውድድሩ በሌኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ማሞ ወልዴ አሸናፊነት ተጠናቀቀ።

አለምን በባዶ እግር ሮጦ በማሸነፍ አንቱታ ያተረፈውን ሻምበል አበበ በቂላ በገጠመው የመኪና አደጋ ምክንያት በ41 ዓመቱ ከዚህ አለም ተለየ።