በዩናይትድ ኪንግደም የተቀጣጠለው ‘ፀረ-ስደተኛ’ ነውጥ መነሻው ምንድነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ብዙዎቹን የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ከተሞችን ያመሰው የቀኝ አክራሪዎች አመጽ አሁንም አልበረደም።
በሊቨርፑል፣ በማንችስተር፣ በብላክፑል፣ በቤልፋስት ትልልቅ ከተሞች ሳይቀር ቀወሱ ተሰራጭቷል።
ሁከቱን ለመቆጣጠር ስድስት ሺህ ፖሊሶች ተሰማርተዋል። 400 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ይህ አመጽ መነሻው ባለፈው ሳምንት ሰኞ፣ በሳውዝፖርት፣ አንድ ወጣት በስለት የሦስት አዳጊ ሴቶችን ሕይወት ማጥፋቱ ነው።
ይህን ተከትሎ ቁጣ ተቀሰቀሰ። አንዳንድ ነጭ ብሪታኒያውያን ጥቁሮችን በተለይም ሙስሊሞችን ማሳደድ ጀመሩ።
ስደተኞች ወደ ተጠለሉባቸው ሆቴሎች ሳይቀር እየሄዱ እሳት ለኮሱ።
በዚህ አመጽ በርካታ ፖሊሶች ተጎድተዋል።
እንደ ኬንያ፣ ሕንድ፣ ናይጄሪያ እና ማሌዥያ ያሉ አገራት ዜጎቻቸው ወደ ዩኬ ሲጓዙ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መግለጫ እስከማውጣት ደርሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር “ይህ የነጭ አክራሪዎች ውንብድና ነው” ሲሉ ድርጊቱን አውግዘውታል።
አመጹ በዚህ ደረጃ እንዴት ሊስፋፋ ቻለ?
ሐሰተኛ ዜና የነበረው ሚና
አንድ የ17 ዓመት ወጣት የፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት እንደተሰማ ዜናው እንደ ሰደድ እሳት በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ተዛመተ።
የቀኝ-ነጭ አክራሪ ቡድኖች ዜናውን ለራሳቸው አጀንዳ ተጠቀሙበት። በእሳት ላይ ነዳጅ አርከፈከፉ።
ጥቃት ፈጻሚው በጀልባ ወደ ዩኬ የገባ ሕገ ወጥ ስደተኛ ነው ብለው ወሬውን አስፋፉት።
የተጠርጣሪው ዕድሜ ከ18 ዓመት በታች ስለሆነ ፍርድ ቤት መጀመሪያ ላይ ማንነቱን ከመግለጽ ታቅቦ የነበረ ቢሆንም፣ ኋላ ላይ ግን አደጋው የከፋ እንደሆነ ሲረዳ ማንነቱ ይፋ ሆኗል።
ይህ ወጣት ስደተኛ አለመሆኑ ቢጠቀስም ቀኝ አክራሪዎች ግን ዕድሉን ማስመለጥ አልፈለጉም።
ሐሰተኛውን ዜና ማራገቡን ገፉበት።
በተለይ ሙስሊም ስደተኞች እና ጥቁሮች ኢላማ ተደረጉ።
ይህን ሐሰተኛ ዜና በኤክስ ገጽ ካራገቡት መሀል ‘ኢንግሊሽ ዲፌንስ ሊግ’ የተሰኘው የቀኝ አክራሪ ቡድን መሥራች ስቴፈን ሌነን ይገኝበታል።
ይህ ሰው ለማኅበራዊ ሚዲያ የሚጠቀመው ስም ቶሚ ሮቢንሰን እንደሆነ ቢቢሲ ማረጋገጥ ችሏል።
የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ሐሰተኛውን ዜና በስፋት ሲያሰራጩት ቀኝ አክራሪ ቡድን አባል ያልሆኑ ብሪታኒያውያን ሳይቀር ቁጣቸውን ለመግለጽ ጊዜ አልወሰደባቸውም።

ዘረኝነት እና ስደት
በዩኬ በሐምሌ ወር የተደረገው ምርጫ አንገብጋቢ አጀንዳ ከነበሩት አንዱ ወደ አገሪቱ በተለይም በጀልባ የሚተሙ ስደተኞች ጉዳይ ነበር።
ናይጅል ፋራጀል ተጽዕኖ ፈጣሪ የዩናይትድ ኪንግደም ፖለቲከኛ ናቸው። በፀረ-መጤ እና በፀረ ሙስሊም የማያወላዳ አቋማቸው ብዙዎች ስማቸውን ያነሱታል።
ዩኬ ከአውሮፓ ኅብረት እንድትወጣ ግፊት ካሳደሩ ዜጎች አንዱ ናቸው። እኒህ ሰው ‘ሪፎርም ዩኬ’ የሚል ፓርቲ ይዘው መጥተዋል።
የሰሞኑን ነውጥ ተከትሎ በሰጡት አስተያየት “የአገሪቱ ዜጎች ቅጥ ባጣው የፍልሰተኞች ወደ ዩኬ መፍለስ የተነሳ እንደ ማኅበረሰብ አደጋ ላይ እየወደቅን ነው፤ እየተሰነጣጠቅን ነው” ብለዋል።
ናይጀል፣ የስለት ጥቃቱ እንደደረሰ “አንዳንድ ዘገባዎች ጥቃት አድራሹ ወንጀለኛ በጀልባ ወደ ዩኬ የገባ ሙስሊም ስደተኛ እንደሆነ ያሳያሉ” የሚል ያልተጣራ መረጃን አሰራጭተው ነበር።
‘ፓትሪዮቲክ ኦልተርኔቲቭ’ የተሰኘው የቀኝ አክራሪዎች ቡድን በዚህ የስለት ጥቃት ሲያራምደው የነበረው አጀንዳው የሰመረለት ይመስላል። በርካታ ፀረ-ስደተኛ ሰልፎችን አሰናድቷል።
ይህ ቡድንን ጨምሮ ብዙዎቹ ቀኝ አክራሪዎች በዩኬ የሚገኙ መጤዎች አንድም ሳይቀር በጅምላ ወደመጡበት እንዲሸኙ ይሻሉ።
ዘረኝነት የተጫናቸው እነዚህ ቀኝ አክራሪዎች በርካታ መስጊዶች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል።
የጥገኝነት ጥያቄ ያቀረቡ ፍልሰተኞች የሚገኙባቸው መቆያዎችን በእሳት ለማጋየት ሞክረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዘረፋን እንደ መዝናኛ
አጋጣሚውን ተጠቅመው ወደ ዝርፊያ የገቡ የአገሪቱ ዜጎችም በርካታ ናቸው።
በሰሜን ምሥራቅ እንግሊዝ በምትገኘው ሰንደርላንድ ባንክ እና ዳቦ ቤት ሳይቀር የዘረፋ ሙከራ ተደርጎባቸዋል።
በብላክፑል ደግሞ በርካታ ሱቆች፣ ሱፐርማርኬቶች ሲዘረፉ ነበር።
የቢቢሲ ዘጋቢ በመሐል ከተማ ነዋሪዎች ሱቅ ሲዘርፉ ለማየት ችሏል። አንዳንድ በስደት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የገቡ ዜጎች ሱቆች እንደሆኑ የሚገመቱ መደብሮች ደግሞ ተለይተው በላያቸው ላይ እሳት ሲለቀቅባቸው ነበር።
የሰንደርላንድ ከተማ ካውንስል በኤክስ ገጹ፣ “ከተማችን ደማቅ እና ሰላማዊ ናት። ድርጊቱ እኛን የሚወክል አይደለም፣ እናወግዛለን” ብሎ ነበር።
መሐመድ ኢድሪስ በቤልፋስት የካፌ ባለቤት ነው። ባሽ ካፌ ይባላል። ነውጠኞች ካፌውን በእሳት አመድ አድርገውበታል።
መሐመድ እንደሚለው የዛሬ ዓመትም እንዲሁ በሳንዲ ሮው የሚገኘው የኮምፒውተር ሱቁ በአመጸኞች ወድሞበታል።
“እንደ አምናው ዘንድሮም ደገሙኝ። ካፌዬን አቃጠሉብኝ። ይህ ማኅበረሰቡ የሚሰባሰብበት ቦታ ነበር። ስለ ተስፋው የሚያወጋበት ቦታ ነበር። ከዚህ ወዲያ ምን ተስፋ አለ?” ሲል ጠይቋል።

አንዳንድ ተንታኞች የኑሮ መወደድ እና ማኅበራዊ ቀውስ ወጣቱ በቀላሉ ወደ ቀኝ አክራሪዎች እንዲገባ እያደረገው ነው ይላሉ።
ይህ የኑሮ ጫና ከኮቪድ ወረርሽኝ ዘመን የጀመረ አሁንም አልተቀረፈም።
“ዜጎች አሁን አሁን ተነጣጥለዋል። ማኅበረሰባዊ ተዛምዶው እየላላ ነው። በስፖርት፣ በመዝናኛ፣ በማኅበራዊ ተሳትፎ፣ በትምህርት ቤት መተሳሰሩ ቀንሷል። ማኅበረሰባዊ መቀራረብ ቢኖር ይህ አይከሰትም ነበር” ይላሉ የፀረ ሽብር ጉዳዮች መርማሪ የሆኑት ጋሬት ሪስ ለቢቢሲ።
ምናልባት ክስተቱ በሰፋ መነጽር ከታየ ምዕራቡ ዓለም በስደተኞች ላይ እያሳየ ያለው ፊት መንሳት አንድ መገለጫ ሆኖ ሊታይ ይችላል።
ቀኝ አክራሪዎች ከስደተኞች ባሻገር የጥገኝነት ጥያቄ አቅራቢዎችን ጉዳይ በፍርድ ቤት የሚይዙ ጠበቆችን ሳይቀር ጥቃት እንዲፈጸምባቸው በማነሳሳት አድራሻቸውን ማጋራት ጀምረዋል።
ፖሊስ በበኩሉ “የስደተኛ ጠበቆች ለጊዜው ከቤት ሆናችሁ ሥሩ” የሚል ምክር ሰጥቷል።
ምናልባት በዩናይትድ ኪንግደም እየሆነ ያለው በሌሎች የአውሮፓ ከተሞች ካለው ስሜት ብዙም የሚርቅ አይሆን ይሆናል። ቀኝ አክራሪዎች እየገፉት ያለው አጀንዳ የሚያጠነጥነው ፀረ ሙስሊም እና ፀረ ስደተኛ የሆነ አቋምን ነው።
ይህ ደግሞ በፈረንሳይ፣ በኔዘርላንድስ፣ በስዊድን፣ በዴንማርክ፣ በጣልያን ታይቷል። ከዓመታት በፊት ለቀኝ አክራሪዎች የፓርላማ መቀመጫ ማግኘት ብርቅ ነበር። አሁን ግን እየቀለለ መጥቷል ማለት ይቻላል።
ሕልማቸው እየሰመረ ይመስላል። በዩኬ እየታየ ያለው ክስተት መጪውን ዘመን ለመተንበይ አንድ ግብአት ተደርጎም ሊታይ ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images












