በዩኬ ስደተኞች ጠል ነውጥ እና ዘረኝነትን የሚነቅፉ ሰልፎች ተካሄዱ

ስደተኞች ጠል ነውጥና ዘረኛነትን የሚነቅፉ ሰልፎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዩናይትድ ኪንግደም ከሳምንት በፊት የተጀመረውን ስደተኞች ጠል ነውጥ የሚቃወሙ የፀረ ዘረኝነት ሰልፎች ተካሄዱ።

ስደተኞች ጠል ሰልፎች ይካሄዱባቸዋል በተባሉባቸው የሰሜናዊ ለንደን፣ ብሪስትል እና ኒው ካስል አካባቢዎች ነውጦቹን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል።

ስደተኞች ጠል ነውጥን በሚቃወሙት ሰልፎች ላይ “ስደተኞች መምጣት ይችላሉ” የሚሉና ሌሎችም ዘረኝነትን የሚኮንኑ መፈክሮች ታይተዋል።

ከ100 በላይ ሰልፎች ይካሄዳሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች ተሰማርተዋል።

ባለፈው ወር በሳውዝፖርት ሦስት ሕጻናት ልጆችን በስለት የወጋው ሙስሊም ጥገኝነት ጠያቂ ነው የሚል የተሳሳተ ዜና ከወጣ በኋላ ነው ነውጡ የተጀመረው።

መጀመሪያ ላይ ጥቃት መሰንዘር የተጀመረው ጥገኝነት ጠያቂዎች የተጠለሉባቸው ሆቴሎችና መስጊዶች ላይ ሲሆን መደብሮችም ተቃጥለዋል፤ ተዘርፈዋል።

ትናንት ስደተኞች ጠል ነውጦችን በመፍራት ሱቆች ተዘግተው ውለዋል።

የስደተኞችን ጉዳይ የሚመለከቱ ሠራተኞች ያሉባቸው የሕግ ተቋማት ስም ዝርዝር ይፋ ከተደረገ በኋላ ጥቃት እንዳይደርስባቸው በመስጋት ከቤት እንዲሠሩ ተነግሯቸዋል።

የፀረ ዘረኝነት ሰልፎቹ በአብላጫው በሰላማዊ መንገድ እንደተካሄዱ ተገልጿል። የተወሰኑ ሰዎች መታሰራቸውም ሪፖርት ተደርጓል።

ከሰላማዊ ሰልፎቹ መካከል በሊቨርፑል የተካሄደው ሰልፍ በጥገኝነት ጠያቂዎች ቢሮ አቅራቢያ ነው። ይህ መሥሪያ ቤት በስደተኞች ጠል ነውጥ ቢጎዳም የፀረ ዘረኝነት ሰልፈኞቹ ለስደተኞቹ ድጋፋቸውን ገልጸውበታል።

በለንደን በሚገኙት ዋልትማስቶው እና ኖርዝ ፊንችሊ በሺዎችን የሚቆጠሩ ሰዎች ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ፀረ ዘረኝነት አቋማቸውን አንፀባርቀዋል።

በብሪስቶል የሠራተኞች ማኅበሮች የፀረ ፋሺስት ቡድኖች እንዲሁም ጥቁሮችና እስያውያን ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።

ስደተኞች ጠል ነውጥና ዘረኛነትን የሚነቅፉ ሰልፎች

በብራይተን የጥገኝነት ጠያቂዎችን ጉዳይ በሚከታተሉ ጠበቆች ቢሮ አቅራቢያ ስምንት ሰዎች ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።

2 ሺህ የሚሆኑ ስደተኛ ጠል ነውጠኞች ሲከቧቸው ግን በአቅራቢያቸው ባለ ፖሊስ ጣቢያ ተጠልለዋል።

ስደተኞች ጠል ነውጥና ዘረኛነትን የሚነቅፉ ሰልፎች

የፎቶው ባለመብት, PA Media

በኒውካስል 1 ሺህ የሚጠጉ በአብዛኛው ሙስሊሞች የሆኑ ሰልፈኞች ለስደተኞች አገልግሎት በሚሰጠው ቤከን ሴንተር አካባቢ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

በአክሪግንተን ለሙስሊሞች ድጋፍ የሚያደርጉ የማኅበራዊ ሚዲያ ንቅናቄዎች ተደርገዋል።

በሳውዝሀምተን ከ300 እስከ 400 የሚሆኑ ሰዎች በገቨርነርስ ስኩዌር ተገኝተው “ዘረኞች ቤታችሁ ግቡ” “ዘረኛነት ከጎዳናችን ይጥፋ” የሚሉ መፈክሮች አሰምተዋል።

10 ስደተኞች ጠል ሰልፈኞች በቦታው ቢደርሱ ፖሊስ ሁለቱን ቡድኖች ለያይቶ ጥበቃ አድርጓል።

ስደተኞች ጠል ነውጥና ዘረኛነትን የሚነቅፉ ሰልፎች

የፎቶው ባለመብት, PA Media

ባለፈው ሳምንት ከተነሳው ስደተኞች ጠል ነውጥ ጋር በተያያዘ 400 ሰዎች ታስረዋል። ከ140 በላይ ሰዎች ሲከሰሱ ከመካከላቸው ፍርድ የተላለፈባቸውም ይገኙበታል።

በሳውዝፖርትና በሊቨርፑል ነውጥ ሦስት ሰዎች እስር ተፈርዶባቸዋል።

ከእነዚህ እስሮች ጋር በተያያዘ በሚመስል ሁኔታ ነገሮች እየረገቡ ይመስላል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አንጅላ ሬይነር በሮተርዳም የሚገኘው ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚጠለሉበት ሆሊደይ ኢን ኤክስፕረስ ሆቴልን ጎብኝተዋል።

ይህ ሆቴል ባለፈው እሑድ በስደተኞች ጠል ነውጠኞች ጉዳት ደርሶበታል።

ስደተኞች ጠል ነውጥና ዘረኛነትን የሚነቅፉ ሰልፎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯ ነውጠኞቹ “በሕግ ይጠየቃሉ” ሲሉ ሌሎች ሰዎችም ከነውጡ “እንዲርቁ” አሳስበዋል።

“ጎዳና ላይ ወጥቶ ፖሊሶች ላይ ጥቃት ማድረስ ወይም እንደዚህ ያሉ ሆቴሎችን መጉዳት ምክንያት አልባ ድርጊት ነው። በዚህ አገር ፖለቲካችንን የምናከናውንበት መንገድ አለ። ያንን የሚያፈርስ ነውጠኛና ሁከተኛ ነው” ብለዋል።

አድማ በታኝ ፖሊሶች በቀጣይ ቀናትም ይሰማራሉ ተብሎ ይጠበቃል።