በሕዝባዊ ተቃውሞ ከአገር የፈረጠጡት የባንግላዴሿ ጠቅላይ ሚኒስትር የመጨረሻዎቹ ሰዓታት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በባንግላዴሽ አድሏዊ በተባለው የመንግሥት የሥራ ቅጥር ኮታ ጋር ተያይዞ ተማሪዎች ያነሱት ተቃውሞ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ሃሲናን ከሥልጣን ገርስሷቸዋል።
ለሳምንታት የዘለቀው የተማሪዎች ተቃውሞ ሕዝባዊ ገጽታን ይዞ ከአድሏዊ አሠራር ባለፈ መልኩ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣን እንዲለቁ የሚጠይቅ ሆኗል።
ሕዝባዊ ተቃውሞው ተቀጣጥሎ ባንግላዴሽን ለአስራ አምስት ዓመታት የመሯትን ሼክ ሃሲናን ከሥልጣን ማውረድ ብቻ ሳይሆን ከአገርም እንዲፈረጥጡ አድርጓቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ከሥልጣን ከመባረረራቸው ከሰዓታት በፊት እሁድ ዕለት በአገሪቱ የቀጠለውን ሕዝባዊ ተቃውሞ እና ሁከት ለመግታት የፀጥታ እና የደኅንነት ውይይት ጠርተው ነበር።
ሆኖም በሰዓታት ውስጥ ሕዝባዊው ኃይል ተጠናክሮ የጠቅላይ ሚኒስትሯን የሥልጣን ዘመን እንዲያከትም አደረገው።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ በፍጥነት ከአገር ይፈረጥጣሉ ብሎ የጠበቀ ባይኖርም ሆኖም ከደኅንነት ከፍተኛ ባለሥልጣናቶቻቸው ይልቅ የቅርብ ቤተሰቦቻቸውን ምክር በመስማት ከአገር እንደወጡም ልጃቸው ለቢቢሲ ተናግሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃሲና በፍጥነት ውሳኔ ላይ ባይደርሱ ምን ያጋጥም እንደነበር መገመት ይከብዳል።
ሃሲና በሸሹ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ነበር ባንግላዴሻውያን መንግሥታዊውን የጠቅላይ ሚኒስትሯን መኖሪያ ጥሰው የገቡት።
እሁድ ረፋዱ ላይ የተጠራው የብሔራዊ ደኅንነት ኮሚቴ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ከአገሪቱ ከፍተኛ ሦስት ወታደራዊ አዛዦች፣ ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣናት እና ከፖሊስ ኃላፊዎች ጋር የመከሩበት ነበር።
ለሳምንታት የዘለቀው ሕዝባዊ ተቃውሞ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠናክሮ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ከሥልጣን እንዲለቁ ጥያቄው በበረታበትም ወቅት ነው ይህ ስብሰባ የተጠራው።
ባንግላዴሽ ነጻነቷን ለማረጋገጥ ከአውሮፓውያኑ 1971 ካደረገችው ጦርነት በኋላ ያጋጠማት ነውበተባለው በዚህ ተቃውሞ እና ሁከት በመቶዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ስብሰባውን በጠሩበት እሁድ ዕለት ብቻ ቢያንስ 90 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተተዋል።
በርካቶች ከፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰባቸው ጥይት የተገደሉ ተቃዋሚዎች ቢሆኑም፤ ነገር ግን በተቃዋሚዎች የተገደሉ ፖሊሶች ቁጥር ጨምሮ ነበር።
ቢቢሲ ከባለሥልጣናቱ እንደተረዳው ተቃውሞው ተጠናክሮ በቀጠለበት ወቅት ከአገር እንዲወጡ ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት እሳቸው ግን በኃይል እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ድረስ በሥልጣን ለመቆየት መፈለጋቸውን ነው።
ወታደራዊ መሪዎች በዚህ ሃሳብ አልተስማሙም።
እሁድ ዕለት ተቃዋሚዎች እና ነዋሪዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከሚገኙ ወታደሮች እና የጦር መኮንኖች ጋር አንድ ላይ ታዩ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ሁኔታዎችን ከገመገሙ በኋላ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ መሆናቸውን ተረዱ።
በስብሰባው ላይ የተገኙት የጦር ጄኔራሎች ወታደሮች በሰላማዊ ሰዎች ላይ መተኮስ እንደማይችሉ፤ ነገር ግን ለፖሊስ የደኅንነት ጥበቃ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሯ መናገራቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከፍተኛ የፖሊስ አዛዦችም ጥይት አልቆብናል ሲሉ ቅሬታቸውን በዚሁ ስብሰባ ላይ ያነሱ ሲሆንም ይህም በኋላ ላይ የታየ ክስተት ሆኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃሲና የጦር ጄኔራሎቹን እና የፖሊስ አዛዦቹን ሃሳብ ማዳመጥ አልፈለጉም። እነዚህ ከፍተኛ የወታደራዊ አዛዦችም ጠቅላይ ሚኒስትሯን ተቃውመው ሊወጡ አልፈለጉም።
ስብሰባውንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ተቃዋሚዎቹን “አሸባሪዎች” ሲሉ እንደጠሯቸው በፕሬስ ሴክሬታሪያቸው በኩል በወጣው መልዕክታቸው ተገልጿል።
ሕዝቡም እነዚህን “አቀጣጣዮች” ሊታገላቸው ይገባል ማለታቸው እንዲሁ ተነገረ።
ብዙም ሳይቆይ የእርስ በርስ ጦርነት ሊነሳበት የሚችልበትን አጋጣሚ ያዩት የፀጥታ ኃይሎች ፍራቻቸው ከፍ ያለ ነበር።
ለሳምንታት በዘለቀው ተቃውሞ የተቀጠፉ ሰዎች እንዲሁም በእሁዱ ተቃውሞ የተገደሉ ሰዎች ምሥል በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ በስፋት ተጋርቷል።
በፖሊስ እና በገዥው ፓርቲ አዋሚ የወጣቶች ክንፍ አባላት ተተኩሶባቸው የተገደሉ ወጣቶች ምሥሎች ከፍተኛ ቁጣን አቀጣጥሏል።
ሕዝባዊ ተቃውሞው ወደ አስከፊ ሁከት በተቀየረበት በዚህ ዕለትም የተማሪ አመራሮች ሕዝባዊ ሰልፍ በመዲናዋ ዳካ በማግስቱ እንዲደረግ ጥሪያቸውን አቀረቡ።
የተማሪዎቹ ጥያቄ በሕዝቡ ተቀባይነት እንዳገኘ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችም በማግስቱ ወደ መዲናዋ ሊመጡ እንደሆነ መረጃዎች ነበሩ።
የፀጥታ ኃይሎች ይህንን ተቃውሞ ለማስቆም ቢሞክሩ የከፋ ደም መፋሰስ እንደሚያጋጥም ተረዱ።
የአገሪቱ ጦር አዛዥ ዋከር ኡዝ ዛማን ጠቅላይ ሚኒስትሯን በድጋሚ ለማነጋገር ወሰኑ።
ሦስት የአገሪቱ ጦር ከፍተኛ አዛዦች እሁድ አመሻሽ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሯን አግኝተው መሬት ላይ ያለው እውነታ ከቁጥጥር ውጪ እንደሆነ እና ሰኞ ጥዋትም ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ እንደሚኖርም አስረዷቸው።
በዚህ ውይይታቸውም የእሳቸውን መኖሪያ ቤት ደኅንነት ለማረጋገጥ ዋስትና መስጠት አንችልም አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ የከፍተኛ የጦር አዛዦቹን ምክር ለመቀበል አሻፈረኝ አሉ።
ሆኖም እሁድ አመሻሽ ላይ ሁኔታዎች መቀየር ጀመሩ። በርካታ በፀጥታ ኃይሎች ወይም በፖሊስ መጠበቅ የነበረባቸው ስፍራዎች ባዶ ሆነው ታዩ።
ሰኞ ጥዋት በርካታ ሕዝብ ወደ መዲናዋ ዳካ አመሩ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዚህም ወቅት የአገሪቱ ጦር አዛዥ ጄኔራል ዛማን በጠቅላይ ሚኒስትሯ መኖሪያ ቤት ተገኝተው የሁኔታውን አስከፊነት እየገለጹላቸው ነበር።
ፖሊሶች ከዋና ከተማዋ ዳካ በአብዛኛው እንዲወጡ የተደረጉ ሲሆን፣ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሯ መኖሪያ ቤት እያቀና የነበረውን ሕዝብም ለረጅም ጊዜ መከላከል እንደማይችሉ እኚሁ አዛዥ ተናገሩ። ከተቻለ ለአንድ ሰዓት ብቻ ነው መከላከል የምንችለው ብለው እውነታውን አስረዱ።
በዚህ ወቅት ነበር እነዚህ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች የጠቅላይ ሚኒስትሯን ቤተሰቦች እንዲማጸኗቸው የጠሩት። የጠቅላይ ሚኒስትሯን ታናሽ እህት ሪሃና ሲዲቅን አግኝተው “እህትሽን ሥልጣን እንድትለቅ አሳምኚያት” አሏት።
እህቷም ሁኔታውን አስረድታ ከሥልጣን እንዲለቁ ብትጠይቃቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ሃሲና አሻፈረኝ ብለው ከሥልጣን አልለቅም አሉ። በውጭ አገር የሚኖሩት የጠቅላይ ሚኒስትሯ ሁለት ልጆችም በስልክ እናታቸውን ሥልጣን እንዲለቁ ተማጸኗቸው።
በእነዚህ የቤተሰብ ተማጽኖ እና ድርድር ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትሯ ጋር በጋብቻ የተዛመዱት የጦሩ አዛዥ በስፍራው እንደነበሩ ተዘግቧል።
“እናቴ ከአገር መውጣት በጭራሽ አልፈለገችም። ማሳመንም ነበረብን” ሲልም ልጃቸው ሳጂብ ዋዚድ ለቢቢሲ የተናገረ ሲሆን፣ እናቱ ከቅዳሜ አመሻሽ ጀምሮ ከሥልጣን ለመልቀቅ እያሰቡ ነበር ብሏል።
“ቤተሰቡ በሙሉ ለመንናት። ተማጸንናት። ከፍተኛ ሕዝብ ነው የወጣው። ለጥቃት የመጡ ናቸው፤ ይገሉሻል። ደኅንነቱ ወደተጠበቀ ስፍራ እንውሰድሽ አልናት። የነበራት ጊዜ ሕዝቡ መኖሪያ ቤቷ እስከሚደርስበት ድረስ የነበረው ነው። ከዚያም ያለ ምንም ዝግጅት ወጡ” ብሏል።
አክሎም “ደልሂ ከገባች በኋላ ደወልኩላት። በጥሩ መንፈስ ላይ ብትሆንም፣ በጣም አዝናለች። የባንግላዴሽ ሕዝብ ያደረገው ነገር ልቧን ሰብሮታል” ሲልም ለቢቢሲ ገልጿል።
ተቃውሞው በበረታበት ሰኞ ማለዳ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሯ በደልሂ ከሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እንደተወያዩ ምንጮች ተናግረዋል።
በሥልጣን ዘመናቸው ጠንካራ አጋሮች የነበሩት የሕንድ ባለሥልጣናትም ከአገር እንዲወጡ መከሯቸው።
ከአንድ ቀን በፊትም አሜሪካ የጠቅላይ ሚኒስትሯ የሥልጣን ጊዜ እንዳከተመ ለሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ነግራቸው ነበር።
በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሳይወዱ በግድ ከሥልጣን ለቅቄያለሁ ሲሉ ለመፈረም የተስማሙ ሲሆን፣ ቀሪው ጥያቄም በሰላም እንዴት ከአገር መውጣት ይችላሉ የሚል ብቻ ነበር።
ስማቸውን እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣን ጠቅላይ ሚኒስትሯ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን የተስማሙበትን ደብዳቤ ሲፈርሙ እና ከመኖሪያ ቤታቸው በሚወስዳቸው ወታደራዊ ሄሊኮፕተር መሳፈራቸውን የሚያውቁት ጥቂት አመራሮች ነበሩ።
ይህንንም መረጃ ልዩ የደኅንነት ኃይል፣ የፕሬዚዳንታዊ ጥበቃ ክፍለ ጦር እና አንዳንድ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ብቻ የሚያውቁ ሲሆን፣ ሁሉም ነገር ምሥጢራዊ በሆነ መንገድ ነበር የተከናወነው።
ሰኞ በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከረፋዱ 4፡30 ላይም ባለሥልጣናቱ የጠቅላይ ሚኒስትሯ ከአገር የመውጣት ዜና ሾልኮ በማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይሰማ በሚልም ኢንተርኔቱን ዘጉት።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ከአገር ከወጡ በኋላ ነው እንደገና የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲመለስ የተደረገው።
እንደ ከፍተኛ የሠራዊቱ ምንጮች ጠቅላይ ሚኒስትሯን ወደ አየር ማረፊያ ለማድረስ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል። ሆኖም በመኪና ቢሄዱ ጥቃት ሊፈጸምባቸው ይችላል በሚልም በሄሊኮፕተር እንዲወሰዱ ተወሰነ።
እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃሲና በሄሊኮፕተር ተሳፍረው መሄድ አልፈለጉም የሚለው ልጃቸው “አክስቴ እንድትሳፈር ነው የፈለገችው። እሷ በጭራሽ በሄሊኮፕተሯ ላይ መሳፈር አልፈለገችም። ደውዬ እናቴን እና አክስቴን ለምኜ እንዲሳፈሩ ሆነ” ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትሯ በባንግላዴሽ አየር ኃይል ሲ-130 ሄርኩለስ አውሮፕላን ተሳፈሩ።
ልጃቸው ሳጂብ እንደሚለው መጀመሪያ ወደ ሕንዷ አጋታላ ከተማ ከተወሰዱ በኋላ በመጨረሻም ደልሂ መድረሳቸውን ገልጿል። ሕንድ ለጠቅላይ ሚኒስትሯ መጠለያ እንዲሆኑ ቀደም ብሎ ተጠይቃ መስማማቷን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።
ከቀኑ ሰባት ተኩል ገደማ ጠቅላይ ሚኒስትሯ፣ እህታቸው፣ የገዢው ፓርቲ አዋሚ ሊግ ከፍተኛ የፓርላማ አባል ሳልማን ፋዝሉር ራህማን ወደ ደልሂ በሚወስዳቸው አውሮፕላን መሳፈራቸውን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋራው ቪዲዮ ከጠቅላይ ሚኒስትሯ ጋር አምስት ያህል ሻንጣዎችን አሳይተዋል።
እሳቸው ወደ ደልሂ እየበረሩ በነበሩበት ወቅት መኖሪያ ቤታቸውን ጥሰው የገቡ ነዋሪዎች ሃሲና ትተውት የሄዱትን ንብረት ጠራርገው ይዘው ሄደዋል።
የእሳቸውን ከሥልጣን መገርሰስ እና ከአገር መውጣትን ተከትሎ የባንግላዴሽ ጎዳናዎች በደስታ እና በጭፈራዎች ተሞሉ። በአንድ ወቅት የዲሞክራሲ ችቦ ተብለው ይታዩ የነበሩት የጠቅላይ ሚኒስትር ሃሲና የ15 ዓመታት የሥልጣን ጉዞም በፍርጠጣ ተጠናቋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters












