የባንግላዴሽ ጠቅላይ ሚኒስትር ሕዝባዊ ተቃውሞ መባባሱን ተከትሎ አገር ጥለው ሸሹ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በባንግላዴሽ የተቀሰቀሰውን ከፍተኛ ሕዝባዊ አመጽ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ሃሲና አገር ጥለው ተሰደዱ።
ባንግላዴሽን ከእአአ 2009 ጀምሮ ሲመሩ የቆዩት ሃሲና አገር ጥለው የሸሹት ቤተ-መንግሥታቸው በተቃዋሚዎች ከተወረረ በኋላ ነው።
ባለፉት ቀናት ፀረ መንግሥት የሆኑ የተቃውሞ ሰልፎች በመላው ባንግላዴሽ ሲካሄዱ ነበር።
የፀረ መንግሥት ተቃውሞው የተቀሰቀሰው ተማሪዎቸ በችሎታ እንጂ በኮታ መሠረት የሚሰጠው የሥራ ዕድል እንዲቀር ድምጻቸው ለማሰማት አደባባይ መውጣት ከጀመሩ በኋላ ነው።
ይሁን እንጂ ተቃውሞው መልኩን እየቀየረ ሄዶ፤ ተቃዋሚዎች ከፖሊስ ጋር እየተጋጩ ባለፉት ቀናት ከ90 ያላነሱ ሰዎች ተገድዋል።
ይህ የተቃዋሚዎች ግድያ ፀረ መንግሥት ተቃውሞን አጠናክሯል።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ ምሥሎች ተቃዋሚዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሯ መኖሪያ ቤት እንደ ሶፋ፣ አልጋ እና ወንበር ያሉ የቤት ዕቃዎች ተሸክመው ሲወጡ አሳይተዋል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
የሼክ ሃሲናን ከአገር መውጣት ተከትሎ የአገሪቱ ጦር አዛዥ ዋኬር-ኡዝ-ዛማን ጊዜያዊ መንግሥት እንደሚያቋቁሙ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሥልጣን ለቀው ከመላ ቤተሰባቸው ጋር ሄሊኮፕተር ተሳፍረው ወደ ሕንድ ማቅናታቸውን የቢቢሲ ምንጮች ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒሰትር ሃሲና ሥልጣን መልቀቃቸው ከተሰማ በኋላ ተቃዋሚዎች ደስታቸውን በአደባባይ እየገለጹ ይገኛሉ።
ኤኤፍፒ በመዲናዋ ዳካ ጎዳናዎች ላይ ደስተኛ ተቃዋሚዎች የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ እና የቆሙ ታንኮች ላይ ወጥተው ደስታቸውን እየገለጹ ነው ብሏል።












