መንግሥት ግማሽ ትሪሊየን ብር ተጨማሪ በጀት ለተወካዮች ምክር ቤት ሊያቀርብ ነው

ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ

የፎቶው ባለመብት, fbc

የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ

የፌደራል መንግሥት 551 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚያቀርብ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ ተናገሩ።ከዚህ ውስጥ 240 ቢሊዮን ብሩ “ለማኅበራዊ ድጋፍ” የሚውል መሆኑን ዶ/ር ኢዮብ ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታ ይህን የገለጹት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን በተመለከተ ለመንግሥት ቅርበት ካለው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው።

እሁድ ሐምሌ 28/2016 ዓ.ም. የተላለፈው 52 ደቂቃ ገደማ የፈጀ ቃለ ምልልስ ከአንድ ሳምንት በፊት ተግባራዊ መሆን የጀመረው የማክሮ ኢኮኖሚ ፕሮግራም ማሻሻያን የተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ የተሰጠበት ነው።

ሚኒስቴር ዴኤታው በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው ላይ “ተጨማሪ በጀት ይዘን ወደ ፓርላማ እንመጣለን” ብለዋል።

መንግሥት ተጨማሪ በጀት ለፓርላማ እንደሚቀርብ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሐምሌ 24/2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረው ነበር።

አቶ አህመድ መንግሥት ተጨማሪ በጀት እንደሚያውጅ የተናገሩት ምክር ቤቱ ዓለም አቀፉ የመንግሥት ልማት ማኅበር ለኢትዮጵያ የሰጠውን የ1.5 ቢሊዮን ዶላር የብድር እና ድጋፍ ስምምነት ባጸደቀበት ወቅት ነው።

ሚኒስትሩ በተጨማሪ በጀት መልክ የሚጸድቀው የገንዘብ ምንጭ ከመጥቀስ በስተቀር ምን ያህል ብር በተጨማሪ መልክ እንደሚጸድቅ ይፋ አላደረጉም ነበር። ነገር ግን “የዘንድሮ በጀታችን በጣም በጣም ከፍተኛ ነው የሚሆነው” ብለዋል።

“1.5 ቢሊዮን ዶላር የዛሬ አንድ ወር በጀታችንን ስናውጅ ያልነበረ ገቢ ስለሆነ፤ እንደገና ወደ ምክር ቤት መጥተን እናሳውጃለን ማለት ነው” ያሉት አቶ አህመድ፤“ከአይኤምኤፍ ከተገኘው 3.5 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ በመጀመሪያ ዙር የሚፈስሰው 30 ፐርሰንቱ፤ ለገንዘብ ሚኒስቴር ለበጀት ጥቅም የሚውል ነው” ሲሉ የተጨማሪውን በጀት ምንጭ አብራርተው ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አቶ አህመድ በዚሁ ወቅት፤ “ገንዘብ ሚኒስቴር ይህንን ገንዘብ ሥራ ላይ የሚያውለው በተጨማሪ በጀት መልክ ይኼው ምክር ቤት ሲያውጀው እና ሲያውጀው ብቻ ነው” ሲሉ በአጽንኦት ተናግረው ነበር።

ከሚኒስትሩ የፓርላማ ማብሪሪያ ጥቂት ቀናት በኋላ ዶ/ር ኢዮብ መንግሥት በተጨማሪ በጀት መልክ የሚቀርበውን የገንዘብ መጠን ይፋ አድርገዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአንድ ወር በፊት አንድ ትሪሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት ማጸዕደቁን ያስታወሱት ዶ/ር እዮብ፤ “አሁን ግን 551 ቢሊዮን አካባቢ የሚሆን ተጨማሪ በጀት ለምክር ቤቱ ይቀርባል” ብለዋል።

ይህ ተጨማሪ በጀት የፌደራል መንግሥቱን ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ያጸደቀውን የ2017 ዓ.ም. በጀት 1.5 ትሪሊዮን ብር ገደማ ያደርሰዋል። ጭማሪው የሚጸድቅ ከሆነ የፌደራል መንግሥቱን ዓመታዊ በጀት ለመጀመሪያ ከአንድ ትሪሊዮን እንዲሻገር ያደርገዋል።

ዶ/ር ኢዮብ በተጨማሪ በጀት መልክ ለፓርላማ ከሚቀርበው ግማሽ ትሪሊዮን ብር ውስጥ 240 ቢሊዮን የሚሆነው “ለማኅበራዊ ድጋፍ፣ ለሴፍቲኔት፣ ለሠራተኛ ደመወዝ፣ ለመድኃኒት ድጎማ፣ ለነዳጅ ድጎማ የሚውል ነው” ብለዋል።

መንግሥት ከወጪው በተጨማሪ የገቢ በጀቱንም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ እንደሚያሳውጅ ዶ/ር ኢዮብ ተናግረዋል። እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ 563 ቢሊዮን የነበረው የፌደራል መንግሥት ገቢ ተከልሶ 851 ቢሊዮን ይሆናል።

ዶ/ር ኢዮብ መንግሥት “ይሄ [የሚሆነው] ግን አንድም የታክስ መጠን ሳንጨምር ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም “ይሄንን ስናደርግ ግን ተጨማሪ ታክስ በመጣል ወይም የታክስ ምጣኔ በመጨመር አይደለም መጨመር ያሰብነው። ኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን distortion [ዝንፈት] በማስተካከል [ነው]” ብለዋል።

“ታክስ ሳይከፍል ይከብር ነበረው ባለሃብት አሁን ቶሎ ወደ መስመር መግባት አለበት” ያሉት ዶ/ር ኢዮብ፤ “ይሄንን የሚፈቅድ ነገር አይኖርም። ጠንካራ የሆነ [enforcement] ሥራ ይሠራል” ሲሉ በአጽኦት ተናግረዋል።