የውጭ ምንዛሪ ተመንን ለገበያ የተወችው ኢትዮጵያ የናይጄሪያ እና የግብፅ ዕጣ ይገጥማት ይሆን?

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና ከዓለም ባንክ 10.7 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለማግኘት በተደረገው ስምምነት በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመንን ተግባራዊ በማድረግ ብሯን አዳክማለች።
ለአስርት ዓመታት መንግሥት በሚወስነው የውጭ ምንዛሪ የግብይት ሥርዓትን (ፊክስድ ፎሬይን ኤክስቸንጅ ማርኬት) ይመራ የነበረውን አሠራር በመቀየር በገበያ ፍላጎት የሚመራ እንዲሆን ውሳኔ ተላልፏል።
ውሳኔው በተላለፈ በ24 ሰዓታት ውስጥ ብር ከዶላር አንጻር 30 በመቶ፣ እንዲሁም በአንድ ሳምንት ውስጥ ከ57 በመቶ በላይ እንዲዳከም ተደርጓል።
መንግሥት ብሩን በማዳከም ከትይዩው ገበያ ጋር ለማመጣጠን እየሠራ ባለበት በአሁኑ ወቅት ከመሠረታዊ ሸቀጦች እስከ ግንባታ ግብዓቶች ድረስ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች፣ ቸርቻሪዎች፣ የጅምላ ነጋዴዎች እንዲሁም በግንባታ ሥራ ላይ የተሠማሩ ባለሙያዎች የሸቀጦች እና የግብዓቶች ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ መታየቱን ገልጸዋል።
በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ ባለው የዋጋ ግሽበት እየተፈተነ ያለው ነዋሪ የኑሮ ውድነት ጫንቃውን በበለጠ እንዳያጎብጠው ተፈርቷል። ብር በበለጠ ይዳከማል በሚል ስጋት በርካቶች ዶላራቸውን እያስቀመጡ ይገኛሉ፤ ከሰሞኑም ዶላር በአዲስ አበባ ገበያዎች እንደጠፋ ተዘግቧል።
ይህንንም ተከትሎ የሚፈጠረ ጫናን ለመከላከል ዝቅተኛ ደመወዝ ለሚከፈላቸው የመንግሥት ሠራተኞች የ300 በመቶ ጭማሪ እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል።
በቅርቡ በአፍሪካ የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ ላይ እንዲመሠረት ያደረገችው ኢትዮጵያ ብቻ አይደለችም፤ ግብፅ እና ናይጄሪያም ቀደም ብለው ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል።
በሁለቱ አገራት የታየው የምጣኔ ሀብት ሁኔታ ተመሳሳይ እርምጃን የተከተለችው የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችልም የሚያሳይ ነው።

የፎቶው ባለመብት, AMENSISA IFA/BBC
ውጭ ምንዛሪ ተመንን በገበያ እንዲወሰን መተው ምን ተጽእኖ ይኖረው ይሆን?
የውጭ ምንዛሪ ተመንን በገበያ ላይ እንዲመሠረት መተው የአገራቱን የመገበያያ ገንዘብ በማዳከም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የበለጠ ውድ ያደርጋቸዋል። በዚህም የተነሳ መሠረታዊ የሚባሉ ሸቀጦች እንደ ምግብ፣ ነዳጅ እና መድኃኒቶች ዋጋን በማናር በነዋሪዎች እንዲሁም በንግድ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል።
የንግድ ተቋማት ከውጭ የሚያስገቧቸው ግብዓቶች (ጥሬ ዕቃዎች) ዋጋቸው በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚንር ይህም አማካዩ ኢትዮጵያዊ በኑሮ ውድነት እንዲፈተን ሊያደርግ ይችላል።
የንግድ ተቋማት ከውጭ የሚያስገቧቸው ምርቶች እና ጥሬ ዕቃዎች ዋጋቸው በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚጨምርባቸው ይህንን ለማካካስ በሸማቾች ላይ ዋጋ መጨመራቸው አይቀሬ እንደሆነ ተንታኞች ይናገራሉ።
ሆኖም አገሪቷ ወደ ውጭ የምትልከው ምርት ዋጋ ከረከሰ ከፍተኛ ገቢ ይገኛል እንዲሁም ለተለያዩ የውጭ አገራት ባለሃብቶች የበለጠ ማራኪ ሊያደርጋት ይችላል።
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ብሯን በዋነኝነት ያዳከመችበት ምክንያት ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች ዋጋ ከረከሰ በርካታ ገቢ ይገኛል፤ እንዲሁም የወጪ ንግዱም ይበረታታል በሚል ቢሆንም ከምርታማነት እንዲሁም ከተወዳዳሪነት ጋር ተያይዞ በርካታ ጥያቄዎች መነሳታቸው አልቀረም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የግብፅ እና የናይጄሪያ ልምድ ምን ይመስላል?
ግብፅ ባለፈው መጋቢት ወር የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ያስቀመጠላትን ቅድመ ሁኔታ በመከተል በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመንን ተግባራዊ አድርጋለች።
በምላሹም አይኤምኤፍ ለአገሪቱ የሚሰጠውን ብድር ከ3 ቢሊዮን ወደ 8 ቢሊዮን ዶላር ከፍ አድርጎታል።
ነገር ግን ውሳኔው በተላለፈ በሰዓታት ውስጥ የግብፅ ፓውንድ ከዶላር አንጻር ከ60 በመቶ በላይ ተዳከመ። ይህም ከአውሮፓውያኑ 2016 ጀምሮ እየተንገታገተ የነበረውን ምጣኔ ሀብት ለማስተካከል እንዲሁም የዋጋ ግሽበቷን ለመቀነስ እየሞከረች ለነበረችው ግብፅም ከድጡ ወደ ማጡ ሆኖ የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት እንዲያሻቅብ አደረገው።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይም የናይጄሪያ ባለሥልጣናት በመንግሥት ሲወሰን የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ተመን በመቀየር ገበያ መር እንዲሆን ማድረጋቸውን ተከትሎ ናይራ [የናይጄሪያ ገንዘብ] ከዶላር አንጻር ያለው ዋጋ በእጅጉ አሽቆልቁሏል።
“የናይጄሪያ የመገበያያ ገንዘብ ካለው የመግዛት አቅም በላይ ዋጋው ከ50 በመቶ በላይ ነበር” ሲሉ በለንደን ተቀማጭነቱን ያደረገው የማክሮ ስትራቴጂ ኩባንያው ኤፍአይኤም ፓርትነርስ ቻርሊ ሮበርትሰን ይናገራሉ።
ሮበርትሰን እንደሚሉት “ናይጄሪያ ውስን ዶላር ነበራት። አገሪቷ ከነበረባት የውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ ውስን ነዋሪዎቿ ነበሩ ይፋዊ በሆነው የመገበያያ ተመን ዶላር ማግኘት ይችሉ የነበሩት።”
ናይጀሪያ ዝቅተኛ በሆነ የምጣኔ ሀብት ዕድገት፣ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመጣ ብድር እንዲሁም የነዳጅ ምርቷ እያሽቆለቆለ መምጣቱን ተከትሎ ዶላር ማግኘት የምትችልበት የወጪ ንግዷ አነስተኛ ሆኖ ነበር።

ነዋሪዎች ላይ ምን ጫና ያሳርፋል?
ለናይጄሪያውያን የዕለት ምግባቸው የሆነው ሩዝ ዋጋ ባለፈው ዓመት በእጥፍ ጨምሯል።
እንዲሁም ነዳጅ አምራች በሆነችው አገር የአንድ ሊትር ነዳጅ ዋጋ በሦስት እጥፍ ጨመረ።
በአገሪቱ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር የነበረው 22.42 በመቶ የዋጋ ግሽበት በዘንድሮው ግንቦት ወር ወደ 33.95 በመቶ አሻቀበ። የምግብ የዋጋ ግሽበት ተባብሶ ሰኔ ወር ላይ 40.8 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ በርካታ ናይጄሪያውያን መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦችን ለመግዛት ፈታኝ ሆኖባቸዋል ተብሏል።
የውጭ ምንዛሪ ዕዳ የነበረባቸው በርካታ የናይጄሪያ ኩባንያዎች በዶላር ዋጋ ተመን ለውጡ ምክንያት ከፍተኛ ኪሳራ እንደረሰባቸው ተገልጿል።
በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ግብፅ ደግሞ ቀድሞውንም በድህነት ውስጥ ላሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ግብፃውያን የውጭ ምንዛሪ ተመኑ በገበያ መወሰኑ በበለጠ መከራ ሆኖባቸዋል። መንግሥት ዳቦ ላይ የቆየ ድጎማ ቢኖረውም ዋጋው በዘንድሮው ዓመት ግንቦት ወር ዋጋው 300 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ምንም እንኳን ነዋሪዎች ላይ የፈጠረው ጫና ከፍተኛ ድንጋጤ ቢፈጥርም አይኤምኤፍ ግብፅ እነዚህን ማሻሻያዎች ተግባራዊ ካደረገች በኋላ “የውጭ ምንዛሪ እጥረቷ ተቀርፏል። እንዲሁም የኢንቨስተሮች (ባለሃብቶች) መተማመንን በአዎንታዊ መልኩ አሳድጓል” ብሏል።
በቀጣይ በኢትዮጵያስ ምን ይፈጠራል?
የተዳከመ ብር የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ በዓለም ገበያ መድረክ ዋጋውን የረከሰ በማድረግ ተወዳዳሪነቱን ሊያሳድግ ይችላል።
መንግሥት ይህ ውሳኔው በዋነኝነት በግብርና እና በማዕድን ዘርፍ ላይ ያሉ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጾ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ገቢም ያሳድጋል ብሏል።
በተለይም አገሪቷ የምታመርታቸው የግብርና ምርቶች እንደ ቡና፣ ሰሊጥ፣ የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶች እንዲሁም የእንስሳት እርባታ ለውጭ ገዥዎች የበለጠ ማራኪ ይሆናሉ።
ሆኖም ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ እውነታ ይሠራል ወይ? የሚለው ጥያቄ የሚነሳ ሲሆን፣ አገሪቱ በዋነኝነት ወደ ውጭ የምትልካቸው የግብርና ምርቶች በዓለም ገበያ ያላቸው ተወዳዳሪነት ጥያቄ ሲነሳበት ቆይቷል።
ስለዚህ የምትሸጠው ምርት መታየት አለበት የሚሉ አልታጡም።
አገሪቷ ለዓመታት በንግድ ሚዛን ጉድለት እየተንገታገች ሲሆን፣ ብር ተገቢውን ዋጋ እንዲይዝ (ዲቫሉዌት) በማድረግ የተከተለችው መንገድ ታስቦ እንደነበረው የወጪ እና የገቢ ንግድን ማመጣጠን አልቻለም።
አገሪቷ በወጪ ንግዷ እና በገቢ ንግዷ መካከል ያለው ከፍተኛ ልዩነትን ማመጣን አለመቻሏ ከፍተኛ ማነቆ ፈጥሮባታል።
ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶቿ በላይ በከፍተኛ ሁኔታ ምርቶችን ከውጭ አገር የምታስገባው ኢትዮጵያ ብሯን ማዳከሟ ካለው በበለጠ የዋጋ ግሽበትን በማስከተል ቀውስ ሊፈጥር ይችላል የሚሉ አልታጡም።
“የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ አገሪቷ በቀጣዮቹ ወራት የምትተገብረው የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ አንዱ አካል ነው” ሲል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በመግለጫው አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር እንዲሁም ምጣኔ ሀብቱን ለማረጋጋት ተጨማሪ የገንዘብ ፖሊሲዎችን ማውጣት እንደሚኖርበት ባለሙያዎች ይመክራሉ።
አገሪቷ ለሁለት ዓመታት በዘለቀው የትግራይ የደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ከውጭ የሚመጣ ኢንቨስትመንት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ተፈጥሯል።
ስለዚህም ኢትዮጵያ ያለችበትን የፖለቲካ አለመረጋጋት ለመፍታት የምትሄድበት መንገድ የገንዘብ ማሻሻያዎቿ የከፋ ውጤት እንዳይኖራቸው ለማድረግ ወሳኝ ይሆናል።












