በአዲሱ የብሔራዊ ባንክ መመሪያ መሠረት የውጭ ምንዛሪ ግብይት እንዴት ይከናወናል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት አዲስ የማክሮ ኢኮኖሚክ ማሻሻያ ፖሊሲን እሑድ ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል። ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዋና የፖሊሲ እርምጃዎች መካከል የገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት አንደኛው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ይፋ ባደረጉ በሰዓታት ውስጥ የብሔራዊ ባንክ ከሰኞ ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ አስተዳዳር ሥርዓት ላይ ማሻሻያ አድርጓል።
በዚህ ማሻሻያ መሠረት የውጭ ምንዛሪ ግብይት እስከዛሬ ድረስ ከነበረበት በመንግሥት የሚወሰን የተመን ሥርዓት፤ በባንኮች እና በደንበኞቻቸው መካከል በሚደረግ ድርድር ወደሚበየንበት የገበያ ሥርዓት ተሸጋግሯል።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ በሰጡት መግለጫ፤ የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ሚና “ገበያውን በማረጋጋት ላይ ያተኮረ ይሆናል” ብለዋል።
የአዲሱ የብሔራዊ ባንክ መመሪያ የውጭ ምንዛሪ በመግዛት እና በመሸጥ ላይ የሚሳተፉ አካላትን እና አሠራራቸውን በዝርዝር ያስቀመጠ ነው።
ባንኮች በዚህ አሰራር ውስጥ ዋና ተዋናይ መሆን እንደሚገባቸው መመሪያው ላይ ሰፍሯል።
ከዚህ በተጨማሪም በባንኮች ከተቋቋሙ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በተጨማሪ ባንክ ያልሆኑ የግል የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች እንደሚቋቋሙ የብሔራዊ ባንክ ገዢው አስታውቀዋል።
የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች እንዴት ነው የሚቋቋሙት?
በአዲሱ መመሪያ መሠረት ብሔራዊ ባንክ፤ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በሁለት ዓይነት መንገዶች ሊቋቋሙ ይችላሉ። በቀዳሚነት የሚነሳው የውጭ ምንዛሪ ቢሮ በሥራ ላይ ያሉ ባንኮች የሚያቋቋሙት ነው።
ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ቢሮን በሥራ ቦታቸው ላይ ለብቻው ማቋቋም የሚችሉ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም በሌላ ቦታ ላይ ይህንን ዓይነቱን ቢሮ ሊከፍቱ ይችላሉ።
ባንኮች ይህንን ቢሮ የሚከፍቱት በቅጥር ግቢያቸው ወይም በቅርንጫፍ መሥሪያ ቤታቸው ውስጥ ከሆነ፤ የውጭ ምንዛሪ ቢሮው የባንኩን ስያሜ መያዝ አለበት። ባንኩ ከቅጥር ግቢው ውጪ የሚከፍተው የውጭ ምንዛሪ ቢሮ ግን የራሱ ስያሜ ሊኖረው እንደሚገባ በመመሪያው ላይ ሰፍሯል።
ሌላኛው ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የሚያገኘው የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት ሰጪ፤ ከባንክ ጋር ግንኙነት የሌለው የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮ ነው።
የውጭ አገር ጥሬ ገንዘብ ኖቶችን በመግዛት እና መሸጥ ላይ ብቻ እንዲሰማሩ የተፈቀደላቸው እነዚህ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች፤ በሌላ የባንክ ሥራ ላይ መሠማራት እንደማይችሉ መመሪያው ያትታል።
ለግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮ ፈቃድ ለመስጠት መስፈርቶች እና ሁኔታዎች መመሪያው ላይ ተዘርዝረዋል።
በመመሪያው መሠረት ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ፣ በአገሪቱ ነዋሪ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ እና ትውልደ ኢትዮጵያዊ የውጭ አገር ዜጋ የውጭ ምንዛሪ ቢሮ ለመክፈት ፈቃድ ማውጣት ይችላሉ።
ይሁንና ብሔራዊ ባንክ የግል የውጭ ምንዛሬ ቢሮ ማቋቋሚያ ፈቃድ በሚጠይቁ አካላት ላይ የካፒታል ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል።
የግል የውጭ ምንዛሬ ቢሮ ለመክፈት ፈቃድ የሚጠይቅ አካል 15 ሚሊዮን ብር ካፒታል ሊኖረው ይገባል። ከዚህ በተጨማሪም 30 ሚሊዮን ብር የዋስትና ተቀማጭ ገንዘብ በዝግ አካውንት ውስጥ በማንኛውም ባንክ ማስቀመጥ አለበት።
የግል ውጭ ምንዛሪ ቢሮው ለሁለት ዓመታት ያህል በሥራ ላይ ከቆየ በኋላ የዋስትና ተቀማጭ ገንዘቡ እንደሚለቀቅለት መመሪያው ላይ ሰፍሯል።
የውጭ ምንዛሬ ግብይት ተመን እንዴት ይወሰናል?
በብሔራዊ ባንክ መመሪያ መሠረት ባንኮች እና የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ከደንበኞቻቸው ጋር እና እርስ በራሳቸው ገበያውን መሠረት ባደረገ ድርድር የውጭ ምንዛሪዎችን መግዛት እና መሸጥ ተፈቅዶላቸዋል።
ይሁንና ባንኮች በየዕለቱ ለሚያደርጉት የውጭ ምንዛሪ ግብይት የተጠቀሙትን የውጭ ምንዛሬ ዋጋ በቀኑ መጨረሻ ለብሔራዊ ባንክ ሪፖርት ማድረግ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
ከተለያዩ ባንኮች እና የግል ቢሮዎች የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ሪፖርትን የሚሰበስበው ብሔራዊ ባንክ በበኩሉ፤ ሪፖርቶቹን በማጠናቀር በሚቀጥለው የሥራ ቀን መጀመሪያ ላይ ዕለታዊ አመላካች ምንዛሪ ተመን ለገበያ እንደሚያቀርብ መመሪያው ያስረዳል።
“ዕለታዊ አመላካች ምንዛሪ ዋጋው እንደ ማጣቀሻ ዋጋ ሆኖ ያገለግላል” የሚለው መመሪያው “ነገር ግን የግዴታ የግብይት ዋጋ እንደማይሆን” አጽንኦት ሰጥቷል።
የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የሚችሉት እነማን ናቸው?
አዲሱ የብሔራዊ ባንክ መመሪያ፤ ፈቃድ የተሰጣቸው የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ለየትኞቹ አገልግሎቶች የውጭ ምንዛሪ መሸጥ የዘረዘረ ነው።
በዚህ ዝርዝር መሠረት የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የተፈቀደላቸው የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ከኢትዮጵያ ውጭ የሚጓዙ ኢትዮጵያዊውያን ወይም በአገሪቱ ውስጥ የሚኖር የውጭ ዜጎች ናቸው።
በዚህ ዓይነት መልኩ ምንዛሪ ለማግኘት የሚፈልጉ ግለሰቦች ለበዓል፣ ለትምህርት፣ ለህክምና ጉዞዎች እና ሌሎች የግል ጉዳዮች እንደሚጓዙ የሚያሳይ ፓስፖርት፣ ሕጋዊ የመግቢያ ቪዛ እና የአየር ትኬት የማቅረብ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
እነዚህ ተጓዦች ከምንዛሪ ቢሮዎች እስከ አምስት ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወይም የዚህ አቻ የሆነ የሌላ አገር ገንዘብ በጥሬ ወይም በክፍያ መፈጸሚያ ካርድ (debit card) አማካኝነት ማግኘት ይችላሉ።
የውጭ ምንዛሪ የባንክ ሂሳብ ያላቸው ተጓዦች ደግሞ እስከ አስር ሺህ የአሜሪካ ዶላር ድረስ ማግኘት ተፈቅዶላቸዋል።
መመሪያው “በብሔራዊ ባንክ ካልተፈቀደ በስተቀር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነዋሪ በአንድ ጉዞ ላይ ከ10,000 የአሜሪካን ዶላር ወይም ተመጣጣኝ ገንዘብ በካሽ መያዝ አይችልም” ሲል ያትታል።
ሌላኛው የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የሚችሉት ለንግድ የሚጓዙ ግለሰቦች ናቸው።
መመሪያው ለንግድ የሚደረግ ጉዞን እና አበልን በተመለከተ በሚያትትበት ክፍሉ፤ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ሕጋዊ የንግድ ፈቃድ፣ ፓስፖርት እና የአየር ትኬት ለሚያቀርቡ ለንግድ ድርጅት ተወካዮች የውጭ ምንዛሪ መሸጥ እንደሚችሉ አስፍሯል።
ከዚህ በተጨማሪም እነዚሁ ቢሮዎች ለንግድ ድርጅቶች፣ ለበጎ አድራጎት ተቋማት እና ለሃይማኖት ማኅበራት፣ ለንግድ ትርኢቶች፣ ለቱሪዝም እንዲሁም ለባህል እና ለስፖርቶች አዘጋጆች የውጭ ምንዛሪ መሸጥ ይችላሉ።
የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ለመንግሥት ተጓዦች ለምግብ፣ ለማረፊያ እና ሌሎች ተያያዥ ወጪዎች ከአስር ሺህ የአሜሪካን ዶላር ወይም ተመጣጣኝ ገንዘብ የማይበልጥ የውጭ ምንዛሬ ሊሸጡ ይችላሉ።
መመሪያው የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ነዋሪ ላልሆኑ የውጭ አገር ዜጎች እና ቱሪስቶች ብርን ወደ ውጭ ምንዛሬ ሊለውጡ የሚችሉበት አሠራርም አስፍሯል።
በመመሪያው መሠረት ፓስፖርት፣ ትክክለኛ ቪዛ እና የአየር ትኬት የሚያቀርቡ ሰዎች ያለማስረጃ እስከ 500 የአሜሪካን ዶላር መለወጥ ይችላሉ።
ከ500 የአሜሪካን ዶላር በላይ መለወጥ የሚፈልጉ ከሆነ ደግሞ ፓስፖርት፣ ሕጋዊ ቪዛ፣ የአየር ትኬት እና ተመጣጣኝ የሆነው የውጭ ምንዛሪ በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ገንዘብ መቀየሩን የሚያሳይ የተረጋገጠ የባንክ ማስረጃ ማቅርብ ይጠበቅባቸዋል።












