ንግድ ባንክ በዶላር መሸጫ እና መግዣ ዋጋ ላይ የ17 ብር ጭማሪ አደረገ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢትዮጵያ መንግሥት የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን በገበያ ሥርዓት እንዲመራ መወሰኑን ተከትሎ፤ መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሜሪካ ዶላር መግዣ እና መሸጫ ዋጋ ላይ የ17 ብር ጭማሪ አደረገ።
ባንኩ ከሌሎች የግል ባንኮች ቀድሞ ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም. ጠዋት ይፋ ያደረገው የውጭ ምንዛሬ ግብይት እንደሚያሳየው አንድ የአሜሪካ ዶላር ባለፈው ሳምንት አርብ ሲሸጥ ከነበረበት 58.63 ብር ወደ 76.23 ብር ከፍ ብሏል።
ይህ በዶላር መሸጫ ዋጋ ላይ የተደረገው ማሻሻያ የ17.6 ጭማሪ ያሳየ ነው።
መንግሥታዊው ባንክ አንድ የአሜሪካ ዶላር መግዣ ዋጋ ላይም የ17.25 ብር ጭማሪ አድርጓል። በዚህም መሠረት በሳምንቱ መጨረሻ ከ57.48 ብር የነበረው የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ ወደ 74.73 ከፍ ብሏል።
በዩናይትድ ኪንግደም ፓዎንድ ሰተርሊናግ ላይ ደግሞ የ20 ብር ገደማ ጭማሪ ታይቷል። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ 1 ፓዎንድ ሰተርሊናግ 72.08 ይሸጥ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ዋጋው 93.71 ደርሷል።
በዩሮ ላይ እንዲሁ በመሸጫ እና መግዛዣ ዋጋ ላይ የ20 ብር ገደማ ጭማሪ ታይቷል።
ንግድ ባንክ በውጭ ምንዛሬ ግብይት ዋጋ ላይ ይህንን ከፍ ያለ ጭማሪ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከዛሬ ጀምሮ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን በገበያ ሥርዓት እንደሚመራ ማስታወቁን ተከትሎ ነው።
ብሔራዊ ባንክ ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም. ንጋት ላይ ባወጣው መግለጫ፤ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን በባንኮች እና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወስንበት የገበያ ሥርዓት እንደሚሸጋገር ገልጿል።
እስከዛሬ ድረስ በውጭ ምንዛሬ የገበያ ተመንን ሲወስን የነበረው ብሔራዊ ባንክ ከአሁን በኋላ በገበያ ሥርዓቱ ላይ የሚኖረው ሚና “ገበያውን በማረጋጋት ላይ ያተኮረ” እንደሚሆንም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
ብሔራዊ ባንክ በመግለጫው የውጭ ምንዛሪን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማስተላለፍ ግዴታ የቀረ መሆኑን ገልጿል።
ማሻሻያው ላኪዎች እና ንግድ ባንኮች ያፈሩትን የውጭ ምንዛሪ ለራሳቸው ማስቀረት በመቻላቸው ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠውን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ያሻሽላል ተብሏል።
ግባራዊ መሆን የጀመረውን ይህንን የፖሊሲ ማሻሻያ ተከትሎ በባንክ በአንድ የአሜሪካ ዶላር የመግዣ እና መሸጫ ዋጋ ላይ የተደረገው የ17 ብር ጭማሪ በትይዩ (ጥቁር) ገበያ ላይም ለውጥ እንደሚያስከትልም ይጠበቃል።
ከዚህ በተጨማሪ የብር የመግዛት አቅም እንዲቀንስ መደረጉ እንዲሁ በምርት እና አገልግሎት አቅርቦቶች ላይ ሊያስከትለው የሚችለው ለውጥ ተጠባቂ ነው።
ትናንት እሁድ ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም. የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ባወጣው የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ፕሮግራም ፖሊሲ ላይ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ተመንን በገበያ እንዲወሰን ልታደርግ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።
ይህ ውሳኔ ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር ሳያግባባት የቆየውን በመንግሥት ቁጥጥር ስር የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ተመን ውሳኔ በገበያው ላይ ባለ የግብይት ተመን እንዲወሰን የሚያደርግ ይሆናል።












