ብሔራዊ ባንክ አዲሱ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መንግሥት የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን በገበያ ሥርዓት እንዲመራ መወሰኑን ተከትሎ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ከዛሬ ሰኞ ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም. ጀምሮ መሻሻሉን አስታወቀ።
ብሔራዊ ባንክ በዛሬው መግለጫው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያው በአዲሱ የውጭ ምንዛሪ መመሪያ መሠረት የሚተገበር ይሆናል ብሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን በባንኮች እና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወስንበት የገበያ ሥርዓት ይሸጋገራል ያለ ሲሆን፤ በዚህ ውስጥ የባንኩ ሚና ገበያውን ማረጋጋት ላይ ያተኮረ እንደሚሆን ተገልጿል።
ብሔራዊ ባንክ በመግለጫው የውጭ ምንዛሪን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማስተላለፍ ግዴታ የቀረ መሆኑን ገልጿል። ማሻሻያው ላኪዎች እና ንግድ ባንኮች ያፈሩትን የውጭ ምንዛሪ ለራሳቸው ማስቀረት በመቻላቸው ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠውን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ያሻሽላል ተብሏል።
ትናንት እሁድ ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም. የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ባወጣው የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ፕሮግራም ፖሊሲ ላይ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ተመንን በገበያ እንዲወሰን ልታደርግ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።
ይህ ውሳኔ ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር ሳያግባባት የቆየውን በመንግሥት ቁጥጥር ስር የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ተመን ውሳኔ በገበያው ላይ ባለ የግብይት ተመን እንዲወሰን የሚያደርግ ይሆናል።
በምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ፖሊሲው መግለጫ ላይ እንደተጠቀሰው በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት “የውጭ ምንዛሪ ግብይት በገበያው አማካኝነት እንዲበየን” የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል።
ለዚህም እንደ ምክንያት የተቀመጠው ይህ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት በአቅርቦት እና በፍላጎት መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሪ መዛባትን በማስተካከል የገቢ እና የወጪ ሸቀጦችን እና አገልግሎቶችን ዋጋ ከገበያ እውነታዎች ጋር እንዲጣጣም ያስችላል ብሏል።
በተጨማሪም ይህ የፖሊሲ ማሻሻያ ኢትዮጵያ አዳዲስ የልማት ፋይናንስ አቅርቦትን ከተለያዩ ምንጮች ለማግኘት ያስችላታል የተባለ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት አገሪቱ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ መንገድ ብዙ ቢሊየን ዶላር ታገኛለች ተብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት ወራት ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር ለማግኘት ውይይት ሲያካሂድ የቆየ ሲሆን፣ ይህ እና ባለፉት ወራት በመንግሥት የተወሰዱ የፋይናንስ እና የማጣኔ ሀብት ማሻሳያዎች ከዚሁ ጋር የተያያዙ እንደሆኑ ይነገራል።
ይህ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን በገበያ ላይ ባለው አቅርቦት እና ፍላጎትን መሠረት አድርጎ እንዲወሰን ማድረጉ የአገሪቱ መንግሥት በበላይነት ሲቆጣጠረው የቆየውን ሂደት ወደ ገበያው ኃይሎች የሚያዞር ነው።
ባለፉት ዓመታት መንግሥት የምንዛሪ ግብይት ተመኑ ላይ ቁጥጥር ቢያደርግም ዋጋው በመደበኛው እንዲሁም መደበኛ ባለሆነው ገበያ ውስጥ በተለያየ መጠን ከእጥፍ በላይ ጭማሪን አሳይቷል። በዚህም ሳቢያ የአንድ ዶላር ዋና በባንኮች ወደ 60 ብር የተጠጋ ሲሆን፣ መደበኛ ባልሆነው ግብይት ደግሞ ከ110 ብር ባላይ ሲያወጣ ቆይቷል።
በአሁን የመንግሥት ውሳኔ መሠረት የውጭ ምንዛሪ ግብይት ዋጋ በገበያው ላይ በሚኖው ፍላጎት እና አቅርቦት መሠረት የሚወሰን በመሆኑ ከኢመደበኛው ገበያ ዋጋ ጋር ሊጠጋጋ አሊያም ከዚያም ከፍ ሊል ይችላል የሚል ስጋት አለ።
በዚህም ሳቢያ የውጭ ምንዛሬ ግብይት ሥርዓቱ ላይ በሚኖረው ለውጥ እና በሌሎች ምጣኔ ሀብታዊ የፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃዎች ምክንያት “ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የሚያስችሉ ተግባራት ይከናወናሉ” ተብሏል።
በዚህም የማኅበራዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራሞች ድጎማ፣ ለዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ድጎማ እና ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ እንዲሁም በነዳጅ ዋጋ ላይ የሚከሰትን የዋጋ ጭማሪ ለማቅለል መንግሥት በከፊል ድጎማ ያደርጋል ተብሏል።
መንግሥት ተግባራዊ የሚያደርጋቸው የፖሊሲ እርምጃዎች ከአገሪቱ የረጅም እና የመካከለኛ ጊዜ የልማት ዕቅዶች ተጣጥመው የሚከናወኑ ሲሆን፣ የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም እና የሕዝቡን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ ሁኔታ ክትትል እንደሚደረግበት ተገልጿል።
ይህ የመንግሥት ውሳኔ ይፋ የተደረገው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ከኢትዮጵያ በቀረበለት የብድር ጥያቄ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም. እንደሚሰበሰብ ከሚጠበቅበት አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነው።
ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት በጦርነት፣ በድርቅ እና በዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች የገጠሟትን ምጣኔ ሀብታዊ ጫናዎችን ለመቋቋም ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር ለማግኘት ጠይቃለች።












