ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና ከወዳጅ አገራት 13.5 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ

ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና ከወዳጅ አገራት 13.5 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ ኢትዮጵያ ዛሬ መተግበር ለጀመረችው በገበያ ሥርዓት የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን ስርዓት እና ሌሎች ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ትግበራ የሚውል 13.5 ቢሊዮን ዶላር ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና ወዳጅ ሀገራት “በድጋፍ” እና ሌሎች አማራጮች መገኘቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

ጭምቅ ሃሳብ

  • ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና ከወዳጅ አገራት 13.5 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ
  • መንግሥት የወሰደው እርምጃ ለአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ጠቀሜታ አለው ይላል።
  • አሜሪካ አዲሱ የውጭ ምንዛሬ የገበያ ስርዓት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ “አስፈላጊ እርምጃ” ነው አለች
  • ንግድ ባንክ በዶላር መሸጫ እና መግዣ ዋጋ ላይ የ17 ብር ጭማሪ አደረገ
  • ብሔራዊ ባንክ አዲሱ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል አለ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በአዲሱ መመሪያ የውጭ ምንዛሪ ግብይት እንዴት ይከናወናል?

    ዶላር እና የኢትዮጵያ ሳንቲሞች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአዲሱ የብሔራዊ ባንክ መመሪያ የውጭ ምንዛሪ በመግዛት እና በመሸጥ ላይ የሚሳተፉ አካላትን እና አሠራራቸውን በዝርዝር ያስቀመጠ ነው።

    ባንኮች በዚህ አሰራር ውስጥ ዋና ተዋናይ መሆን እንደሚገባቸው መመሪያው ላይ ሰፍሯል።

    ከዚህ በተጨማሪም በባንኮች ከተቋቋሙ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በተጨማሪ ባንክ ያልሆኑ የግል የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች ይቋቋማሉ። በተጨማሪም መመሪያ ከውጭ ምንዛሪ ግብይት ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ይመልሳል።

    • የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች እንዴት ነው የሚቋቋሙት?
    • የውጭ ምንዛሬ ግብይት ተመን እንዴት ይወሰናል?
    • የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የሚችሉት እነማን ናቸው?
  2. “አዲሱ የውጭ ምንዛሪ ገበያ ‘እንኳን ደስ አላችሁ’ የሚያስብል አይደለም” ክቡር ገና

    ክቡር ገና

    የፎቶው ባለመብት, ETHIOPIAN BUSINESS REVIEW

    ክቡር ገና፡ይህ ገንዘብ “ድጋፍ” አይመስለኝም። በብድር መልክ ይመስለኛል የተጠቀሰው ገንዘብ ሊመጣ ይችላል ነው የተባለው። በአንድ ጊዜ የሚሰጥ ገንዘብም አይደለም። እየተለካ፤ ውጤቱ እየታየ፤ የጠየቁት ለውጥ ሥራ ላይ መዋሉን እያረጋገጡ ሲመጡ ነው ይህ ገንዘብ የሚለቀቀው። አይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ ይህን የሚያደርጉት ለኢትዮጵያ በጎ ለመሥራት ብለው እንዳልሆነ መታወቅ አለበት። ይህ ሌላው ዓለም የታየ ነገር ነው። ሙሉውን ይህንን ሊንክ ተጭነው ያንብቡ “አዲሱ የውጭ ምንዛሪ ገበያ ‘እንኳን ደስ አላችሁ’ የሚያስብል አይደለም” ክቡር ገና

  3. የዩኬ ኤምባሲ አዲሱ የውጭ ምንዛሪ የገበያ ሥርዓት ‘የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማጠናከር ይረዳል’ አለ

    አርማ

    የፎቶው ባለመብት, uk embassy/fb

    የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) መንግሥት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ማወጁን “በደስታ እንደሚቀበል” አስታወቀ።

    በአዲስ አበባ የሚገኘው የዩኬ ኤምባሲ ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ላይ ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 22/2016 ዓ. ም. በወጣው መግለጫ “ይህ ጉልህ እርምጃ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማጠናከር፣ የበለጠ አሳታፊ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማስፋፋት እና ድህነትን ለመቀነስ ይረዳል ብለን እናምናል” ብሏል።

    የአሜሪካ መንግሥትም በተመሳሳይ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያደርጋቸውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች እንደሚደግፍ ማስታወቁ ይታወሳል።

    በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ በገበያ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ግብይት የአገሪቱን “የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ለመፍታት አስፈላጊ እርምጃ” መሆኑን በመግለጽ ለመንግሥት እርምጃ ድጋፉን አሳይቷል።

    የዩኬ መንግሥት በበኩሉ የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ አጋር እንደመሆኗ “ለኢትዮጵያ ብልጽግና እና መረጋጋት ጠንካራ ድጋፉን ይቀጥላል” ሲል አቋሙን ገልጿል።

  4. በአዲሱ የብሔራዊ ባንክ መመሪያ መሠረት የውጭ ምንዛሪ ግብይት እንዴት ይከናወናል?

  5. ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና ከወዳጅ አገራት 13.5 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ

    የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ

    የፎቶው ባለመብት, National Bank of Ethiopia

    የምስሉ መግለጫ, የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ

    ኢትዮጵያ ዛሬ መተግበር ለጀመረችው በገበያ ሥርዓት የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን ስርዓት እና ሌሎች ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ትግበራ የሚውል 13.5 ቢሊዮን ዶላር ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና ወዳጅ ሀገራት “በድጋፍ” እና ሌሎች አማራጮች መገኘቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

    ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 10.7 ቢሊዮን ዶላሩ የገንዘብ “ድጋፍ” የተገኘው ከዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይ.ኤም.ኤፍ)፣ ከዓለም ባንክ እና “ከአበዳሪዎች” እንደሆነ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ አስታውቀዋል።

    የብሔራዊ ባንክ ገዢው ይህንን ያስታወቁት ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም. ንጋት ላይ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያን አስመልክቶ በወጣ መግለጫ እና ማብራሪያ ላይ ነው።

    መንግሥት መተግበር የጀመራቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የሚያመጡት “የሽግግር ወቅት ወጪዎችን” እንደሚኖሩ እንዲሁም አዲሱ የውጭ ምንዛሬ ግብይት ስርዓት “የሚያስከትላቸው ጫናዎች” እንደሚኖሩ አቶ ማሞ በመግለጫቸው ላይ ጠቁመዋል።

    ይሁንና እነዚህን ጫናዎች ለመቀነስ የሚውል 10.7 ቢሊዮን ዶላር “ትልቅ ድጋፍ ከውጭ አጋሮች” እንደተገኘ ገልጸዋል።

    የብሔራዊ ባንክ ገዢው፤ “ይህ የገንዘብ ድጋፍ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት፣ ከዓለም ባንክ እና ከአበዳሪዎች የሚገኘውን ይህንን ሪፎርም የሚመለከተውን ይጨምራል” በማለት “ድጋፍ” ሲሉ የጠሩት ገንዘብ ምንጮችን ጠቅሰዋል።

    ከዚህም ባሻገር ከኢትዮጵያ “ወዳጅ ሀገራት” በሌሎች አማራጮች ተጨማሪ 2.8 ቢሊዮን ዶላር እንደተገኘ አቶ ማሞ አስታውቀዋል።

    ይህ ገንዘብ የተገኘው “በማዕከላዊ ባንክ ተቀማጭ ሂሳብ (central bank diposite) እና በሀገራት የገንዘብ ልውውጥ (currency swap)” መልክ እንደሆነም አብራርተዋል።

    የብሔራዊ ባንክ ገዢው በእነዚህ አማራጮች ገንዘብ የተገኘባቸውን ሀገራት ባይጠቅሱም ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ኢትዮጵያ እና የተባበሩት የአረብ ኢምሬቶች የገንዘብ ልውውጥ ስምምነት ተፈራርመው ነበር።

    ማሞ ዛሬ በሰጡት መግለጫቸው ላይ በሌሎች አማጮችም ተጨማሪ ገንዘብ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

    “እነዚህ አሃዞች [የተገኘው 13.5 ቢሊዮን ዶላር ] ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC)፣ ከሌሎች ባለብዙ ወገኖች ፕሮጀክትን አስመልክቶ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀውን እና በሂደት ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት ይፋ የሚደረገውን ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ አያካትትም” ብለዋል።

    የኢትዮጵያ መንግሥት ”የገንዘብ ድርጅት፣ ከዓለም ባንክ እና ከወዳጅ ሀገራት” ያገኘው ገንዘብ ሀብት “የመንግሥትን የሪፎርም ስራዎች ጥንካሬ ያገናዘበ” እንደሆነ አቶ ማሞ ጠቅሰዋል።

    “በአፍሪካ አህጉር ትልቁ ከሚባሉት የገንዘብ ድጋፎች አንዱ ነው” ሲሉም አሞካሽተውታል።

  6. መንግሥት የወሰደው እርምጃ ምን ጠቀሜታ አለው ይላል?

    የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ግብይት በገበያ ሥርዓት አማካይነት እንዲወሰን ማድረጉ የተለያዩ ጥቅሞች አሉት ይላል? ይህ እርምጃ ያስገኛል የተባሉት ጠቀሜታዎች ምንድን ናቸው?

    • የውጭ ምንዛሪ ገብይት ማሻሻያው የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ገቢ በተገቢው መንገድ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን እና ለነዋሪዎች እንዲሁም ለአምራቾች ጥቅም መዋሉን ለማረጋገጥ ያግዛል።
    • ውጭ የሚገቡ ምርቶች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ እና የገበያ ድርሻቸው እንዲያድግ ያበረታታል።
    • የግሉን ዘርፍ ለማሳደግ እና የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ለማሻሻል እንዲሁም ለውጭ ባለሀብቶች ምጣኔ ሀብቱን ክፍት ለማድረግ የተወሰዱ እርምጃዎችን ያጠናክራል።
    • የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ፣ የአገሪቱን የንግድ ሥርዓት ለማሻሻል አስተዋጽኦ ይያደርጋል።
    • በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ውስጥ መደበኛ ያልሆኑ እና ሕገ ወጥ የሆኑ የንግድ አሠራሮችን ለማስቀረት ይረዳል።
  7. አሜሪካ አዲሱ የውጭ ምንዛሬ የገበያ ሥርዓት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ “አስፈላጊ እርምጃ” ነው አለች

    US Embassy

    የፎቶው ባለመብት, US Embassy

    አሜሪካ መንግሥት የሚያደርጋቸውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች እንደምትደግፍ አስታወቀች።

    በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ይህን ያለው ኢትዮጵያ መንግሥት በገበያ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን ሥርዓትን መተግበር በጀመረበት ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም. ባወጣው አጭር መግለጫ ነው።

    ዛሬ መተግብር የጀመረውን ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ግብይት ተመንን የጠቀሰው የኤምባሲው መግለጫ፤ ይህ ዓይነቱ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት “አስቸጋሪ” እንደሆነ ጠቅሷል።

    ይሁን እንጂ የአገሪቱን “የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ለመፍታት አስፈላጊ እርምጃ” መሆኑን በመግለጽ ለመንግሥት እርምጃ ድጋፉን አሳይቷል።

    የኢትዮጵያ መንግሥት ሕዝቡን “ለመርዳት” የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን እንዲተገብር እንዲሁም አገሪቱ “ይበልጥ ነጻ እና ጠንካራ ወደ ሆነ ኢኮኖሚ” ለመድረስ የምታደርገውን ጉዞ አሜሪካ “እንደምታበረታታ” በመግለጫው ላይ ሰፍሯል።

  8. ንግድ ባንክ በዶላር መሸጫ እና መግዣ ዋጋ ላይ የ17 ብር ጭማሪ አደረገ

    CBE

    የፎቶው ባለመብት, CBE

    የኢትዮጵያ መንግሥት የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን በገበያ ሥርዓት እንዲመራ መወሰኑን ተከትሎ፤ መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሜሪካ ዶላር መግዣ እና መሸጫ ዋጋ ላይ የ17 ብር ጭማሪ አደረገ።

    ባንኩ ከሌሎች የግል ባንኮች ቀድሞ ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም. ጠዋት ይፋ ያደረገው የውጭ ምንዛሬ ግብይት እንደሚያሳየው አንድ የአሜሪካ ዶላር ባለፈው ሳምንት አርብ ሲሸጥ ከነበረበት 58.63 ብር ወደ 76.23 ብር ከፍ ብሏል።

    ይህ በዶላር መሸጫ ዋጋ ላይ የተደረገው ማሻሻያ የ17.6 ጭማሪ ያሳየ ነው።

  9. ብሔራዊ ባንክ አዲሱ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል አለ

    ዶላር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መንግሥት የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን በገበያ ሥርዓት እንዲመራ መወሰኑን ተከትሎ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ከዛሬ ሰኞ ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም. ጀምሮ መሻሻሉን አስታወቀ።

    ብሔራዊ ባንክ በዛሬው መግለጫው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያው በአዲሱ የውጭ ምንዛሪ መመሪያ መሠረት የሚተገበር ይሆናል ብሏል።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን በባንኮች እና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወስንበት የገበያ ሥርዓት ይሸጋገራል ያለ ሲሆን፤ በዚህ ውስጥ የባንኩ ሚና ገበያውን ማረጋጋት ላይ ያተኮረ እንደሚሆን ተገልጿል።