“አዲሱ የውጭ ምንዛሪ ገበያ ‘እንኳን ደስ አላችሁ’ የሚያስብል አይደለም” ክቡር ገና

ክቡር ገና

የፎቶው ባለመብት, ETHIOPIAN BUSINESS REVIEW

የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን በገበያ ሥርዓት እንዲመራ ወስኗል። ይህን ተከትሎ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ከሰኞ ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ተሻሽሏል።

ብሔራዊ ባንክ በሰጠው መግለጫው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያው በአዲሱ የውጭ ምንዛሪ መመሪያ መሠረት የሚተገበር ይሆናል ብሏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን በባንኮች እና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወስንበት የገበያ ሥርዓት ይሸጋገራል ያለ ሲሆን፤ በዚህ ውስጥ የባንኩ ሚና ገበያውን ማረጋጋት ላይ ያተኮረ እንደሚሆን ተገልጿል።

ይህ አዲሱ የፖሊሲ ትግበራ በርካቶችን እያነጋገረ ሲሆን፣ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እና የፖለቲካ ሰዎችም በመገናኛ ብዙኃን እና በማኅበራዊ ሚድያ ገፆቻቸው አማካይነት ሐሳባቸውን እየሰጡ ነው።

የፓን አፍሪካን ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ኤንድ ኢንደስትሪ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ክቡር ገና “አዲሱ ፖሊሲ ለውጥ ያመጣል ብዬ አላምንም” ይላሉ።

ቢቢሲ ከአቶ ክቡር ጋር ያደረገውን ቃለ-ምልልስ የጀመረው አዲሱ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ምን ይዞ ሊመጣ ይችላል? በሚል ጥያቄ ነው።

ክቡር ገና፡ አዲሱን ፖሊሲ አዲስ የሚያደርገው ነገር ይፋ መደረጉ ነው። ይህ ፖሊሲ ተግባራዊ እንደሚድረግ ሲነገር ነው የቆየው። አዲሱ የውጭ ምንዛሪ ጭማሪ እነዚን ነገሮች ይዞ ሊመጣ ይችላል። አንደኛ፤ ገበያው ይወስን በሚባልበት ጊዜ ኢኮኖሚውን በእንግሊዝኛው “ስፔኪዩሌቲቭ” ለሚባለው ሁኔታ ያጋልጣል። [ይህ ማለት] የውጭ ምንዛሪው በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደላይ ሊወጣ አሊያም ሊወርድ ይችላል ማለት ነው።

በለተይ ደግሞ “ማርኬት ቤዝድ ኤክስጄንጅ” የብር የመግዛት አቅምን እያዳከመ፤ የዶላርን የመግዛት ዋጋ ከፍ እያደረገው ሲሄድ ድርጅቶችን ይጎዳል። ምክንያቱም የሚያስገቡትን ግብዓት በውጭ ምንዛሪ ስለሚያስመጡ አገር ቤት ገብቶ ከተመረተ በኋላ ለሸማቹ የሚቀርብበት ዋጋ ከፍ ማለቱ አይቀርም። ይህ ደግሞ የኑሮ ሁኔታውን የበለጠ ያናጋዋል የሚል ፍትሀት አለኝ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቢቢሲ፡ አዲሱ ፖሊሲ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም [አይአይምኤፍ] ያደረገውን “ድጋፍ” ተከትሎ የመጣ ይመስላል። በዚህ ገንዘብ የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ገበያ መር ሆኖ እንዲቀጥል ዘላቂ መፍትሔ ይሆናል?

ክቡር ገና፡ ይህ ገንዘብ “ድጋፍ” አይመስለኝም። በብድር መልክ ይመስለኛል የተጠቀሰው ገንዘብ ሊመጣ ይችላል ነው የተባለው። በአንድ ጊዜ የሚሰጥ ገንዘብም አይደለም። እየተለካ፤ ውጤቱ እየታየ፤ የጠየቁት ለውጥ ሥራ ላይ መዋሉን እያረጋገጡ ሲመጡ ነው ይህ ገንዘብ የሚለቀቀው። አይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ ይህን የሚያደርጉት ለኢትዮጵያ በጎ ለመሥራት ብለው እንዳልሆነ መታወቅ አለበት። ይህ ሌላው ዓለም የታየ ነገር ነው።

በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከአይኤምኤፍ መበደር ከእናት እንደመበደር ነው” ብለው ነበር። ነገር ግን ዞሮ ዞሮ ብድር፤ ብድር ነው። ብድሩ መመለስ መቻል አለበት። ይህን ብድር መመለስ የምንችልበት ሁኔታ ላይ ነን ወይ ያለነው? በእኔ አስተያየት ከሁሉ በፊት ሰላም እና መረጋጋት እንዲሁም እየጠፋ ያለው የሕግ የበላይነት መመለስ አለበት። ካልሆነ ገንዘቡን እንዲሁ እንደመበተን ነው የሚታየኝ።

ቢቢሲ፡ ለምሳሌ ጎረቤት ሀገር ኬንያ በገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ነው የምትዳደረው። ኢትዮጵያ ወደዚህ ፖሊሲ መሻገሯ ለምን አስጊ ይሆናል? የኢትዮጵያ ጉዳይ ከሌሎች አገራት የገበያ መር ፖሊሲዎች በምን ይለያል?

ክቡር ገና፡ ለምሳሌ ኬንያውያን ባለፉት ሳምንታት ጎዳና ላይ ወጥተው ሰላማዊ ሰልፍ እያደረጉ ነው። ለዚህ ምክንያቱ አንደኛ የአይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ ብድር ለአገሪቱ በሚጠቅም ሁኔታ ስላለቀረበ፤ የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ እየጎዳው ስለሆነ፤ የጤና፣ የትምህርት እና የመሠረተ ልማት በተለይ ደግሞ የትራንስፖር ዋጋ መናር ስላለ ነው።

ይህ ሁሉ ነገር የመጣው ገበያውን ነፃ በማድረጋቸው ነው ለማለት አይደለም። ነገር ግን አይኤምኤፍ እና ዓለም ባንክ ብዙውን ጊዜ ብድር ለመስጠት የሚጠይቁት ቅድመ ሁኔታ አገራትን ችግር ላይ ሲጥል እንጂ ከችግር ሲያወጣ አይታይም። እና የእኛም ወደዚያው እንዳይሆነ ነው የሚያስፈራው።

አንደኛው ጉዳይ የአገሪቱን የማምረት አቅም መገንባት ነው። ዛሬ ያለው ሁኔታ አንድ ድርጅት ብድር ወስዶ መክፈል የሚችልበት አይደለም። ኢትዮጵያ የወለድ ዋጋ እስከ 20 በመቶ ይደርሳል። አንድ ድርጅት 20 በመቶ ብድር ለመክፈል 40 በመቶ ማትረፍ ይኖርበታል።

ብር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቢቢሲ፡ ትይዩ ገበያው ላይ ያለው የዶላር ዋጋ ትክክለኛው የዶላር ዋጋ ነው የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ። ስለዚህ የባንክ የምንዛሪ ዋጋ ከፍ ማለቱ ምንም ለውጥ አያመጣም ሲሉ ይከራከራሉ። ይህ ሐሳብ ያስኬዳል?

ክቡር ገና፡ [የዶላርን] የምንዛሪ ዋጋ ከትይዩ ገበያው ጋር እኩል ማድረጉ ለአገሪቱ ልማት አሊያም የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻል የሚሆን መፍትሔ አይደለም። አንዳንድ አገራት አስፈላጊ ለሚሏቸው የልማት ግብዓቶች የሚወስኑት የወለድ ዋጋ አለ። ለሌላው ነገር ደግሞ ሌላ የወለድ ዋጋ ይወስናሉ ማለት ነው።

ለምሳሌ መካከለኛ ገቢ ላላቸው ሸማቾች ይሆናሉ የሚባሉ ምርቶች በትይዩ ገበያ [ብላክ ማርኬት] ዋጋ ሊወሰኑ ይችላሉ። ነገር ግን አንድ የማምረቻ መሣሪያ ለማምጣት ከተፈገለ በባንኩ [ብሔራዊ ባንክ] ማምጣት የበለጠ ጠቀሜታ አለው። የዶላር ዋጋ ገበያው ላይ እኩል ሲሆን ይሻሻላል የሚለው ሐሳብ የማያስማማኝ በሌሎች አገራት ሲሻሻል ስላላየን ነው።

እርግጥ ነው የአገሪቱ የልማት አቅጣጫ እና በዚያ የልማት አቅጣጫ ላይ የተመሠረተ ብድርም ሆነ ድጋፍ መሰጠት ያለበት ከምሥራቅ ኤዥያ አገራት በተወሰደ ልምድ ነው። እንደ ኮሪያ እና ጃፓን ባሉ አገራት ለልማት የሚሆን ብድር የሚጠይቁ ሰዎች የሚሰጣቸው ድጋፍ ከሌላው ይለያል። የምንፈልገው የልማት አቅጣጫ ምንድነው? እንዴት አድርገን ነው ባንኮቻችን እነዚህ የልማት አቅጣጫ ላይ ማተኮር የሚችሉት?

ባንኮቻችን ውጤት ሊያመጣ የሚችል የወለድ ዋጋ [ኢንተረስት ሬት] ላይ ማተኮር መቻል አለባቸው። አምራቹ የወለድ መጠኑ ከአቅሙ በላይ ሲሆን፣ ድርጅቱ እየደቀቀ ነው የሚሄደው። ስለዚህ ገበያ ብቻ አይደለም መወሰን ያለበት። እኔ የልማት አቅጣጫችን እንደገና መታየት ያለበት ይመስለኛል።

ቢቢሲ፡ የገቢና ወጭ ገበያ አለመመጣጠን፤ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት [ኤፍዲአይ] ከፍተኛ አለመሆን እና የሰላም እና መረጋጋት እጦት እንዳለ ይታወቃል። አይኤምኤፍ የሚሰጠው ገንዘብ ለጥቂት ጊዜ ገበያውን ሊያረጋገው ይችላሉ የሚሉ ሐሳቦች አሉ። ከዚያ በኋላስ ምን ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት አለዎት?

ክቡር ገና፡ ከሁሉም በላይ እኛ በአቅማችን መኖር መቻል አለብን። እንደተጠቀሰው የገቢ እና ወጪ ገበያ አለመመጣጠን የተከሰተው በአቅማችን መሄድ ስላልቻልን ነው ብዬ ነው የምገምተው። ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ቀደም ሲል እንዳነሳሁት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ዘርፎች ቅድሚያ ባለመስጠታችን ነው። እኔ አሁን የተወሰዱት እርምጃዎች በአጭር ጊዜ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ የሚል እምነት የለኝም።

ቢያንስ አንድ ሁለት ዓመት ይፈጅበታል። በተለይ ደግሞ ወደ ውጭ የሚላኩ እንደ ሰሊጥና ቡና ያሉ ምርቶች ተመርተው ወደ ውጭ እስኪላኩ ድረስ ጊዜ ይወስዳሉ። በአንድ እና በሁለት ዓመት ውስጥ ለውጥ መጠበቅ የሚቻል አይመስለኝም። በሚቀጥሉት ጊዜያት ደግሞ ችግሩ እየተባባሰ እንጂ እየቀነሰ ይመጣል የሚል ግምት የለኝም።

እርግጥ ነው መንግሥት ይህን ለመቀነስ የወሰዳቸው እርምጃዎች አሉ። ለምሳሌ የቤት ኪራይ ዋጋ እንዳይጨመር ተደርጓል፤ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ጭማሪ ለማድረግ መታሰቡን ሰምተናል። እነዚህ ድጎማዎች መደረጋቸው ትክክል ቢሆንም [የተወሰነው ውሳኔ] “እንኳን ደስ አላችሁ” የሚያስብል አይደለም።

መገናኛ ብዙኃን ስንሰማ “እንኳ ደስ አላችሁ” ብድር ተፈቅዷል፤ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገበያ ተስተካክሏል ብሎ መናገር ተገቢ አይመስለኝም፤ ማሳሳትም ይመስለኛል።

ቢቢሲ፡ ከዚህ ቀደም በመንግሥት በሚወሰን ተመን [ፊክስድ ሬት]ነበር ገበያው የሚንቀሳቀሰው። አሁን ደግሞ ወደ ገበያ መር ፖሊሲ ተሻግረናል። ነገር ግን አዲሱ ፖሊሲ መፍትሔ አያመጣም የምንል ከሆነ የተሻለ የሚባለው አማራጭ የትኛው ነው ብለው ያስባሉ?

ክቡር ገና፡ እኔ ስለወለድ ዋጋ ያለኝ አስተያየት ከዚህ ቀደም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ከፃፉት የተለየ አይደለም። ለእኔ “ኢንተረስት ሬት” [የወለድ መጠን] ያሠራል ወይስ አያሠራም? ኢንዱስትሪውን ሊያሳድግ ይችላል ወይስ አይችልም? ነው።

በነገራችን ላይ ገበያ የሚወስነው “ኢንተረስት ሬት” የለም። የትኛው ገበያ ነው የወለድ ዋጋውን የሚወስነው? በሁለት ወይም በሦስት ባንኮች መካከል የሚደረግ “የኢንተረስት ሬት” ልውውጥ ነው? አንድ ገበያ ላይ ያለ ድርጅት በስንት የወለድ ዋጋ ብንሰጠው ነው አትርፎ የባንኩን ዕዳ መክፈል የሚችለው? ነው መወሰን ያለበት።

የአሜሪካንን ኢንተረስት ሬት ጠጋ ብለን ካየነው ከዚህ የተለየ አይደለም። እርግጥ ነው የእነሱ ገበያ ያደገ ነው። ድርጅቶች ዛሬ ይሄን እንቀንስ አሊያም እንጨምር፤ ካልሆነ ደግሞ ዛሬ እንዝለለው እና ከወራት በኋላ እንጨምር ማለት ገበያ መር አይባልም።