ለኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ተጎጂ ቤተሰቦች 58 ቢሊዮን ዶላር ካሳ ሊጠየቅ ነው

በአደጋው የሞቱ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, The Washington Post / Getty Images

በ2011 ዓ.ም. በተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ 737 ማክስ 9 አውሮፕላን ሕይወታቸው ያለፉ መንገደኛ ቤተሰቦችን የወከሉ ጠበቆች ከፍተኛ ካሳ ክፍያ እየጠየቁ ነው።

ይህም የአሜሪካ ፍትሕ መስሪያ ቤት እና ቦይንግ ኩባንያ የደረሱበትን ስምምነት የሚቃረን ነው።

ባለፈው ሐምሌ ወር አሜሪካዊው አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ በማጭበርበር ወንጀል ጥፋተኝነቱን አምኖ ከ243.6 ሚሊዮን ዶላር እስከ 487 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ቅጣት ለመክፈል ተስማምቷል።

በዚህም ስምምነት መሰረት ቦይንግ ለተጎጂ ቤተሰቦች 24.8 ቢሊዮን ዶላር ቅጣት እንዲከፍል የተወሰነ ሲሆን ተጨማሪ የካሳ ክፍያ እየጠየቀ ያለው ሪቢክ የተባለው የጠበቆች ድርጅት የተወሰነላቸው ክፍያ ቤተሰቦቹ አስቀድመው ከጠየቁት ሽራፊውን ነው ብሏል።

89 የተጎጂ ቤተሰቦችን የወከለው ድርጅቱ ለአሜሪካ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያለ ሲሆን፤ ስምምነቱን በመቃወም የካሳ ክፍያው “በጣም አነስተኛ” መሆኑን ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

የጠበቆች ድርጅት በአንጻሩ የካሳ ክፍያው ከ47 ቢሊዮን ዶላር እስከ 58 ቢሊዮን ዶላር ከፍ እንዲከፍል እየወተወተ ነው።

ለዚህም ከዚህ ቀደም በኮርፖሬት ድርጅቶች የነበሩ የማጭበርበር መዝገቦችን በመጥቀስ፤ የሰው ሕይወት ሳይጠፋባቸው እንኳን የከፈሉት ካሳ በቢሊዮን ዶላሮች ነው ብሏል።

ሪቢክ የጠበቆች ድርጅት ለፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ምክረ ሀሳቡ እንዲሰረዝ እና ቦይንግ ለ346 ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ለሆነው አደጋ ዋጋ የሚሰጥ ከፍተኛ ቅጣት እንዲቀጣ እና ሌሎች ላይ ላደረሰው ከፍተኛ ጉዳት የወንጀል ፈጻሚ ተከሳሾች በሚቀጡት ልክ እንዲቀጣ ጠይቋል።

የድርቱ የጋራ መስራች የሆኑት ማንኤል ቫን ሪቢክ “በደንበኞቻችን ስም በቅርቡ የአሜሪካ ፍትሕ መስሪያ ቤት እና ቦይንግ የወንጀል ማጭበርበር ክስ ላይ የደረሱትን ስምምነት በእጅጉ እንቃወማለን። በምክረ ሀሳቡ ላይ የተቀመጠው ቅጣት በጣም አነስተኛ እና በተመሳሳይ መዝገቦች ቅጣት የተላለፈባቸው ኮርፖሬቶች ጋር አይቀራረብም” ብለዋል።

የጠበቆች ድርጅት ከዚህ በፊት የተፈጸሙ ተመሳሳይ የወንጀል ጉዳዮችን በማሳያነት በማንሳት፤ የገንዘብ ማጭበርበር የፈጸሙ ባንኮችን ጠቅሶ በቢሊዮን ዶላሮች እንዲከፍሉ መደረጋቸውን ገልጿል።

በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዢያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ላይ በደረሱ አደጋዎች ሕይወታቸውን ያጡ 15 ቤተሰቦች ቦይንግ ጥፋተኝነቱን አምኖ የወንጀል ክሱ እንዲቀርለት ከአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤት ጋር የደረሰው ስምምነት ውድቅ እንዲደረግ የፌደራሉ ፍርድ ቤትን መጠየቃቸው ይታወሳል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቦይንግ ኩባንያ ከዚህ በፊት የቀረበበትን ክስም ለአብነት በማንሳት፤መንግሥታዊ ውሎችን ለማግኘት ከአሜሪካ መንግሥት ሹማምንት ሚስጥራዊ መረጃ ወስዷል በሚል ለቀረበበት ክስ በፍትሃብሔር ክርክር 650 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም 50 ሚሊዮን ደግሞ ለወንጀል ድርጊት ከፍሏል ብሏል።

የ346 ሰዎች ሕይወት በአሳዛኝ ሁኔታ ለጠፋበት አደጋ የቦይንግ እርምጃ የክብደቱን ያህል የገንዘብ ቅጣቱም ከበድ ማለቱ አስፈላጊ እንደሆነ ጠበቆች ተናግረዋል።

“ከዚህ ቀደም የኮርፖሬት ድርጅቶች የጥፋታቸውን ክብደት ለማሳየት እና ለሌሎችም ለማስተማር የወንጀል ማጭበርበር ክሶች ቅጣት በቢሊዮን ዶላር ነው። ለቦይንግ የቀረበው ምክረ ሀሳብ ከዚህ ጋር ሲነጻጸር የገንዘብ መጠኑ ሽራፊ፣ ኩባንያው ለፈጸመው ከባድ ጥፋት ተጠያቂነትን የሚያሳንስ እና በፍትሕ ስርዓቱ የሕዝብን አመኔታ የሚያሳጣ ነው” ብለዋል።

ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ አውሮፕላን ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ወደ ናይሮቢ ሲጓዝ በተነሳ በአጭር ጊዜ ተከስክሶ የ149 ሰዎች አልፏል።

ዘጠኙ ሟቾች ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ የ35 አገራት ዜግነት ያላቸው ናቸው።

ከዚህ አደጋ አምስት ወር አስቀድሞ በተመሳሳይ አውሮፕላን ኢንዶኔዢያ አቅራቢያ በደረሰ አደጋ 189 ሰዎች ሕይወት አልፏል።

ሪቢክ የተባለው የጠበቆች ድርጅት እንዳለው የአሜሪካ ፍትሕ መስሪያ ቤት ምክረ ሀሳብ ከደረሰው ጉዳት ጋር የሚቀራረብ አይደለም።

ምክረ ሀሳቡ የሕዝብን ደኅንነት እና አመኔታ አደጋ ላይ በሚጥል የወንጀል እንቅስቃሴ የተሳተፉ ግዙፍ ኮርፖሬት ድርጅቶች የሚገባቸውን ቅጣት እንዳያገኙ አደገኛ ተምሳሌት ይሆናል ብሏል።

“የቦይንግ ድርጊቶች የተለመዱ ስህተቶች አይደሉም። ከሰው ሕይወት ይልቅ ትርፍን ያስቀደሙ ሆን ተብለው እና በማታለል የተፈጸሙ ናቸው። እንደዚህ አይነት ጥፋቶች የወንጀሉን ክብደት በግልጽ በሚያሳይ መክሉ ከፍተኛ ተጠያቂነት እና ቅጣት ያስፈልጋቸዋል” ሲሉ ማንኤል ቫን ሪቢክ ተናግረዋል።