ቦይንግ በኢትዮጵያው አየር መንገድ አደጋ በወንጀል ሊከሰስ እንደሚችል አሜሪካ አስታወቀች

በአደጋው የሞቱ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, The Washington Post / Getty Images

ለ346 ሰዎች ህይወት እልቂት ለሆነው የኢትዮጵያው አየር መንገድ እና የኢንዶኔዥያው የ737 ማክስ 9 አውሮፕላን አደጋዎች ቦይንግን በወንጀል ለመክሰስ እያጤነው እንደሆነ የአሜሪካ የፍትህ መስሪያ ቤት አስታወቀ።

ቦይንግ የሚያመርታቸውን አውሮፕላን ምርቶች ደኅንነት እና ጥራት ለማስጠበቅ ከሦስት ዓመት በፊት ከአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ጋር የገባውን የቁጥጥር መርሃ ግብር ስምምነት መጣሱንም መስሪያ ቤቱ ገልጿል።

ቦይንግ የቀረበበትን ስምምነት ጥሷል ክስ አስተባብሏል።

በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው አሰቃቂ በተባለው የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አደጋዎች በኢትዮጵያው 157 እንዲሁም በኢንዶኔዥያው አየር መንገድ 189 ሰዎች ህይወት ተቀጥፏል።

የአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤት በአውሮፕላንን አምራቹ ላይ ካደረገው የረዥም ጊዜ ምርመራ በኋላ ቦይንግ ለ737 ማክስ አውሮፕላኑ ፍቃድ ለማግኘት ሲል ሆን ብሎ የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር ተቆጣጣሪዎችን እንዳሳሳተ ደርሸበታለሁ በሚል “አሜሪካን ለማጭበርበር በማሴር” በሚል ከሦስት ዓመት በፊት ክስ መስርቶበት ነበር።

ቦይንግ ቺካጎ በነበረው የፍርድ ሂደት በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ መንገደኞች ቤተሰቦች ካሳ ለመክፈል ተስማምቶ በምላሹም የአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ለአውሮፕላን አምራቹ ከ737 ማክስ ዲዛይን ጉድለት ጋር በተያያዘ በማጭበርበር ሴራ በወንጀል እንዳይከሰስ ከለላ ሰጥቶት ነበር።

የአውሮፕላን አምራቹ በአደጋው ለሞቱት ሰዎች ኃላፊነቱን እንደሚወስድ እና ተጠያቂነቱን ተቀብሎ ለአሜሪካ መንግሥት፣ አደጋ ለደረሰባቸው አየር መንገዶች እና ለተጎጂዎች የሚሆን 2.5 ቢሊዮን ዶላር የቅጣት ካሳ ለመክፈል ተስማምቷል።

ቦይንግ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ለመክፈል ከአሜሪካ ዐቃቢያነ ሕጎች ጋር የደረሰው ስምምነት ኩባንያው በአደጋው ዙሪያ የሚካሄደው የወንጀል ምርመራ እንዲቀር የተስማማበት ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በወቅቱም የፌደራል ዐቃቢያነ ሕጎች ቦይንግ ለመጪው ሦስት ዓመታት ያህል ለስምምነቱ ተገዢ ከሆነ የወንጀል ክሱን ለመተው ተስማምተው ነበር።

ሆኖም ስምምነቱ ጊዜው ከማለፉ በፊት በአላስካው አየር መንገድ የቦይንግ ማክስ 9 በር በአየር ላይ ተገንጥሎ መውደቁን ተከትሎ የምርቶቹን ደህንንት እና ጥራት ለማስጠበቅ የገባውን የቁጥጥር መርሃ ግብር ስምምነቱን መጣሱን ማሳያ እንደሆነም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመላክቷል።

በያዝነው ዓመት ታህሳስ ወር ከኦሬገን ግዛት ፖርትላንድ ከተማ ተነስቶ ወደ ካሊፎርኒያ ሲበር የነበረው አዲስ ሞዴል የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ከተነሳ በኋላ የኋላ በሩ በበረራ ላይ እያለ ተገንጥሎ መውደቁን ተከትሎ በአውሮፕላኑ ደኅነት ላይ ከፍተኛ ጥያቄዎች እየተነሱበት ይገኛል።

የአውሮፕላን አምራቹ ለቀረበበት ክስ ምላሽ ለመስጠት እስከ ሰኔ 6 ጊዜ እንዳለው የገለጸው የፍትህ ሚኒስቴር በቀጣይ ምን መደረግ እንዳለበት ለመወሰንም የቦይንግ ምላሽ ግምት ውስጥ ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ 737 ማክስ 9 አውሮፕላን ከአምስት ዓመት በፊት ሕይወታቸውን ያጡ መንገደኞች ቤተሰቦች ለአደጋው መንስዔ የሆነው የአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ላይ የወንጀል ክስ እንዲመሠረት የአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤትን መጠየቃቸው ይታወሳል።

የመንገደኞቹ ቤተሰቦች በዋሽንግተን ከአሜሪካ የፍትህ ባለሥልጣናት ጋር ሚያዝያ አጋማሽ ላይ በተነጋገሩበት ወቅት የአሜሪካው ኩባንያ ቦይንግ ለፍርድ እንዲቀርብ ጠይቀዋል።

“ይህ የመጀመሪያ አዎንታዊ እርምጃ ነው። ቤተሰቦች ለረጅም ጊዜ ሲጠብቁት የቆየ ጉዳይ ነው። ነገር ግን ቦይንግን ተጠያቂ ለማድረግ ከፍትህ ሚኒስቴር ተጨማሪ እርምጃ ማየት አለብን" ሲሉ ሲሉ የአደጋው ተጎጂ ቤተሰቦች ጠበቃ ፖል ጂ ካሴል በሰጡት መግለጫው ተናግረዋል።

መጋቢት 01/2011 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ናይሮቢ የሚያደርገውን ጉዞ ከጀመረ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ነበር አሰቃቂው አደጋ የደረሰው።

በዚህ አደጋ ከ35 የተለያዩ አገራት የተውጣጡ የ157 ሰዎችን ሕይወት ተቀጥፏል።

በ737 ማክስ አውሮፕላን ላይ የደረሱት የኢትዮጵያው አየር መንገድ እና የኢንዶኔዢያ ላየን ኤር አውሮፕላን አደጋዎችን ተከትሎ ቦይንግ የአብራሪዎቹን አቅም ጥያቄ ውስጥ በማስገባት እና ጥፋቱን ወደ ሌሎች በማዛወር ትችት ሲቀርብበት ነበር።

ከአምስት ዓመት ገደማ በፊት ለደረሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-ማክስ 8 አደጋ ምክንያት የቦይንግ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት (ኤምካስ) ችግር መሆኑን የኢትዮጵያ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።

በሪፖርቱም መሠረት ለአውሮፕላኑ አደጋ ምክንያት ቦይንግ የገጠመው ኤምካስ (ማኑቨሪንግ ካራክተርስቲክስ ኦግመንቴሽን ሲስተም) የተሰኘው የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ችግር እንደሆነም ገልጿል።

ቦይንግ 737- ማክስ- 8 ለሁለት የአውሮፕላን አደጋዎች እና ለበርካታ ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት መሆኑን ተከትሎ በዓለም ላይ ያሉ አውሮፕላኖቹ እንዳይበሩ እግድ ተጥሎበት ነበር።

በቦይንግ አስፈላጊው ማስተካካያ ተደርጎ ተገቢው ምርመራ እና ሙከራ ከተደረገ በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሁለት ዓመት በፊት አውሮፕላኑን ወደ አገልግሎት መመለሱን መግለጹ አይዘነጋም።