የባንግላዴሽ ፖሊስ የተቃውሞ አመራሮችን ከሆስፒታል ወስዶ አሰረ

የፎቶው ባለመብት, BBC Bangla
በቅርቡ በባንግላዴሽ የተካሄዱ የአደባባይ ተቃውሞዎችን የመሩ ሶስት ተማሪዎች ሲታከሙበት ከነበረው ሆስፒታል በፖሊስ ወጥተው እንዲታሰሩ ተደረገ።
ናሂድ ኢስላም፣ አሲፍ ማህሙ እና አቡ ባከር ማጁምደር የተባሉት ተማሪዎች በመዲናዋ ዳካ ከሚገኝ ሆስፒታል በግዳጅ መወሰዳቸውን የሆስፒታሉ ሰራተኞች አርብ ዕለት ተናግረዋል።
ተማሪዎቹ በህክምና ላይ እያሉ ሲቪል የለበሱ ፖሊሶች መጥተው ከሆስፒታሉ እንዲወጡ እንዳስገደዷቸው ሰራተኞቹ ገልጸዋል።
የተቃውሞ አመራሮቹ ተማሪዎች በፖሊስ በተፈጸመባቸው ድብደባ በደረሰባቸው ጉዳት በህክምና ላይ ነበሩ ተብሏል።
ተማሪዎቹ ሲታከሙ የነበሩበት ጎኖሻስታሻያ ሆስፒታል ተቆጣጣሪ አንዋራ ቤጉም ሎኪ ህክምናቸውን ሳይጨርሱ እንዲወጡ ባይፈልጉም በፖሊስ ግፊት እንደተደረገባቸው ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
የአንደኛው ተማሪ ናሂድ ታላቅ እህት ስድስት ሲቪል የለበሱ መርማሪዎች ሶስቱንም እንደወሰዷቸው ከሆስፒታል ለኤኤፍፒ ገልጻለች።
ናሂድ ለህይወቱ እንደሚሰጋ ባለፈው ሳምንት ለጋዜጠኞች ተናግሮ ነበር።
ባለፈው ሳምንት እንዲሁ መርማሪ ነን ባሉ ግለሰቦች ከጓደኛው ቤት ታፍኖ ተወስዶ አካላዊ እንግልት እና የአዕምሮ ስቃይ ደርሶበታል።
በስፍራው ራሱን የሳተው ናሂድ ሲነቃም በሁለቱም ትከሻዎቹ በኩል እና በግራ እግሩ ደም እየፈሰሰው ስለነበር ወደ ሆስፒታል ማቅናቱ ተገልጿል።
ተማሪው ላቀረበው ክስ ምላሽ የሰጡት የማስታወቂያ ሚኒስትሩ መሃመድ አሊ አራፋት ክስተቱ እንደሚጣራ ለቢቢሲ ገልጸው ነገር ግን የፖሊስን ስም ለማጥፋት የሚሰራ “አሻጥር” ሳይሆን አይቀርም ብለዋል።
በአገሪቱ ባለፈው ሳምንት በነበረው የአደባባይ ተቃውሞ በተፈጠረ ሁከት ፖሊስ ከ4 ሺህ በላይ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሏል።
ሶስቱም ተማሪዎች በአገሪቱ መድልዎን የተከተለ ነው የተባለውን የሲቪል ሰርቪስ ቅጥር ደንቦች የሚቃወሙ የአደባባይ ሰልፎችን የማስተባበር ኃላፊነት ያለው ቡድን አባላት ናቸው።
በባለፈው ሳምንት የነበረው ተቃውሞ ደም መፋሰስ በማስከተሉ ምክንያት የተማሪዎቹ ቡድን ተጨማሪ የአደባባይ ሰልፎች እንዳይካሄድ አግዷል።
አገር አቀፍ በነበረው የአደባባይ ተቃውሞ በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እና በፖሊሶች መካከል በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ 150 ሰዎች ተገድለዋል።
ከነዚህ ግድያዎች ጋር ተያይዞ የጸጥታ ኃይሎች ያለ አግባብ ኃይል ተጠቅመዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ተቃዋሚዎች የመንግሥት ስራዎች ላይ የተቀመጠው ኮታ እንዲነሳ ሲጠይቁ ነበር።
ባንግላዴሽ ከፓኪስታን ነጻ በወጣችበት በአውሮፓውያኑ 1971 ጦርነት ለተሳተፉ የቤተሰብ አባላት 30 በመቶ የሚሆነውን ከፍተኛ ክፍያ የሚከፍለው የመንግሥት ስራ ኮታ አስቀምጣለች።












