አዲሱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የሥልጣን ዘመን ስንት ነው? ሁለት ወይስ አምስት ዓመት?

የፎቶው ባለመብት, Benishangul Gumuz Comm.
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ በኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ዘመነ መንግሥት የተመረጠውን ምክር ቤቱን አሰናብቶ ባለፈው ሳምንት አዲስ መንግሥት መሥርቷል። 2007 ዓ.ም. በተደረገው ጠቅላላ ምርጫ የተመረጡት የምክር ቤት አባላት ከዘጠኝ ዓመት አገልግሎት በኋላ የተሰናበቱት ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም. ነው።
ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሐምሌ 23፤ መሥራች ጉባኤውን ያደረገው አዲሱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት፤ ላለፉት ስምንት ዓመታት ክልሉን በርዕሰ መስተዳደርነት ሲመሩ የነበሩትን አቶ አሻድሊ ሐሰንን በድጋሚ መርጧል። ርዕሰ መስተዳድሩም፤ ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ያካተተውን ካቢኔያቸውን ለምክር ቤቱ አቅርበው አጸድቀዋል።
አዲሱ ምክር ቤትም፤ በዕለቱ በተመረጡት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ አስካል አልቦሮ እየተመራ ሥራውን ጀምሯል። በዚህም ላለፉት ዓመታት ደጋግሞ ሲሰማ የቆየው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል “አዲስ መንግስት የሚመሠረተው መቼ ነው?” የሚል ጥያቄ አሁን ምላሽ አግኝቷል።
የፌደራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም ሌሎች የክልል እና የከተማ መስተዳደር ምክር ቤቶች አራተኛ የሥራ ዘመናቸውን ለመጀመር ሲቃረቡ ምሥረታውን ያካሄደው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት “ስንት ዓመት ያገለግላል?” የሚለው ግን ግልፅ አልሆነም።
ባለፈው ሳምንት በተደረገው የምክር ቤቱ ምሥረታ ጉባኤ ላይም ይህ ጉዳይ በግልጽ አለመነሳቱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው አምስት የገዢው ብልጽግና እና የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ የሆኑ የምክር ቤት አባላት ተናግረዋል።
ይሁንና አብዛኞቹ የክልሉ መንግሥት አካላት ምክር ቤቱ የሥራ ዘመኑ የሚቆየው “ለሁለት ዓመት ብቻ ነው” የሚለው ሀሳብ ያስማማቸው ይመስላል። ተቃዋሚውን የፖለቲካ ፓርቲ የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን (ጉሕዴን) ወክለው ምክር ቤቱን የተቀላቀሉ አባላትም ተመሳሳይ ሀሳብ አንስተዋል።
በምክር ቤቱ ውስጥ አራት ወንበሮችን ያገኘው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) በአንጻሩ የምክር ቤቱ የሥልጣን ዘመን ጉዳይ “ሕገ መንግሥታዊ እና አከራካሪ” እንደሆነ ገልጿል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት የሕግ እና የምርጫ ባለሙያዎች በአንጻሩ ምክር ቤቱ አምስት ዓመታት የሥራ ዘመን እንዳለው ይከራከራሉ።
ሌላ የሕገ መንግሥት ባለሙያ ደግሞ ጉዳዩ የሚፈታው ክልሉ “የሕገ መንግሥት ተርጓሚ ኮሚሽን” ውሳኔ ሲሰጥበት ነው በሚል የተለየ ሀሳብ አንስተዋል
ዘጠኝ ዓመት በአንድ ምክር ቤት
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እስካለፈው ሳምንት ድረስ ምክር ቤቱን ሳይቀይር የቆየው መንግሥት መመሥረት የሚያስችል የምክር ቤት ወንበሮች በምርጫ ባለመያዛቸው ነው። የክልሉ ምክር ቤት ካሉት 99 ወንበሮች ውስጥ በ2013 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ተወካይ የተገኘባቸው 28 መቀመጫዎች ብቻ ነበሩ።
በወቅቱ በመተከል እና ካማሺ ዞኖች የፀጥታ ችግር የነበረ መሆኑ በክልሉ ሙሉ በሙሉ ምርጫ ላለመደረጉ ምክንያት ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጭራሹኑ ምርጫ ባልተደረገባቸው 65 የምክር ቤት ወንበሮች ላይ እና ድምጽ የመስጠት ሂደቱ እንዲደገም በተወሰነባቸው ስድስት መቀመጫዎች ላይ ምርጫ ለማድረግ ተደጋጋሚ ዕቅዶችን እና ሁለት የጊዜ ሰሌዳዎችን ይፋ አድርጎ የነበረ ቢሆንም፣ እስካለፈው ሰኔ ድረስ ውጥኑ ሳይሳካ ቆይቷል።
ሰኔ 16/2016 ዓ.ም. የተደረገው ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር፣ ሶማሌ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎችን ያካተተ ነው። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተደረገው ምርጫ ለፌደራሉ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልሉ ምክር ቤት አባላት የሚሆኑ ተወካዮችን ተመርጠዋል።
ለሁለቱም ምክር ቤቶች በተደረጉት ምርጫዎች ገዢው ብልጽግና ፓርቲ አብላጫውን ውጤት ማግኘቱን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። ድምጽ ከተሰጠባቸው ስድስት የሕዝብ ተወካዮች ምክት ቤት ወንበሮች ውስጥ አራቱን ያሸነፈው ብልጽግና ሲሆን፣ በክልሉ የሚንቀሳቀሱት ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) እና የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) ቀሪዎቹን ሁለት መቀመጫዎች ተካፍለዋል።
ምርጫ ከተደረገባቸው 71 የክልሉ ምክር ቤት ወንበሮች ውስጥም በ60ው ላይ አብላጫውን ድምጽ ያገኘው ብልጽግና ፓርቲ፤ በ2013 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ ካሸነፋቸው ወንበሮች ጋር በድምሩ 88 የምክር ቤቱን መቀመጫዎች አግኝቷል። ጉሕዴን፤ ስምንት የምክር ቤቱን ወንበሮችን ያገኘ ሲሆን፣ ቦዴፓ ደግሞ ሦስት ተወካዮቹን ወደ ምክር ቤቱ ማስገባት ችሏል።

የፎቶው ባለመብት, NEBE
አዲሱ ምክር ቤት
በ2010 ዓ.ም. የተሻሻለው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የአሠራር እና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ፤ የክልሉ ምክር ቤት የሥራ ዘመን አምስት ዓመት እንደሆነ አስፍሯል። በ1995 ዓ.ም. የተሻሻለው የክልሉ ሕገ መንግሥትም በተመሳሳይ የክልሉ ምክር ቤት አባላት የሚመረጡት ለአምስት ዓመታት እንደሆነ ይደነግጋል።
ባለፈው ሰኔ ወር የተመረጡት እና ከሦስት ዓመት በፊት ያሸነፉት የምክር ቤት አባላት ባለፈው ሳምንት ባደረጉት መሥራች ጉባኤ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ አዲሱን ምክር ቤት በይፋ ሥራ አስጀምረዋል።
በ2013 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ አሸናፊ የሆኑ ተመራጮች ከምርጫ ቦርድ ያገኙትን “የተመራጭነት የምስክር ወረቀት” ይዘው የምክር ቤቱን መሟላት ሲጠባበቁ እንደነበር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የቀድሞ አፈ ጉባኤ ዶ/ር ተመስገን ዲሳሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የቀድሞው አፈጉባኤ እንደሚያስረዱት፤ 28ቱ ተመራጮች ላለፉት ሦስት ዓመታት የምክር ቤት አባልነት ሥራቸውን ያልጀመሩት ምክር ቤቱ ያሉት “99 ወንበሮች ሳይሟሉ [ወደ ሥራ] መግባት ስለማይችሉ” ነው።
እነዚህ የምክር ቤት አባላት ምንም እንኳን ከተመረጡ በኋላ ያለ ሥራ ቢቆዩም የምክር ቤት አባልነት ዘመናቸው “ምርጫ ቦርድ ሰርቲፊኬቱን ከሰጠበት ቀን ጀምሮ” እንደሆነ አሁን የክልሉን ትምህርት ቢሮ የሚመሩት የቀድሞው አፈ ጉባኤ ይናገራሉ።
የእነዚህን ተወካዮች የምርጫ ጊዜ እንደ መነሻ የሚቆጥሩት ዶ/ር ተመስገን፤ ከዚህ በመነሳት አዲሱ ምክር ቤት የሚቆየው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በአገር አቀፍ ደረጃ እስከሚካሄድበት 2018 ዓ.ም. ድረስ እንደሆነ ይገልጻሉ።
ዶ/ር ተመስገን፤ “[ሌሎች የአገሪቱ ምክር ቤቶች] ሦስተኛ ዓመት ጨርሰው አራተኛ ላይ ናቸው። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል [ምክር ቤት] ሁለት ዓመት ነው የሚቀረው። [ክልሉ] በ2018 ከሚደረገው የአገር አቀፍ ምርጫ ጋር እንደገና ድምጽ ይሰጣል” ሲሉ ሀሳባቸውን ያብራራሉ። ይህ የሚደረገውም የክልሉ ምክር ቤት የሥራ ዘመን ከአገሪቱ የምርጫ ጊዜ ጋር “ተመሳሳይ ሆኖ እንዲሄድ” ለማድረግ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ቢቢሲ፤ የምክር ቤቱን የሥራ ዘመን በተመለከተ ከምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወ/ሮ አስካል እና ምክትላቸው አቶ መለሰ ኪዊ ምላሽ ለማድረግ ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም። የክልሉ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ በበኩላቸው ወደ ኃላፊነት የመጡት በቅርቡ መሆኑን በመጥቀስ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
በቀድሞው አፈ ጉባኤ የቀረበው የሁለት ዓመት የሥራ ዘመን ጉዳይ ግን ባለፈው ሳምንት ሥራ በጀመሩት የክልሉ ምክር ቤት አባላት ዘንድም የሚነሳ ነው። ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት የብልጽግና ፓርቲ ተወካይ የምክር ቤት አባላት በክልሉ መንግሥት ለመመሥረት የሚደረግ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ በአገር አቀፍ ከሚደረገው ጋር ተመሳሳይ መሆን እንዳለበት ይናገራሉ።
2013 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ ብልጽግና ፓርቲን ወክለው በማኦ-ኮሞ ልዩ ምርጫ ክልል የተመረጡት አቶ ዚያድ አብዱላሂ፤ ጉዳዩ “ግራ አጋቢ” አይደለም ባይ ናቸው። እንደሳቸው ገለጻ፤ የምርጫው ዝግጅት ሲደረግ ጀምሮ “ከሁለት ዓመት በኋላ ምርጫ ሊካሄድ እንደሚችል” ንግግር ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Benishangul Gumuz Comm.
የክልሉን ገንዘብ ቢሮ የሚመሩት እኚህ የምክር ቤት አባል፤ “[የቤኒሻንጉል ምክር ቤት ምርጫ] ዘግይቶ ስለተካሄደ ቀጣይ 2018 ዓ.ም. በአገር ደረጃ የሚካሄድ ከሆነ በእኛም [ክልል] ይካሄዳል። የተለየ ነገር የለውም፤ [በይፋ] ሊገለጽም አይችልም። ምክንያቱም ክልሉ የራሱ ምርጫ ሕግ የለውም” ይላሉ።
በካማሺ ምርጫ ክልል የብልጽግና ተመራጩ አቶ ገርቢ ሎላሳም ይህንን ሀሳብ ይደግፋሉ። የክልሉን ውሃ ሀብት ቢሮ በምክትል ኃላፊነት የሚመሩት እኚህ የምክር ቤት አባል፣ በሰኔ አጋማሽ የተደረገውን ምርጫ የሚቆጥሩት “እንደ ማሟያ” መሆኑን ይናገራሉ።
“ሕገ መንግሥቱ የአንድ የምክር ቤት አባል የቆይታ ጊዜ አምስት ዓመት ነው የሚለው። ከአምስት ዓመት በኋላ ምክር ቤቱ በአዲስ መልክ ለምርጫ ይዘጋጃል ነው የሚለው። በክልላችን ደግሞ በ2014 ላይ ምርጫ ተካሂዷል። ነገር ግን በከፊል ምርጫ ስላልተካሄደ ማሟያ ምርጫ ነው የተካሄደው” ሲሉ ሀሳባቸውን አቅርበዋል።
ባለፈው ሰኔ የተካሄደውን ምርጫ እንደ “ማሟያ” የሚመለከቱት ብልጽግና ፓርቲን የወከሉት የምክር ቤት አባላት ብቻ አይደሉም። ከዛይ (ያሶ) ምርጫ ክልል ተቃዋሚውን ጉሕዴንን ወክለው የምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ለሜሳ ኔኖ፤ “ማሟያ ምርጫ ስለሆነ የሚቆጠረው እንደ 2013 ምርጫ ነው” ሲሉ የተደረገውም የመንግሥት ምሥረታ ለሁለት ዓመት የሚቆይ ነው የሚል ሀሳባቸውን ገልጸዋል።
በምክር ቤቱ የፍትህ፣ ሠላም እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የጉህዴን ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ግራኝ ጉደታም ይህንን ሀሳብ ተጋርተው፤ መጪዎቹ ሁለት ዓመታት ፓርቲያቸው “ለቀጣይ ምርጫ የሚዘጋጅበት” እንደሆነ አስረድተዋል።
በምክር ቤቱ ውስጥ ሦስት ወንበሮችን ያሸፈነው ሌላኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ቦሮ በአንጻሩ የምክር ቤቱን የሥራ ዘመን በተመለከተ እስካሁን ድረስ አቋም አለመያዙን አስታውቋል። በመተከል ዞን ቡለን ምርጫ ክልል ተመርጠው ምክር ቤት የገቡት የተቃዋሚው ቦሮ ፓርቲ አመራር አቶ ዮሐንስ ተሰማ፤ የምክር ቤቱን የሥራ ዘመንን በተመለከተ ሁለት ክርክሮች እንዳሉ ያስረዳሉ።
በአብዛኞቹ የምክር ቤቱ አባላት ዘንድ ያለው አረዳድ “ምክር ቤቱ የሚቆየው ሁለት ዓመት ነው” የሚል እንደሆነ ይናገራሉ። በአንጻሩ ሕገ መንግሥቱን እና የምክር ቤቱን መተዳደሪያ ደንብ “ቀጥታ በመተርጎም የተመረጥነው ለአምስት ዓመት ነው” የሚል መከራከሪያ ሊነሳ እንደሚችል የምክር ቤት አባሉ ይጠቅሳሉ።
አቶ ዮሐንስ፤ “ጉዳዩ ሕገ መንግሥታዊ ነው፤ አከራካሪ ነው። ‘ለአምስት ዓመት ነው የምንቆየው ወይስ ለሁለት ዓመት ነው?’ የሚለው ጥልቅ ውይይት ይፈልጋል። ሕገ መንግሥቱንም ተያያዥ ሕጎችንም ማየት ይፈልጋል። ጊዜ ተወስዶበት የሚመከርበት ነው” ሲሉ ፓርቲያቸው በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ አቋም እንደሚይዝ አስረድተዋል።
የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ሁለት ወይስ አምስት ዓመት?
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት የሕግ እና የምርጫ ባለሙያዎች፤ አዲስ የተመሠረተው ምክር ቤት የሥራ ዘመን ሁለት ዓመት ነው የሚለውን መከራከሪያ አይቀበሉትም። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ሕገ መንግሥት መነሻ የሚያደርጉት ባለሙያዎቹ፤ የክልሉ ምክር ቤት አባላት የሚመረጡት ለአምስት ዓመታት መሆኑን ያስረዳሉ።
የሕግ ባለሙያው አቶ አንዱዓለም በዕውቀቱ፤ ምርጫ የሚደረገው “መንግሥት ሆኖ የፖለቲካ ሥልጣኑን የሚይዘው አካል ለመምረጥ” እንደሆነ ያስረዳሉ። ሥልጣን የሚይዘው አካል የሚታወቀው በአንድ ምክር ቤት ውስጥ ካሉት መቀመጫዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በምርጫ አሸናፊ ሲገኝባቸው እንደሆነ የሚገልጹት አቶ አንዱዓለም፤ በዚህ አካሄድ መንግሥት የመሠረተ የፖለቲካ ስብስብም አምስት ዓመት በሥልጣን ላይ እንደሚቆይ በክልሉ ሕገ መንግሥት ላይ መስፈሩን ይጠቅሳሉ።
“ስለዚህ እኔ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን [ጉዳይ] የምገመግመው፤ 99 ወንበር ለሚይዝ ምክር ቤት 28 ወንበር ላይ ብቻ የተደረገ ምርጫ የተሟላ ምርጫ ነው ተብሎ አይታሰብም። ስለዚህ ይበልጥ ቅቡልነት ያለው እና መንግሥት ለመመሥረት ምርጫ ተካሂዷል ተብሎ መታሰብ ያለበት አሁን ላይ የተደረገው ምርጫ ነው ማለት ነው። አሁን ላይ የተደረገው ምርጫ ለአምስት ዓመት ሥልጣን የሚያስይዝ ነው” ሲሉ ምልከታቸውን አጋርተዋል።
በዚህ ሀሳብ የሚስማሙ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሕግ እና ምርጫ ባለሙያ፤ አዲሱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የሥልጣን ዘመኑ አምስት ዓመት መሆኑ “ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ አይደለም” ሲሉ ሀሳቡን አጠናክረዋል።
“ስለዚህ የሚቀጥለው አገር አቀፍ ምርጫ 2018 ዓ.ም. ሲከናወን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ ለክልል ምክር ቤት ምርጫ አያደርግም” የሚሉት የሕግ እና የምርጫ ባለሙያው፤ የምክር ቤቱ አባላትም “አምስት ዓመት እስኪሞላቸው” በውክልናው ላይ የመቆየት መብት እንዳላቸው ይገልጻሉ።
ይህ የአምስት ዓመት የውክልና ዘመን በ2013 ዓ.ም. ተመርጠው ባለፈው ሳምንት ሥራ በጀመሩት የምክር ቤት አባላት ላይም እንደሚሠራ ባለሙያው ይከራከራሉ። ለዚህም በምክንያትነት የሚያቀርቡት የምክር ቤት አባላቱ ከተመረጡ ሦስት ዓመት ቢሆናቸውም “የምክር ቤቱ አባል ሆነው የሕዝብ ውክልናቸውን መተግበር የጀመሩት አሁን” መሆኑን ነው።
“የምክር ቤቱ አባል እና የሕዝብ ውክልና መተግበር የጀመሩበትን ጊዜ ነው የምንቆጥረው እንጂ ሰርቲፊኬቱን ያገኙበትን ጊዜ አይደለም” የሚሉት ባለሙያው፤ አስቀድመው ሥራ ጀምረው የነበረ ቢሆን ደግሞ አምስት ዓመት ሲሞላቸው በማሟያ ምርጫ ሊተኩ እንደሚገባ አክለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Benishangul Gumuz Comm.
በ1995 ዓ.ም. የተሻሻለው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕገ መንግሥት የክልሉ ምክር ቤት አባላት በየአምስት ዓመቱ በሚደረግ “ነፃ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ በሆነ እና ድምጽ በምሥጢር በሚሰጥበት ሥርዓት” እንደሚመረጡ ይገልጻል።
ይህ ዓይነቱ ምርጫ የሚደረገው ነባሩ ምክር ቤት “የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት” እንደሆነ ያሰፈረው ሕገ መንግሥቱ፤ “የቀድሞው ምክር ቤት የሥራ ዘመን በተጠናቀቀ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አዲሱ ምክር ቤት ሥራውን ይጀምራል” ሲል የሥራ ዘመኑ የሚጀመርበትንም ጊዜ ደንግጓል።
በክልሉ ሕገ መንግሥት ላይ የሰፈረው ይህ አሰራር ባለፉት ዓመታት ሳይተገበር እንደቆየ የሚያነሱት በጅማ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ቤት የሕገ መንግሥት እና መንግሥታዊ ሕጎች መምህር አቶ አባይ አዲስ፤ በ2007 ዓ.ም. የተመረጠው የክልሉ ምክር ቤት የሥልጣን ዘመን ከተጠናቀቀ በኋላ የመተግበር የነበረበት “ትልቅ ጉዳይ እንደተዘለለ” ያስረዳሉ።
የሕገ መንግሥት መምህሩ፤ በፀጥታ ችግር ምክንያት በ71 መቀመጫዎች ላይ ምርጫ ማድረግ አይቻልም በተባለበት ወቅት ጉዳዩ የሕገ መንግሥት ትርጉም የመስጠት ሥልጣን ወዳለው የክልሉ “የሕገ መንግሥት ትርጓሚ ኮሚሽን” መቅረብ እንደነበረበት ያነሳሉ።
የኮቪድ 19 ወረርሽን መከሰትን ተከትከሎ በ2012 ዓ.ም. መደረግ የነበረበት ምርጫ ሲራዘም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሥራቸውን እንዲቀጥሉ የተሰጠውን የሕገ መንግሥት ትርጉም የሚጠቅሱት አቶ አዲስ፤ “[በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም] በ2007 ዓ.ም. የተመረጡት የምክር ቤት አባላት ‘ሥራቸውን ይቀጥላሉ’ የሚል የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገው ነበር” ይላሉ።
አሁን የተመሠረተውን የክልሉ ምክር ቤት የሥልጣን ዘመንን በተመለከተም ተመሳሳይ መፍትሄ እንደሚሻ ይጠቅሳሉ። “ሕገ መንግሥቱ ይህንን ጉዳይ በቀጥታ አይፈታውም። [በ2013 ዓ.ም. የተመረጡት] 28ቱ የምክር ቤት አባላት ሥራ ላይ መሆን ነበረባቸው። በእኔ ዕይታ ለ71ዱ የተደረገው ምርጫን ልናየው የምንችለው እንደ ማሟያ ምርጫ ነው” ሲሉ ጉዳዩ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደሚያስፈልገው ያስረዳሉ።
የክልሉ ሕገ መንግሥት ተርጓሚ ኮሚሽን “አሁን እና 2013 ላይ የተመረጡ የምክር ቤት አባላት የሥራ ዘመናቸው ምን ያህል ነው የሚሆነው?” የሚለው ጥያቄ ላይ የሚሰጠው ውሳኔ ለጉዳዩ እልባት እንደሚሆን የሕገ መንግሥት መምህሩ ገልጸዋል።
የክልሉ ምክር ቤት ምርጫ ለብቻው ሊደረግ ይችላል?
ባለፈው ሳምንት የተመሠረተው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ለአምስት ዓመታት በሥራ ላይ ከሚቆይ ከሆነ ከጠቅላላ ምርጫው ጋር የሚኖረው የጊዜ ሰሌዳ ይዛነፋል። ይህም ለክልሉ ምክር ቤት የሚደረገው ምርጫ በተለየ የጊዜ ሰሌዳ እንዲካሄድ ያስገድዳል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚደረግ ጠቅላላ ምርጫ በተለየ የጊዜ ሰሌዳ ድምጽ መስጠት እና ምክር ቤትን መመሥረት ለኢትዮጵያ አዲስ ጉዳይ አይደለም። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ከአገር አቀፉ ምርጫ በተለየ የጊዜ ሰሌዳ ውጪ ሁለት ጊዜ ምርጫ አደርጎ ያውቃል።
በ1997 ዓ.ም. በተደረገው ሦስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የአዲስ አበባ ምክር ቤትን ያሸነፈው “ቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ” አስተዳደሩን ለመረከብ ፈቃደኛ አልሆነም መባሉን ተከትሎ አዲስ አበባ ከተማ በባለ አደራ አስተዳደር ተመርታለች። ባለ አደራ አስተዳደሩ ሥልጣኑን ያስረከበው በ2000 ዓ.ም. ምርጫ ከተደረገ በኋላ ነበር።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤትን ለመመሥረት ቀጣዩ ምርጫ የተደረገው ከአምስት ዓመት በኋላ በ2005 ዓ.ም. ነው። ከ1997 ዓ.ም. በኋላ በተደረጉት የ2002 እና 2007 ምርጫዎች ላይ በአዲስ አበባ ድምጽ የተሰጠው ወደ ፌደራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚገቡ የከተማዋ ተወካዮችን ለመምረጥ ነበር።
የከተማዋ ምክር ቤት ምርጫ ከአገር አቀፉ የጊዜ ሰሌዳ ጋር መልሶ የተጣጣመው በ2010 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር ተሻሽሎ ምርጫው ከተራዘመ በኋላ ነው።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የገንዘብ ቢሮ ኃላፊው እና የምክር ቤት አባሉ አቶ ዚያድ፤ “[በአዲስ አበባ ጊዜ] የነበረው የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ [እና] አጠቃላይ የተቋሞቻችንም ነጻነት አሁን ካለው ጋር ተመሳሳይ አይደለም” ሲሉ የከተማዋ ልምድ በክልሉ ለተፈጠረው የምርጫ ጊዜ መዛነፍ መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል ይጠቁማሉ።
“ያኔ የነበረው ምርጫ ቦርድ ሙሉ ነጻነት አልነበረውም” የሚሉት አቶ ዚያድ፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ምርጫ እና መንግሥት ምሥረታ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚደረገው “መለየት አይችልም” ይላሉ።
የምክር ቤት አባሉ፤ በክልሎች ውስጥ “ምርጫ መቼ እና እንዴት መካሄድ እንዳለበት የሚወስነው” ምርጫ ቦርድ መሆኑን ይናገራሉ። እንደ ፀጥታ ችግር ያሉ ሂደቱን ለማከናወን የማያስችሉ ጉዳዮች ካላጋጠሙ በስተቀር ቦርዱ የሚያደርገው “ምርጫ ወጥ በሆነ አግባብ” እንደሚካሄድ ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Benishangul Gumuz Comm.
“ከምርጫ ቦርድ ጋር የሚቃረን የትኛውም ሕግ ካለ ተቀባይነት ያለው የምርጫ ቦርዱ ነው” የሚሉት አቶ ዚያድ፤ በዚህ ምክንያት ምንም እንኳን የምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ አምስት ዓመት የሥራ ደንብ እንደሚኖር ቢደነግግም “የምክር ቤቶች ውስጠ ደንብ ምርጫውን እንደማያግድ” ይከራከራሉ።
ቢሲሲ ላነጋገራቸው የሕግ እና ምርጫ ባለሙያ ግን ይህ ሃሳብ የሚዋጥ አይደለም። ባለሙያው ጉዳዩን የሚመለከቱት ኢትዮጵያ በምትከተለው የፌደራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ለክልሎች ከተሰጠው ራስን በራስ የማስተዳደር መብት አንጻር ነው።
ክልሎች ካላቸው ሥልጣን መካከል የክልል መስተዳድር እና የክልል ምክር ቤት ማቋቋም የሚጠቅሱት ባለሙያው፤ “የምክር ቤቶቹ የሥልጣን ዘመን የሚወሰነው በየክልሎቹ እና በፌደራል ደረጃ ባለ ሕገ መንግሥት” መሆኑን ያነሳሉ።
“በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕገ መንግሥት [መሠረት] የክልሉ የሥልጣን ዘመን አምስት ዓመት ነው። [ሕገ መንግሥቱ] አምስት ዓመት የሥልጣን ዘመን ከመሙላቱ አንድ ወር ቀድሞ ‘ምርጫ ይካሄዳል እና አዲስ ምክር ቤት ይቋቋማል’ ይላል እንጂ የክልሉ ምክር ቤት ከፌደራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በተመሳሳይ የሥልጣን ዘመን መጀመር እና መጨረስ አይጠበቅበትም” ሲሉ መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ።
በክልሉ በ2018 ዓ.ም. ይደረጋል የሚለው ሀሳብ የሚነሳው የፌደራሉ ፓርላማ እና የክልሎች ምክር ቤት የሥልጣን ዘመን “በተመሳሳይ ሁኔታ ማለፍ አለበት” ከሚል የአረዳድ ልዩነት መሆኑን የሚያነሱት ባለሙያው፤ ይህንን መከራከሪያ ለመቃረን የምርጫ ሕጉን ይጠቅሳሉ።
ባለሙያ የሚጠቅሱት በ2011 ዓ.ም. በወጣው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ላይ ስለ ጠቅላላ ምርጫ የሚያትተውን አንቀጽ ነው። “ጠቅላላ ምርጫ” በየአምስት ዓመቱ የሚካሄድ የሕዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ እንደሆነ የሚገልጸው አዋጁ፤ ይህ ምርጫ “በመላ አገሪቱ በተመሳሳይ ጊዜ” እንደሚደረግ አስፍሯል።
ይሁንና ምርጫ ቦርድ “አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው እና ጉዳዩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ ሲያገኝ በተለያየ ጊዜ” ሊያካሂድ እንደሚችል ይገልጻል። ቢቢሲ፤ በጉዳዩ ላይ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምላሽ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።
በአዋጁ ላይ ቦርዱ በተለያየ ጊዜ ምርጫ ሊያደርግ እንደሚችል መገለጹን የሚጠቅሱት የሕግ እና ምርጫ ባለሙያው፤ “በተለያየ ጊዜ ምርጫ የሚከናነወንበት ጊዜ ካለ የምክር ቤቶቹ የሥልጣን ዘመን ሊለያይ እንደሚችል ግልጽ ነው” ይላሉ።
ይህንን ሀሳብ የሚደግፉት የሕግ ባለሙያው አቶ አንዱዓለም፤ ምርጫ በተመሳሳይ ጊዜ የሚደረገው “እስከተቻለ ድረስ” መሆኑን በማንሳት ሀሳቡን ያጠናክራሉ። የክልል ምክር ቤት ምርጫ የሚደረገው “ከክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ጋር በተያያዘ” እንደሆነ የሚያስረዱት አቶ አንዱዓለም፤ በተመሳሳይ ወቅት ምርጫ አለመደረጉ በአንድ ክልል ውስጥ ያለን ምክር ቤት “ዋጋ አያሳጣውም” ባይ ናቸው።
“የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ያለ ሕዝብ ይህንን ምርጫ ያደረገው ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን ለመጠቀም ነው። ይህንን መብቱን ሲጠቀም በሌሎች ክልሎች ምርጫ መደረጉ አለመደረጉ ለዚህ ጉዳይ ወሳኝ አይደለም” ሲሉ ይከራከራሉ።
አቶ አንዱዓለም፤ “[የክልል ምክር ቤቱ ጊዜ የሚያልቀው] አምስት ዓመት ጠብቆ ነው እንጂ እነ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ ክልሎች [ምርጫ] ሲያደርጉ ጠብቆ፤ አሁን ያለውን [ምክር ቤት] ማፍረስም በየትኛውም አመክንዮ አያስኬድም። የሕጉም ሀሳብ እንደዚያ አይመስለኝም፣ ወጪ ቆጣቢም አይደለም” በማለት በክልሉ “በሁለት ዓመት ውስጥ ሌላ ምርጫ ለማድረግ አሳማኝ ምክንያት አለ” ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል።















