‘በንብ ምልክት’ ባሸነፈ ፓርቲ ለዘጠኝ ዓመታት የሚተዳደረው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል

በኢትዮጵያ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ እንደሚካሄድ በሕግ የተደነገገ ሲሆን፣ እስካሁንም ስድስት ጠቅላላ ምርጫዎች ተካሂደዋል።
ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ሁለት ጊዜ ከተራዘመ በኋላ በ2013 ዓ.ም. ተካሂዷል። አብላጫውን ድምጽ ያሸነፈው ብልጽግና ፓርቲም መንግሥት ከመሠረተ ሁለት ዓመት አልፎታል።
ምርጫው በሁለት ዙሮች ቢካሄድም፤ ጥቂት በማይባሉ [የምርጫ] ክልሎች ግን እስካሁን አልተካሄደም።
ለዚህም በዋናነት የደኅንነት ስጋት እና ሌሎች ምክንያቶች ይነሳሉ።
ሰኔ 14/2013 ዓ.ም. እና መስከረም 20/2014 ዓ.ም. የተካሄደው ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ የአማራ፣ የአፋር፣ የኦሮሚያ፣ የቀድሞው ደቡብ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ የተወሰኑ አካባቢዎች አልተካሄደም።
ይሁን እንጂ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የምርጫ ጉዳይ ግን “ልዩ” ነው።
ምርጫ ባልተካሄዳባቸው አብዛኞቹ ክልሎች በአብላጫ ድምጽ መርኅ መንግሥት መመሥረት ተችሏል።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምንም እንኳ ምርጫ ከ20 በላይ በሚሆኑ ምርጫ ክልሎች ምርጫ ቢካሄድም፣ መንግሥት መመሥረት ግን አልተቻለም።
በዚህም ክልሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሕገ ወጥ በሚሉት በኮቪድ-19 ጊዜ በታወጀ አዋጅ ምክር ቤቱ ሥልጣኑን አራዝሞ ለዘጠኝ ዓመታት የሕግ አውጪነቱን ሚና ቀጥሎበታል።
ክልሉ በ2015 ዓ.ም. በአንጻራዊነት ሲረጋጋ ይደረጋል የተባለው ምርጫም እንደ ውጥኑ ሳይሆን ቀርቷል።
‘በንብ ምልክት ያሸነፈ ም/ቤት’
ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለስድስተኛ አጠቃላይ ምርጫ ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት በኮማንድ ፖስት ስር ነበር። ቢሆንም ግን የመራጮች እና የዕጩዎች ምዝገባ እንዲሁም የምርጫ የማስታወቂያ ሰሌዳ መለጠፍን የመሰሉ እንቅስቃሴ ተደርገዋል።
የቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ የውጭና አለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር መብራቱ ዓለሙ በፀጥታ ጉዳዮች ምክንያት “ተንቀሳቅሰን የምረጡኝ ዘመቻ ማድረግ አንችልም” በሚል ፓርቲዎች ምርጫው እንዲራዘም ማድረጋቸውን ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ ጥቂት በማይባሉ የምርጫ ክልሎች ምርጫውን ማካሄድ ተችሏል። በዚህም ሦስት የፌደራል እና 28 የክልል ምክር ቤቶች መቀመጫዎች አሸናፊ አግኝተዋል።
ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዘጠኝ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና 99 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች አሉት።
ክልሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሉት ቀሪ ስድስት መቀመጫዎች “ወኪል አልባ” ቢሆኑም፤ በም/ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ ፓርቲ በመኖሩ ተጽዕኖው እምብዛም መሆኑን ፖለቲከኞች ይናገራሉ።
የቤንሻንጉል ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ (ቤሕነን)፣ ኢዜማ፣ አብን እና ብልጽግናን የመሰሉ ፓርቲዎች የተወዳደሩባቸውን 28 የክልል ም/ቤት መቀመጫዎች ሁሉንም ብልጽግና አሸንፏል።
በአገሪቱ የምርጫ ሕግ መሠረት ግን ብልጽግና መንግሥት መመሥረት የሚያስችለውን አብላጫ ድምጽ አላገኘም። ይህ ከሆነም ሁለት ዓመታት አልፈዋል።
በዚህ ምክንያትም ክልሉ የሥልጣን ዘመናቸውን ባጠናቀቁ የም/ቤት አባላት እና ሥራ አስፈጻሚዎች እስካሁንም እየተመራ ነው ይላሉ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ሰብሳቢ እንዲሁም የቤሕነን ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አብዱልሰላም ሸንገል የክልሉ ጉዳይ “ልዩ” ነው ይላሉ። ለዚህም ምክንያታቸው ሌሎች ምርጫ ያልተደረገባቸው ክልሎች መንግሥት መመሥረታቸው፤ ክልሉ ግን ሕገ ወጥ በሚሉት መንግሥት ስር መሆኑ ነው።
በ2007 ዓ.ም. በተደረገው አምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሁሉንም የፌደራል እና የክልል ም/ቤት መቀመጫዎች የቀድሞው ኢሕአዴግ አጋር የነበረው ቤጉሕዴፓ አሸንፏል።
የክልሉ ምክር ቤት እንደራሴዎች ሕግ የማውጣት የሥልጣን ዘመን ካበቃ ዓመታት ቢቆጠሩም አሁንም በሥራ ላይ ይገኛል።
ኢህአዴግ ከስሞ ብልጽግና አገሪቱን እያስተዳደረ ባለበት በአሁኑ ወቅት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ባሸነፈው “የኢሕአዴግ ም/ቤት” እየተመራ ነው የሚሉት ዶ/ር መብራቱ፤ “ይህም ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር ነው” ይላሉ።
“አንድ የምርጫ ዘመን አምስት ዓመት ነው። ከዚያ ካለፈ አስገዳጅ ሁኔታ ሲፈጠር የሕግ ትርጓሜ ተሰጥቶ ነው መቀጠል የሚቻለው። የቤንሻንጉል ግን ምንም ዓይነት የሕግ ትርጓሜ ሳይሰጠው መንግሥት ለመሆን የሚያስችል የምርጫ ድምጽ ሳያገኙ ነው ክልሉን እየመሩ ያሉት።”
ምርጫው በወቅቱ ባለመደረጉ የአገሪቱም የክልሉም ሕግ ተጥሷል ሲሉ የዶ/ር መብራቱን ሀሳብ የሚጋሩት አቶ አብዱልሰላም፤ “ተጽዕኖው ቀላል የሚባል አይደለም” ይላሉ።
“የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመንን ወደ ዘጠኝ ዓመት ማሻገር በሕብረተሰቡ ላይ ተጽዕኖ አለው። ሌላው የተሻለ ሀሳብ እናመጣለን የሚሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ዓላማቸውን ለማሳካት ዕድል ይነፍጋል” በማለት ያብራራሉ።
የክልሉን የምርጫ ጉዳይ “አሳሳቢ” ሲሉ የሚገልጹት ዶ/ር መብራቱ ዓለሙ፤ በአስቸኳይ ምርጫ እንዲካሄድ ጠይቀዋል።

የፎቶው ባለመብት, BG comm.
ምርጫ ለማካሄድ የተያዘ ዕቅድ
አሶሳ፣ መተከል እና ካማሺ የተባሉ ሦስት ዞኖች ያሉት ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም. በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ ምርጫ ተካሂዷል።
ማኦ ኮሞ፣ ድርቆሊ እና ባምባሲ የተባሉ የምርጫ ክልሎች በተወካዮች ምክር ቤት ወኪል አግኝተዋል።
ለክልል ም/ቤት የተካሄደው ምርጫ ውጤት የክልሉን ም/ቤት በአብላጫ ድምጽ መያዝ የሚያስችል አልነበረም። ይህም ከሌሎች ምርጫ ካልተካሄደባቸው ክልሎች ጉዳዩን “ለየት” በማድረጉ፤ በክልሉ በአፋጣኝ ምርጫ እንዲደረግ ጥሪዎች በርትተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ባልተደረገባቸው አካባቢዎች በ2015 ዓ.ም. ምርጫ እንደሚደረግ አስታውቆ የነበረ ቢሆንም አልተሳካም።
ዶ/ር መብራቱ ቦርዱ ሕዝበ ውሳኔዎች በማድረግ ከመወጠሩ ባለፈ የቤንሻንጉል ክልል መንግሥት ምርጫ የማድረግ ፍላጎት “አነስተኛ” መሆንን እንደ ምክንያት ሲያስቀምጡ፤ አቶ አብዱልሰላም ደግሞ “የበጀት አለመፈቀድ” እንቅፋት ሆኗል ይላሉ።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ “የኦፕሬሽናል ዕቅድ ዝግጅት” እተጠናቀቀ ነው ያለ ሲሆን፤ ምክረ ሃሳቦችንም ከባለድርሻዎች በውይይት መውሰዱን ጠቁሟል።
ሆኖም ቦርዱ ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ እንዳጠናቀቀ አሳውቃለሁ ከማለት ውጪ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።
ባለፈው ጥር ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ባደረገው ምክክር የተሳተፉ አንድ ፓለቲከኛ በሁለት አጀንዳዎች ላይ ውይይት መደረጉን ግለጸው፤ ቦርዱ እያደረገው ያለውን ዝግጅት በተመለከተ በስብሰባው ላይ የተነሳውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ምርጫውን ለማካሄድ በክልሎች ያለው የፀጥታ ሁኔታ በቀዳሚ አጀንዳነት መፈተሹን የተናገሩት ፖለቲከኛው፤ አጠቃላይ ዝግጅቱን በተመለከተ እና የዕጩ ተወዳዳሪዎችን ዝርዝር መከለስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይም መነጋገራቸውን ገልጸዋል።
ቢቢሲ ምርጫ ላልተካሄደባቸው አካባቢዎች የሚሆን የማስፈጸሚያ በጀት ከተወካዮች ም/ቤት እንደጸደቀ ማረጋገጥ ችሏል። 320 ሚሊዮን ብር ነው የተባለው በጀቱ ገንዘብ ሚኒስቴር እስኪለቀው ድረስ እየተጠበቀ ነው ተብሏል።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና ምርጫ ባልተደረገባቸው ሌሎች ክልሎች “በቅርቡ” ምርጫው የሚመራበትን የትግበራ ዕቅድ ቦርዱ ይፋ እንደሚያደርግ መናገሩን ፖለቲከኞቹ ገልጸዋል።
ምርጫ በዚህ ዓመት ግንቦት አጋማሽ አካባቢ እንደሚካሄድ ምርጫ ቦርድ ማሳወቁን ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በእንጥልጥል ያለው የሕግ ትርጓሜ ጉዳይ
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምርጫ አብላጫ ወንበር ያሸነፈ ፓርቲ ባለመገኘቱ በ2007 ዓ.ም. የተመረጠው መንግሥት እንዲቀጥል ሲደረግ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ያስፈልገው እንደነበር ቢቢሲ ያነጋገራቸው ፖለቲከኞች ገልጸዋል።
የክልሉ መንግሥት የሥልጣን ጊዜ ሲራዘም የሕገመንግሥት ትርጓሜ ያስፈልገዋል በሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን የጠቀሱት ፖለቲከኞቹ መልስ አላገኘንም ይላሉ።
በመሆኑም ያለ ሕገመንግሥት ትርጓሜ የሥልጣን ጊዜ እንዲራዘም ሆኗል ሲሉም ይወቅሳሉ።
“ለኮቪድ ተብሎ በተደረገው የሕገመንግሥት ትርጉም ነው የቀጠለው። ያ ደግሞ ለመላው አገሪቱ የተደረገ የሕግ ትርጉም ነው። ለቤንሻንጉል የተለየ የሕግ ትርጉም ያስፈልጋል የሚል እምነት ነበረን። በወቅቱ አልተደረገም” የሚሉት አቶ አብዱልሰላም፤ አዎንታዊ ምላሽ እንዳላገኙ ይናገራሉ።
ላቀረቡት ጥያቄም በጥቅሉ “ባለፈው [በኮቪድ ጊዜ ምርጫው ሲራዘም በተሰጠው] የሕግ ትርጉም እንዲቀጥል ተደርጓል የሚል ነው የተሰጠን ምላሽ” ብለዋል።
በሥራቸው ምክንያት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የምርጫ እና የሕግ ባለሙያ “ምርጫ እስኪደረግ ድረስ” የሁሉንም ም/ቤቶችን የሥልጣን ዘመን ያራዘመው ውሳኔ አሁንም ለቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈጻሚ መሆን የለበትም ሲሉ ሕጋዊነቱ ላይ ጥያቄ ያነሳሉ።
“የቤንሻንጉል ጉሙዝ ም/ቤት በዚያ ውሳኔ ምክንያት አሁንም ሕጋዊ ሥልጣን አለኝ ሊል አይችልም” የሚሉት የሕግ ባለሙያው “ያ ውሳኔ የተላለፈው ኮቪድን መነሻ በማድረግ ነው” ይላሉ።
አክለውም “ከዚያ በኋላ የሕገ መንግሥት ትርጉም ተሰጥቶ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በፀጥታ ምክንያት ወይም በሌላ ምክንያት ‘የም/ቤቱ የሥልጣን ዘመን ተራዝሟል’ የሚል ውሳኔ ስላልተሰጠ፤ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ም/ቤት ሕጋዊ መሠረት የለውም” በማለት ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ዶ/ር መብራቱ ፓርቲያቸው ከአንድ ዓመት በፊት “ሕዝብ ያልመረጠው መንግሥት ሊኖር አይገባም” በሚል ለፌደሬሽን ም/ቤት እና ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በደብዳቤ መጠየቁን የሚያነሱት ዶ/ር መብራቱ፤ የሕገመንግሥት ትርጓሜ እንዲሰጠው ጠይቀው ምላሽ አላገኙም።
አዲስ የሚመረጠው አስተዳደር በየሥልጣን ዘመን
በቤኒሻንጉል ውስጥ ላጋጠመው የምርጫ መጓተት እና ለተነሱ ጥያቄዎች አስካሁን ተጨባጭ ምላሽ አልተገኘም የሚሉት የክልሉ ተፎካካሪ ፖለቲከኞች በተለያዩ ጊዜያት አማራጭ ሃሳቦችን አቅርበው ነበር።
ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከዚህ ቀደም የሽግግር መንግሥትን ጨምሮ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ አሊያም የባለደራ መንግሥት በክልሉ እንዲመሠረት የሚሉ የመፍትሄ አማራጮችን አቅርቦ ነበር።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ ምርጫው ተካሂዶ የሚያሸንፈው መንግሥት የሥልጣን ዘመን ስንት ዓመት ይሆናል የሚለውም ሌላው አወዛጋቢ ጉዳይ ነው።
“የአዲሱ መንግሥት” የሥልጣን ዘመኑ የሚቆጠረው ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ከተደረገበት ከ2013 ዓ.ም. ወዲህ ነው ወይስ በክልሉ ምርጫው ከሚደረግበት ጊዜ አንስቶ? ጉዳይ እየተነሳ ነው።
ይህን ጥያቄ “አሻሚ ነው” የሚሉት የቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ የውጭና አለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ፤ ይህም ጉዳይ የሕገመንግሥት ትርጓሜ እንደሚያስፈልገው ይናገራሉ።
የዶ/ር መብራቱን ሀሳብ የሚጋሩት አቶ አብዱልሰላም ይህን ጥያቄ ለሚመለከታቸው ተቋማት ማንሳታቸውን ጠቅሰው፤ ለሰባተኛው አገራዊ ምርጫ የሚቀሩት ዓመታት ጥቂት በመሆናቸው የሕገመንግሥት ትርጉም ያሻዋል ይላሉ።
የምርጫ እና የሕግ ባለሙያው ግን ሕገመንግሥታዊ ትርጓሜ አያስፈልገውም ባይ ናቸው። ለዚህም በአስረጂነት የሚያቀርቡት የፌደራሉም ሆነ የክልሉ ሕገመንግሥት ምርጫ በየአምስት ዓመቱ ይካሄዳል ብለው መደንገጋቸውን ነው።
“...በመደበኛ ሁኔታ የም/ቤቶቹ የሥልጣን ዘመን አምስት ዓመት ነው። ስለዚህ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዲስ ምርጫ ቢደራጅና አዲስ መንግሥት ቢመሠረት፤ አዲስ ም/ቤት ቢቋቋም ምንም ጥያቄ የለውም የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመን ይኖረዋል። ከፌደራል የም/ቤት እና የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ጋር አንድ ዓይነት መሆን አይጠበቅበትም” ይላሉ።
ነገር ግን ክልሉን ወክለው በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መቀመጫ ያላቸው አባላት ግን ውክልናቸው የም/ቤቱ የሥልጣን ዘመን ሲያበቃ አብሮ እንደሚጠናቀቅ ባለሙያው ጠቁመዋል።












