ገርበ ጉራቻ አካባቢ ከታገቱት ተማሪዎች ውስጥ 16ቱ ገንዘብ ከፍለው መለቀቃቸው ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከአዲስ አበባ በስተሰሜን በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ገርበ ጉራቻ አካባቢ በታጣቂዎች ታግተው ከሚገኙ ተማሪዎች መካከል ባለፉት ቀናት 16ቱ ገንዘብ ከፍለው መለቀቃቸው ተሰማ።
ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ በኦሮሚያ ክልል ገርበ ጉራቻ አካባቢ የታገቱት የደባርቅ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አንድ በእገታ ስር አንድ ወር አልፏቸዋል።
ከ100 በላይ ተማሪዎች ሰኔ 26/2016 ዓ.ም. ከአማራ ክልል ተነስተው ወደ ዋና ከተማዋ በመጓዝ ላይ እያሉ በጎሃ ጽዮን እና ቱሉ ሚልኪ መካከል በታጣቂዎች መታገታቸው ይታወሳል።
ምንም እንኳ መንግሥት ወሰድኩት ባለው እርምጃ ተማሪዎቹን ማስለቀቁን ቢናገርም፤ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ቢቢሲ ያናገራቸው ቤተሰቦች እና ምንጮች ግን ተማሪዎቹ እንዳልተለቀቁ እና የማስለቀቂያ ገንዘብ እየተጠየቀባቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንትም በእገታ ስር ከሚገኙ ተማሪዎች መካከልም 16 የሚሆኑ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የማስለቀቂያ ገንዘብ ከፍለው መለቀቃቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ባለፈው ረቡዕ ሐምሌ 24/2016 ዓ.ም. ከ100 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር የከፈሉ 11 ተማሪዎች መለቀቃቸውን ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ሁለት የተለቀቁ ተማሪዎች ቤተሰቦች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
የተለቀቁት ተማሪዎች ዘጠኝ ሴቶች እና ሁለት ወንዶች መሆናቸውን የተናገሩ ሲሆን፣ ለማስለቀቂያ “የተለያየ መጠን ያለው” ገንዘብ ቤተሰቦች ስሙን መጥቀስ ባለፈለጉት ባንክ በኩል አስተላለፈው ልጆቻቸውን ማስለቀቃቸውን ገልጸዋል።
በእገታው ስር የቆዩት ተማሪዎች በፍርሃት እና በሰቆቃ ውስጥ በመሆናቸው ምንም ነገር ለመናገር ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ቤተሰቦች ጠቅሰው፤ ክፍያው ከተፈጸመ በኋላ ታግተው ከነበሩበት ገጠራማ አካባቢ ለሰዓታት በእግር ተጉዘው ሌሊት ቱሉ ሚልኪ ከተማ አካባቢ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
በአካባቢው ነዋሪዎች ተሸኝተው ቱሉ ሚልኪ ከተማ ሲደርሱ በአካባቢው የነበሩ “የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች” እንደተቀበሏቸው የተናገሩት ተማሪዎቹ፤ በማግሥቱ ሐሙስ አዲስ አበባ መግባታቸው ታውቋል።
ተማሪዎቹ በዕለቱ አዲስ አበባ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ የደረሱ ሲሆን፤ ቤተሰቦቻቸው እና ጓደኞቻቸው እንደተቀበሏቸው የቢቢሲ ምንጮች ተናግረዋል።
አጋቾቹ መጀመሪያ ለማስለቀቂያ ከጠየቁት ገንዘብ ቀንሰው እንደተቀበሉ ምንጮች የተናገሩ ሲሆን፤ ቤተሰብ ከተለያዩ አማራጮች ያሰባሰበውን ገንዘብ ከፍሎ ልጆቹን ማስለቀቁን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ሐሙስ ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም. ተጨማሪ አምስት ሰዎች (አራት ተማሪዎች እና አንድ ተማሪ ያልሆኑ መንገደኛ) የማስለቀቂያ ገንዘብ ከፍለው እንደተለቀቁ ምንጮች ገልጸዋል።
እንዲሁም ሰኞ ጠዋት ሐምሌ 29 ደግሞ ሌላ አንድ ተማሪ በተመሳሳይ የማስለቀቂያ ገንዘብ በመክፈል ተለቆ አዲስ አበባ መግባቱን አረጋግጠዋል።
አንድ ወር የሆነውን ተማሪዎቹ እገታ ከቤተሰብ ጋር ሆነው በቅርበት እየተከታተሉ ያሉ ምንጮች እንዳሉት በታጋቾቹ ላይ ግርፋት፣ ድብደባ እንዲሁም ጾታዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።
በተጨማሪም ተማሪዎቹ በእገታ ቆየረታቸው ወቅት የነበራቸው አያያዝን በተመለከተ የተደበላለቀ ስሜት እንዳላቸው ለወላጆቻቸው “አንዳንድ ቀን ይራሩልናል፤ አንዳንድ ቀን ደግሞ ይጨክኑብናል” ሲሉ ተናግረዋል።
አጋቾቹ በተማሪዎቹ ላይ በሚወስዷቸው እርምጃዎች ላይ በመካከላቸው ጭቅጭቅ እንደነበር መመልከታቸውን ተማሪዎች ገልጸው “ስምምነት አልነበራቸውም” ብለዋል።
የተለቀቁት ተማሪዎች ከባሕር ዳር በጎደሉ ወንበሮች የተሳፈሩ 15 የሚሆኑ (ተማሪ ያልሆኑ) መንገደኞች አብረዋቸው እንደታገቱ [አሁንም በእገታ ላይ እንደሚገኙ] ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያናገራቸው አንድ የታጋች ተማሪ ቤተሰብ “ታጣቂዎቹ በተማሪዎቹ ፊት ሁለት ሰዎችን መግደላቸውን እያለቀሱ ነግረውናል” ብለዋል።
ይህንም የተለቀቁ ተማሪዎች ያረጋገጡ ሲሆን፤ ከተማሪዎቹ ውጭ የነበሩ ሁለት መንገደኞች በታጣቂዎቹ መገደላቸውን ተናግረዋል።
ተገድለዋል የተባሉት ሰዎች ሁለቱም ወንዶች ሲሆኑ፤ አንዱ ‘ገንዘብ እያለው የለኝም ብሎ ዋሽቷል’ የተባለ ወጣት እና አንድ ጎልማሳ የሆኑ ሰው መሆናቸውንም ገልጸዋል።
“ልጆቹ በጣም ከስተዋል፤ ጠቁረዋል” ያሉ ተማሪዎችን በአካል አዲስ አበባ ላይ ያገኟቸው አንድ ምንጭ፤ “በቆሎ በሽንኩርት እና ቃሪያ ተለውሶ” የሚዘጋጅ (በአካባቢው የተለመደ) ምግብ ሲመገቡ እንደነበር ጠቅሰዋል።
ከ30 በላይ ይሆናሉ የተባሉት ታጣቂዎቹ ‘ፀጉራቸውን የተሰሩ፣ የሲቪል ልብስ የለበሱ እና የተማሩ’ መሆናቸውን ተማሪዎቹ አመልክተዋል።
ተማሪዎቹ አካባቢውን የሚለይ የመልከዓ ምድር አቀማመጥም ይሁን አመላካች የሆኑ ጽሁፎችን (ታፔላ) እንዳላዩ ጠቁመው፤ አካባቢው የተመለደውን የኢትዮጵያን ገጠር የሚመስል ነው ብለዋል።
ተማሪዎቹ በአካባቢው እንደ ትምህርት ቤት እና ጤና ጣቢያ ያሉ ተቋማትንም እንዳላዩ ተናግረዋል።
ከ100 በላይ ይሆናሉ ከተባሉት ተማሪዎች መካከል በእገታ ወቅት ካመለጡት ባሻገር “በብሔራቸው የተለዩ” እና የማስለቀቂያ ገንዘብ የከፈሉ ናቸው የተባሉ ስምንት ተማሪዎች ጨምሮ 40 የሚሆኑ ተማሪዎቹ መለቀቃቸው ቢቢሲ መዘገቡ ይታወሳል።
ተማሪዎቹ በተለያየ ቡድን ተከፋፍለው የቆዩ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በእገታ ላይ ምን ያህል ተማሪዎች እንደሚገኙ አልታወቀም።
እገታውን እየመረመረ ያለው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለቢቢሲ ምርመራውን እስካሁን እንዳላለቀ ገልጾ፤ “አሁንም በምርመራ ላይ ነን” ብሏል።
የኦሮሚያ ክልል መስተዳደር ‘አብዛኞቹ ተማሪዎቹን አስለቀቅኩ’ ባለበት እና ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ “ሸኔ” የሚለውን እና በአሸባሪነት የተፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ለእገታው ተጠያቂ እድርጎ የነበረ ሲሆን ታጣቂ ቡድኑ ግን የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል።












