ገርበ ጉራቻ አካባቢ 100 የሚጠጉ ተማሪዎች በታጣቂዎች ታገቱ

ከአማራ ክልል ተነስተው ወደ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በአውቶብሶች ሲጓዙ የነበሩ ከአንድ መቶ በላይ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በታጣቂዎች መታገታቸው ተነገረ።
አብዛኞቹ የደባርቅ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ናቸው የተባሉት መንገደኛ በታጣቂዎች የታገቱት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገርበ ጉራቻ አካባቢ መሆኑን የዐይን እማኖች እና የታጋች ቤተሰቦች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከአዲስ አበባ በስተ ሰሜን 155 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከተፈጸመው እገታ የተወሰኑ ተማሪዎች ሲያመልጡ ሌሎች ደግሞ መለቀቃቸው ተነግሯል።
ተማሪዎቹ መነሻቸውን ከአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ እና ከባሕር ዳር ያደረጉ ሲሆን፣ ሲጓዙባቸው ከነበሩ “ታታ” ከሚባሉ ሦስት የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ረቡዕ ሰኔ 25/2016 ዓ.ም. “ሸኔ” ናቸው በተባሉ ታጣቂዎች መታገታቸው ተነግሯል።
ሁለቱ አውቶብሶች ከደባርቅ ዩኒቨርስቲ፤ አንዱ አውቶብስ ደግሞ ከባሕር ዳር ከተማ (መናኸሪያ) ተነስተው ደጀን አድረው ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ እያሉ በጎሃ ጽዮን እና በቱሉ ሚልኪ መካከል ላይ ባለች “ትንሽ መንደር” ላይ እገታው እንደተፈጸመ ከእገታው ያመለጡ ሁለት ተማሪዎች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
አንድ የአራተኛ ዓመት ተማሪ አውቶብሶቹ ተከታትለው ጠዋት 12፡00 ላይ ከደጀን እንደተነሱ እና አባይ በርሃን ወጥተው ጎሃ ጽዮን ከተማን እንዳለፉ ተማሪው “ሸኔ ናቸው” ያላቸው ታጣቂዎች እገታውን እንደፈጸሙ ተናግሯል።
“ከፊት መሳሪያ ደቅነዋል፤ ስናይፐር፣ ክላሽ ታጥቀዋል። መሳሪያ ደቅነው አስቁሙን፤ ከመኪናው ላይ ሁላችንንም በዱላ እየመቱ አስወረዱን። ከዚያ በኋላ ወደ ጫካ ይዘውን ነው የሮጡት” በማለት ስለ እገታው ቅጽበት ተናግሯል።
“አሰቃቂ” ሲል ድርጊቱን የገለጸው ተማሪው፤ ስደስት ሆነው ከእገታው በመደበቅ ማምለጣቸውን ተናግሯል።
“እኛ የሆነ ጫካ ቦታ ስንደርስ መንደር አገኘን፤ የገበሬ ቤት። ከዚያ ወደ ጎን ተገንጥለን፤ ስድስታችንም ቤቱ ውስጥ ገባን፤ እዚያም ተኝተን አመለጥን። እነሱም ሳያዩን አልፈውን ሄዱ። ትንሽ ቆይቶ መከላከያ እና ሚሊሻዎች፤ ልዩ ኃይል ደረሰ” ብሏል።
አውቶብሱ ከተማሪዎች በተጨማሪ ልጅ የያዙ እናቶችን እና ሌሎች መንገደኞችን አሳፍሮ እንደነበር የጠቆመው ተማሪው፤ የታጋቾቹን ቁጥር ከ120 እስከ 130 ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል።
ሌላ ከእገታው ሮጣ ማምለጧን የተናገረች አንድ ተማሪ፤ ከሦስት አውቶብስ ውስጥ እሷን ጨምሮ 56 ሰዎች ማምለጣቸውን ተናግራለች።
“በጣም ብዙ ነበርን ወዴት እንደምንሮጥ [አናውቅም ነበር] እየወደቅን እየተነሳን” ስትል ሁኔታውን የገለጸችው ተማሪዋ፤ በድንጋጤ ተውጣ እንደነበር ገልጻለች።
“ነፍሳችንን ለማዳን ነው ሁላችንም የሮጠው” ያለችው ተማሪዋ ጉዳት ደርሶባት ሆስፒታል ገብታ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግራለች።
ታጣቂዎቹ መንገደኞችን ይዘው አምስት ኪሎ ሜትር ገደማ ከሄዱ በኋላ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በታጣቂዎቹ መካከል የተኩስ ልውውጥ መደረጉን የአራተኛ ዓመት ተማሪው ተናግሯል።
ተማሪዎቹ ለእገታ ማስለቀቂያ ገንዘብ መጠየቁንም ከጓደኞቻቸው እንደተረዱም ተናግረዋል።
በዩኒቨርስቲው ተማሪ የሆነች እህታቸው እንደታገተችባቸው የተናገሩ አንድ ግለሰብ፣ ለማስለቀቂያ 700 ሺህ ብር እንደተጠየቁ ተናግረዋል።
እህታቸው በአጋቾች ስልክ ደውላ “በሦስት ቀን ውስጥ 700 ሺህ ብር ካላስገባሽ እንገድልሻለን ብለውኛል” ማለቷን የተናገሩት ግለሰቡ፤ ምን እንደሚያደርጉ ግራ እንደገባቸው ተናግረዋል።
ዛሬ አርብ (ሰኔ 28) ለሦስተኛ ጊዜ የማስለቀቂያ ገንዘብ እንዲከፈል እህታቸው ደውላ እንደጠየቀች የጠቀሱ ሲሆን፤ የተጠየቀውን ማስለቀቂያ ለመክፈል ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ተናግረዋል።
“. . . [እንኳን] 700 ሺህ ሰባት ሺህ ብር መክፈል የሚችል አቅም የለም” ብለዋል።
ስለ እገታው በቢቢሲ የተጠየቀው ደባርቅ ዩኒቨርስቲ፤ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።
ክስተቱን በተመለከተ ቢቢሲ እገታው ተፈጽሞበታል የተባለውን አካባቢ ኃላፊዎች አግኝቶ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት “ለሚመለከተው የፌደራል ተቋም ስለጉዳዩ አመልክተናል” ከማለት ባለፈ ተጨማሪ መረጃ መስጠት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።
ከትናንት ሐሙስ ማምሻ ጀምሮ 50 የሚሆኑ ተማሪዎች ‘በመጡበት አካባቢ ተለይተው’ መለቀቃቸውን ሁለቱ ተማሪዎች ለቢቢሲ ጠቁመዋል።
እገታው በተፈጸመበት የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎችን በሚያገናኘው በሰሜን ሸዋ ውስጥ ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከዚህ በፊትም በተለያዩ ጊዜያት እገታዎች ተፈጽመው ሰዎችን ለመልቀቅ ገንዘብ መጠየቁ ይታወሳል።
በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለሚፈጸሙት ገንዘብ ለሚጠየቅባቸው እገታዎች መንግሥት “ሸኔ” የሚለው እና በሽብር ቡድንነት የተፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ተጠያቂ ይደረጋሉ።












