በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂዎች የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶች አሳሳቢ ሆነው ቀጥለዋል፡ ኢሰመኮ

ታጣቂዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለፈው አንድ ዓመት በኢትዮጵያ በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በአሳሳቢነት መቀጠሉን የኢሰመኮ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ያለፈውን አንድ ዓመት በአገሪቱ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን በተመለከተ ባወጣው ዝርዝር ሪፖርት ላይ እንዳመለከተው በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች የትጥቅ ግጭቶች፣ ጥቃቶች ወይም የፀጥታ መደፍረሶች አጋጥመዋል።

በእነዚህ ሰበብም “በታጣቂዎች እና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተወሰዱ እርምጃዎች በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርስ የሞት እና የአካል ጉዳት አሳሳቢነት ቀጥሏል” በማለት፤ በተለይም በትጥቅ ግጭት ዐውድ ውስጥ በሲቪሎች ላይ የሚፈጸሙ “የመብት ጥሰቶች እንደቀጠሉ እና እንደተስፋፉ” ኮሚሽኑ ገልጿል።

ጨምሮም ከሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. እስከ ሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በትጥቅ ግጭት ውስጥ በቆዩ አካባቢዎች እንዲሁም ግጭት በሌለባቸው በአንዳንድ ሁኔታዎች ጭምር የሚፈጸሙ “ከሕግ ውጪ የሆኑ የሲቪል ሰዎች ግድያዎች አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል” ብሏል።

ባለፉት ዓመታት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ግጭት ሲያካሂዱ የቆዩ ሲሆን፤ በዚህም ሳቢያ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ እስር እና መፈናቀሎች ማጋጠማቸውን በተመለከተ ሪፖርቶች ሲወጡ መቆየታቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እንዳለው በእነዚህ ክልሎች ውስጥ ከሚካሄዱ ግጭቶች ጋር በተያያዘ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ከሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተጨማሪ ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ያደረገ እገታ አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል።

ለ10 ወራት ተፈጻሚ የሆነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አተገባበርን በተመለከተም ኮሚሽኑ ከአዋጁ ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች መደበኛ እና መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ቦታዎች ለተራዘመ እስር መዳረጋቸውን፣ ለቀናት ወይንም ለሳምንታት ለቆየ ጊዜ ያሉበት ቦታ ሳይገለጽ/ሳይታወቅ በእስር መቆየታቻውን በተመለከተ ክትትል እና ምርመራ ማድረጉን አመልክቷል።

በተጨማሪም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ ከኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ ውጪ በተለይ በአዲስ አበባ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሲዳማ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የመገናኛ ብዙኃን እና የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን ገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሌላ በኩል “ወቅታዊ ሁኔታ” በሚል ምክንያት ሰዎች ለዘፈቀደ እስር እንዲሁም ለአስገድዶ መሰወር የተዳረጉበት በርካታ ክስተቶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መመዝገባቸውን፣ ከመንቀሳቀስ መብትን አንጻር ደግሞ ባለው የፀጥታ ሁኔታ ወይም በሚጣሉ ገደቦች ምክንያት የየብስ እንቅስቃሴዎች አስቸጋሪ ሆነዋል ብሏል።

ኢሰመኮ ክትትል በተደረገባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች እና ማረሚያ ቤቶች መሻሻሎች እንዳሉ ጠቅሶ፣ ነገር ግን “በሁሉም ክልሎች ለማለት በሚያስችል ሁኔታ የዘፈቀደ እስር፣ የጅምላ እስር ወይም የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን ባለማክበር ሰዎችን ይዞ የማቆየት፣ መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ቦታዎች ሰዎችን የመያዝ ድርጊቶች ተፈጽመዋል” ብሏል በሪፖርቱ።

ኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን በአገሪቱ ለማሻሻል ከሚያስችሉ እርምጃዎች መካከል የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ መጽደቁ በዋነኝነት የሚጠቀስ መሆኑን ጠቅሶ፤ ሰላምን የማምጣት ከታጠቁ ኃይሎች ጋር የተጀመሩ ጥረቶች አበረታች ናቸው ብሏል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ኮሚሽኑን በዋና ኮሚሽነርነት ሲመሩ የቆዩት እና የሥራ ጊዜያቸውን አጠናቀው ይህ ሪፖርት በወጣበት ዕለት የተሰናበቱት ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የሚያጋጥሙ የመበት ጥሰቶችን ለማስተካከል በዋናነት ግጭቶች በንግግር መፍትሄ እንዲያገኙ ጥሪ አቅርበዋል።

ዶ/ር ዳንኤል “ኢትዮጵያ ከምትገኝበት የግጭት አዙሪት ዐውድ ለመውጣት እና በዚሁ ዐውድ ለደረሱ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በዘላቂነት እልባት ለመስጠት ከሰላማዊ መንገድ፣ ከውይይት፣ ከምክክር እና ከሽግግር ፍትሕ ሂደት ውጪ ሌላ አማራጭ የለም” ብለዋል።

ኢሰመኮ አርብ ሰኔ 28/2016 ዓ.ም. ባወጣው ባለ 132 ገጽ ባለፈው አንድ ዓመት በአገሪቱ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን በዝርዝር በተመለከተው ሪፖርቱ በቀጣይ ዓመት የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን ለማሻሻል ፤ኢወሰዱ ይገባል ያላቸውን እርምጃዎችንም ጠቁሟል።

ከእነዚህም መካከል የትጥቅ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት፣ የአገራዊ ምክክር እና የሽግግር ፍትሕ ሂደት ተዓማኒ አተገባበርን ማረጋገጥ፣ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች ሁሉ በአፋጣኝ እንዲለቀቁ ወይም የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ማድረግ ግን በቀዳሚነት ሰፍሯል።