የሰባት ዓመቷን ሄቨን ደፍሮ በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለው ግለሰብ ፍርድ የፈጠረው ቁጣ

ሄቨን ከመገደሏ ከሶስት ቀናት በፊት

የፎቶው ባለመብት, Courtesy of the family

የምስሉ መግለጫ, ሄቨን ከመገደሏ ከሶስት ቀናት በፊት

ማስጠንቀቂያ፦ ይህ ጽሁፍ ህጻንን መድፈር እና አሰቃቂ ግድያን የያዙ የሚረብሹ ነገሮችን ይዟል

የሰባት ሄቨን አወት ተደፍራ በአረመኔያዊ ሁኔታ በቤት አከራይዋ ግለሰብ መገደሏ በርካቶችን አስደንግጧል እንዲሁም አስቆጥቷል።

የሁለተኛ ክፍል ተማሪ የነበረችው ሄቨንን በመድፈር በዘግናኝ ሁኔታ የገደላት የሦስት ልጆች አባት ጌትነት ባዬ የተበየነበት ፍርድ በአገሪቱ ውስጥ ቁጣን እንዲሁም ውግዘትን ፈጥሯል።

መደፈሩ እና ግድያው የተፈጸመው ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር ውስጥ ቢሆንም በበርካቶች ዘንድ የተሰማው በቅርቡ ነው።

ህጻኗ ተደፍራ፣ እንዳትጮህ አፏ ውስጥ አሸዋ ተጨምሮባት፣ ታንቃ እንዲሁም ሰውነቷ ተተልትሎ ደጃፍ ላይ ተጥላ ነበር የተገኘችው። የህጻኗን ሕይወት በዚህ አሰቃቂ መንገድ የነጠቀው ጌትነት 25 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።

ግለሰቡ ይግባኝ መጠየቁን ተከትሎ እናቷ ጉዳዩን ወደ ወደ መገናኛ ብዙኃን ይዛው የመጣች ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለመስጠት ለሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት ወር ቀጠሮ ሰጥቷል።

ህጻን ልጇን ዘግናኝ በሆነ ግድያ ያጣችው እናቷ አበቅየለሽ አደባ “ሕይወት አልባነት” እንደሚሰማት ለቢቢሲ ተናግራለች።

በወንጀለኛው ላይ የተላላፈው ፍርድ የፈጸመውን ወንጀል ክብደት አያሳይም ያሉ የቅጣት ውሳኔው እንደገና እንዲታይ እንዲሁም በከፍተኛ ሰቆቃ ላይ ያለችውን እናት ለመደገፍ ፊርማ ማሰባሰብ የተጀመረ ሲሆን፣ እስካሁን ከ200 ሺህ ሰዎች በላይ ፊርማቸውን አኑረዋል።

በአገሪቱ የሴቶችን መብት ወደፊት በማምጣት ስመ ጥር የሆነችው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ግለሰቡ የተበየነበት ቅጣት “በጣም ቀላል ነው” ብላ እንደምታምን አስታውቃለች።

“የፈጸመው ግድያ ብቻ የእድሜ ልክ እስራት ወይም ሞት የሚያስፈርድበት ነው። በተለይም በልጆች ላይ እንደዚህ አይነት አጸያፊ ወንጀል ሲፈጸም የሚያሳምም እንዲሁም የሚያስቆጣ ነው” ብላለች ማኅበሯ።

ማኅበሯ ብቻ ሳትሆን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በፍርዱ ሂደት ላይ ወቀሳቸውን አሰምተዋል። የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ በሄቨን ላይ የተፈጸመውን ዘግናኝ ግድያ “ኢሰብዓዊ” ድርጊት ሲሉ ያወገዙት ሲሆን፣ መሥሪያ ቤታቸው ጉዳዩን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚከታተል አጽንኦት ሰጥተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሄቨን ላይ የተፈጸመው አረመኔያዊ ጥቃት በኢትዮጵያ ሕጻናት እና ሴቶች የሚደርሱባቸውን ወሲባዊ ጥቃቶች፣ መደፈር እና ግድያዎች ጉዳይ እንደገና ወደ መወያያው መድረክ አምጥቶታል።

የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪው ሂውማን ራይትስ ዋች በኢትዮጵያ ከግጭት ጋር የተያያዙ ወሲባዊ ጥቃቶች “አስጊ ደረጃ” ላይ መድረሳቸውን ግንቦት ወር ባወጣው ሪፖርት አሳስቧል።

ጥቃቱን የሚፈጽሙ ወንጀለኞች ተጠያቂነት አለመስፈኑ ለመስፋፋቱ አንድ ምክንያት መሆኑ በአንዳንዶች ዘንድ የሚነሳ ጉዳይ ነው።

ለሁለት ዓመት በዘለቀው የትግራይ ደም አፋሳሽ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳጊዎች እና ሴቶች የተደፈሩ ሲሆን፣ በዚህ ጦርነት ላይ መደፈር እንደ ጦር መሳሪያነት ጥቅም ላይ መዋሉን የተለያዩ ሪፖርቶች ያሳያል።

ተደፍራ በአሰቃቂ ሁኔታ ከመገደሏ በፊት ሕጻኗ ሄቨን ይህ ጦርነት ቤታቸውን አንኳኩቶ ለቤተሰባቸው መበተን ምክንያት መሆኑን ተመልክታለች።

የትግራይ ተወላጅ የሆነው አባቷ ጦርነቱ በተፋፋመበት ወቅት ለወራት ታስሮ ተፈቷል። በሌሎች አካባቢዎች በማንነታቸው እንደታሰሩ የትግራይ ተወላጆች ክስ አልተመሰረተበትም። ከተፈታም በኋላ በአማራ ክልል በጥርጣሬ እና በጠላትነት እንደሚታይ ስለተሰማው ወደ ትግራይ ተመለሰ።

በዚህም ምክንያት በሙያዋ ነርስ የሆነችው የሄቨን እናት አበቅየለሽ እሷን እና ታናሽ እህቷን ብቻዋን እንድታሳድግ ሆነች።

በዚህም ወቅት ነው ዘመድ የሆነች ግለሰብ ግቢ ውስጥ ቤት የተከራየችው። ይህች ዘመድ የሆነችው ግለሰብ ሄቨንን ደፍሮ የገደላት የጌትነት ባለቤት ናት።

እናት ከዘመድ እና ልጆች ካላቸው ቤተሰቦች ቤት ተከራይታ መኖሯ ምቾት እንደሰጣት እና ልጆቿ ይጠቃሉ የሚል ስጋት አድሮባት እንደማያውቅ አስረድታለች።

ሄቨን ጥቃት በደረሰባት ወቅት አበቅየለሽ በምትሰራበት ክሊኒክ ቀዶ ህክምና እያገዘች ነበር። ፌቨንን ቤት ውስጥ እየጠበቀቻት የነበረው የአበቅየለሽ ታናሽ እህት፣ አክስቷ ነበረች።

ህጻኗ ሽንት ቤት ደርሼ ልምጣ ብላ ውሃ ይዛ ከሄደች በኋላ እንዳልተመለሰች አክስቷ ተናግራለች። ለምን ይህን ያህል ጊዜ እንደፈጀባት ለማወቅ ወጥታ ብትፈልጋትም ልታገኛት አልቻለችም። ቤት አከራዩ ጌትነት በዚህ ወቅት ቤት ውስጥ እንዳስገባት ታምናለች።

ከጥቂት ጊዜ ቆይታ በኋላ የሕጻኗ ሰውነቷ ተተልትሎ፣ አንገቷ ላይ አምስት ጣት የሚታይበት የመታነቅ ምልክት፣ አፏ አካባቢ አረፋ ተሸፍኖ እና ልብሷ ረጥቦ ሕይወት አልባ አካሏ ደጃፋቸው ላይ ተጥሎ ተገኘ ።

ጥቃት ፈጻሚው አከራይ አስከሬኗን እዚያ እንደጣለው እናት ታምናለች።

“ልጆቻችን በቤታቸው ውስጥ ደኅንነታቸው ካልተጠበቀ ሌላ ወደየት መሄድ እንችላለን?” ስትል እናት ትጠይቃለች።

“ሥራ አቁመን ልጆቻችንን ቤት ስንጠብቅ እንዋል? ምንስ እናበላቸዋለን” ስትል የምትጠይቀው እናት፣ “በርካታ ሄቨኖች አሉ” ትላለች።

የልጇ በአሰቃቂ ሁኔታ በመገደሏ ልቧ የተሰበረው አበቅየለሽ በባለፉት ወራት መከራ፣ ስቃይ እና እንግልት አይታለች።

ልጇን በመግደል የተከሰሰው ጌትነት ከእስር ማምለጡን ተከትሎ ለራሷ እና ለልጇ ሕይወት በመስጋት መደበቅ ነበረባት።

በክልሉ ከመከላከያ ጋር እየተፋለሙ ያሉት የፋኖ ታጣቂዎች አባሎቻቸውን ለማስፈታት በባሕር ዳር ታስሮበት የነበረው ፖሊስ ጣቢያ መስበራቸውን ተከትሎ ነበር ጌትነት ያመለጠው።

ከእስር ያመለጠው ጌትነት መሳሪያ ታጥቆ የሄቨንን እናት ይፈልግ ጀመር። ግለሰቡ ለአንድ ወር ያህል አልታሰረም ነበር።

የከተማው የፀጥታ ኃይሎች ጌትነትን እንደገና ለማሰር ቸልተኝነት እንደታየባቸው የምትናገረው እናት፤ በድጋሚ እንዲይዙትም መለመን ነበረባት። በዚህ ሁሉ መካከል ጌትነት ያስፈራራት ነበር።

ልጇን ከማጣት ሰቆቃ በላይ የግለሰቡ ማስፈራራት የተደራረበባት አበቅየለሽ ከአንድ ቤት ወደ ሌላ ቤት እንዲሁም ሥራዋን በተደጋጋሚ ለመልቀቅ ተገዳለች።

የፍትህ ሥርዓቱ የምትጠብቀውን አጉድሎብኛል የምትለው እናት በጌትነት ላይ የተፈረደው የ25 ዓመት እስር በቂ አይደለም ትላለች።

ከዚህ በበለጠ እያሳሰባት ያለው ጉዳይ ግለሰቡ የጠየቀውን ይግባኝ አሸንፎ በነጻ ይወጣል የሚለው ጉዳይ ነው።

“ሄቨኔን አጣሁ። ሕይወት የለኝም” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

የጤና ሠራተኛ እንደመሆኗ መጠን ወሲባዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው በርካታ ሕጻናት እና ሴቶች አውቃለሁ ብላለች።

“ብዙ ሄቨኖች እንዳሉ አውቃለሁ” ትላለች።

ይህ ከዓመት በፊት የተፈጸመው አሰቃቂ ወንጅል እና እሱን ተከትሎ ልጇን በአሰቃቂ ሁኔታ ያጣችው እናት ላይ ከወንጀሉ ፈጻሚ ተባባሪዎች በኩል የሚደርስባት ጫና የእሷንም ሕይወት አደጋ ላይ እንደጣለው ትናገራለች።

እናት አበቅየለሽ በደሏን እና እየተደጸመባት ያለውን ማሳደድ በተመለከተ ከተናገረች በኋላ በአገሪቱ ውስጥ በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ቁጣ እና ተቃውሞ እየተሰማ ነው።