ትግራይ ለታዳጊዎቿ እና ለሴቶቿ ለምን 'እሳት' ሆነች?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ እና የተመረጡ ተማሪዎች በሚማሩበት በመቀለው አዳሪ ትምህርት ቤት ቃላሚኖ ተማሪ የነበረችው ቤተልሔም ገብረሚካኤል ለ10 ቀናት ደብዛዋ ከጠፋ በኋላ አስከሬኗ ተገኝቷል።
ለቀናት የደረሰችበት ሳይታወቅ የቆየችው ቤተልሔም ግንቦት 11/2016 ዓ.ም. እሁድ በጠዋት ቤተ ክርስቲያን ለመሳለም ከቤት እንደወጣች መቅረቷን አባቷ አቶ ገብረሚካኤል ነጋሽ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እስካሁን የቤተልሔም ገዳይ ያልታወቀ ሲሆን፣ የከተማዋ ፖሊስም ምርመራውን ቀጥሏል። ከባድ ሐዘን ላይ የሚገኙት ወላጆቿም ወንጀሉ ተጣርቶ ፍትህ እናገኛለን ብለው እየተጠባበቁ ነው።
ለሁለት ዓመታት ከቆየችበት ደም አፋሳሽ ጦርነት ተጽእኖ ውስጥ ለመውጣት እየተጣጣረች ባለችው ትግራይ ውስጥ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እና ግድያዎች በተደጋጋሚ እየተሰሙ ነው።
ከቤቴልሔም በተጨማሪም ባለፉት ወራት በትግራይ ክልል ጥቂት የማይባሉ ሴቶች እንግልት እና ሞት አጋጥሟቸዋል።
ከእነዚህም መካከል የመቀለ ከተማ ነዋሪዋ ዘውዱ ሐፍቱ በአሰቃቂ ሁኔታ ከተገደለች ዓመት ሊሆን ቢቃረብም ፖሊስ አራት ተጠርጣሪዎችን እየመረመረ ከመሆኑ ውጪ ቤተሰቧ ፍትህ አላገኘም።
የአዲግራት ከተማ ነዋሪዋ አዳነሽ አብርሃም እንዲሁ እንቆቅልሽ በሆነ ሁኔታ ተገድላ አስከሬኗ ከ10 ወራት በኋላ ነበር የተገኘው።
በአድዋ ከተማ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እና የ16 ዓመቷ ታዳጊ ማኅሌት ተኽላይም እንዲሁ ለትምህርት ወጥታ ታግታ ሦስት ሚሊዮን ብር የተጠየቀባት ሲሆን፣ ከሦስት ወራት በኋላ መገደሏ ታውቋል።
እነዚህ እንደማሳያ የቀረቡ ጥቃቶች ሲሆኑ፣ በትግራይ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ አሰቃቂ ግድያዎች ብቻ ሳይሆኑ መደፈሮችም ተበራክተው ቀጥለዋል።
በክልሉ በሴቶች ላይ እየተፈጸመ ያሉ ግድያዎች፣ እገታዎች እና ጾታዊ ጥቃቶች እንዲቆሙ በትግራይ ያሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት አደባባይ ወጥተው ጠይቀዋል። ጊዜያዊ አስተዳደሩም ጥቃት ፈጻሚዎች ተጠያቂ እንዲሆኑም ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
በትግራይ የቀጠለው መደፈር
በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ባለቁበት የትግራዩ ጦርነት ወቅት ወሲባዊ ጥቃቶች እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶችን የሚያጣራው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን ያወጣው ሪፖርት አትቷል።
ወሲባዊ ባርነትን ጨምሮ አሰቃቂ ጥቃቶች በትግራይ ታዳጊ እና ሴቶች ላይ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መከላከያ ኃይሎች እንዲሁም በአማራ ኃይሎች መፈጸማቸውን ይኸው ሪፖርት አመልክቷል።
ነገር ግን ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ጦርነትን የቋጨው የፕሪቶሪያ ግጭትን በዘላቂነት የመቋጨት ስምምነት ከተፈረመ በኋላ አሁንም በሴቶች ላይ የሚፈጸመው መደፈሩ በከፍተኛ ሁኔታ እንደቀጠለ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ለተደፈሩ ሴቶች የህክምና እና የሥነ ልቦና አገልግሎት የሚሰጠው በዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል የሚገኘው ‘ዋን ስቶፕ ሴንተር’ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የጤና ባለሙያ በዚህ ዓመት “በግንቦት እና ሰኔ ወር ብቻ በየወሩ 100 የተደፈሩ ሴቶች መጥተዋል” ይላሉ።
ባለፈው ዓመት ደግሞ በወር ከ200 እስከ 100 ሴቶች ተደፍረው ይመጡ እንደነበር የሚናገሩት የሆስፒታሉ ባለሙያ፣ በዚህም ሳቢያ የመደፈር ሰለባ የሆኑት ታዳጊዎች እና ሴቶች ለኤችአይቪ እንዲሁም ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ መሆናቸውን ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።
“በጦርነቱ ጊዜ በጠላት ኃይሎች ሲደፈሩ ነበር። አሁን ግን በትግራይ ሰዎች ነው እየተደፈሩ ያሉት። በጣም የሚያሳዝነው በሌሎች ኃይሎች ሴቶች ሲደፈሩ ብዙ ጩኸት ነበር፤ የራሳችን ሰው ሲፈፅመው ግን ለፖለቲካዊ ትርፍ ሲባል ዝም ተባለ” በማለት በሴቶች ላይ እየተፈጸመ ያለው ወንጀል ትኩረት አለማግኘቱን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል እየተፈጸሙ ባሉ ግድያዎች፣ እገታዎች እና ጥቃቶች ምክንያት በነዋሪው ዘንድ ከፍተኛ ፍርሃት እንዳለ እና በሰላም ወጥቶ መመለስ እጅግ አስጨናቂ እንደሆነ ታዳጊዎች እና ሴቶች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ግድያዎች፣ እገታዎች መደፈሮች በትግራይ ለምን ተበራከቱ?
ሂዩማን ራይትስ ፈርስት የተሰኘው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በትግራይ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሱ ይፋ አድርጓል።
ለዚህም ከጦርነቱ በኋላ በክልሉ ውስጥ በተለይም በከተሞች አካባቢ የወንጀል መከታተል ሥራን የሚሠራው የፖሊስ ኃይል መዳከም እና የፀጥታ ክፍተት አንደኛው ችግር እንደሆነ ጠቁሟል።
በትግራይ የጦርነቱን መቋጨት ተከትሎ ህወሓት ወደ መቀለ ሲመለስ በጦርነቱ ወቅት የትግራይ ፖሊስ ኮሚሽን “በጦርነቱ ጊዜ ክዶናል” በሚል ተቋሙ ፈርሶ አባላቱ እንዲበተኑ ተደርገዋል።
በዚህም ሦስት ሺህ የሚሆኑ ነባር የትግራይ የፖሊስ አባላትን ከሥራቸው በማባረር ከትግራይ ሠራዊት በተውጣጡ እንዲተኩ የተደረገ ሲሆን፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሲቋቋምም ይኸው እንዲቀጥል ተደርጓል።
የሂዩማን ራይትስ ፈርስት ምክትል ዳይሬክተር አቶ መብርሂ ብርሃነ የትግራይ ፖሊስ መበተን አሁን ለተፈጠረው የፀጥታ ችግር አንዱ ምክንያት እንደሆነ ያስረዳሉ።
“ፖሊስነት ራሱን የቻለ ሙያ ነው። በልምድ የሚሠራ አይደለም። ፖሊስን እንዲተኩ የተደረጉ የትግራይ ሠራዊት አባላት የወንጀል መከላከል እና የምርመራ ቴክኒክ ልምድ የላቸውም። የፖሊስ ግንዛቤ እና እውቀት የላቸውም፤ የሕግ ዕውቀታቸውም የተወሰነ ነው” ይላሉ።
ጨምረውም ይህ ሙያው የሌላቸው ሰዎች የፖሊስን ኃላፊነት መረከባቸው በወንጀል መከላከል በኩል ትልቅ ክፍተት እንደፈጠረ እንዲሁም ገለልተኛ የሆነ ተቋም እንዳይኖር ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ።
ጠበቃ እና የሕግ አማካሪዋ ሰላም ኪዳነ በበኩላቸው የትግራይ ፖሊስን እንደ ተቋም በፖለቲካዊ ውሳኔ በማፍረስ ልምድ በሌለው አዲስ ፖሊስ መተካቱ ሕጋዊ እንዳልነበር ጠቅሰው፤ ተቋማቱ በዚያው መቀጠል ነበረባቸው ይላሉ።
አንድ መንግሥት የሚቋቋምበት ዓላማ የሕብረተሰብን ደኅንነት ለመጠበቅ ነው የሚሉት የሕግ ባለሙያዋ፤ በትግራይ ግን ይህ እየታየ እንዳልሆነ ያስረዳሉ።
“አሁን ፖሊስ የሆኑት በርካቶቹ በጦርነቱ ጓዶቻቸውን እየሰዉ የመጡ እና ዘግናኝ ነገሮች ያዩ ሲሆኑ፣ ከዚህ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት እንዲያገግሙ በቂ ሥልጠና ሳይሰጣቸው ወደ ፖሊስነት ተቀላቅለዋል። ከዚህም በተጨማሪ በቂ ደመወዝ አይከፈላቸውም ይህም ክፍተት ፈጥሯል” ይላሉ።
የሴቶች መብት እና ብቃት ላይ የሚሰራው “ጎርዞ” የተባለው ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ሰብለወርቅ ለማ ትግራይን እያስተዳደረ ያለው አካል ፀጥታውን በማስከበሩ ረገድ ቆራጥነት እንዳልታየበት ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, MILLION
በክልሉ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር እየሠሩ እንዳሉ የሚገልጹት ሰብለወርቅ አንድ አገር ደህንነቱ የተጠበቀ የሚሆነው ህፃናት እና ሴቶች ደህንነታቸው ሲጠበቅ እንደሆነ ያስረዳሉ።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለሴቶች ዋስትና እንዲሰጥ እና የጥቃት ሰለባ ለሆኑት ፍትህ እንዲያረጋግጥ በደብዳቤ ጠይቀው መልስ እንዳልተሰጣቸውም ገልጸው “እንደ መንግሥት አስተዳድራለሁ የሚል አካል የዜጎቹን ዋስትና ማረጋገጥ ግዴታው ነው። ይህን ካላደረገ ግን እኛም ተራችን ነው የምንጠብቀው” በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የሕግ አማካሪዋ በበኩላቸው በክልሉ በዳኝነት ላይ ፖለቲካዊ ጣልቃገብነት መታየቱ፣ ፍርድ ቤቶች እና ዳኞች ነጻ በሆነ መንገድ አለመሥራታቸው እንዲሁም ጫና እያረፈባቸው በመሆኑ የፍትህ ሂደቱን አስተጓጉሎታል ይላሉ።
በዚህም ሳቢያ የጥቃት ሰለባዎችም በአስቸኳይ ፍትህ እንዳያገኙ ክፍተት ፈጥሯልም ይላሉ።
በህወሓት እና በጊዜያዊ አስተዳደር መካከል እየታየ ያለው አለመግባባት በክልሉ ለተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች እና ወንጀሎች መበራከት ምክንያት እንደሆነም የሚናገሩ አሉ።
የፀጥታ ባለሙያ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር የሆኑት አቶ ብስራት አማረ በትግራይ የተከሰተው የፀጥታ እና ደኅንነት ተግዳሮት ከጦርነቱ በኋላ በክልሉ ያጋጠመው “ፖለቲካዊ ውድቀት” መገለጫ ነው የሚል እምነት አላቸው።
ለዚህም በአሁኑ ወቅት በክልሉ የተፈጠረው “የፋይናንስ ኦሊጋርኪ” የሚሉት እንደ ሁለተኛ መንግሥት የሆነው አካል ሁሉንም የተቆጣጠረ የተደራጀ ኃይል ነው ይላሉ።
ምሁሩ “አሁን በትግራይ አንድ ገዢ ኃይል ተፈጥሯል። የክልሉን ሀብት፣ ንብረት እና ሥልጣን ተቆጣጥሯል። ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ያለው እና ጄኔራሎች፣ ነጋዴዎች፣ የከሰሩ ፖለቲከኞች እንዲሁም የራሱን ትርክት ያየዘ ‘የኢኮኖሚ መደብ’ ተፈጥሯል። ይህ ቡድን ማንን እንደሚወክል አይታወቅም፤ ከዚህም ከዚያም የተሰባሰቡ “የፋይናንስ ኦሊጋርኪ ናቸው” ይላሉ።
ይህ ቡድን በትግራይ ሁሉንም ያማከለ መንግሥት እንዳይኖር እየሠራ ነው የሚሉት ምሁሩ፤ ክልሉ ከዚህ ኃይል ጋር እየታገለ ነው ይላሉ።
ሌሎች ደግሞ በበኩላቸው በትግራይ ፀጥታ እና ደኅንነት ማስፈን የሚችል አቅም እንዳለ እና አሁን እየታየ ያለው ከባድ የፀጥታ ችግር ገዢው አካል ሕዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎችን ላለመመለስ ሆን ብሎ ችላ ያለው ነገር ነው ሲሉ ይተቻሉ።
ቀጣይ የትግራይ ትልቁ ስጋት እና መፍትሄ
አቶ መብርሂ በሴቶች እና ታዳጊዎች ላይ እየተፈፀሙ ያሉት ጥቃቶች ካልተገቱ ትግራይ የወንጀሎች፣ የሴቶች መደፈር እና የግድያ ማዕከል ስለምትሆን ወደ “ሥርዓት አልበኝነት (አናርኪዝም) ሊኬድ ይችላል” የሚል ስጋት አላቸው።
ምክትል ዳይሬክተሩ እንደ መፍትሄ “ከ20/30 ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው የትግራይ ነባር ፖሊሶች ወደ ሥራ ገበታቸው መመለስ አለባቸው። የሥነ ምግባር ችግር ካለም በሕግ ይጠየቁ። ሕብረተሰብን የሚያሳትፍ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂም ያስፈልጋል” ይላሉ።
ሰላም በበኩላቸው ትግራይን እያስተዳደረ ያለው አካል አፋጣኝ መፍትሄ ማምጣት ካልቻለ አሁን እየተፈጸሙ ያሉ ወንጀሎች እየጨመሩ ሥርዓት አልበኝነት እንደሚፈጠር እና ፍትህን በራስ ወደማረጋገጥ እርምጃ ይገባል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
የፈረሰው የፀጥታ ሁኔታ ወደነበረበት የሚመለሰው ሁሉም ሕብረተሰብ የሚቀበለው እና የተለያዩ የፖለቲካዊ ኃይሎች የሚሳተፉበት የጋራ አስተዳደር ሲመሠረት እንደሆነ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ብስራት ያስረዳሉ።












