ለወሲባዊ ጥቃት ሰለባዎች ባደረገችው ድጋፍ ከካናዳው ድርጅት ዕውቅና የተሰጣት ሲስተር ካህሳ ሀጎስ

ሲስተር ካህሳ ሀጎስ

በአዲግራት ሆስፒታል ነርስ የሆነችው ሲስተር ካህሳ ሀጎስ በትግራይ ጦርነት ወቅት ወሲባዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ታዳጊዎች እና ሴቶች ላደረገችው ሙያዊና ሰብአዊ ድጋፍ ግሎባል አፌይርስ ከተባለው የካናዳ ድርጅት ሽልማት ተበርክቶላታል።

ድርጅቱ የካናዳ ዲፕሎማሲያዊ እና ቆንስላ ትብብሮችን የሚያስተዳድር ሲሆን የሀገሪቱን አለም አቀፍ ንግድ የሚያስፋፋ እና አለም አቀፍ ልማት እና ሰብአዊ እርዳታን የሚመራ መንግስታዊ ክፍል ነው።

ሲስተር ካህሳ ሀጎስ፤ የካናዳ ድርጅት ከተባበሩት መንግስታት ጋር በመተባበር የሚያበረክተው “ሰላምና ደህንነት በሴቶች” የተሰኘው ሽልማት ተቀባይ ሆናለች።

ካህሳ “ከ2013 ጀምሮ ላበረከትኩት አስተዋጽዖ የተሰጠኝ ነው። ለሁለት ዓመታት ያህል የወሲባዊ ጥቃት ሰለባዎችን እንከባከብ ነበር” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት በርካታ ሴቶች፣ እናቶች እና ሕፃናት አሰቃቂ የሚባሉ የወሲባዊ ጥቃቶች ሰለባ መሆናቸውን በርካታ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች አረጋግጠዋል።

በጦርነቱ በትግራይ በሰላማዊ ዜጎች ላይ መደፈር፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የዘፈቀደ ግድያ እና ረሃብ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ሪፖርት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶች በሚያጣራው የሰብዓዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን ባወጣው ሪፖርት ወሲባዊ ባርነትን ጨምሮ፣ በደቦ መደፈርና በተደጋጋሚ መደፈርና እንዲሁም በልጆቻቸውና በቤተሰቦቻቸው ፊትም የተደፈሩ አሉ ብሏል።

ከመደፈሩ በተጨማሪ የማዋረድ ስራዎች፣ ድብደባዎች፣ ባዕድ ቁሶችን በብልት ውስጥ መጨመርም ነበሩ ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጥቅምት 24/ 2013 ዓ.ም የትግራይ ጦርነት ሲቀሰቀስ ሲስተር ካህሳ ሀጎስ በአዲግራት ሆስፒታል የእናቶች እና ህጻናት እንክብካቤ ክፍል አስተባባሪ ሆና ትሰራ ነበር።

በትግራይ እና በማዕከላዊ መንግሥት እና አጋሮቹ መካከል የነበረው ውጊያ እየተባባሰ ሲሄድ የወሲባዊ ጥቃቶች ሰለባ ሆነው ወደ ሆስፒታል የሚመጡ ሴቶች እና እናቶች ቁጥር እየጨመረ መጣ።

ሲስተር ካህሳ በጦርነቱ ምክንያት ተጎጂ ለሆኑ ከ400 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ቤት ተከራይታ፤ ሙያዊ ክትትልና ድጋፍ አድርጋለች።

“ጦርነቱ ሲጀመር [እርዳታ ፈላጊዎች] በብዛት ወደኛ መምጣት ጀመሩ። ብዙ ችግር ነበረብን። ብዙ ዓይነት በደል የደረሰባቸው እናቶች ናቸው። የሚሄዱበት ቦታ የሌላቸውም ነበሩ። ምክንያቱ የእነርሱ የደህንነት ጉዳይ ነው” ትላለች።

ምንም እንኳ ሁኔታዎች ምቹ ባይሆኑላትም ካህሳ ለወሲባዊ ጥቃት ሰለባዎች የማቆያ ማዕከል ለማቋቋም ወሰነች። ከዚህ ባለፈው የተወሰኑ ታካሚዎችን ደግሞ ለተሻለ ሕክምና ወደ መቀለ አይደር ሆስፒታል እንዲላኩ ማድረግ ጀመረች።

"በወቅቱ በርካታ ታካሚዎች ነበሩን። ፊስቱላ የነበረባቸውን ለሕክምና ወደ መቀለ ላክናቸው" ትላለች ሲስተር ካህሳ ሀጎስ።

ሲስተር ካህሳ እንደምትለው ጦርነቱን ተከትሎ ከ4 ሺህ በላይ ተጎጂዎች ወደ አዲግራት ሆስፒታል መጥተው ሪፖርት አድርገዋል።

የሕክምና ባለሙያዋ ተጎጂዎችን ለመርዳት በምታደርገው ጥረት እንደ ካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን እና አይሲአርሲ ያሉ ድርጅቶች የገንዘብ እና ሙያዊ ድጋፍ እንዳደረጉላት ትናገራለች።

"ወደ ቤተ-ክርስትያን አሊያም ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ የሚቸገሩ እናቶች ነበሩ። አሁንም ገና ሙሉ በሙሉ አላገገሙም። እኛ ደኅንነታቸውን ስንጠብቅ ነው የቆየነው እንጂ ሥነ-ልቦናዊ ሁኔታቸው እና ኢኮኖሚያቸው ክፉኛ ተጎድቷል። መድኃኒት ስንሰጣቸው ለመዋጥ የሚቸገሩ ተጎጂዎች ነበሩን" ስትል የነበረውን ሁኔታ ታወሳለች።

እሷ ተጎጂዎችን ለመርዳት በምታደርገው ጥረት ምክንያት በሆስፒታሉ ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች የሚረዱበት የሥነ-ልቦና፣ የሥነ-አእምሮ እና የሥነ-ተዋልዶ ማዕከል እንዲከፈት ሆኗል።

ነገር ግን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያሳለፈችው ሕይወት የራሱን ጠበሳ አሳርፎባታል። ለከፍተኛ ሥነ-ልቦናዊ ቀውስ አጋልጧታል።

"ከቶውንም ቢሆንም ከጭንቅላትሽ የማይፋቁ ብዙ ጠባሳዎች አሉ። ሰምተነው በማናውቀው መንገድ ጥቃት የደረሰባቸው አሉ። መኖሬን የጠላሁበት አጋጣሚ ነበር። በኢኮኖሚና በሌላ መንገድ እየተሰቃየሁ ነው የምሠራው" ስትል ያሳለፈችውን መንገድ ታወሳለች።

ትግራይ የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች ተዛምቶ፤ በርካታ ዜጎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፤ ሚሊዮኖች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለማሕበራዊ ቀውስ ተጋልጠዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በጦርነቱ የጦር ወንጀሎች፣ በሰብዓዊነት የሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ የዘር ማጽዳት እና መደፈር እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን የተለያዩ የሰብዓዊ ተቋማት መግለጣቸው አይዘነጋም።

ለእነዚህ ተጎጂዎች ሥነ-ልቦናዊ ድጋፍ ለማድረግ የባለሙያዎች እጥረት መኖሩን የምትናገረው ሲስተር ካህሳ በርካቶች ለተላላፊ በሽታዎች መጋለጣቸውን እንዲሁም መገለል እየደረሰባቸው እንዳለና ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት መበላሸቱን ትናገራለች።

"ወሲባዊ ጥቃት ሲደርስባቸው ለበሽታ እና ላልተፈለገ እርግዝና ሊጋለጡ ይችላሉ። ከማያውቋቸው ወንዶች የተወለዱ ልጆችን ለማሳደግ የተገደዱ እናቶችም አሉ። ሕፃናቱን ባዩዋቸው ቁጥር ጥሩ ስሜት እንደማይሰማቸው የሚናገሩ እናቶችም አጋጥመውኛል" ትላለች።

ወሲባዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር እርዳታ እንዲያገኙ ለማድረግ የምትሞክረው ሲስተር ካህሳ "በገንዘብ እና በአንዳንድ ሁኔታዎች ስለታገዙ ብቻ መፍትሔ ይመጣል ማለት አይደለም" ትላለች።

ተጎጂዎቹ የደረሰባቸውን ነገር ማንም እንዲያውቀው ስለማይፈልጉ ብዙውን ጊዜ "ከሰው ተገልለው" እንደሚያሳልፉም ትናገራለች።