በ12 ሰከንድ 25 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ክሪፕቶ የሰረቁት አሜሪካዊያን ወንድማማቾች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ክሪፕቶከረንሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ካሉ ስመ ገናና ዩኒቨርሲቲዎች በአንዱ የተማሩ ሁለት ወንድማማቾች በ12 ሰከንድ ውስጥ 25 ሚሊዮን ዶላር በክሪፕቶከረንሲ ዘርፈዋል ተብሎ ክስ ተመሰረተባቸው።

የ24 ዓመቱ አንቶን ፔርየር-ቡኖ እና የ28 ዓመቱ ጀምስ ፔርየር-ቡኖ በበይነ መረብ ማጭበርበር እና በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ተከሰዋል።

የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ዝርፊያው በዓይነቱ የመጀመሪያው ነው ሲል ገልጾታል።

በማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (ኤምአይቲ) ተምረዋል የተባሉት ወንድማማቾች ዝርፊያውን ሚያዝያ 2023 መፈጸማቸውን ዓቃቤ ህግ ተናግሯል።

"የፔርየር-ቡኖ ወንድማማቾች በቴክኖሎጂ የተራቀቀውን ዝርፊያ በኢቴርየም ክሪፕቶከረንሲ ላይ መፈጸማቸውን እና ለዚህ ለወራት ሲያሴሩ ቆይተው በሰከንዶች ውስጥ 25 ሚሊዮን ዶላር መዝረፋቸውን” ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ሊዛ ሞናኮ ተናግረዋል።

“በዓይነቱ የመጀመሪያው የሆነውን የበይነ መረብ ማጭበርበር እና ህወጥ የገንዘብ ዝውውርን ዘዴን” ለመፍታት የአገር ውስጥ ገቢ አገልግሎት (አይአርኤስ) ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል ሲሉ አክለዋል።

ዓቃቤ ህግ አክሎም "በአለም ላይ ስመ ገናና ከሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች በአንዱ" የተማሩትን ልዩ ችሎታ በመጠቀም የኢቴርየምን የገንዘብ ዝውውርን ለማጽደቅ ተጠቅመውበታል ብሏል።

ከክስ ፋይሉ መረዳት እንደሚቻለው ወንድማማቾቹ ሒሳብ እና ኮምፒዩተር ሳይንስ ያጠኑ ሲሆን፤ ሁለቱም ኤምአይቲ መማራቸውን የዜና ዘገባዎች ጠቁመዋል።

የአሜሪካ አቃቤ ህግ ዴሚያን ዊሊያምስ ረቡዕ ዕለት በሰጠው መግለጫ የክሪፕቶ ክፍያዎችን የሚመዘግብውን የህዝብ መዝገብ በመጥቀስ "የተከሳሾቹ ድርጊት የብሎክቼይን ትክክለኛነት ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል” ብለዋል።

ወንድማማቾቹ ከኢቴርየም ነጋዴዎች መስረቅ የቻሉ ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ በህገወጥ መንገድ በመግባት በሂደት ላይ ያለ ግዢን በመቀየር የተጎጂዎቻቸውን ክሪፕቶከረንሲ ማግኘት መቻላቸው ተነግሯል።

መርማሪዎች “መበዝበዝ” ሲሉ የገለጹትን ሂደት ለመፈጸም የሰከንዶች ጊዜ ብቻ ፈጅቷል።

በኤቴሬም ተወካይ ገንዘቡን እንዲመልሱ የተጠየቁት ወንድማማቾቹ ፈቃደኛ ካመሆናቸውም በላይ የተሰረቁትን ለመደበቅ የተለያዩ እርምጃዎችን እንደወሰዱ ባለስልጠናት ተናግረዋል።

"ልብ ወለድ" በሚመስለው የማጭበርበር ጉዳይ የወንጀል ክስ ሲቀርብ ይህ የመጀመሪያው እንደሆነ ዓቃቤ ህግ አስታውቋል።

ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እያንዳንዳቸው ከ20 ዓመት በላይ እስራት ይጠብቃቸዋል።