የኢትዮጵያ መንግሥት የአሜሪካው አምባሳደር "ያልተጠየቁትን ምክር" ሰጥተዋል ሲል ወቀሰ

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሰደር ኧርቪን ማሲንጋ

የፎቶው ባለመብት, US EMBASSY AA/FB

በኢትዮጵያ የአሜሪካው አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ በቅርቡ በሀገሪቱ ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ ያሰሙት ንግግር "በደንብ ያልተጤነ" ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወቀሰ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሐሙስ፣ ግንቦት 8/ 2016 ባወጣው መግለጫ የተቸው ንግግር አምባሰደር ማሲንጋ ከጥቂት ቀናት በፊት በኢትዮጵያ ያሉ ሰብዓዊ መብቶች እና ውይይቶችን በተመለከተ አገራቸው ያላትን ፖሊሲ በተመለከተ ያሰሙትን ነው።

አምባሳደር ማሲንጋ መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች እንዲቆሙ፤ ያልተገደበ ሰብአዊ አቅርቦት እንዲኖር እና ለዚህም መነሻ የሚሆን ጊዜያዊ አገር አቀፍ የተኩስ አቁም አንዲደረግ አሳስበው ነበር።

አምባሳደሩ ጠንከር ባለ ንግግራቸው ሽፍቶች፣ ታጣቂ ቡድኖችና አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በህይወት የመኖር እና የመከባበር መብቶች ላይ ጥሰት መፈፀማቸው የሕግ ሂደትንና የሕግ የበላይነት አለማክበርን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአምባሳደሩ ንግግር "ብልኃት የሚጎድለው" ነው ብሏል።

መግለጫው አክሎ አምባሳደር ማሲንጋ "ሳይጠየቁ" ለኢትዮጵያ መንግሥት ምክር ለመለገስ ሞክረዋል ሲል ወቅሶ "ያልተገባ ክስ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ቀርቧል" ብሏል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአዲስ አበባ የዋሺንግተን ተወካይ የሆኑት ማሲንጋ የሰጡት አስተያየት "ከሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ እና መልካም ወዳጅነት ጋር የሚቃረን" ነው ሲልም ተችቷል።

"ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት፣ ሰብዓዊ መብት ለማስጠበቅና ዲሞክራሲን ማለምለምን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከአሜሪካ ጋር ውይይት ለማድረግ ዝግጁ ናት። ሚኒስቴሩ አዲስ አበባ ከሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ጋር ተባብሮ መግለጫውን ላይ የተንፀባረቁ ስኅተቶችና አለመጣጣሞችን ለማረም ዝግጁ ነው።" ብሏል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሰደር ኧርቪን ማሲንጋ

የፎቶው ባለመብት, US DEPT OF STATE

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አምባሳደሩ ይህን ንግግር ያሰሙት በጣሊያን ወረራ ወቅት የየካቲት 12 ጭፍጨፋ ሲካሄድ 750 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ተሸሽገውበት በነበረበት እና በአሁኑ ወቅት ደግሞ የየመን ማህበረሰብ ትምህርት ቤት አካል በመሆን በሚያገለግለው በቀድሞው የአሜሪካ ቆንስላ ግቢ ነው።

በጦርነት እና ግጭት ጊዜም ቢሆን “የሰብዓዊ መብት እና ሰብዓዊ ክብር” ሊረሱ አይገባም ያሉት አምባሳደር ማሲንጋ በግጭት ወቅት “የሁሉም ዜጎች በተለይም የሰላማዊ ነዋሪዎች ደህንነት መጠበቅ አለበት” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

አምባሳደር ማሲንጋ በንግግራቸው የታጠቁ ኃይሎች "ከውይይት ይልቅ በሁከት ፖለቲካዊ ዓላማዎችን ለማሳካት መሞከራቸው በደሎች እንዲፈጸሙ በር ይከፍታል" የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

በመላ አገሪቱ ያሉ ሰላማዊ ዜጎች ከሕግ አግባብ ውጭ ግድያ፣ የዘፈቀደ እስራት፣ በግዳጅ መሰወር፣ ከግጭት ጋር የተያያዘ ጾታዊ ጥቃት እና ሌሎችም ጥቃቶች በተለያዩ ተዋናዮች እየተፈጸመባቸው መሆኑን የሚገልጹ ዘገባዎችን በማየታቸው ማዘናቸውንም ጠቅሰዋል።

ማሲንጋ እኒህ ችግሮች "እውነተኛ እና ግልጽ የሽግግር ፍትሕ ሂደትን በመሳሰሉ መንገዶች በአስቸኳይ እና ተጠያቂነት በሰፈነበት መልኩ ሊፈቱ ይገባል” ብለዋል።

"የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት ዳሬሰላም ድረስ በመጓዝ ችግሩን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ልባዊ ጥረት አድርጋችኋል። እጅ አትስጡ” በማለት በግጭቱ እየተሰቃየ ላለው ኅብረተሰብ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት መሥራታቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

ፋኖን በተመለከተ ደግሞ “እናንተ ራሳችሁን ፋኖ ብላችሁ የምትጠሩ” ያሉት አምባሳደሩ “ለውይይት ዕድል መንፈጋችሁ የሚጠቅማችሁ እንዳልሆነ ልትረዱ ይገባል። እንደሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች በቀጠለው ግጭት ምክንያት እየተሰቃዩ ያሉት ንጹሀን ዜጎች ናቸው። ብዙ የአማራ ተወላጆች ጥያቄያቸው ፍትሃዊ እንደሆነ ያምናሉ። ይህንን ደግሞ ማሳካት የሚቻለው በውይይት እንጂ በግጭት አይደለም” ብለዋል።

ህወሓት በበኩሉ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ መኖሪያቸው መመለስን ጨምሮ ሌሎችም እልባት ያላገኙ ጉዳዮችን በተመለከተ፤ “አካታች፣ ስርዓት እና የሰዎችን ክብር የጠበቀ” አካሄድ እንዲከተል አምባሳደር ማሲንጋ መክረዋል።

“ለውይይት ጊዜው አሁን ነው” ያሉት ማሲንጋ፤ ታጣቂ ቡድኖች ራሳቸውን ለውይይት እንዲያዘጋጁ መክረዋል። በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያለው የሀገራዊ ምክክር ሂደት “ፍጹም ባይሆንም” ሁሉም ወገኖች የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባቸው አበክረው አስገንዝበዋል።

የዋሺንግተን አምባሳደር በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ላይ እንዲህ ዓይነት ጠንከር ያለ አስተያየት ሲሰጡ መመልከት እምብዛም የተለመደ አይደለም።

አሜሪካ በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አፋር እና አማራ ክልልሎች የተዛመተውን የርስ በርስ እልባት እንዲያገኝ ሚና መጫወቷ የሚጠቀስ ሲሆን በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል በዳሬሰላም በነበረው ድርድር በተለያየ ደረጃ ተሳታፊ መሆኗ ይታወቃል።