‘ኢጃዛ ቤት’፡ በዱባይ ከ30 በላይ ኢትዮጵያውያን በአንድ ክፍል ውስጥ የሚኖሩበት ቤት

ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞች በብዛት በሚኖሩባቸው የአረብ አገራት የተለመደ ነው። ስያሜውን ብዙዎቹ እንደ አገርኛ ቋንቋ ቆጥረው ይግባቡበታል።
በቤት ሠራተኝነት የሚሠሩ ሴቶች እና ሥራ ያጡ ዜጎች እንደመቆያ የሚጠቀሙበት ነው። በተለምዶ “ኢጃዛ ቤት” ይሉታል።
ኢጃዛ ቤት ማረፊያ ብቻ አይደለም። ብዙ ሰቆቃዎችን እና ብሶቶችን በውስጣቸው የያዙ ኢትዮጵያውያን የሚጠለሉበት ቦታ ነው።
በአሠሪዎቻቸው የተደፈሩ፣ በሰውነታቸው ላይ ሙቅ ውሃ የተደፋባቸው፣ በደላሎች ተታለው ገንዘባቸውን የተቀሙ፣ በራሳቸው ቤተሰብ [የቅርብ ቤተሰብ ወይም የፍቅር ጓደኛ] ክህደት የተፈጸመባቸው፣ ፓስፖርታቸው በወቅቱ ባለመታደሱ ሕጋዊነታቸውን ያጡ፣ ለዓመታት የሠሩበትን ደመወዝ የተከለከሉ እና ሌሎች አሳዛኝ ገጠመኞችን ያስተናገዱ ኢትዮጵያውያን የሚሰባሰቡበት ነው።
እነዚህ ኢጃዛ ቤቶች በስፋት ከሚገኙባቸው የአረብ አገራት ከተሞች መካከል የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የንግድ ከተማ ዱባይ አንዷ ነች።
ከአገሬው ሰው በላይ የሌሎች አገራት ሰዎች በብዛት የሚገኙባት ዱባይ፣ ከቅንጡ የመዝናኛ እና የመኖሪያ ቤቶቿ በተጨማሪ እስከ 30 እና 40 ሰዎች በአንድ ቤት ታጭቀው የሚኖሩባትም ናት።
ከአገሪቱ ሰባት ግዛቶች የንግድ እና የቱሪዝም መዳረሻ የሆነችው ዱባይ፣ ከአቡ ዳቢ እና ሻርጃ ጋር ትዋሰናለች።
ሻርጃ እና ዱባይ እንደ አንድ ከተማ የሚታወቁ ነገር ግን ሁለት የተለያየ የግዛት አስተዳደር ያላቸው ከተሞች ናቸው።
በተለይ በአነስተኛ የሥራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ዱባይ እየሠሩ መኖሪያቸው ሻርጃ ያደርጋሉ። ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ሻርጃ የቤት ኪራይ አንጻራዊ ቅናሽ ስላለው ለኑሮ ተመራጭ ነው።
በአንጻሩ ዱባይ ደግሞ የተሻለ ሥራ ይገኛል። በዚህም ምክንያት አብዛኛው ሰው ዱባይ ይሠራል፣ ሻርጃ ይኖራል። ለዚህም ይመስላል የኢትዮጵያውያን ኢጃዛ ቤቶች ከዱባይ ይልቅ በሻርጃ በብዛት የሚገኙት።
የእረፍት ማሳለፊያ እና መጠለያ
አቶ ብርሃኑ አቦታ* በዱባይ መኖር ከጀመረ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል። ሻርጃ ውስጥ የተከራየው ሁለት ክፍል ቤት አለው። ኢጃዛ ቤት ነው። ብርሃኑ ይህንን ሥራ ከጀመረ ከሁለት ዓመት በላይ ሆኖታል።
በተከራየው ሁለት ክፍል ቤት ውስጥ እንደየጊዜው ሁኔታ ቁጥራቸው የሚለያይ በርካታ ኢትዮጵያውያን ተጠልለው ይኖራሉ። አንዳንዴ እስከ 40 የሚደርሱ ሰዎች በሁለቱ ክፍሎች ውስጥ እንደሚኖሩ ብርሃኑ ይናገራል።
የኢጃዛ ቤት ደንበኞች ሁለት ዓይነት ናቸው። ግማሾቹ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥረው የሚሠሩ ነገር ግን የእረፍት ቀናቸውን ለማሳለፍ የሚመጡ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሥራ ተፈናቅለው በጊዜያዊነት የሚጠለሉ ናቸው።
ብርሃኑ በአሁኑ ወቅት በሁለቱ ክፍል የሚያኖራቸው 33 ተከራዮች አሉት። ከእነዚህ መካከል 16 የሚሆኑት ሥራ የሌላቸው ናቸው።
ቀሪዎቹ ደግሞ የእረፍት ጊዜያቸውን ለማሳለፍ ወደ ጎራ የሚሉ ናቸው። አንደኛው ክፍል ለሴቶች ሲሆን፣ ሌላኛው የወንዶች ነው።
የተከራዮቹ ልብስ እና አንዳንድ መገልገያዎች በሻንጣ እና በማዳበሪያ ውስጥ ታጭቀው ጥግ ላይ ተቀምጠዋል። በሌላኛው ጥግ ደግሞ ለእርሱ መኝታ የተዘጋጀች አነስተኛ አልጋ አለች።
ወለሉ ላይ ምንጣፍ ዘርግተው ተከራዮቹ ሌሊቱን ያሳልፋሉ። ሁሉም አንድ መጸዳጃ ቤት እና አንድ ማብሰያ ቤት ይጋራሉ።
ቤቱን በጎበኘንበት ወቅት 10 የሚደርሱ ተከራዮች በቤት ውስጥ ነበሩ። ብዙዎቹ ሥራ የሌላቸው ናቸው። ሁሉም የየራሳቸው የበደል ገጠመኝ አላቸው።
ብርሃኑ እስከ ዛሬ ከሰማቸው ገጠመኞች መካከል በቅርቡ ወደ እርሱ ቤት የመጣችው የሕይወት ገጠመኝ ይለይበታል።

የሕይወት እንግልት በደላሎች እጅ
ሕይወት* የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ በደላሎች አማካይነት ዱባይ የሄደችው ከጥቂት ወራት በፊት ነው። እንደ ደረሰች አጅማን ወደ ተባለው የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ግዛት ተወሰደች።
የአንድ ወር የቱሪስት ቪዛ ተሰጥቷት ነው ወደ ኤምሬትስ የሄደችው። ቪዛው ከማለቁ በፊት ሥራ አስጀምረው የሥራ ፈቃድ እንደሚያሰጧት ደላሎቹ ቃል ገብተውላት ነበር። የሆነው ግን ከተባለው ተቃራኒ ነው።
ሕይወት አጅማን እንደደረሰች ለአንዲት ኢትዮጵያዊት ተላልፋ ተሰጠች። ይህች ኢትዮጵያዊትም ደላላ ነች። ከዛሬ ነገ ሥራ ያስጀምሩኛል ብላ ብትጠብቅም መልስ የለም። እንዲያውም ደላላዋ “አንቺን ለማምጣት ላወጣሁት ወጪ ቤተሰቦችሽ እንዲከፍሉ ንገሪያቸው” የሚል ትዕዛዝ ሰጠቻት።
የሕይወት ቤተሰቦች የተጠየቀውን ገንዘብ መክፈል የማይችሉ በዝቅተኛ የኑሮ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን በመግለጽ መክፈል እንደማይችሉ ለማስረዳት ብትሞክርም የሚራራላት አላገኘችም።
በዚህ ሁኔታ ሕይወት ለሁለት ወር አንድ ቤት ውስጥ ታግታ ቆየች። ለአንድ ወር የተሰጣት የቱሪስት ቪዛ በማብቃቱ ሕጋዊነቷን አጥታ ችግሯን “አቤት” የምትልበት መብት አጣች።
በዚህም ምክንያት ደላላወ ከፍተኛ ወከባ ፈጸሙባት። ሕይወትም በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ እየደወለች ገንዘብ ከፍለው ሕይወቷን እንዲያተርፉላት ቤተሰቦቿን እና ጓደኞቿን ስትማጸን ቆየች። ያም ሆኖ ግን የተጠየቀውን ገንዘብ መክፈል የሚችል ወገን ማግኘት አልቻለችም።
ያገኘቻት ሴት ሕይወት ገንዘቡን መክፈል እንደማትችል ስትረዳ በደረቅ ሌሊት ከቤት አስወጥታ መንገድ ላይ ጣለቻት። ምን ማድረግ እንዳለባት ግራ የገባት ሕይወት የሚረዳት ሰው ፍለጋ ጎዳና ላይ ስትንከራተት አደረች።
በማግሥቱ አንድ ኢትዮጵያዊ አግኝታ የገጠማትን ሁኔታ አስረዳችው። ይህ ሰው በቀጥታ ችግሯን ሊቀርፍላት ባይችልም መፍትሔ ይሆናል ብሎ ያመነበትን አማራጭ አቀረበላት።
ለጊዜው ወደ ኢጃዛ ቤት እንድትሄድ እና ከዚያም ራሷን አረጋግታ ሥራ እንድትፈልግ ምክር ለገሳት። አማራጭ ያልነበራት ሕይወት በሐሳቡ ተስማማች። ያ ሰው ከብርሃኑ ጋር አገናኛት።
በብርሃኑ ኢጃዛ ቤት የምትገኘው ሕይወት በተፈጸመባት ወከባ እና ጫና ምክንያት የአዕምሮ መታወክ ስለገጠማት ከሰዎች ጋር ያላት ግንኙነት ነው። ስለሁኔታው ወደኋላ ተመልሳ ማውራትም ሆነ ማስታወስ አትፈልግም።
ከሕጋዊነት ወደ ሕገ ወጥነት
ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ተመሳሳይ ገጠመኝ አላቸው። በቤት ሠራተኝነት ከሄዱ በኋላ ብዙ በደል የሚደርስባቸው በራሳቸው ወገኖች [በኢትዮጵያውያን] ነው።
በሕጋዊ መንገድ ያገኙትን ሥራ ለቀው እንዲወጡ የድለላ ሥራ የሚሠሩት ኢትዮጵያውያን ናቸው። እነዚህ የቤት ሠራተኞች ከሕጋዊ የሥራ ቦታቸው ሲወጡ ደላሎቹን በማመን የሥራ ፈቃዳቸውን እና ፓስፖርታቸውን አሠሪዎቻቸው ጋር በመተው ነው።
አንዴ ሕጋዊነታቸውን ካጡ በኋላ ደግሞ ኑሯቸው ከፍተኛ ምስቅልቅል ውስጥ ይገባል።
በኤጀንሲዎች አማካኝነት የሚሄዱት የቤት ሠራተኞች እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ በኮንትራታቸው መሠረት ከደመወዛቸው ለእነሱ የሚቆረጥ ክፍያ አለ። ብዙዎቹ ከሕጋዊ ሥራቸው የሚፈናቀሉት ይህንን ገንዘብ ላለመክፈል ነው። ለዚህ ደግሞ ደላሎቹ ትልቅ ሚና አላቸው።
ደላሎቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው። የቤት ሠራተኞቹን ለማሳመን የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። ዋናው ማማለያቸው ደግሞ “የተሻለ ክፍያ እንድታገኙ እናድርጋለን” የሚል ሲሆን፣ በተለያዩ መንገዶች ይቀርቧቸዋል።
በተለይ ቋንቋ፣ ብሔር እና ሃይማኖት ሁነኛ የደላሎቹ የመቅረቢያ መንገዶች ናቸው። የአንድ እምነት ተጋሪነት ወይም ተመሳሳይ ቋንቋ ተናጋሪ መሆን ደላሎች በቀላሉ አቅርቦት እና መታመንን ለመፍጠር ይጠቀሙበታል።
የአበበች* ታሪክ ግን ከዚህ የተለየ ነው። አበበች የተጭበረበረችው በፓኪስታን ደላሎች ነው። ደላሎቹ የራሳቸው ቢሮ ያላቸው፣ ቢሯቸው በር ላይ ማስታወቂያ ያስቀመጡ እና ሕጋዊ ውክልና ያላቸው ነበሩ።
ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት አበበች በደላሎቹ ላይ ሙሉ እምነት አሳድራ የሥራ ፈቃድ እንዲያሳድሱላት ውል ፈጸመች።
በተለያየ ጊዜ ለአገልግሎት ማስፈጸሚያ የምትጠየቀውን ገንዘብ እየከፈለች ከአንድ ዓመት በላይ ጠበቀች።
በየጊዜው የማያልቅ ተስፋ እና ቀጠሮ ይሰጧታል። ከዓመት በላይ ብትጠብቅም ምንም ጠብ ያለላት ነገር ግን አልነበረም።
ነገር ግን በየጊዜው ገንዘብ ያስከፍሏታል። በድምሩ 15 ሺህ ድርሃም (230 ሺህ ብር) አካባቢ ከፍላለች።
ከዚህ ሁሉ ጥበቃ በኋላ የተፈጠረው ነገር የአበበችን ተስፋ ያጨለመ ነበር። ለዓመታት በሰው ቤት ተቀጥራ ያፈራችውን ገንዘብ የከፈለቸው ድርጅት ከተከራየው ቤት በመልቀቅ አድራሻውን አጥፍቶ ተሰወረ።
አበበች በቻለችው አቅም ሁሉ ድርጅቱን ለማፈላለግ ሞከረች፤ አልተሳካም። ወደ ኤምባሲም ሆነ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ በመሄድ ዕርዳታ መጠየቅን ግን አልፈለገችም።
የመኖሪያ ፈቃዷ ሰለተቃጠለ ያላት አማራጭ እንደሌሎች ጓደኞቿ ኢጃዛ ቤት በመግባት ሌላ ዕድል እስኪመጣ ራሷን መደበቅ ነበር። አበበች በዚህ ምክንያት ነው በብርሃኑ ኢጃዛ ቤት የተገኘችው።
ብርሃኑ ከእያንዳንዱ የኢጃዛ ቤት ተከራይን ወርሃዊ 200 ድርሃም ያስከፍላል።
ሥራ የሌላቸው ከሆኑ ደግሞ ለምግብ ወጭም ተጨማሪ ክፍያ ይታሰብባቸዋል። ሥራ ያላቸው ወዲያውኑ ይከፍላሉ፤ ሥራ የሌላቸው በቀጣይ ሥራ ሲያገኙ ለመክፈል “በዱቤ” ይኖራሉ።
አበበች በቀጣይ ሥራ ሲያገኙ ለመክፈል “በዱቤ ተከራይተው ከሚኖሩ” ኢትዮጵያውያን መካከል አንዷ ነች።

“ዜጎቻችንን አስኮብልለው የሚያጉሩበት ስፍራ ነው”
አንዳንዶቹ ሥራ ሳያገኙ እስከ ስድስት ወር በዚሁ ኢጃዛ ቤት የቆዩ መኖራቸውን ብርሃኑ ይናገራል። በቤቱ ለተጠጉ ልጆች በአብዛኛው ሥራ የሚፈልግላቸው ራሱ ብርሃኑ ነው።
“ሥራ የምፈልገው አንድም እነርሱን ለመርዳት፤ ሁለትም ያለባቸውን ዕዳ እንዲከፍሉኝ ነው” ይላል ብርሃኑ።
ከዚህም በተጨማሪ ሥራ ሲያስቀጥራቸው 200 ድርሃም ኮሚሽን ይቀበላል። ይህ የብርሃኑ መተዳደሪያው ነው። ግን ይህም ሆኖ የብርሃኑ ሥራም በአገሪቱ ሕግ ያልተፈቀደ ነው።
በዱባይ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል አምባሳደር አክሊሉ ከበደ “ኢጃዛ ቤት በሕገ ወጥ መንገድ ሴት ዜጎቻችንን አስኮብልለው የሚያጉሩበት ስፍራ ነው” ይላሉ።
አምባሳደሩ እንደሚሉት ኢጃዛ ቤቶች “ሰብዓዊነትን ባልጠበቀ መልኩ በርካታ ሰዎች በአንድ ጠባብ ቤት ውስጥ የሚታጨቁበት ሕገ ወጥ ቦታ” በመሆኑ እኛም የአገሪቱ ፖሊስም የማንደግፈው ነው ብለዋል።
ብርሃኑ እንደሚለው እርሱ በሚኖርበት አቅራቢያ ሌሎች ኢጃዛ ቤቶችም አሉ። ቁጥራቸውም ከ30 በላይ እንደሚሆን ይገምታል።
ብዙዎቹ በእነዚህ ቤቶች የሚጠለሉ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ በደሎች የደረሱባቸው፣ አንዳንዶቹም ከኤምባሲ ጋር በመነጋገር ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮች ያላቸው ናቸው። ነገር ግን “ኤምባሲው ችግራቸውን እንደሚፈታላቸው” እርግጠኞች አይደሉም።
“ኤምባሲ የምንሄደው ሰው ሲሞትብን ነው” የሚለው ብርሃኑ፣ አስከሬኑን ወደ አገር ቤት ለመላክ የግድ ሊሴ ፓሴ ስለሚያስፈልግ ያንን ለማግኘት ወደዚያ እንደሚሄዱ ገልጿል። ሌሎች በብርሃኑ ቤት ያሉ ኢትዮጵያውያንም ተመሳሳይ ሃሳብ ነው ያላቸው።
የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት ለኤምባሲ ከማመልከት ይልቅ ሌሎች አማራጮችን እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ። አምባሳደር አክሊሉ ግን ተገልጋዮቹ የሰጡትን አስተያየት አይቀበሉትም።
አንደኛው ዜጎች ወደ ቆንስላው በመሄድ አገልግሎት እንዳያገኙ የሚያደርጋቸው የቢሮክራሲ መንዛዛት እና የአገልግሉት አሰጣጡ ወከባ የበዛበት መሆኑን ተገልጋዮቹ አንስተዋል።
ከዚህ በፊት በነበሩት ጊዜያት “የተወሰኑ ችግሮች አልነበሩም ማለት አይቻልመ” የሚሉት አምባሳደር አክሊሉ፣ አሁን ግን “ከበር ጀምሮ የአገልግሎት አሰጣጣችንን አስተካከለናል” ይላሉ።
ከዚህ በተጨማሪ በሚሠሩበት ቦታ ሆነው ዜጎች በደል ሲደርስባቸው “ስልክ ደውለውልን ሰው ልከን ችግራቸውን የፈታንላቸው አሉ፤ በአካል የሚመጡትንም እያስተናገድን ነው” ብለዋል አምባሳደሩ።
በአጠቃላይ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በሚገኙ ሰባት ግዛቶች እስከ 200 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ ይገመታል።
ኢትዮጵያውያኑ በሁሉም አካባቢዎች ተበታትነው መኖራቸው እና አገልግሎት ለማግኘት የሚችሉባቸው ቦታዎች ውስን መሆናቸው ችግሩን እንዳባባሰው ይታመናል።
በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ኡመር ሐሰን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እና የዜጎችን እንግልት ለመቀነስ የሚያስችል ሥራ እያከናወኑ ነው።
“የሁሉንም ዜጎች መረጃ ሰብስቦ የሚይዝ የመረጃ ቋት ተዘጋጅቷል። ከዚህ ምበተጨማሪ ዜጎች ወደ ኤምባሲ ሳይሄዱ ባሉበት አገልግሎት ሊያገኙ የሚችሉበትን አሠራር ለመዘርጋት ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ የሞባይል መተግበሪያ እያዘጋጀን ነው።”
ሕጋዊ ሰነድ ሳይኖራቸው በኤምሬትስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተም ከአገሪቱ ፖሊስ እና ባለሥልጣናት ጋር በመነጋገር ወደ ሕጋዊው መስመር ለማስገባት እንደሚሠሩ አምባሳደሩ ተናግረዋል።












