ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከተጣለባት ማዕቀብ እንድታመልጥ ቻይና እንዴት እየደገፈቻት ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ በቤጂንግ ባደረጉት ውይይት በአገራቸው መካከል ያለውን ጥልቅ ግንኙነት አድንቀዋል።
ሩሲያ እአአ በ2022 ዩክሬንን ከወረረች በኋላ አራተኛው ግንኙነታቸው ነው።
በአሜሪካ እና በሌሎች አገራት የተጣለባትን ማዕቀብ ለማለስለስ ለምትፈልገው ሞስኮው፤ ቤጂንግ ወሳኝ አጋር ሆና ደርሳለች።
ቻይና ለሩሲያ የጦር መሳሪያ እየሰጠች ነው?
ቻይና ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ትሰጣለች የሚለውን ውንጀላ ደጋግማ አስተባብላለች።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ቻይና ለሩሲያ የምታቀርበውን የጦር መሳሪያ በዩክሬን እንድትጠቀም መፍቀድ የማይሆን ነገር ነው” ብለዋል።
ቻይና ግን ለመሣሪያ ማምረቻ የሚውሉ ወሳኝ አካላትን በማቅረብ የሞስኮውን ጦር እየገነባች ነው በሚል ትከሰሳለች።
"ሩሲያ እነዚህ ተጠቅማ ተጨማሪ ጥይቶችን፣ ታንኮችን፣ የታጠቁ ተሽከርካሪዎችንና ሚሳኤሎችን ታመርትበታለች" ብለዋል ብሊንከን።
ሩሲያ 70 በመቶውን የማሽን ክፍሎች እና 90 በመቶውን ማይክሮኤሌክትሮኒክስ የምታስገባው ከቻይና ነው ብለዋል ።
በግንቦት ወር ዋሽንግተን ይፋ ያደረገችው ማዕቀብ በቻይና እና በሆንግ ኮንግ የሚገኙ ወደ 20 የሚጠጉ ድርጅቶች ላይ ያነጣጠረ ነበር። አንድም ለድሮኖች አካላት በመላክ ሁለትም ቴክኖሎጂዎችን በመላክ ሞስኮው በምዕራባዊያን የተጣሉባትን ማዕቀቦች እንድታልፍ ረድተዋታል።
ቻይና ከሞስኮው ጋር የምታደርገውን የንግድ ልውውጥ የጦር መሳሪያ አያካትትም ብላለች። "በሕግ እና በመመሪያው መሠረት ሁለት ጥቅም ያላቸውን ዕቃዎችን ወደ ውጭ መላክን ትተገብራለች" ስትል አስተባብላለች።
ካርኔጊ ኢንዶውመንት የቻይና የጉምሩክ መረጃ ትንተና መሠረት አድርጎ ይፋ እንዳደረገው ከሆነ ቤጂንግ ከ 300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸውን ለሁለት ጉዳይ ጥቅም ላይ የሚውሉ ዕቃዎችን (ለንግድ እና ለወታደራዊ መሣሪያ የሚሆኑትን) በየወሩ ወደ ሩሲያ ትልካለች።
ዩናይትድ ስቴትስ ከድሮን እስከ ታንክ ድረስ ለማምረት አስፈላጊ የሆኑትን እና "ቅድሚያ የሰጠቻቸውን" ዕቃዎች ያካትታል ብሏል።
ሩሲ የተሰኘው እና መቀመጫውን በዩኬ ያደረገው ተቋም በበኩሉ በዩክሬን ጦርነት ወቅት የቻይናን የሳተላይት ቴክኖሎጂን ለስለላ ሥራ የምትጥቀምበት ሁኔታም ይኖራል ሲል አስጠንቅቋል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
በቻይና እና በሩሲያ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ ምን ያህል ጨምሯል?
የምዕራባውያንን ማዕቀብ ተከትሎ ቤጂንግ መኪና፣ አልባሳት፣ ጥሬ ዕቃዎች እና ሌሎች በርካታ ምርቶችን በዋነኝነት ለሞስኮ አቅራቢ ሆናለች።
እአአ በ2023 በቻይና እና በሩሲያ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ 240 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል (ይህ አሃዝ ክብረ ወሰን ነው።) ከ2021 አንጻር ከ64 በመቶ በላይ ጭማሪ ማሳየቱን ከቻይና የተገኘው መረጃ እያመለክታል።
ሩሲያ ከቻይና የምታስገባው 111 ቢሊዮን ዶላር ያላቸውን ምርቶች ሲሆን ወደ ቤጂንግ የምትልከው ደግሞ 129 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር መረጃው ያሳያል።
በግንቦት ወር በቤጂንግ ባደረጉት ስብሰባ ወቅት ዢ እና ፑቲን በሁለቱ አገራት መካከል እያደገ ያለውን የንግድ ልውውጥ አድንቀዋል።
ሁለቱ አገራት 90 በመቶ ለሚሆነው የንግድ ልውውጣቸው የአሜሪካ ዶላርን ሳይሆን የየራሳቸውን ገንዘቦች እንደሚጠቀሙም አስታውቀዋል።
ፑቲን ቻይናውያን መኪና አምራቾችንም ወደ ሩሲያ ጋብዘዋል። ይህ የሆነው ዩናይትድ ስቴትስ በቻይና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ የጣለቸውን ታሪፍ በአራት እጥፍ በመጨመር 100% መድረሱን ካወጀች ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው።
በ2023 ወደ ሩሲያ የተላከው የቻይና መኪኖች እና መለዋወጫዎች ዋጋ 23 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። ይህም ካለፈው ዓመት በስድስት ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል።
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዩ "የሩሲያ የተፈጥሮ ጋዝ ብዙ የቻይናውያን ቤተሰቦችን እያሞቀ ነው። በቻይና የተሠሩ ተሽከርካሪዎች በሩሲያ ጎዳዎች ላይ እየፈሰሱ" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አንዳንድ ባለሙያዎች ግን ሩሲያ በቻይና ላይ የበለጠ ጥገኛ የሆነችበት "የተዘበራረቀ" ግንኙነት እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል።
እአአ ከ 2023 ወዲህ ቻይና የሩሲያ ከፍተኛ የንግድ አጋር ብትሆንም ሩሲያ ግን ለቻይና ስድስተኛዋ ትልቋ የንግድ አጋር ነች።
ቻይና ከሩሲያ ምን ያህል ዘይት እና ጋዝ ትገዛለች?
ከጠቅላላው የሩሲያ መንግስት ዓመታዊ ገቢ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ከነዳጅ እና ጋዝ ገቢ የሚገኝ ነው።
ከወረራ ወዲህ ለአሜሪካ፣ ለዩናይትድ ኪንግደም እና ለአውሮፓ ኅብረት አገሮች የምትሸጠው በማዕቀቡ ምክንያት ቀንሷል።
ይህንን የገበያ እጥረት ለማካካስ ፊቷን ወደ እስያ በተለይም ወደ ቻይና እና ህንድ አዙራለች።
እአአ በ2023 ሩሲያ ሳዑዲ አረቢያን በመብለጥ የቻይና ከፍተኛ ድፍድፍ ዘይት አቅራቢ ሆናለች። ቤጂንግ 107 ሚሊዮን ቶን ድፍድፍ ዘይት ከሞስኮ ገዝታለች። እአአ ከ2022 አንጻር በ24 በመቶ ጭማሪ ያለው ነው።
የጂ7 አባል አገራት ከአውሮፓ ኅብረት እና ከአውስትራሊያ ጋር በመሆን በባህር በሚጓጓዘው የነዳጅ ዋጋ ላይ ዓለም አቀፍ ገደብ በመጣል የሩስያ ገቢን ለመገደብ ሞክረዋል።
ቻይና ግን የሩስያ ድፍድፍ ነዳጅ ከተቀመጠው ዋጋ በላይ መግዛቷን ቀጥላለች።
ለአስርት አመታት ከሩሲያ ጋር የነበራትን ግንኙነት ጠብቃ የቀጠለችው ህንድ ከዩክሬን ወረራ ወዲህ በቅናሽ ዋጋ ነዳጅ ገዥ ሆና ቀጥላለች።
በህንድ መንግስት ቁጥጥር ስር እንደሚገኘው የአበዳሪው ባንክ ኦፍ ባሮዳ እንደገለፀው ከሆነ ከህንድ አጠቃላይ የነዳጅ ግዢ ውስጥ የሩሲያ ድርሻ በሰኔ 2023 ክብረ ወሰን በሆነ መልኩ 44 በመቶ ደርሷል።
እአአ በ 2023 ቻይና ስምንት ሚሊዮን ቶን ፈሳሽ ጋዝ (ኤልፒጂ) ከሩሲያ የገዛች ሲሆን፣ ይህም ከ 2021 አንጻር በ 77 በመቶ ጭማሪ ያለው ነው።
ሁለቱ አገራት የተፈጥሮ ጋዝን ከሩሲያ ምዕራባዊ ሳይቤሪያ ክልል ወደ ሰሜን ምስራቅ ቻይና ለመላክ ፓወር ኦፍ ሳይቤሪያ 2 የተባለ አዲስ የቧንቧ መስመርን ዝርጋታን ጨምሮ የኃይል ትስስራቸውን ለማስፋት አቅደዋል።
ቻይና ከ 2019 ጀምሮ ሥራ ላይ በሚገኘው ፓወር ኦፍ ሳይቤሪያ መስመር በኩል ከሩሲያ ጋዝ ትገዛለች ።












