የጦር መሳሪያዎችን የጫኑ የግብጽ የጦር አውሮፕላኖች ሞቃዲሾ ማረፋቸው ተዘገበ

የፎቶው ባለመብት, Social Media
የጦር መሳሪያዎችን የጫኑ ሁለት የግብጽ የጦር አውሮፕላኖች በሞቃዲሾ አየር ማረፊያ ማክሰኞ ነሐሴ 21/ 2016 ዓ.ም መድረሳቸው ተዘገበ።
የጦር መሳሪያዎቹ ግብጽ ከአራት አስርት ዓመታት በኋላ ለሶማሊያ ያደረገችው ወታደራዊ ዕርዳታ መሆኑን የዲፕሎማቲክ እና የሶማሊያ መንግሥት ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ ዘግቧል።
ጥይት እና የጦር መሳሪያዎችን የጫኑ ሁለት የጦር አውሮፕላኖች ሞቃዲሾ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የሚያሳይ ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ የተጋራ ሲሆን ሮይተርስም ትክክለኛነቱን አረጋግጫለሁ ብሏል።
ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት የወጡ ተንቃሳቃሽ ምስሎች የግብጽ ዓርማ ያለባቸው ሁለት ሲ-130 የተባሉ ሁለት ወታደራዊ ዕቃ አጓጓዥ አውሮፕላኖች በሞቃዲሾ አየር ማረፊያ አሳይተዋል።
የግብጽ የጦር አውሮፕላኖች በሶማሊያ የታዩት ከጥቂት ሳምንታት በፊት ካይሮ እና ሞቃዲሾ የወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ነው።
ከሁለት ሳምንታት በፊት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ካይሮ ባቀኑ ወቅት ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ ኤል ሲሲ ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ዝርዝሩ ይፋ ያልተደረገ የወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል።
በስምምነቱ መሠረት ግብጽ የሶማሊያን የመከላከያ እና የደኅንነት አቅምን ለማሻሻል የሚያስችሉ ተጨማሪ ድጋፎችን፣ ሥልጠናዎችን እንደምታደርግ እና በሁለቱ አገራት መካከል የመረጃ ልውውጥ እንደሚኖር ተገልጿል።
በወቅቱ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ስምምነቱ “ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እና ሰላምን ለማጎልበት አስፈላጊ ነው” ካሉ በኋላ ግብፅ ለአገራቸው ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለምትሰጠው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ነበር።
ግብጽ ከሶማሊያ ጋር ወታደራዊ ትብብር ስምምነት ከመፈራረሟ በተጨማሪ ካይሮ ሠራዊቷን ለሰላም ማስከበር የኢትዮጵያ ጎረቤት ወደ ሆነችው ሶማሊያ ለመላክ ጥያቄዋን በይፋ አቅርባለች።
ኢትዮጵያ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ወታደሮቿን እንድታስገባ ከጠየቀበት ጊዜ ጀምሮ ለአስራ ሰባት ዓመታት ያህል በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሚገኘው የሰላም አስከባሪ ልዑክ አሰማርታ ትገኛለች።
ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተፈረመ የባሕር በር መግባቢያ አወዛጋቢ ስምምነት ምክንያት የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ተልዕኮ ከመጠናቀቁ በፊት ሶማሊያ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮችን እንዲወጡ እንደምትፈልግ አስታውቃለች።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያላትን ስምምነት አዲሱ ተልዕኮ ከሚወሰንበት፣ ከሰኔ መጨረሻ በፊት ካልሰረዘች በአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ስር እንዲሁም በሁለትዮሽ ስምምነት የሰፈሩት ሁሉም የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ከአገሪቱ እንደሚወጡ እንደሚደረግ የአገሪቱ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሑሴን አሊ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳለ።
ኢትዮጵያ በአትሚስ ስር 3 ሺህ ያህል ወታደሮችን እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር ባላት የሁለትዮሽ ስምምነት እስከ 7 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮችን አሰማርታለች።
ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ወታደሮችን ጨምሮ በሶማሊያ ተሰማርተው ከሚገኙት 18 ሺህ 500 ያህሉ 5 ሺዎቹ ከአገሪቱ እንዲወጡ ተደርገዋል።
በሚቀጥሉት ሳምንታትም በርካታ ወታደሮች የሚቀነሱ ሲሆን የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር የሰላም ተልዕኮ በመጪው ዓመት ጥር ተልዕኮውን አጠናቆ የፀጥታውን ሁኔታም የሶማሊያ መንግሥት እንዲረከብ ይደረጋል።
ሆኖም የፀጥታ ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ ከአስር ሺህ የማይበልጡ ወታደሮች ያሉበት የሰላም አስከባሪዎች ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባለበት እንደሚሰማራ ተጠቅሷል።
ግብጽ በሚቀጥለው ዓመት በሶማሊያ ለሚሰማራው አዲስ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ወታደሮች ለመዋጣት ያቀረበችው ሃሳብ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአፍሪካ ህብረት መግለጫ ላይ ይፋ ሆኗል። ካይሮ በጉዳዩ ላይ በይፋ የሰጠችው መግለጫ የለም።
የአፍሪካ ኅብረት እንዲሁ ግብፅ ጦር ሠራዊቷን ለሰላም ማስከበር ሥራ ወደ ሶማሊያ ለመላክ ያቀረበችውን ጥያቄ በበጎ እንደሚቀበለው አስታውቋል።
ከወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈረም በኋላ የግብጽ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ቃል አቀባይ ኤል ሲሲ አገራቸው የሶማሊያን በግዛቷ ላይ ያላትን አንድነት እና ሉዓላዊነትን እንደምትደግፍ እንዲሁም በውስጥ ጉዳይዋ ላይ የሚኖርን ማንኛውንም ጣልቃ ገብነት እንደምትቃወም በድጋሚ አረጋግጠዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የገባችውን ስምምነት ተከትሎ የግብጽ እና የሶማሊያ ግንኙነት ተጠናክሯል።ኢትዮጵያ በምትገነባው የህዳሴ ግድብ ምክንያት ለዓመታት ውስጥ በማያባራ ውዝግብ ውስጥ የገባችው ግብጽ የመግባቢያ ስምምነቱን አውግዛለች።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ብዙ ያወዛገበውን የባሕር በር ስምምነት የመግባቢያ ሰነድ በተፈራረሙ በቀናት ልዩነት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ከግብፁ አቻቸው አብዱል ፋታህ አል-ሲሲ ጋር በስልክ ከመነጋገራቸው በተጨማሪ ባለፉት ወራት በተደጋጋሚ ወደ ካይሮ አቅንተዋል።
የባሕር በር አልባዋ ኢትዮጵያ የንግድ መተላለፊያ ወደብ ለምግኘት እና የባሕር ኃይሏን ለማጠናከር ካላት ፍላጎት የተነሳ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር ስምምነት መፈረሟ ከሞቃዲሾ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ውስጥ ከትቷት ቆይቷል።
ሞቃዲሾ የአዲስ አበባ እና ሃርጌሳ ግንኙነት ሉዓላዊነቴን እና የግዛት አንድነቴን የሚጥስ ነው ስትል ጠንከር ያለ ተቃውሞ ስታሰማ ቆይታለች።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር በደረሰችው የባሕር በር አጠቃቀም መግባቢያ ስምምነት ምክንያት ውጥረት ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ ለሁለት ጊዜ ያህል ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይት አድርገዋል።
በቱርክ አሸማጋይነት የተደረጉት ሁለቱ ድርድሮች ፍሬ ባያፈሩም ሶስተኛው ዙር በሚቀጥለው ወር እንደሚካሄድ ይጠበቃል።












