ግብፅ እና ሶማሊያ የወታደራዊ ትብብር ስምምነት ተፈራረሙ

የፎቶው ባለመብት, presidency.eg
ለሁለት ቀናት ካይሮ ከተገኙት ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ጉብኝት ጋር በተያያዘ ግብፅ እና የሶማሊያ ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ የሚያስችላቸው ስምምነት ተፈራረሙ።
ረቡዕ እና ሐሙስ ለይፋዊ ጉብኝት ካይሮ የሚገኙት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ከግብፁ አቻቸው አብደል ፋታህ ኤል ሲሲ ጋር ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን በሁሉም ዘርፎች ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መስማማታቸው ተገልጿል።
ሁለቱ አገራት ፕሬዝዳንታዊ ጽህፈት ቤት እንዳስታወቁት መሪዎቹ የመከላከያ ስምምነቱ በተፈረመበት ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል። ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ግብፅ ለአገራቸው ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለምትሰጠው ድጋፍ አመስግነው “ስምምነቱ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እና ሰላምን ለማጎልበት አስፈላጊ ነው” ብለዋል።
የግብፅ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ኤል ሲሲ አገራቸው የሶማሊያን በግዛቷ ላይ ያላትን አንድነት እና እና ሉዓላዊነትን እንደምትደግፍ እንዲሁም በውስጥ ጉዳይዋ ላይ የሚኖርን ማንኛውንም ጣልቃ ገብነት እንደምትቃወም በድጋሚ አረጋግጠዋል ብለዋል።
ምንም እንኳን ከየትኛውም አገር እውቅናን ባታገኝም ከሷማሊያ በመነጠል ነጻ አገርነቷን ካወጀች ሦስት አስርት ዓመታትን ያስኦቀጠረችው ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ስምምነትን ተከትሎ ግብፅ እና ሶማሊያ ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ ነው።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ባለፈው ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. በተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ላይ ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ ለምትሰጠው የባሕር መተላለፊያ ምላሽ የአገርነት እውቅናን ታገኛለች መባሉ ሶማሊያን አስቆጥቶ በአፍሪካ ቀንድ ውጥረት ከሰፈነ ወራት ተቆጥረዋል።
ከሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ እና ግብፅ ከአስር ዓመታት በላይ በውዝግብ ውስጥ የቆዩ ሲሆን፣ ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት መሻከሩን ተከትሎ ግብፅ ከሷማሊያ ጋር ያላትን ግንኙነት በተለያዩ መስኮች እያጠናከረች ትገኛለች።
ግብፅ ከሶማሊያ ጋር የጋራ መከላከያ ስምምነት ከመፈራረሟ በተጨማሪ በሞቃዲሾ ኤምባሲዋን የከፈተች ሲሆን፣ አየር መንገዷም ወደ ዋና ከተማዋ በረራ ማድረግ ጀምሯል።
በተጨማሪም የሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናት አልሻባብን እየተዋጋ በአገሪቱ ከ15 ዓመታት በላይ የቆየው የኢትዮጵያ ሠራዊት እንዲወጣ በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን ተከትሎ፣ ግብፅ ጦሯን በሶማሊያ ውስጥ ለማሰማርት ፍላጎት እንዳላት ገልጻ አውንታዊ ምላሽ አግኝታለች።
የግብፅ ጦር በሶማሊያ ውስጥ የሚሰማራ ከሆነ በዓባይ ወንዝ የውሃ አጠቃቀም አለመግበባት ውስጥ ባሉት በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል ያለውን ያለውን ፍጥጫ ወደ ኢትዮጵያ የሚያቀርበው ይሆናል ተብሎ ተሰግቷል።
በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ለመግባባት ከተፈጠረ በኋላ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ተደጋጋሚ ጉብኝት በግብፅ አድርገዋል። አሁን ለሁለት ቀናት በግብፅ ያደረጉት ጉብኝት በዋናነት በሁለቱ አገራት መካከል በተፈረመው የወታደራዊ ትብብር ስምምነት ላይ ለመገኘት መሆኑ ተገልጿል።
ፕሬዝዳንቱ የስምምነቱን መፈረም አስመልክተው ካይሮ ውስጥ እንደተናገሩት “በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የደኅንነት ትብብር ለማጠናከር የመከላከያ ስምምነቱ ወሳኝ ነው” በማለት ታሪካዊ እርምጃ መሆኑን አመልክተዋል።
ይህ ከወራት በፊት ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ የተነገረለት በግብፅ እና በሶማሊያ መካከል የተፈረመው የወታደራዊ ስምምነት ዝርዝር ይዘት የተገለጸ ባይሆንም ባለፈው ሐምሌ ወር የሶማሊያ ካቢኔ እንደተቀበለው መግለጹ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር አጠቃቀምን በተመለከተ የደረሰችውን ስምምነት ተከትሎ የግብፁ ፕሬዝዳንት የሶማሊያን ሉዓላዊነት በተመለከተ አገራቸው ከጓኗ እንደምትቆም በተዳጋጋሚ የተናገሩ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስምምነቱን በተመለከተ ያደረጉት ንግግር ከሶማሊላንድ በኩል ቁጣ ገጥሞታል።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ “የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን የሚጎዳ ማንኛውንም ድርጊት በጽኑ እንቃወማለን” ማለታቸውን ተከትሎ የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር የተቃውሞ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።















