“የጠበቅነው ሽልማት መኪና እንጂ ብር አልነበረም” አሠልጣኝ ገመዶ ደደፎ

አሠልጣኝ ገመዶ ደደፎ

የፎቶው ባለመብት, etv

የምስሉ መግለጫ, አሠልጣኝ ገመዶ ደደፎ

በፓሪስ ኦሊምፒክ ለተሳተፉ የኢትዮጵያ ቡድን አባላት በተዘጋጀ የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ የተበረከተላቸውን የ2 ሚሊዮን ብር ሽልማት አልቀበልም በማለት መወዛገቢያ የሆኑት አሠልጣኝ ገመዶ ደደፎ መኪና እንዲሰጣቸው ጠብቀው እንደነበር ለቢቢሲ ተናገሩ።

በፓሪስ ኦሊምፒክ ለኢትዮጵያ በማራቶን የሩጫ ውድድር የወርቅ እና የብር ሜዳሊያ ያስገኙትን ሁለት አትሌቶች አሠልጣኝ የሆኑት ገመዶ ደደፎ መኪና መሸለም እንደነበረባቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የጠበቁት ሽልማት መቀየር እንዲሁም በዘንድሮው ለአሰልጣኞች የተሰጠው ሽልማት ከዚህ ቀደም ከነበረው ያነሰ በመሆኑ ምክንያት የተበረከተላቸውን ሽልማት እንዳይቀበሉ ምክንያት እንደሆናቸው አክለው ገልጸዋል።

አሠልጣኙ ከፓሪስ ኦሊምፒክ መልስ ለቡድኑ አባላት ማክሰኞ ምሽት ነሐሴ 7/ 2016 ዓ.ም የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በተካሄደ ሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ የተበረከተላቸውን ሽልማት እንደማይቀበሉ በይፋ ተናግረዋል።

አሠልጣኝ ገመዶ ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ የተበረከተላቸውን የሁለት ሚሊዮን ብር ሽልማት ከተቀበሉ በኋላ እዚያው መድረክ ላይ የተሰጣቸው ሽልማት ልፋታቸውን እንደማይመጥን ገልጸዋል።

“ሁለት ወርቅ እና ብር እንዲሁም ዲፕሎማ አስገኝቼ. . . ለእኔ ሁለት ሚሊዮን የስድብ ያህል ነው” በማለት የብር ሽልማቱን መመለስ እንደሚፈልጉ ጠንከር ባሉ ቃላት ሲናገሩ ታይተዋል።

አሠልጣኙ ከዚህ ንግግራቸው በኋላ በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገሪያ በመሆን የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰነዘሩባቸው ይገኛል።

ቢቢሲ አሰልጣኝ ገመዶ ለምን ሽልማቱን መመለስ እንደፈለጉ ላቀረበላቸው ጥያቄ ከዚህ ቀደም ለአሠልጣኞች የሚሰጠው ሽልማት መቀየሩ እንዲሁም የተሰጠው ዋጋ አነስተኛ በመሆኑ ተበሳጭተው መሆኑን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

“ከዚህ ቀደም በቤተ መንግሥት በነበሩ ስነ ስርዓቶች አትሌቶች እና አሠልጣኞች መኪና ነበር የሚሸለሙት፤ ዘንድሮ ለምን እንደተቀየረ አላውቅም” በማለት ቀደም ሲል የተበረከቱ የመኪና ሽልማቶችን አንስተዋል።

በለንደን ኦሊምፒክ ተሳትፈው ውጤት ላመጡ አትሌቶች እና አሠልጣኞች የመኪና ሽልማት እንደተበረከተላቸው የሚጠቅሱት አሠልጣኝ ገመዶ “በለንደን ኦሊምፒክ ወቅት ሦስት መኪና ነው የተሸለሙት። ሁሴን ሺቦ [የረዥም ርቀት አሰልጣኝ] እና መላኩ መኪና ተሸልመዋል” ሲሉ ምክንያታቸውን ምሳሌ በመጥቀስ አስረድተዋል።

በተጨማሪም የረዥም ርቀት ሩጫ አሰልጣኝ የነበሩት ዶ/ር ይልማ ብርታ እና ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ የመኪና ሽልማት እንደዚሁ ከዚህ ቀደም እንደተሰጣቸው አሠልጣኝ ገመዶ ደደፎ ገልጸዋል።

አሰልጣኙ ከዚህ በፊት በነበረው የቶኪዮ ኦሊምፒክ በ10 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ላሸነፈው ሰለሞን ባረጋ የስድስት ሚሊዮን ብር መኪና መሸለሙን በማስታወስ አሁን በማራቶን ወርቅ ላገኘው ታምራት የተሰጠውን ሽልማት ዋጋ አነጻጽረውታል።

“ለታምራት7 ሚሊዮን ብር ተሰጥቶታል። የዚያን ጊዜ ዶላር 50 ብር አካባቢ ነበር። ይህ ማለት አሁን ላይ ለታምራት የተሰጠው ሦስት ሚሊዮን ብር ብቻ ነው ማለት ነው። ሌላ ምንም ሽልማት የለም” በማለት ለቢቢሲ ሁኔታውን አስረድተዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በተካሄደው የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ በወንዶች ማራቶን በፓሪስ ኦሊምፒክ ለኢትዮጵያ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘው ታምራት ቶላ የ7 ሚሊዮን ብር እና የወርቅ ኒሻን ሽልማት ተበርክቶለታል።

በሽልማቱ ወቅት ከመንግሥት በተሰጣቸው የሁለት ሚሊዮን ብር ደስተኛ አለመሆናቸውን በጠንካራ ቃላት የተናገሩት አሠልጣኝ ገመዶ ደደፎ “መኪና እንጂ የብር ሽልማትን አልጠበቅንም። ሽልማቱ መኪና መሆን ነበረበት” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በፓሪስ ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ካገኘው ታምራት ቶላ በተጨማሪ የብር ሜዳሊያ ላስገኙ አትሌቶች ትዕግስት አሰፋ ፣ ጽጌ ዱጉማ እና በሪሁ አረጋዊ አራት ሚሊዮን ብር በነብስ ወከፍ ሲሸለሙ፣ ለተቀሩት የቡድኑ አባላት እንደየተሳትፏቸው ከ50ሺ ብር ጀምሮ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።